የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 10/8 ገጽ 5-9
  • ልጆቻችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልጆቻችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ልጃችሁን አስተምሩ!
  • የምትሰጡት ሥልጠና የተሟላ ይሁን
  • እንደ እባብ ብልሆች
  • ልጆቻችሁን ከጥቃት መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
    ንቁ!—2007
  • በቤት ውስጥ እንዳይከሰት መከላከል
    ንቁ!—1997
  • ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ፆታ ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 10/8 ገጽ 5-9

ልጆቻችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

“ለማንም እንዳትናገሪ። ምሥጢር ነው።”

“ብትናገሪ ማንም አያምንሽም።”

“ከተናገርሽ ወላጆችሽ ይጠሉሻል። ደግሞ የአንቺ ጥፋት እንደሆነ ያውቃሉ።”

“ጓደኝነታችን እንዲቀጥል አትፈልጊም?”

“እኔ እንድታሰርብሽ ትፈልጊያለሽ?”

“ብትናገሪ አባትና እናትሽን እገድላቸዋለሁ።”

በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙ ሰዎች ርካሽ የጾታ ፍላጎታቸውን ለማርካት ልጆችን መሣሪያ አድርገው ከተጠቀሙባቸው፣ ሕይወታቸውን ስጋት ላይ ከጣሉትና ምንም የማያውቁትን ምስኪን ልጆች ካበላሿቸውም በኋላ እንኳ ከእነሱ የሚፈልጉት ነገር አለ፤ ዝም እንዲሉ ይፈልጋሉ። ዝም እንዲሉ ለማድረግ ደግሞ እንዲያፍሩ ያደርጓቸዋል፣ ምሥጢር እንደሆነ ይነግሯቸዋል፣ አልፎ ተርፎም በቀጥታ ያስፈራሯቸዋል። በዚህ መንገድ ልጆች በጾታ የማስነወርን ድርጊት መከላከል የሚችሉበትን ከሁሉ የተሻለ መሣሪያ ይነጠቃሉ፤ ለአንድ አዋቂ ሰው ነግረው ከለላ እንዲሆናቸው መጠየቅ የሚችሉበትን የመናገር መብት ይገፈፋሉ።

የሚያሳዝነው፣ ብዙውን ጊዜ አዋቂ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ሳያውቀው ልጆችን በጾታ ከሚያስነውሩ ሰዎች ጋር የሚተባበር መሆኑ ነው። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ለአደጋው ንቁ ለመሆን ፈቃደኛ አይደለም፤ ከዚህም በላይ እንዲያው ተከድኖ ይብሰል የሚል ፈሊጥ የሚያራምድና ብዙውን ጊዜ ይህን ድርጊት እንደ ተረት አድርጎ የሚመለከት ነው። አለማወቅ፣ የተሳሳተ መረጃና ነገሩ በምሥጢር መያዙ ከለላ የሚሆነው ለጥቃቱ ሰለባዎች ሳይሆን ድርጊቱን ለሚፈጽሙት ሰዎች ነው።

ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የካቶሊክ ጳጳሳት በካናዳ ባካሄዱት ኮንፈረንስ የካቶሊክ ቀሳውስት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ልጆችን በጾታ የማስነወር ጸያፍ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው “ነገሩን በምሥጢር ለመያዝ የተደረገው ሴራ” ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ታይም መጽሔት እጅግ የተስፋፋውን በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚፈጸመውን የጾታ ግንኙነት አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ ላይ በቤተሰቦች ውስጥ “ይህን የመሰለ አሳዛኝ ድርጊት መፈጸሙን እንዲቀጥል አስተዋጽኦ የሚያደርገው” ‘ነገሩን በምሥጢር ለመያዝ የሚደረገው ሴራ’ እንደሆነ ገልጿል።

