የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g94 4/8 ገጽ 12-24
  • የእናት ጡት ወተት የሚመረጥበት ምክንያት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የእናት ጡት ወተት የሚመረጥበት ምክንያት
  • ንቁ!—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሁሉ የላቀ ገንቢ ምግብ
  • ጡት ማጥባት ሕፃናትን ከሞት ያድናል
  • ጡት የሚያጠቡ እናቶች የሚያገኟቸው ጥቅሞች
  • ጡት ለማጥባት መወሰን
  • የኤድስ ተጠቂ የሆኑ እናቶች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል
    ንቁ!—2000
  • የእናት ጡት ወተት
    ንድፍ አውጪ አለው?
  • ሴቶች ስለ ጡት ካንሰር ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮች
    ንቁ!—1998
  • ሕፃናት የሚያስፈልጋቸውና የሚፈልጉት
    ንቁ!—2004
ንቁ!—1994
g94 4/8 ገጽ 12-24

የእናት ጡት ወተት የሚመረጥበት ምክንያት

በናይጄሪያ የሚገኝ የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በጣም ጣፋጭ የሆነ፣ በሕፃኑ አንጀት በቀላሉ የሚፈጭና ለሕፃናት እድገት የሚያስፈልጉትን አልሚ ምግቦች አሟልቶ የያዘ የሕፃናት ምግብ ነው። ይህ ምግብ በሽታ ለመፈወስም ሆነ ለመከላከል የሚያገለግል “ግሩም መድኃኒት” ነው። በማንኛውም አገር የሚኖሩ ቤተሰቦች በቀላሉ የሚያገኙትና ገንዘብ የማይከፈልበት ነው።

እንዲህ ያለ የሕፃናት ምግብ ፈጽሞ ሊገኝ አይችልም ብለህ ታስብ ይሆን? በእንዱስትሪ ሳይንቲስቶች የተዘጋጀ አይሁን እንጂ እንዲህ ያለ ምግብ አለ። ይህ ምግብ የእናት ጡት ወተት ነው።

ይህ ግሩም ምግብ በሰው ልጅ የታሪክ ዘመናት በሙሉ ለሕፃናት እድገት በጣም አስፈላጊ መሆኑ ይታመን ነበር። ለምሳሌ የፈርዖን ልጅ ሕፃኑን ሙሴን ወድቆ ባገኘችው ጊዜ ‘እያጠባች የምታሳድገው ሴት’ እንድትጠራላት የሙሴን እህት አዝዛት እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ዘጸአት 2:​5–9) ቆይቶም በግሪካውያንና በሮማውያን ኅብረተሰብ፣ ባለጠጋ ወላጆች ልጆቻቸውን ጡት የምታጠባላቸው ጤነኛና ጠንካራ ሴት ይቀጥሩ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሕፃናትን ጡት የማጥባት ልማድ በጣም ቀንሷል። ለዚህ በከፊል ምክንያት የሚሆነው በዘመናዊው ቴክኖሎጂ ስለሚዘጋጁት የሕፃናት ምግቦች የሚነገሩት ማስታወቂያዎች፣ እነዚህ ምግቦች የጡት ወተትን የሚያስንቁ እንደሆኑ ተደርጎ እንዲታመን ማድረጋቸው ነው። በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙ እናቶች “ከሁሉ የሚበልጠው የጡት ወተት” መሆኑን እየተገነዘቡት ስለመጡ ቀደም ብሎ የነበረው አመለካከት መለወጥ ጀምሯል።

ከሁሉ የላቀ ገንቢ ምግብ

ሳይንቲስቶች ፈጣሪ ያዘጋጀውን ሕፃናትን የመመገብ ተፈጥሯዊ ዘዴ ማሻሻል ችለዋልን? በፍጹም አልቻሉም። ዩኒሴፍ (በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት) “ከአራት እስከ ስድስት ወር ባለው ዕድሜ ለሚገኙ ሕፃናት ከእናት ጡት ወተት የተሻለ ምግብና መጠጥ ሊገኝ አይችልም” ብሏል። የጡት ወተት ሁሉንም ዓይነት ፕሮቲኖች፣ እድገትን የሚያፋጥኑ ቅመሞች፣ ቅባቶች፣ ካርቦሃድሬቶች፣ ኢንዛየሞች፣ ቪታሚኖችና አንድ ሕፃን በመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ ጤነኛ ሆኖ እንዲያድግ የሚያስፈልጉትን ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች ሁሉ አሟልቶ ይዟል።

