የአባቴ የታማኝነት ምሳሌ
ቤተሰባችን በሐምሌ 6, 1947 በእንግሊዝ አገር በለንደን ከተማ ውስጥ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ነበር። ከመጠመቂያ ገንዳ ውስጥ እንድወጣ ሊረዳኝ አባቴ እጁን ሲዘረጋ አይኖቹ የደስታ እንባ አቅርረው ነበር። እኔና አባቴ የአጽናፈ ዓለም ልዑልና ፈጣሪ ለሆነው ለይሖዋ ሕይወታችንን መወሰናችንን ለማሳየት ገና መጠመቃችን ነበር። በዚህ አስደሳች ወቅት እናቴና ሦስቱ ወንድሞቼም ተገኝተው ነበር።
የሚያሳዝነው ግን ቤተሰባችን በክርስቲያን አምልኮ ያገኘው አንድነት ምንም ሳይቆይ መፈራረስ መጀመሩ ነው። ይህንንና የአባቴ የታማኝነት ምሳሌ እኔን እንዴት እንደነካኝ ከመናገሬ በፊት እርሱ ቀደም ሲል ስላሳለፈው ሕይወት ትንሽ ልናገር።
በምሥራቁና በምዕራቡ ዓለም የነበረው አስተዳደግ
አባቴ ሌስተር የተወለደው በመጋቢት 1908 በሆንግ ኮንግ ነበር። አባቱ ረዳት የወደብ ኃላፊ ነበር። አባቴ ልጅ እያለ አባቱ በሆንግ ኮንግ ዙሪያና በአካባቢው ደሴቶች የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በጀልባ ሲጓዝ ይዞት ይሄድ ነበር። ሌስተር ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለ አባቱ ሞተ። ከዚያ በኋላ እናቱ አግብታ ቤተሰቡ ወደ ሻንጋይ ሄደ። በ1920 እናቱ እርሱንና አሥር ዓመት የሞላትን እኅቱን ፊልን ትምህርት ቤት እንዲገቡ ወደ እንግሊዝ አገር ወሰደቻቸው።
አባቴ ቀጣዮቹን ዓመታት ያሳለፈው የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ማደሪያ በሆነው በካንተርቤሪ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ነበር። በቤተ ክርስቲያን ይገኝ ስለነበር ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር የተዋወቀው በዚህ ወቅት ነበር። ፊል በለንደን በስተሰሜን በሚገኝ አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብታ ነበር፤ ነገር ግን እርሷና አባቴ የትምህርት ቤት እረፍታቸውን አንድ ላይ ያሳልፉ ስለነበር በእነዚያ ዓመታት በጣም ተቀራርበዋል። ከአምስት ዓመት በኋላ በ1925 አባቴ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ እናቱ ወደ እንግሊዝ አገር ተመልሳ መጣችና ሥራ አስገባችው። ከዚያ በሚቀጥለው ዓመት ፊሊን ይዛ ወደ ሻንጋይ ተመለሰች።
የሌስተር እናት ተመልሳ ከመሄዷ በፊት ቅድመ አያቱ የጻፈውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ ሰጥታው ነበር። መጽሐፉ “ዘ ላይት ኦቭ ኤዥያ” በሚል ርዕስ የቡድሃን የሕይወት ታሪክ በጥልቀት የሚዘረዝር ነበር። ይህም አባቴ የሕይወት እውነተኛ ትርጉም ምን ይሆን ብሎ እንዲያስብ አደረገው። በካንተርቤሪ እያለ በካቴድራሉ ውበትና በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ታላቅነት ይደነቅ ነበር። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ መመሪያ ለማግኘት አለመቻሉ የባዶነት ስሜት እንዲሰማው አድርጎታል። ስለዚህ የምሥራቃውያን ሃይማኖቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይኖራቸው ይሆን? እያለ ራሱን ይጠይቅ ስለነበር መርምሮ ለማወቅ ወሰነ። በሚቀጥሉት ዓመታትም የቡድሃን፣ የሺንቶን፣ የሂንዱን፣ የኮንፊሺያንንና የእስልምናን ሃይማኖቶች መረመረ። ሆኖም ማናቸውም ቢሆኑ ለጥያቄው መልስ ሊሰጡት አልቻሉም።