ይሁን እንጂ ይህ ሴራ በመጨረሻ እየከሸፈ እንደመጣ ታይም መጽሔት ዘግቧል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በትምህርት አማካኝነት ነው። ኤዥያዊክ የተባለው መጽሔት ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ልጆችን የማስነወር ድርጊትን ለመከላከል የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መሣሪያ ሕዝቡ እንዲያውቀው ማድረግ እንደሆነ ሁሉም ጠበብት ይስማሙበታል።” ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ እንዲችሉ የዚህን አደጋ እውነታዎች መገንዘብ አለባቸው። ለልጆች ሳይሆን ልጆችን ለሚያስነውሩ ሰዎች ከለላ በሆኑ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ተታልላችሁ እውነታው ሊጨልምባችሁ አይገባም።—ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከቱ።

ልጃችሁን አስተምሩ!

ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እውቀት፣ ጥበብና የማሰብ ችሎታ ‘ከክፉ መንገድ፣ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩ ሰዎችም’ ሊጠብቁት እንደሚችሉ ለልጁ ነግሮት ነበር። (ምሳሌ 2:10-12) ልጆች የሚያስፈልጋቸው ይህ አይደለምን? ቻይልድ ሞለስተርስ:- ኤ ቢሄቭየራል አናሊስስ የተባለው የኤፍ ቢ አይ ፓምፍሌት “ዋነኛ የጥቃቱ ሰለባ” በሚል ርዕስ ሥር እንዲህ ይላል:- “አብዛኞቹ ልጆች ስለ ጾታ መወያየትን እንደ ነውር ይቆጥሩታል፤ በተለይ ወላጆቻቸው ጾታን አስመልክቶ ትክክለኛውን ነገር አይነግሯቸውም።” ልጆቻችሁ “ዋነኛ የጥቃቱ ሰለባዎች” እንዲሆኑ መፍቀድ የለባችሁም። ስለ ጾታ አስተምሯቸው።a ለምሳሌ ያህል ማንኛውም ልጅ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከመድረሱ በፊት በዚህ የዕድሜ ክልል ላይ ስለሚከሰቱት አካላዊ ለውጦች ማወቅ ይኖርበታል። ይህን አለማወቃቸው ግራ እንዲጋቡና እንዲያፍሩ የሚያደርጋቸው ከመሆኑም በላይ ለአደጋ የተጋለጡ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ጃኔት (ስሟን ለውጠነዋል) በልጅነቷ በጾታ የማስነወር ወንጀል ተፈጽሞባት የነበረ ሲሆን ከብዙ ዓመታት በኋላ ደግሞ ሁለት ልጆቿ እንደዚሁ በጾታ የማስነወር ወንጀል ተፈጽሞባቸዋል። ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ ብላለች:- “በልጅነታችን በቤተሰባችን ውስጥ ፈጽሞ ስለ ጾታ አናወራም ነበር። ስለዚህ ካደግኩም በኋላ ስለ ጾታ ማውራት ያሳፍረኝ ነበር። እንደ ነውር እቆጥረው ነበር። ልጆች ስወልድም ይህ አመለካከቴ አልተለወጠም። ከሌሎች ሰዎች ልጆች ጋር ስለ ጾታ ማውራት እችላለሁ፤ ከራሴ ልጆች ጋር ማውራት ግን ያሳፍረኛል። ይህ ደግሞ ጥሩ አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ልጆቻችሁን ስለ ጾታ የማትነግሯቸው ከሆነ ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።”