የጡት ወተት አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት ከሁሉ የተሻለ ምግብ ከመሆኑም በላይ ምንም ዓይነት ሌላ ምግብ አያስፈልጋቸውም። በግንቦት 1992 ተደርጎ የነበረው የዓለም የጤና ጉባኤ “በመጀመሪያዎቹ ከአራት እስከ ስድስት ወራት የሕፃኑን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት ምንም ዓይነት ምግብ ወይም ፈሳሽ ውኃ እንኳን ቢሆን አስፈላጊ አይደለም” ሲል አረጋግጧል። የጡት ወተት ሞቃትና ደረቅ የአየር ጠባይ ባለባቸው አካባቢዎችም ቢሆን የአንድን ሕፃን ጥም ለማርካት የሚችል በቂ ውኃ አለው። ተጨማሪ ውኃ ወይም ስኳር የተጨመረባቸው መጠጦችን በጡጦ ማጠጣት የማያስፈልግ ከመሆኑም በተጨማሪ ሕፃኑ ጨርሶ ጡት መጥባት እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል። ምክንያቱም ሕፃናት ከጡት ይልቅ ጡጦ መጥባት ቀላል ሆኖ ስለሚያገኙት ብዙውን ጊዜ ጡጦ መጥባት ይመርጣሉ። እርግጥ ነው፣ ከመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት በኋላ ከጡት ወተት በተጨማሪ ቀስ በቀስ ሌሎች ምግቦችና መጠጦችን መስጠት ያስፈልጋል።

የጡት ወተትን ያህል የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ያለውና ሕፃናት ጤነኛ ሆነው እንዲያድጉ የሚረዳ የጡት ወተትን ሊተካ የሚችል ምግብ የለም። ሪፕሮዳክቲቭ ኸልዝ — ግሎባል ኢሹስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ያትታል:- “የጡት ወተትን የሚተካ ምግብ ለማዘጋጀት ሲደረጉ የቆዩት ሙከራዎች የተሳካ ውጤት አላስገኙም። ስለ ሕፃናት አመጋገብ የተጻፉ የታሪክ መጻሕፍት ጡት ያልጠቡት ሕፃናት ጡት ከጠቡት ይልቅ ለተመጣጣኝ ምግብ እጦትና በተላላፊ በሽታዎች የመጠቃት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ያቀርባሉ።”

ጡት ማጥባት ሕፃናትን ከሞት ያድናል

ሁሉም እናቶች ልጆቻቸውን በመጀመሪያዎቹ ከአራት እስከ ስድስት ወራት ዕድሜያቸው ጡት ቢያጠቡ ኖሮ በዓለም ዙርያ በየዓመቱ የሚሞቱትን የአንድ ሚልዮን ሕፃናት ሕይወት ማትረፍ ይቻል እንደነበር የዓለም ጤና ድርጅት ዘግቧል። ስቴት ኦቭ ዘ ወርልድስ ችልድረን 1992 (በ1992 የዓለም ሕፃናት ሁኔታ) በሚል ርዕስ ዩኒሴፍ ያቀረበው ሪፖርት “በአንድ ድሀ ማኅበረሰብ ውስጥ ጡጦ የሚጠባ ሕፃን ጡት ብቻ ከሚጠባው ሕፃን የበለጠ 15 እጅ በተቅማጥ በሽታ 4 እጅ ደግሞ በኒሞኒያ (በሳንባ ምች) የመሞት ዕድል አለው” ብሏል።

ለምን? አንዱ ምክንያት ዱቄት ወተት በምግብነቱ ከእናት ጡት ወተት ያነሰ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ ንጹሕ ባልሆነ ውኃ ከመጠን በላይ ቀጥኖ ስለሚበጠበጥ ነው። ሕፃኑ የሚጠባው ጡጦ በሽታ ከሚያመጡ ተሕዋስያን ሙሉ በሙሉ የፀዳ አይደለም። ስለዚህ ሕፃኑ በጡጦ የሚጠባው ወተት በታዳጊ አገሮች ለሕፃናት መሞት ዋነኛ ምክንያት የሆኑትን የተቅማጥና የመተንፈሻ አካል በሽታዎች በሚያመጡ ባክቴሪያዎችና ቫይረሶች በቀላሉ ሊበከል ይችላል። በቀጥታ ከጡት የሚገኘው ወተት ግን በሽታ በሚያመጡ ተዋሕስያን በቀላሉ አይበከልም፣ ከሌላ ነገር ጋር መቀየጥ አያስፈልገውም፣ አይበላሽም ወይም ከመጠን በላይ ሊቀጥን አይችልም።