አባቴ ተቀጥሮ ይሠራ በነበረበት መሥሪያ ቤት ሥር በሚንቀሳቀሰው ክለብ ውስጥ ይኖር ስለነበር የጀልባ ቀዘፋ፣ የራጊቢ ጨዋታና ሌሎችንም ስፖርቶች ይወድ ነበር። ወዲያው እንደርሱ ለስፖርቶቹ ፍቅር የነበራትን ኤድና የምትባል ማራኪ ልጃገረድ አፈቀረ። በ1929 ተጋቡና በቀጣዮቹ ዓመታት አራት ወንዶች ልጆችን በመውለድ ተባረኩ።
አስከፊዎቹ የጦርነት ዓመታት
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጭጋግ በ19 30ዎቹ ዓመታት እያንዣበበ ስለነበር አባቴ ከለንደን ወደ ገጠሩ ክፍል እንድንሄድ ወሰነ። ከዚያ ቦታ ለቀን የሄድነው ጦርነቱ በመስከረም 1939 ከመፈንዳቱ ከጥቂት ወራት በፊት ነበር።
ለጦርነቱ ምልመላ ተጀምሮ ነበር። ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ ግን ቀስ በቀስ የዕድሜ ገደቡ ተነሳ። አባቴ እስኪመለመል ድረስ ሳይጠብቅ በሮያል አየር ኃይል ውስጥ ለማገልገል ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበና በግንቦት 1941 ተጠራ። አልፎ አልፎ ፈቃድ እየወሰደ ወደ ቤት ይመጣ የነበረ ቢሆንም እንኳን የቤተሰቡ የተለመደ ግንኙነት ከመቀጠሉ በፊት ግን ስድስት ዓመታት አልፈዋል። እኛን የመንከባከቡ ኃላፊነት በእናታችን ላይ ወደቀ። በዚያን ጊዜ ከሁላችንም ትልቅ የነበርነው ሁለታችን ወደ አሥራዎቹ ዕድሜያችን እየገባን ነበር።
መንፈሳዊ ማነቃቂያ
አባቴ ከአየር ኃይል ከመውጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት እናቴን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች አነጋገሯትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች። እናቴ የምትማረው ነገር ምን ያህል እንዳስደሰታት ለአባቴ በደብዳቤ ነገረችው። ለእረፍት መጥቶ በነበረበት ጊዜ በግል ቤት ውስጥ ይደረግ ወደነበረው የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይዛው ሄደች።
አባቴ በታኅሣሥ 1946 ከጦር ሠራዊቱ ሲወጣ እናቴ ከሁለቱ ሴት ምሥክሮች ጋር በምታደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ላይ መገኘት ጀመረ። ፍላጎቱን ስላዩ የጉባኤው መሪ የበላይ ተመልካች የነበረው ወንድም ኤርኒ ቢቮር እንዲጠይቀው አደረጉ። ወንድም ቢቮር በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሞ የአባቴን የተቃውሞ ጥያቄዎች በሙሉ በአንድ ምሽት መለሰለት። ወንድም ቢቮር የሰጠውን ሦስት መጻሕፍት በየዕለቱ በባቡር ለሥራ ወደ ለንደን ሲጓዝ እያነበበ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ጨረሳቸው። በሚቀጥለው ጊዜ ወንድም ቢቮር ተመልሶ ሲጠይቀው አባቴ:- “ስፈልገው የነበረው እውነት ይህ ነው! አሁን ማድረግ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?” ብሎ በመጠየቅ በፈገግታ ተቀበለው።