ልጆች በጾታ እንዳይነወሩ እንዴት መከላከል እንደሚችሉ ገና ትንንሽ እያሉ ልታስተምሯቸው ትችላላችሁ። ልጆቻችሁን እንደ የሴት የጾታ ብልት፣ ጡት፣ ፊንጢጣና የወንድ የጾታ ብልት ያሉትን ስሞች ስታስተምሯቸው እነዚህ ብልቶች ጥሩና ልዩ የሰውነት ክፍሎች እንደሆኑና ማንም ሊነካቸው እንደማይገባ ንገሯቸው። “ሌሎች ሰዎች እነዚህን የሰውነት ክፍሎች መንካት አይፈቀድላቸውም፤ እማዬና አባዬም እንኳ መንካት አይችሉም፤ ሐኪምም ቢሆን እንኳ እማዬ ወይም አባዬ እስካልፈቀዱ ድረስ መንካት አይችልም።”b ሁለቱም ወላጆች ወይም እያንዳንዱ ሞግዚትና አሳዳጊ እንዲህ እያለ ቢነግራቸው ጥሩ ይሆናል።

ሼሪል ክሬዘር ዘ ሴፍ ቻይልድ ቡክ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ልጆች በጾታ የሚያስነውርን ሰው ትኩረት የመንፈግ፣ የመጮኽ አሊያም ደግሞ ሮጦ የማምለጥ ነጻነት ሊሰማቸው የሚገባ ቢሆንም በጾታ የተነወሩ ብዙዎቹ ልጆች በወቅቱ እንደዚያ ማድረጉ ነውር ሆኖ ታይቷቸው እንደነበረ ገልጸዋል። ስለዚህ ልጆች አንዳንድ ትልልቅ ሰዎች መጥፎ ነገር እንደሚያደርጉና እንዲያውም መጥፎ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ የሚነግራቸውን ማንኛውንም ሰው መታዘዝ እንደሌለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል። በዚህ ጊዜ ልጆች ዳንኤልና ጓደኞቹ በባቢሎን የነበሩ ትልልቅ ሰዎች ርኩስ የሆነ ምግብ እንዲበሉ በጠየቋቸው ጊዜ እንዳደረጉት እምቢ ለማለት ሙሉ መብት አላቸው።—ዳንኤል 1:4, 8፤ 3:16-18

በአብዛኛው የሚሠራበት አንዱ የማስተማሪያ ዘዴ በጨዋታ መልክ ልጆችን “እንዲህ ቢሆን ምን ታደርጋለህ/ጊያለሽ?” እያሉ መጠየቅ ነው። ለምሳሌ ያህል “አስተማሪህ አንድን ልጅ እንድትመታው ቢያዝህ ምን ታደርጋለህ?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ወይም ደግሞ “(እማዬ፣ አባዬ፣ አንድ ቄስ፣ አንድ ፖሊስ) ከአንድ ትልቅ ፎቅ ላይ ዝለል ቢሉህ ምን ታደርጋለህ?” ብላችሁ ጠይቁት። የልጁ መልስ አጥጋቢ ያልሆነ ወይም ደግሞ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፤ ቢሆንም ልጁን በቁጣ ከማረም ተቆጠቡ። ጨዋታው የሚያስደነግጥ ወይም ልጁን የሚያሸብር ዓይነት መሆን የለበትም፤ እንዲያውም ጨዋታው ረጋ ባለ መንፈስ፣ በፍቅርና በሚያዝናና ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት የሙያው ጠበብት ይናገራሉ።

ከዚህ በመቀጠል ልጆች ተገቢ ያልሆኑ ወይም ደግሞ ስሜታቸውን የሚረብሹና የሚያስጨንቋቸውን የፍቅር መግለጫዎች እንዴት መቃወም እንደሚችሉ አስተምሯቸው። ለምሳሌ ያህል “የእማዬ ወይም የአባዬ ጓደኛ ስሜትህን/ሽን በሚረብሽ ወይም በሚያስጨንቅ መንገድ ሊስምህ/ሽ ቢፈልግ ምን ታደርጋለህ/ጊያለሽ?” ብላችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ።c ብዙውን ጊዜ “እያስመሰሉ” በመጫወት ልጁ ወይም ልጅቷ የሚያደርጉትን ነገር በተግባር እንዲያሳዩ ማበረታታቱ ጥሩ ነው።

