የብቸኝነትን ስሜት ተዋግተህ ለማሸነፍ ቆርጠሃልን?
ብቸኝነት ይሰማሃልን? ባለትዳርም ሆንክ ነጠላ፣ ወንድም ሆንክ ሴት፣ አዋቂም ሆንክ ወጣት በሕይወትህ ውስጥ ብቸኝነት የሚሰማህ ጊዜ አለ። በተጨማሪም ብቻህን መሆንህ ብቻ ብቸኝነት እንዲሰማህ እንደማያደርግ ልትገነዘበው ይገባል። ብቻውን ሆኖ በተመስጦ ምርምር እያደረገ ያለ ተመራማሪ ብቸኝነት አይሰማውም። ሥዕል እየሳለ ያለ ሰዓሊም ብቸኝነት አይሰማውም። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ብቻቸውን መሆን ይመርጣሉ። ለብቻቸው መሆናቸው ራሱ ከሁሉ የተሻለ ጓደኛቸው ነው።
እውነተኛው የብቸኝነት ስሜት የሚመጣው ከውጪ ሳይሆን ከውስጣችን ነው። የብቸኝነት ስሜት እንደ ሞት፣ ፍቺ፣ ከሥራ መባረር በመሳሰሉት ወይም በሌላ አሳዛኝ ነገር ሊቀሰቀስ ይችላል። በውስጣችን ያለውን ዓለም ብሩህ ስናደርገው የብቸኝነት ስሜታችን ይቀንሳል፤ ምናልባትም ውሎ አድሮ ሊጠፋ ይችል ይሆናል። የደረሰብንን ጉዳት ልንለምደውና ልንረሳው እንችላለን።
የተለያዩ ስሜቶች የሚፈጠሩት ከምታስባቸው ነገሮች ነው። ችግሩ በደረሰብህ ጊዜ የተሰማህ ሐዘን ካለፈ በኋላ ቀሪውን የሕይወት ዘመንህን በጥሩ ሁኔታ እንድትመራ የሚያደርጉህን ገንቢ ሐሳቦች ማሰብ መጀመርህ በጣም አስፈላጊ ነው።
ነቃ በል። ራስህን ተቆጣጠር። ልታደርጋቸው የሚገቡህ ገንቢ ነገሮች አሉ። ስለዚህ ተግባቢ ሁን ለአንድ ሰው ስልክ ደውል። ደብዳቤ ጻፍ። መጽሐፍ አንብብ። ሰዎች ወደ ቤትህ እንዲመጡ ጋብዝ። ከሰዎች ጋር ሐሳብ ለሐሳብ ተለዋወጥ። ጓደኛ ለማግኘት አንተ ራስህ የወዳጅነት መልክ የምታሳይ ሁን። ከሌሎች ጋር ለመግባባት በመጀመሪያ ከራስህ ጋር ተግባባ። ደግ ሁን። የሚያጽናኑ መንፈሳዊ ነገሮች አጫውታቸው። እንዲህ ካደረግህ ኢየሱስ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” በማለት የተናገረው እውነት መሆኑን ትገነዘባለህ። በተጨማሪም “ያረካ እርሱ ደግሞ ይረካል” የሚለው ምሳሌ እውነት ሆኖ ታገኘዋለህ።—ሥራ 20:35፤ ምሳሌ 11:25 አዓት
ያንተው ፈንታ ነው
እንዲህ ማድረግ ይከብዳልን? ከማድረጉስ ይልቅ መናገሩ ይቀላልን? ጠቃሚ የሆነ ማንኛውም ነገር ከማድረጉ ይልቅ መናገሩ ቀላል ነው። ያደረግኸው ነገር የሚያረካ የሚሆንልህ ለዚህ ነው። ልዩ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። እንዲህ ማድረግህ ለሌሎች እንድታካፍል ስለሚያስችልህ የውስጥ ደስታህ ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል። ሊቆጣጠርህ የሚፈልገውን የብቸኝነት ስሜት ድል ለማድረግ ጥረት ማድረጉ ያንተው ፈንታ ነው። ሞደርን ማቹሪቲ በተባለው መጽሔት ላይ አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብለው ነበር:– “ለብቸኝነት ስሜትህ ማንም ሌላ ሰው ተጠያቂ አይደለም። የብቸኝነት ስሜትህን ለማጥፋት ግን አንተ አንድ ነገር ልታደርግ ትችላለህ። አንድ ጓደኛ በማበጀት ሕይወትህን ልትጀምር ትችላለህ። አሳዝኖኛል የምትለውን ሰው ይቅርታ ልታደርግለት ትችላለህ። ደብዳቤ ልትጽፍ ትችላለህ። ስልክ ልትደውል ትችላለህ። ሕይወትህን ልትለውጠው የምትችለው አንተ እንጂ ሌላ ማንም ሰው አይደለም።” ‘ብቸኝነት እንዳይሰማችሁና ሕይወታችሁ የተሰናከለ እንዳይሆን ማስተካከል የምትችሉት እናንተው ራሳችሁ ናችሁ እላቸዋለሁ። የብቸኝነት ስሜታችሁን የማጥፋቱን ሥራ ተያያዙት!’ የሚለውን “ይህንኑ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከት ነጥብ” ከደረሳቸው አንድ ደብዳቤ ላይ ቀንጨብ አድርገው ጽፈዋል።