ጡት ማጥባት ሕፃናትን ከሞት የሚያድንበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የእናት ጡት ወተት አንቲቦዲስ (ፀረ እንግዳ አካሎች) የሚባሉ የተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ ኃይሎችን ስለያዘ ሕፃኑ በቀላሉ በበሽታ እንዳይጠቃ ይረዳዋል። ጡት የሚጠቡ ሕፃናት የተቅማጥ በሽታ ወይም ሌላ ተላላፊ በሽታ ቢይዛቸውም እንኳ ጡት እንደማይጠቡት አይጠናባቸውም። በሽታ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ስለሚያገኙ ቶሎ ይሻላቸዋል። በተጨማሪም ጡት የጠቡ ሕፃናት በጥርስ በሽታ፣ በካንሰር፣ በስኳር በሽታና በልዩ ልዩ የአለርጂ በሽታዎች የመያዝ ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ከዚህም በላይ ሕፃናት ጡት ለመጥባት በኃይል መሳብ ስለሚያስፈልጋቸው የሕፃናቱ የፊት አጥንቶችና ጡንቻዎች በትክክል እንዲያድጉ ይረዳል።

ጡት የሚያጠቡ እናቶች የሚያገኟቸው ጥቅሞች

ጡት ማጥባት ሕፃኑን ብቻ ሳይሆን እናቲቱንም ይጠቅማል። እናቲቱ ጥቅም ከምታገኝባቸው መንገዶች አንደኛው ሕፃኑ ጡቷን መጥባቱ ሰውነቷ ኦክሲቶሲን የተባለውን ሆርሞን እንዲያመነጭ ያደርገዋል። ይህ ሆርሞን ደግሞ ጡቷ የበለጠ ወተት እንዲያወጣ ከመርዳቱ በተጨማሪ ማኅፀኗ እንዲኮማተር ያደርጋል። የእናቲቱ ማኅፀን ወዲያው እንደወለደች መኮማተሩ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ደም እንዳይፈሳት ይረዳል። በተጨማሪም ጡት ማጥባት በማኅፀን ውስጥ እንቁላል የሚፈጠርበትንና የወር አበባ እንደገና የሚመጣበትን ጊዜ ያዘገየዋል። ይህም ቀጣዩን የእርግዝና ጊዜ ያራዝማል። የእርግዝና ወቅቶችን ማራዘም ማለት ደግሞ እናቶችና ሕፃናት ይበልጥ ጤናማ እንዲሆኑ መርዳት ነው።

ሴቶች ጡት በማጥባታቸው የሚያገኙት ሌላው ትልቅ ጥቅም እንቁላል አመንጭ የሆነው የመራቢያ አካላቸውና (በእንግሊዝኛ ኦቫሪ ተብሎ የሚጠራው) ጡታቸው በካንሰር በሽታ የመያዛቸውን አጋጣሚ መቀነሱ ነው። ልጅዋን ጡት የምታጠባ ሴት በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድሏ ልጅዋን ባታጠባ ከሚኖራት የመያዝ ዕድል በግማሽ እንደሚቀንስ አንዳንድ ጠበብት ይናገራሉ።

ጡት ማጥባት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ውስጥ ሳይወሳ መታለፍ የሌለበት በእናትና በልጅ መካከል የሚኖረው ትስስር ነው። ጡት ማጥባት ሕፃኑን ከመመገብ በተጨማሪ የቃል ግንኙነት ለማድረግ፣ ቆዳ ለቆዳ ለመነካካትና ሙቀት ለመስጠትም ስለሚያስችል በእናትና በልጅ መካከል በጣም ጠቃሚ የሆነ ትስስር እንዲመሠረት ይረዳል። ይህም ለልጁ ስሜታዊና ማኅበራዊ እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ጡት ለማጥባት መወሰን

ሁሉም እናቶች አንዳንድ ሁኔታዎች ከተሟሉላቸው ለልጆቻቸው የሚበቃ ወተት ይኖራቸዋል። በተቻለ መጠን ወዲያውኑ ማለትም ሕፃኑ በተወለደ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ጡት መጥባት መጀመር ይኖርበታል። (የመጀመሪያው ወፈር ያለና ቢጫ ቀለም ያለው እንገር የሚባለው የጡት ወተት ለሕፃናት ጥሩ ነው። በበሽታ እንዳይለከፉም ይከላከልላቸዋል።) ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ቋሚ የማጥቢያ ፕሮግራም ማውጣት አያስፈልግም። በተወሰነ ፕሮግራም ሳይሆን ሕፃኑ ባስፈለገው ጊዜ ሁሉ ሌሊትም ሳይቀር ጡት ሊሰጠው ይገባል። በተጨማሪም ሕፃኑን ለመጥባት እንዲያመቸው አስተካክሎ መያዝ አስፈላጊ ነው። ይህን በተመለከተ ጥሩ ልምድ ያለውና የእናቲቱ ችግር የሚገባው ሰው ማማከር ይቻ⁠ላል።