ልጆች በጾታ የሚያስነውሩ ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን ሌሎች ዘዴዎችም መቃወም የሚችሉበትን መንገድ በዚሁ ዓይነት ሁኔታ ሊማሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ሴት ልጃችሁን “አንድ ሰው ‘እኔ እኮ በጣም ነው የምወድሽ። የእኔ ጓደኛ መሆን አትፈልጊም?’ ቢልሽስ?” ብላችሁ ልትጠይቋት ትችላላችሁ። ልጆቹ እንዲህ ዓይነት የማታለያ ዘዴዎችን እንዴት መቃወም እንደሚችሉ ካወቁ በኋላ ሌሎች ዘዴዎችንም እያነሳችሁ ጠይቋቸው። “አንድ ሰው ‘እኔ ብበሳጭ ደስ ይልሻል?’ ቢልሽ ምን ትይዋለሽ?” ብላችሁ ልትጠይቋት ትችላላችሁ። ልጆቻችሁ በቃልና ጠንካራ አቋምን በሚያንጸባርቅ አካላዊ መግለጫ እንዴት አይሆንም ማለት እንደሚችሉ አሳዩአቸው። ብዙውን ጊዜ በጾታ የሚያስነውሩ ሰዎች በመጀመሪያ የረቀቁ የማባበያ ቃላት በመሰንዘር የልጆቹን ሁኔታ ለማወቅ እንደሚሞክሩ አትዘንጉ። ስለዚህ ልጆች አጥብቀው መቃወምንና “እናገርብሃለሁ” ማለትን እንዲማሩ ማድረግ ያስፈልጋል።

የምትሰጡት ሥልጠና የተሟላ ይሁን

እንዲህ ዓይነቱ ሥልጠና የሚሰጠው አንድ ጊዜ ብቻ መሆን የለበትም። ልጆች ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ሊነገራቸው ይገባል። የምትሰጡት ማሰልጠኛ ምን ያህል ግልጽ መሆን እንዳለበት ለመወሰን የራሳችሁን የማመዛዘን ችሎታ ተጠቀሙ። ሆኖም ሥልጠናችሁ የተሟላ ይሁን።

ለምሳሌ ያህል በጾታ የሚያስነውሩ ሰዎች ልጆቹ ጉዳዩን በምሥጢር እንዲይዙ ቃል ለማስገባት የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች ሁሉ አስቀድማችሁ ለልጆቻችሁ ልትነግሯቸው ይገባል። ልጆች አንድ አዋቂ ሰው ምንም ነገር ከወላጆቻቸው ደብቀው በምሥጢር እንዲይዙ ሊነግራቸው እንደማይገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል። ማንኛውንም ነገር፣ እንደማይናገሩ ቃል የገቡትንም ነገር እንኳ ሳይቀር ምንጊዜም ከእናንተ ሊደብቁ እንደማይገባ ንገሯቸው። (ከዘኁልቁ 30:12, 16 ጋር አወዳድር።) አንዳንድ በጾታ የሚያስነውሩ ሰዎች ልጅቷ አንድ ያጠፋችው ጥፋት እንዳለ የሚያውቁ ከሆነ ይህን እንደ ማስፈራሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። “አንቺ ካልተናገርሺብኝ እኔም አልናገርብሽም” ይሏታል። ስለዚህ ልጆች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ወቅትም እንኳ ቢናገሩ ወላጆቻቸው ምንም እንደማያደርጓቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ቢናገሩ ምንም እንደማይሆኑ ንገሯቸው።