ሊረዱህ የሚችሉ ጓደኞችህ የግድ ሰዎች ብቻ መሆን አያስፈልጋቸውም። አንድ የእንስሳት ሐኪም “በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚያጋጥማቸው ትልቁ ችግር አካላዊ ሕመም ሳይሆን ብቸኝነታቸውና የተተዉ መሆናቸው ነው። አረጋውያን ከኅብረተሰቡ የተገለሉ በሚሆኑበት ጊዜ ለማዳ እንስሳት (ውሾችም ጭምር) ጓደኞቻቸው እንዲሆኑ በማድረግ . . . ለሕይወታቸው ዓላማና ትርጉም ይሰጡታል” ብለዋል። ቤተር ሆምስ ኤንድ ጋርደንስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሎ ነበር:- “ለማዳ እንስሳት ስሜቱ የተረበሸ ሰው እንዲያገግም፣ አካላዊ ደዌ ያለባቸውን፣ አካለ ጎዶሎዎችንና አካለ ስንኩላንን ለማበረታታትና ብቸኝነት የሚሰማቸውንና አረጋውያንን ለማነቃቃት ይረዳሉ።” በሌላ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ለማዳ እንስሳትን ለማሳደግ አዲስ ፍላጎት እያዳበሩ ስላሉ ሰዎች ሲናገር “የበሽተኞች ሥጋት ይቀንሳል። ይጠሉኛል ብለው ሳይፈሩ ለለማዳ እንስሶቻቸው ያላቸውን ፍቅር መግለጽ ችለዋል። በመጀመሪያ ለለማዳ እንስሶቻቸው ስለሚያደርጉላቸው እንክብካቤ ማውራት ይጀምሩና ከጊዜ በኋላ ከሰዎች ጋር በግልጽ መወያየት ይጀምራሉ። ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆን ይጀምራሉ። በነሱ ጥገኝነት ሥር የሚኖር እንዳለ ስለሚያውቁ ጠቃሚነታቸው ይሰማቸዋል” ብሏል።
በብቸኝነት ስሜት እየተሠቃየ ያለ ሰው ብዙውን ጊዜ ራሱን በራሱ ለማሻሻል ወይም ከገባበት የተስፋ መቁረጥ አዘቅት ራሱን ለማውጣት ብቁ አይደለም። ትንሽ ለመሞከርና ጥረት ለማድረግ እንኳ አይፈልግም። ሆኖም የብቸኝነትን ስሜት ምን ያህል እንደሚጠሉት ሲገልጹ:- “ባጠቃላይ ሰዎች ስንባል ስለ ጠባያችን የማንፈልገው ነገር ሲነገረን መስማት ደስ አይለንም። ወይም ቢያንስ ቢያንስ ያን የተነገረንን ነገር ባለመፈጸም እንደጠላነው እናሳያለን” ብለው ጽፈዋል። አንድ ሰው ከብቸኝነት ስሜቱ መላቀቅ ቢፈልግ ከዚያ ለመላቀቅ የሚያስፈልገውን ያህል ቆራጥ ለመሆን ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል።
እንዲሰማህ የምትፈልገውን አድርግ
አንድ ሰው ያለበትን የመንፈስ ጭንቀት ለማሸነፍ እንዲችል ደስተኛና ደግ ለመሆን ጥረት ማድረጉን መቀጠል ያስፈልገዋል። (ከሥራ 20:35 ጋር አወዳድር።) ይህም ከብቸኝነት አስከፊ የልፍስፍስነት ባሕርይ ተቃራኒ የሆነ ነገር በማድረግ ሥር የሰደደውን የብቸኝነት ስሜት መነቃቀልን ይጠይቃል። ደስተኛ ሁን፣ ጨፍር፣ ደስ የሚል ዘፈን ዝፈን። መደሰትህን የሚያሳይ ማንኛውንም ነገር አድርግ። የሚያስደስትህን ነገር አጋንነው፣ ደጋግመህ አድርገው፣ የመከፋትን መንፈስ አጥፍተህ በሚያስደስቱ ሐሳቦች ተካው። እንዴት ባሉ ሐሳቦች?