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አባቴ እኛን ወንዶች ልጆቹን ወደ ስብሰባዎች ይወስደን ጀመር። ይሁን እንጂ እናቴ ከእኛ ጋር አዘውትራ መሄድ አትፈልግም ነበር። ፍላጎቷ እየቀነሰ መሄድ ጀምሮ ነበር። ይሁንና አባቴና እኔ በተጠመቅንበት በሐምሌ 1947 በለንደን በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ሁላችንም ተገኝተን ነበር። ከዚያ ጊዜ በኋላ እናታችን ወደ ስብሰባ ትመጣ የነበረው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር።
ከተጠመቅን ብዙም ሳይቆይ አክስቴ ፊል ወደ እንግሊዝ ለጉብኝት መጥታ እውነትን ደስ ብሏት መቀበሏና ከዚያም መጠመቋ አባቴን በጣም አስደሰተው። ወደ ሻንጋይ ስትመለስም ከዚያ ትንሽ ቀደም ብሎ በዚያ እንዲያገለግሉ የተላኩትን ሚስዮናውያን የይሖዋ ምሥክሮች አገኘቻቸው። እነዚህም ስታንሊ ጆንስንና ሃሮልድ ኪንግ ይባሉ ነበር። ትንሽ ቆይቶ እነዚህ ሚስዮናውያን በጊዜው ስልጣን ላይ በነበረው የኮሚኒስት አስተዳደር ታስረው ነበር። ስታንሊ ጆንስ ሰባት ዓመት ሃሮልድ ኪንግ ደግሞ አምስት ዓመት በእስር ቤት አሳልፈዋል። ፊል ባለቤቷ በቻይና ውስጥ ይሠራ ከነበረበት ቦታ ጡረታ እስኪወጣ ድረስ እነዚህ ወንድሞች በመንፈሳዊ ረድተዋታል። ከዚያም እርሷና ባሏ ወደ እንግሊዝ ተመልሰው እኛ ባለንበት አካባቢ መኖር ጀመሩ።
አሳዛኙ የቤተሰብ መፈራረስ
በዚህ ጊዜ እናቴና አባቴ የሐሳብ ግንኙነት የማድረግ ችግር ነበረባቸው። ሌስተር አዲሱን እምነቱን በምን ዓይነት ቅንዓት እየተከተለ እንዳለ እናቴ ስትመለከት የቤተሰቡ ቁሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ይወድቃል ብላ ስላሰበች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴውን መቃወም ጀመረች። በመጨረሻ በመስከረም 1947 ይህንን የክርስቲያን እምነቱን እንዲያቆም አለበለዚያም እርሷ ጥላው እንደምትሄድ በመንገር የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠችው።
አባቴ በቅዱሳን ጽሑፎች ተጠቅሞ ምንም የሚያስፈራ ነገር እንደሌለ ምክንያቱን ከእናቴ ጋር በመወያየት ያረጋጋት መስሎ ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ ሌላ ምንም ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሳትሰጠው በጥቅምት 1, 1947 ጉዳዩን መደምደሚያ ላይ አደረሰችው። በዚያ ዕለት አባቴ ከሥራ ሲመለስ ባዶ ቤትና እኔን በቤቱ ደረጃ ላይ ከሻንጣዎቻችን ጋር ተቀምጬ አገኘኝ። እናቴ ሦስቱን ወንድሞቼን ጨምራ ሁሉንም ነገር ይዛ ሄዳ ነበር። እኔ ከእርሱ ጋር መቆየትን እንደመረጥኩ ለአባቴ ነገርኩት። እናቴ ማስታዎሻ እንኳ አልተወችም ነበር። — ማቴዎስ 10:35–39