ለልጆቻችሁ የምትሰጡት ሥልጠና ማስፈራሪያንም መቋቋም የሚያስችላቸው ዓይነት መሆን ይገባዋል። በጾታ የሚያስነውሩ አንዳንድ ሰዎች ልጆቹ ፊት ትንንሽ እንስሳትን በመግደል የተፈጸመባቸውን ድርጊት ከተናገሩ ወላጆቻቸውን ልክ እንደዚያ እንስሳ እንደሚገድሏቸው በመናገር ያስፈራሯቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ ታናናሽ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በጾታ እንደሚያስነውሩ በመናገር አስፈራርተዋቸዋል። ስለዚህ በጾታ የሚያስነውር ሰው የፈለገውን ብሎ ቢያስፈራራቸው ምንጊዜም ከመናገር መቆጠብ እንደሌለባቸው ንገሯቸው።

በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ የማስተማሪያ መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ሁሉን ማድረግ የሚችለውን የይሖዋን ኃይል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ በጾታ የሚያስነውሩ ሰዎችን ማስፈራሪያ እንዳይፈሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። ልጆች ምንም ዓይነት ማስፈራሪያ ቢነገራቸው ይሖዋ ሕዝቡን መርዳት እንደሚችል እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል። (ዳንኤል 3:8-30) ክፉ ሰዎች ይሖዋ በሚወዳቸው ሰዎች ላይ ጉዳት በሚያደርሱበት ጊዜም እንኳ ይሖዋ ምንጊዜም የደረሰውን ጉዳት በማስወገድ ሁኔታውን ማስተካከል ይችላል። (ኢዮብ ምዕራፍ 1 እና 2፤ 42:10-17፤ ኢሳይያስ 65:17) ይሖዋ መጥፎ ነገር የሚሠሩ ሰዎችንና እነዚህን ሰዎች ለመቋቋም የተቻላቸውን ያህል የሚጥሩትን ጥሩ ሰዎች ጨምሮ ሁሉንም ነገር እንደሚመለከት ንገሯቸው።—ከዕብራውያን 4:13 ጋር አወዳድር።

እንደ እባብ ብልሆች

ልጆችን በጾታ ከሚያስነውሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ለመፈጸም ኃይል አይጠቀሙም። ብዙውን ጊዜ ልጆቹን በወዳጅነት መንፈስ መቅረብ ይመርጣሉ። ስለዚህ ኢየሱስ “እንደ እባብ ብልኆች” ሁኑ ሲል የሰጠው ምክር ተስማሚ ነው። (ማቴዎስ 10:16 የ1980 ትርጉም) አፍቃሪ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው በጾታ እንዳይነወሩ ለመጠበቅ ከሚያስችሏቸው ጠቃሚ መንገዶች አንዱ የቅርብ ክትትል ማድረግ ነው። በልጆች ላይ ወሲባዊ ጥቃት የሚፈጽሙ አንዳንድ ሰዎች ሕዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ብቻቸውን የሆኑ ልጆች ይፈልጉና የልጆቹን የማወቅ ፍላጎት ለመቀስቀስ ውይይት ይጀምራሉ። (“ሞተር ብስክሌት ትወዳለህ?” “ነይ፣ መኪናዬ ውስጥ ያሉትን ቡችሎች ላሳይሽ” ይሏቸዋል።) ሁልጊዜ ከልጆቻችሁ ጋር መሆን እንደማትችሉ የታወቀ ነው። ልጆችን በመንከባከብ ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም ልጆች ብቻቸውን መንቀሳቀስ የሚችሉበት የተወሰነ ነጻነት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይገነዘባሉ። ሆኖም አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ገና በለጋ ዕድሜ ላይ ላሉ ልጆቻቸው ከልክ ያለፈ ነፃነት አይሰጧቸውም።