በፊልጵስዩስ 4:8 ላይ እንዳሉት ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ:- “በቀረውስ፣ ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን እነዚህን አስቡ።”
የሚያስፈልገው ነገር ሕይወትህ ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ ነው። ሕይወትህ ትርጉም ወይም ዓላማ እንዳለው የሚሰማህ ከሆነ ያንን ለማድረግ ኃይልህን ታጠናክራለህ፣ ያንን ዓላማ ለማሳካት በመፈለግም ጥረት ታደርጋለህ። የሐዘንና የትካዜ ስሜት የሚያሳድረው የብቸኝነት ስሜት አይኖርብህም። ይህ ጉዳይ ቪክተር ፍራንክል በጻፉት ማንስ ሰርች ፎር ሚኒንግ በተባለው መጽሐፍ ላይ በጥሩ ሁኔታ ተገልጿል። ጉዳዩን ያብራሩት ሂትለር ባዘጋጃቸው የእሥረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ከነበሩ እሥረኞች ጋር አያይዘው ነው። ሕይወታቸው ትርጉም እንደሌለው ሆኖ የተሰማቸው እሥረኞች ለብቸኝነት እጃቸውን ስለሰጡ ለመኖር ያላቸው ፍላጎት ጠፍቶ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የራሱን ጠቃሚነት በመገንዘብ ከፍ ባሉና ይበልጥ መንፈሳዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ካተኮረ በካምፑ ውስጥ ባለው ኑሮ ሊፍረከረክ አይችልም።” ቀጥለውም “አንድ ሰው ሥቃይ የሚደርስበት ለምን እንደሆነ ከገባው ማለትም፣ ለምሳሌ የሚሠቃየው መሥዋዕት ለመሆን መሆኑን ካወቀ የሚቀበለው ሥቃይ ለጊዜው ሥቃይ መሆኑ በሆነ መንገድ ያቆማል። ሰውን የሚያሳስበው ትልቁ ነገር የሥቃዩ መወገድ ወይም ደስታ ማግኘቱ ሳይሆን ሕይወቱ ትርጉም ያለው መሆኑ ነው። ሰው የሚሠቃይበት ምክንያት ከገባው መከራን ለመቀበል ፈቃደኛ ነው።”
ሊኖርህ የሚገባው ከፍተኛው ወዳጅ
እውነተኛ መንፈሳዊ አመለካከት ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ወደ አምላክና ወደ ቃሉ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር ማለት ነው። በአምላክ ማመንና ወደ እርሱ ከልብ መጸለይ ለሕይወታችን ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። እንዲህ ካደረግን ከሰው ጋር ያለን ወዳጅነት ቢቋረጥ እንኳን ብቻችንን አንሆንም፤ የብቸኝነት ተገዢም አንሆንም። ፍራንክል እንዳሉት የሚደርስብን መከራ ትርጉም ካለው እንችለዋለን፤ እንዲያውም የደስታ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ስለ ሰው ተፈጥሯዊ ባሕርይ የሚያጠኑ አንድ ሰው እንዲህ ብለው ነበር:- “አንድ የተሰቀለ ሰማዕት በዙፋን ላይ የተቀመጠን ንጉሥ የሚያስቀና ደስታ ሊኖረው ይችላል።”
የክርስቶስ ሐዋርያት ሰዎች ሲያሳድዷቸው በይሖዋ ደስ ብሏቸው ነበር። ስደቱ ለነሱ ትልቅ ትርጉም ነበረው። “ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፣ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሐሤትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” (ማቴዎስ 5:10–12) በሥራ 5:40, 41 ላይ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት ተመዝግቧል:- “ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፣ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው [ከሳንሄድሪን ሸንጎ] ፊት ደስ እያላቸው ወጡ።”