እርግጥ ነው፣ አንዲት እናት ልጅዋን ጡት ለማጥባትም ሆነ ላለማጥባት የምታደርገው ውሳኔ የሚመካው ባላት አካላዊ አቅም ብቻ አይደለም። ዘ ስቴት ኦቭ ወርልድስ ችልድረን 1992 (በ1992 በዓለም ያሉ ሕፃናት የሚገኙበት ሁኔታ) “እናቶች በጥሩ ሁኔታ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጉ ከተፈለገ የሆስፒታሎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ጡት ማጥባታቸውን እንዲቀጥሉ ከተፈለገ ግን የአሠሪዎች፣ የሠራተኛ ማኅበራትና የኅብረተሰቡ በተለይም የወንዶች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ብሏል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ጡት ማጥባት

1. ለአንድ ሕፃን በመጀመሪያዎቹ ከአራት እስከ ስድስት ወራት ዕድሜ ከጡት የተሻለ ምግብና መጠጥ መስጠት አይቻልም።

2. ሕፃናት በተቻለ መጠን እንደተወለዱ ወዲያውኑ ጡት መጥባት መጀመር ይኖርባቸዋል። ልጅዋን ጡት ማጥባት የማትችል እናት የለችም ማለት ይቻላል።

3. ለሕፃኑ የሚበቃ የጡት ወተት እንዲወጣ አዘውትሮ ማጥባት ያስፈልጋል።

4. ጡጦ ማጥባት በሕፃኑ ላይ ከባድ ሕመም አልፎ ተርፎም ሞት ሊያስከትል ይችላል።

5. ልጁ ሁለት ዓመት እስኪሆነው ድረስ ከተቻለም ከዚያ ለበለጠ ጊዜ ጡት መጥባቱን መቀጠል ይኖርበ⁠ታል።

ምንጭ:- ዩኒሴፍ፣ የዓለም ጤና ድርጅትና ዩኔስኮ በመተባበር ያሳተሙት ፋክትስ ፎር ላይፍ የተባለ የእንግሊዝኛ ጽሑፍ።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጡት ማጥባትና ኤድስ

በ1992 በሚያዝያ ወር ማለቂያ ላይ በዓለም ጤና ድርጅትና በዩኒሴፍ አስተባባሪነት በዓለም አቀፍ ከሚገኙ ጠበብት የተውጣጣ አንድ ቡድን ጡት ማጥባት ከኤድስ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጥናት ስብሳባ አካሂዶ ነበር። በዓለም ጤና ድርጅት የኤድስ ዓለም አቀፍ ፕሮግራም ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ማይክል ሜርሰን ስብሰባው አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ገልጸው ነበር። እርሳቸውም “ለሕፃኑ ሕልውና አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ጡት መጥባቱ ነው። አንድ ሕፃን ጡት በመጥባቱ ምክንያት የሚደርስበትን በኤድስ የመሞት አደጋ ጡት ባለመጥባቱ ከሚደርሱበት ሌሎች አደጋዎች ጋር አመዛዝኖ መመልከት ይገባል” ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በኤች አይ ቪ ከተለከፉ እናቶች ከሚወለዱት ሕፃናት መካከልም አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በቫይረሱ ይለከፋሉ። የኤድስ በሽታ ጡት በማጥባት ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ እንደሚችል የሚያሳዩ ማስረጃዎች ቢኖሩም በአብዛኛው ግን ከእናት ወደ ልጅ የሚተላለፈው በእርግዝናና በወሊድ ጊዜያት ነው። ይሁን እንጂ የዓለም ጤና ድርጅት “በኤች አይ ቪ የተለከፉ እናቶችን ጡት ከጠቡት ሕፃናት መካከል አብዛኞቹ ጡት በመጥባታቻው በበሽታው አይያዙም” በማለት አብራርቷል።

የጠበብቱ ቡድን ከሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሷል:- “አብዛኞቹ ሕፃናት በኢንፌክሽንና በተመጣጣኝ ምግብ እጦት ምክንያት በሚሞቱባቸውና የሚሞቱ ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ለነፍሰ ጡር ሴቶች፣ በኤች አይ ቪ ለተበከሉ ጭምር ጡት ማጥባት እንደሚገባቸው ምክር ሊሰጣቸው ይገባል። ምክንያቱም ሕፃናቱ ጡት በመጥባታቸው በኤች አይ ቪ ቫይረስ ከመያዛቸው ይበልጥ ጡት ባለመጥባታቸው ምክንያት የሚደርስባቸው አደጋ ስለሚያመዝን ነው።

“በሌላ በኩል ደግሞ ሕፃናትን በጨቅላነታቸው በኢንፌክሽን በሽታዎች ምክንያት በብዛት በማይሞቱባቸውና የሕፃናት ሞት በማይበዛባቸው አካባቢዎች . . . በኤች አይ ቪ ለተለከፉ ነፍሰ ጡር ሴቶች የሚሰጠው ምክር ልጆቻቸውን ጡት ከማጥባት ይልቅ አስተማማኝ የሆነ ሌላ የመመገቢያ አማራጭ እንዲጠቀሙ የሚያሳስብ መሆን ይኖርበታል።”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