ከተሸነቆረው ዖዞን በታች የተከሰቱ እንግዳና አስፈሪ ነገሮች
በቺሊ ደቡባዊ ጫፍ በምትገኘው ፑንታ አሬናስ የተባለች ከተማ የሚኖሩት 125,000 ነዋሪዎች የምንኖረው “በዓለም ጫፍ ላይ ነው” እያሉ ይቀልዱ ነበር። ባለፈው ዓመት የተፈጸመው እንግዳና አስፈሪ ክስተት ግን ቀልዱን እውነት ሊያስመስለው ተቃርቧል። አንዳንድ ሳይንቲስቶች “እዚህ ቦታ ከፀሐይ በታች እየተፈጸመ ያለ አዲስ ነገር ሳይኖር አይቀርም” እያሉ ማሰብ ጀምረዋል። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ በጥር 12, 1993 እትሙ ላይ ያወጣው አንድ ዘገባ ስለ ጉዳዩ አንዳንድ ዝርዝር መግለጫዎችን ይሰጣል።
በዚህ አገር በሚገኘው ማላጋንስ ዩኒቨርሲቲ የከባቢ አየር አጥኚዎች ቡድን አባል የሆኑት ፌሊክስ ሳሞራኖ እንዲህ ሲሉ ሪፖርት አድርገዋል:– “በጥቅምት ወር እስከ ዛሬ ከተመዘገበው ሁሉ ያነሰ የዖዞን መጠን መዝግበናል። የዖዞኑ ሽፋን በሦስት ቀናት ውስጥ ከትክክለኛው መጠኑ በግማሽ በመቀነስ ሳስቶ ከቆየ በኋላ አደገኛ ደረጃ ከሚባለው መጠን እንኳን አነሰ።” ጆርናሉ በተሸነቆረው የዖዞን ሽፋን በኩል የሚገባው የአልትራቫዮሌት ጨረር መጠን መጨመሩ “የቆዳ ካንሰርና ካታራክት የሚባል የዓይን በሽታ ከማስከተሉ በተጨማሪ ውኃ ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት መሠረታዊ ምግብ በሆነው ፋይቶፕላንክተን ላይ ችግር እንዲፈጠር ያደርጋል” ሲል ገልጿል።
ባለፈው ዓመት ራድቮን ቪሊቺች የተባሉ ሰው ካሏቸው 1,200 ከብቶች መካከል ግማሾቹ የዓይን ቆባቸው የውስጠኛው ክፍል (ኮንጀንክቲቫ) በመታመሙ ምክንያት በመታወራቸው ልክ እንደ መኪና እርስ በርስ ይጋጩ ነበር። አምስቱ ደግሞ ምግባቸው ያለበትን ቦታ ማወቅ ስለተሳናቸው ተርበዋል።”
የጆርናሉ ዘገባ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:– “ሆሴ ባሞንዴም እንዲሁ ዓይነት ነገር እንዳጋጠመው ተናግሯል። ከዚህ 125 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የእርሻ ቦታው ላይ ሆኖ ውብ የሆነውን የማጀላን የባሕር ሰርጥ ማየት ይቻላል። 4,300 የሚሆኑት በጎቹ ግን ይህንን ቦታም ሆነ ምንም ዓይነት ሌላ ነገር ማየት አይችሉም። ከበጎቹ ውስጥ 10% የሚሆኑት የዓይን ኢንፌክሽን ስላለባቸው ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን 200 የሚሆኑት ደግሞ በዚያው ዓመት ታውረዋል።”
የቆዳ ሐኪም የሆኑት ሂማ አባርካ “እዚህ እየተፈጸመ ያለው ነገር በዓለም ሆኖ የማያውቅ አዲስ ነገር ነው። ከማርስ የመጡ ሰዎች ምድራችን ላይ የማረፋቸውን ያህል ያልተለመደ ነገር ነው” ብለዋል። ወደርሳቸው የሚመጡት የቆዳ በሽተኞች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል። በፀሐይ የተለበለቡ ሰዎች ብዛት ያስደነግጣል፤ እንዲሁም ከሜላኖማ ካንሰር ይበልጥ አደገኛ የሆነ አዲስ ዓይነት የቆዳ ካንሰር የያዛቸው ሰዎች ቁጥር ከሌላው ጊዜ በአምስት እጥፍ ጨምሯል። እኚህ ሰው ይህ ሁኔታ እየጨመረ ከመጣው የአልትራቫዮሌት ጨረር ጋር አንድ ዓይነት ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም ብለው ያምናሉ።
ሁኔታው የፑንታ አሬናስን ነዋሪዎች እያሳሰባቸው ሄዷል። አንድ መድኃኒት ቤት በዚህ ዓመት የሸጠው የፀሐይ ጨረር መከላከያ ቅባት ካለፈው ዓመት በ40 በመቶ ይበልጣል። የየዕለቱን የአልትራቫዮሌት ጨረር መጠን ወደሚናገር ድርጅት ስልክ ደውሎ መጠኑን ማወቅ ይቻላል። የአገሪቱ ሦስት ራዲዮ ጣቢያዎችም መጠኑን ለሕዝብ ያሳውቃሉ። ተማሪዎች ኮፍያ እንዲያደርጉ፣ የፀሐይ ጨረር መከላከያ ቅባት እንዲቀቡና የፀሐይ መነጽር እንዲያደርጉ በትምህርት ቤት ይነገራቸዋል። አንድ መደብር የሚሸጣቸው የፀሐይ መነጽሮች ብዛት 30 በመቶ ከፍ ብሏል። አንድ “የአካባቢው ገበሬ ደግሞ ለበጎቹ የፀሐይ መነጽር ሊያሠራላቸው እየሞከረ ነው።”
ስካርፓ የተባሉት የአካባቢው አስተዳዳሪ እንዲህ ብለዋል:– “እውነታውን ለመካድ አልችልም። . . . ግን ምን ማድረግ ይቻላል? አካባቢውን በጠቅላላ የሚሸፍን ጣሪያ ልንሠራ አንችልም።”