ጽጌረዳ በምታሳድግበት ቦታ እሾህ ሊበቅል አይችልም
አፍራሽ ለሆነ የተስፋ መቁረጥና አስቀያሚ ለሆነው የብቸኝነት ዘር ምንም ቦታ ሳትተው የአእምሮህን አፈር በውበት ዘርና ገንቢ በሆነ ዓላማ ሙላው። (ከቆላስይስ 3:2፤ 4:2 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ማድረግ ይከብዳልን? አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ይህ በጭራሽ የማይቻል ነገር ይመስላል። አንድ ባለ ቅኔ “ጽጌረዳ በምታሳድግበት ቦታ . . . እሾህ ሊበቅል አይችልም” በማለት ጽፈዋል። ይህንንም ለማድረግ ቢሆን ገንቢ ጥረትና በቆራጥነት መነሣት ያስፈልጋል። ማድረግ ግን ይቻላል፤ በመደረግም ላይ ነው።
ለምሳሌ ላውረል ኒስቤትን እንውሰድ። በ36 ዓመቷ ፖሊዮ ያዛትና ከብረት በተሠራ ለመተንፈስ በሚያገለግል መሣሪያ ውስጥ እንድትገባ ተደረገች። እዚያ ውስጥ ለ37 ዓመታት በጀርባዋ ተኝታለች። ከአንገቷ በታች ሙሉ በሙሉ ሽባ በመሆኗ ከጭንቅላቷ በስተቀር ምንም መንቀሳቀስ አትችልም ነበር። በመጀመሪያ ላይ በጣም ተስፋ ቆርጣና ተክዛ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን ሙሉ ለራሷ ስታዝን ከቆየች በኋላ ‘አሁንስ ይበቃኛል!’ ብላ ወሰነች። የምታሳድጋቸው ሁለት ልጆችና የምታስብለት ባል ነበራት። እንደገና ተበረታታች። ከብረት በተሠራው ለመተንፈስ የሚያስችላት መሣሪያ ውስጥ ሆና ቤቷን መምራት ቻለች።
ላውረል ብዙም እንቅልፍ አይወስዳትም ነበር። ታዲያ ረጅሙን ሌሊት እንዴት ያልፍላት ነበር? ለብቸኝነት ስሜት በመሸነፍ? አይደለም። ለሰማዩ አባቷ ለይሖዋ ትጸልይ ነበር። ጥንካሬ እንድታገኝ ስለራሷ ትጸልይ ነበር፤ ስለ ክርስቲያን ወንድሞቿና እህቶቿ ትጸልይ ነበር፤ ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች ለመመሥከር የምትችልባቸው አጋጣሚዎች እንድታገኝ ትጸልይ ነበር። ለመሥበክ የምትችልባቸውን መንገዶች ቀየሰች፤ ስለ ይሖዋ ስም በመመሥከርም ብዙዎችን አስገርማለች። ጽጌረዳዎቹን ስለምትኮተኩት የብቸኝነት እሾህ እንዲበቅል አልፈቀደችለትም።
የመጠበቂያ ግንብ ሚስዮናዊ የነበረው ሐሮልድ ኪንግም እንዲሁ ያደርግ ነበር። ለአምስት ዓመታት በቻይና እስር ቤት ገለልተኛ በሆነ ክፍል ውስጥ ለብቻው ታስሮ በነበረበት ጊዜ ብቸኝነት ሊይዘው ይችል ነበር። እርሱ ግን ይህን አፍራሽ አመለካከት አስወግዶ አንድ ነገር ለማድረግ አሰበና በቆራጥነት አእምሮው በብቸኝነት ላይ ሳይሆን በሌላ ነገር ላይ እንዲያተኩር አደረገ። ከጊዜ በኋላ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጾታል:-
“‘የምሰብክበት’ ፕሮግራም አወጣሁ። ነገር ግን አንድ ሰው ገለልተኛ በሆነ ክፍል ለብቻው ታስሮ እያለ እንዴት መስበክ ይችላል? ከማስታውሳቸው ነገሮች በመነሣት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን አዘጋጅቼ በሃሳቤ ለፈጠርኳቸው ሰዎች ለመስበክ ወሰንኩ። ከዚያ ሥራውን ጀመርኩ። በሃሳቤ የፈጠርኳቸውን ቤቶች እያንኳኳሁ በሃሳቤ ለፈጠርኳቸው የቤት ባለቤቶች እመሠክራለሁ። በዚህ ዓይነት ጠዋት ጠዋት ብዙ ቤቶችን አንኳኳለሁ። ውሎ አድሮ ወይዘሮ ካርተር የምትባል ፍላጎት ያሳየች አንዲት ሴት አገኘሁ። ብዙ ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ካደረግሁላት በኋላ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተቀጣጠርን። ከእሷም ጋር ‘እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን ’ ከተባለው መጽሐፍ የማስታውሳቸውን ዋና ዋና ሐሳቦች አጠናን። ድምፄ የምናገራቸውን ነገሮች ይበልጥ በአእምሮዬ ውስጥ እንዲቀርጻቸው ስል ይህን ሁሉ የማደርገው ጮክ ብዬ እየተናገርኩ ነበር።”