ከልጆቻችሁ ጋር የሚቀራረቡትን አዋቂ ሰዎች ወይም በዕድሜ ከፍ ያሉ ወጣቶች በሚገባ ማወቅ ይኖርባችኋል። እናንተ በማትኖሩበት ጊዜ ልጆቻችሁን መጠበቅ ያለበት ማን እንደሆነ ስትወስኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ። ልጆቻችሁ እንዲጨነቁ ወይም ስሜታቸው እንዲረበሽ የሚያደርግ ነገር የሚፈጽሙ ሞግዚቶችን በጥርጣሬ ዓይን ልትመለከቷቸው ይገባል። ልክ እንደዚሁም በትንንሽ ልጆች ላይ ዓይናቸውን የሚጥሉና እኩዮቻቸው የሆኑ ጓደኞች የሌሏቸውን በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶችንም ማመን የለባችሁም። ልጆቻችሁ የሚውሉባቸውን ቦታዎችና ትምህርት ቤቶች በሚገባ መርምሩ። ግቢውን በሙሉ ዞራችሁ ተመልከቱ፤ ሠራተኞቹን በማነጋገር ከልጆች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጥሩ አድርጋችሁ አጥኑ። ባልታሰበ ሰዓት ድንገት መጥታችሁ ልጆቻችሁን ማየት ትችሉ እንደሆነ ጠይቋቸው፤ ካልፈቀዱላችሁ ልጆቻችሁን ወደ ሌላ ቦታ አዛውሩ።—የታኅሣሥ 8, 1987 ንቁ! መጽሔት ገጽ 3-11 ተመልከት።

የሚያሳዝነው ግን በጣም ጠንቃቃ የሆኑ ወላጆችም እንኳ በልጆቻቸው ላይ የሚደርሰውን ነገር ሁሉ መቆጣጠር የማይችሉ መሆናቸው ነው።—መክብብ 9:11

ወላጆች ተባብረው የሚሠሩ ከሆነ አንድ ሊቆጣጠሩት የሚችሉት ነገር አለ፤ በቤታቸው የሚከናወነውን ነገር መቆጣጠር ይችላሉ። ቤት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ልጆች በጾታ የሚነወሩበት ቦታ በመሆኑ የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የየካቲት 22, 1992 ንቁ! (የእንግሊዝኛ) መጽሔት ገጽ 3-11 እና የሐምሌ 8, 1992 ንቁ! (የእንግሊዝኛ) መጽሔት ገጽ 30⁠ን ተመልከት።

b እርግጥ ወላጆች ትንንሽ የሆኑ ልጆችን ማጠብና ልብሳቸውን መቀየር አለባቸው፤ በእንዲህ ዓይነት ጊዜያት ወላጆች እነዚህን ብልቶች ያጥባሉ። ሆኖም ልጆቻችሁ ገና ትንንሽ እያሉ ራሳቸው መታጠብ እንዲችሉ አሰልጥኗቸው፤ በልጆች እንክብካቤ ሙያ የሰለጠኑ አንዳንድ ጠበብት የሚቻል ከሆነ ልጆች ከሦስት ዓመታቸው ጀምሮ የጾታ ብልቶቻቸውን ራሳቸው እንዲያጥቡ ማሠልጠኑ ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ።

c ልጆቻችሁ ሊያቅፋቸው ወይም ሊስማቸው የሚፈልገውን ሰው ሁሉ እንዲያቅፉና እንዲስሙ የምታስገድዷቸው ከሆነ ሥልጠናውን መና ልታስቀሩት እንደምትችሉ አንዳንድ ጠበብት ያስጠነቅቃሉ። ስለዚህ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲህ ያሉ አላስፈላጊ ነገሮች እንዲያደርጉ በሚጠየቁበት ጊዜ ይቅርታ ጠይቀው እንዲህ ዓይነቱን ነገር ማድረግ እንደማይፈልጉ እንዲገልጹ ወይም በዚያ ፋንታ ሌላ ነገር እንዲያደርጉ ያሰለጥኗቸዋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆቻችሁ የሚቀርብላቸውን ተገቢ ያልሆነ ማባበያ በአንደበታቸውም ሆነ ጠንካራ አቋም እንዳላቸው በሚያሳይ አካላዊ መግለጫ እንዲቃወሙ አሠልጥኗቸው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