ሂትለር ባዘጋጃቸው የእሥረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረው የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እምነታችንን ክደናል ብቻ ቢሉ እንኳን ነፃ ሊወጡ ይችሉ ነበር። ጥቂቶች ክደዋል። በሺህ የሚቆጠሩት በታማኝነት ሞተዋል። አንዳንዶቹ ሞት ተፈርዶባቸው ሌሎቹ ደግሞ በበሽታና በምግብ እጥረት የተነሣ ሞተዋል። ጆሴፍ የተባለ ታስሮ የነበረ አንድ ምሥክር በሌሎች ካምፖች ውስጥ የታሰሩ ሁለት ወንድሞች ነበሩት። አንደኛው ወንድሙ በጀርባው እንዲተኛና አንገቱን የሚቆርጠው ስለት ሲሰነዘርበት እንዲመለከት ተደርጓል። ጆሴፍ ስለ ሁኔታው ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “በካምፑ ውስጥ የነበሩ ሌሎች እሥረኞች ይህንን ሲሰሙ እንኳን ደስ አለህ አሉኝ። ገንቢ አመለካከታቸው በጥልቅ ነካኝ። እምነታችንን ክደን ከሞት ከመትረፍ ይልቅ ታማኝነታችንን ጠብቀን መሞት ይሻለን ነበር።”
ሌላው ወንድሙ ደግሞ በሚረሽኑት ወታደሮች ፊት ቆሞ እያለ ከመሞቱ በፊት መናገር የሚፈልገው ነገር እንዳለ ተጠየቀ። እርሱም መጸለይ እንዲፈቀድለት ጠየቀና ተፈቀደለት። ጸሎቱ በሚያሳዝኑ ታሪኮች የተሞላና ከልብ የመነጨ ደስታ እንዳለው የሚገልጽ ስለነበር ወታደሮቹ ተኩሱ ሲባሉ አንዳቸውም ትዕዛዙን ሳይፈጽሙ ቀሩ። ትዕዛዙ ተደገመ። በዚህ ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ ተኮሰ። ግን ሊገድለው በሚችል ቦታ ላይ አልመታውም። ከዚያ መኮንኑ በጣም በመናደዱ የራሱን ሽጉጥ አውጥቶ ገደለው።
ሕይወትን ትርጉም ያለው ሊያደርግ የሚችለው ምንድን ነው?
እነዚህ ሁሉ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ማሳደርን የሚጠይቁ ነበሩ። ሁሉንም ነገር ሞክረን አልሳካ ቢለንም በእርሱ ላይ ያለን እምነት ግን የብቸኝነትን ስሜት ድል ለማድረግና በፊት ባዶ የነበረውን ሕይወታችንን ትርጉም ያለው ለማድረግ ያስችለናል። በዓለማዊ መንገድ ትርጉም አለው ተብሎ የሚታሰብ ሕይወት ምንም ትርጉም የለውም። ለምን? ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች መጨረሻቸው ሞቶ አፈር መሆን፣ መረሳት ነው። በስብዕና ባሕር ላይ ትንሽም ሞገድ ሳያሳልፉና በጊዜ አሸዋ ላይ ለምልክት የሚሆን ዱካ ሳይተዉ ያልፋሉ። መክብብ 9:5 እንደሚለው ነው:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸው ተረስቷልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም።” ሕይወት ከይሖዋ ዓላማዎች ጋር ምንም ግንኙነት ከሌለው፣ ትርጉም ያለው ኑሮ ኖርኩ ማለት ከንቱና ባዶ ነው።
በከዋክብት የተሞላውን ሰማይ ስትመለከትና ከበላይህ እንደ ጣርያ የተዘረጋውን ጨለማ ግዝፈት ስታስተውል ስለራስህ ዋጋማነት ይሰማህ የነበረው ስሜት በንኖ ይጠፋል። እንግዲያው መዝሙራዊው ዳዊት “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጎበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” ብሎ ሲጽፍ ምን ዓይነት ስሜት እንደተሰማው ይገባሃል። የዳዊት ልጅ ሰሎሞን “ሁሉ ከንቱ ነው” በማለት የሰዎች ሥራ ሁሉ ዋጋ ቢስ መሆኑን ከገለጸ በኋላ “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ” ሲል ደምድሟል።—መዝሙር 8:3, 4፤ መክብብ 12:8, 13
እንግዲያው ነገሩን ለማጠቃለል አንድ የብቸኝነት ስሜት ያለበት ሰው ወይም ማንኛውም ሰው ለሕይወቱ ትርጉም ሊሰጠው የሚችለው እንዴት ነው? አምላክን እየፈራና ሕግጋቱን እየታዘዘ በመኖር ነው። የግዙፉ ጽንፈ ዓለም ፈጣሪ ከሆነው አምላክ ዓላማዎች ጋር የሚስማማውና ዘላለማዊ የሆነው መለኮታዊ ዝግጅት ክፍል ሊሆን የሚችለው እንዲህ ካደረገ ብቻ ነው።
አምላክ ከአንተ ጋር ካለ በፍጹም ብቻህን አይደለህም
የይሖዋ ምሥክር የሆነች አንዲት ታማኝ አፍሪካዊት የደረሰባትን ከባድ ስደትና እንደተተወች ያህል ይሰማት የነበረውን ስሜት ችላ ከተቋቋመች በኋላ ምንም እንኳን ከሰዎች ጋር የነበራት ግንኙነት ቢቋረጥም ብቻዋን እንዳልነበረች ተናግራለች። “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ” የሚለውን መዝሙር 27:10ን ጠቀሰች። ኢየሱስ እንደዚህ ተሰምቶት ነበር። “እነሆ፣ እያንዳንዳችሁ ወደ ቤት የምትበታተኑበት እኔንም ለብቻዬ የምትተዉበት ሰዓት ይመጣል፣ አሁንም ደርሶአል፤ ነገር ግን አብ ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ብቻዬን አይደለሁም” ብሎ ነበር።—ዮሐንስ 16:32
ኢየሱስ ብቻዬን እሆናለሁ ብሎ አልፈራም። ብዙ ጊዜ ብቻውን መሆን ይፈልግ ነበር። ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ ግን ብቸኝነት አይሰማውም ነበር። የአምላክ መንፈስ እንዲፈስስለት ራሱን ባዘጋጀና በአምላክ ፍጥረታት በተከበበ ጊዜ ወደ እርሱ እንደቀረበ ይሰማው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከአምላክ ጋር ብቻ ለመሆን ሲል ሰዎች አብረውት እንዳይሆኑ ይፈልግ ነበር። ‘ወደ አምላክ ቀረበ፤ አምላክም ወደ እርሱ ቀረበ።’ (ያዕቆብ 4:8) እርሱ የአምላክ የቅርብ ወዳጅ የነበረ ለመሆኑ ምንም አያጠራጥርም።
ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተገለጸው ዓይነት ጓደኛ ውድ ሀብት ነው። (ምሳሌ 17:17፤ 18:24) አብርሃም በይሖዋ አምላክ ላይ በነበረው ሙሉ እምነትና ሳይጠራጠር ለእርሱ በመታዘዙ ምክንያት ‘የይሖዋ ወዳጅ’ ለመባል በቅቷል። (ያዕቆብ 2:23) ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ። ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፣ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።”—ዮሐንስ 15:14, 15
እምነት ያላቸው ሰዎች ይሖዋ አምላክንና ክርስቶስ ኢየሱስን የመሰሉ ጓደኞች እያሉላቸው ብቸኝነትን ለማጥፋት በሚያደርጉት ውጊያ እንዴት ሊሸነፉ ይችላሉ?
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጸለይና ሌሎች ሥራዎችን መሥራት ከብቸኝነት ስሜት ለመላቀቅ ሊረዳህ ይችላል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሐሮልድ ኪንግና በእሥረኞች ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረው የነበሩ የብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ተሞክሮዎች እጅግ አስከፊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆንም እንኳን በአምላክ ላይ ያለን እምነት የብቸኝነትን ስሜት ማሸነፍ እንደሚችል ያሳያሉ
[ምንጭ]
U.S. National Archives photo