አባቴ መኖሪያ ቤት እስኪያገኝ ድረስ ኤርኒ ቢቮር በአንድ አረጋውያን ባልና ሚስት ቤት እንድናርፍ ዝግጅት አደረገልን። በደግነት ስሜት ይንከባከቡንና “የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን ወይም እህት እንዲህ በሚመስል ነገር አይገዙም፤ እግዚአብሔር ግን በሰላም ጠርቶናል [ጠርቷችኋል አዓት] ” በሚሉት በ1 ቆሮንቶስ 7:15 ላይ በሚገኙት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ያጽናኑን ነበር።
በመጨረሻም ቤተሰባችን የት እንዳለ ስላወቅን ሄደን ጠየቅናቸው፤ ይሁን እንጂ እናታችን ልትቀበለን የምትችለው በእምነታችን ከተደራደርን ብቻ እንደሆነ ተገነዘብን። እርሷን ለማስደሰት ብለን እምነታችንን መተዋችን ደግሞ ከይሖዋ በረከት እንደማያመጣልን ተገነዘብን። ስለዚህ አባቴ ወንድሞቼን ለማሳደግ የሚያስችላትን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሰብዓዊ ሥራ መሥራቱን ቀጠለ። በ1947 ትምህርቴን እንደጨረስኩ የትርፍ ሰዓት ሥራ መሥራት ጀመርኩና በጥር 1948 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ለመሰማራት ተቀባይነት አገኘሁ።
የማይረሳው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት
አንድ ቀን ገና የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ መስክ አገልግሎት ወጥቼ በአንድ እርሻ አጠገብ ባለች የገበሬ ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው አነጋገርኩኝ። ከሰውዬው ጋር እየተነጋገርኩ እያለ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የእንግሊዝ መሪ የነበሩት ዊንስተን ቸርችል መጡ። ውይይታችን ተቋረጠ፤ ሚስተር ቸርችል የመጠበቂያ ግንቡን አንዳንድ ሐሳቦች በትኩረት ከተመለከቱ በኋላ ስለምሠራው ሥራ አመሰገኑኝ።
እንደገና ከሦስትና ከአራት ቀናት በኋላ ለስብከት ወጥቼ የአንድ ትልቅ ቤት የበር ደወል ደወልኩ። የቤቱ ባለሟል ቤቱን ሲከፍትልኝ ከቤቱ ባለቤት ጋር ለመነጋገር እንደምፈልግ ስጠይቀው ‘የቤቱ ባለቤት ማን መሆኑን ታውቃለህ?’ ብሎ ጠየቀኝ። ምንም የማውቀው ነገር አልነበረኝም። “ይህ ቻርት ዌል ይባላል የዊንስተን ቸርችል መኖሪያ ነው” አለኝ። እርሱ እንዲህ እያለኝ ሚስተር ቸርችል ከቤት ውስጥ ብቅ አሉ። ቀደም ሲል መገናኘታችንን አስታውሰው ወደ ቤት እንድገባ ፈቀዱልኝ። ጥቂት ከተወያየን በኋላ ሦስት መጽሐፍትን ወሰዱና ሌላ ቀን ተመለስ አሉኝ።
ጥቂት ቀናት ቆይቼ ሞቅ ያለ አየር በነበረው አንድ ከሰዓት በኋላ ተመልሼ ሄድኩና እንድገባ ተፈቀደልኝ። ሚስተር ቸርችል የሎሚ ጭማቂ ጋበዙኝና ትንሽ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ:- “ግማሽ ሰዓት እሰጥሃለሁ በዚህ ጊዜ ውስጥ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነች ብለህ እንደምታምን ትነግረኛለህ። ከዚያ በኋላ ግን እኔም ያለኝን አመለካከት እንድነግርህ ትፈቅድልኛለህ” አሉኝ። ልክ እንዳሉት አደረግን።
ሚስተር ቸርችል የአምላክ መንግሥት የምትቋቋመው አምላክን በሚፈሩ የመንግሥት አስተዳዳሪዎች አማካኝነት እንደሆነና ሰዎች በሰላም መኖርን እስካልተማሩ ድረስ ደግሞ ፈጽሞ እንደማትመጣ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንግሥት ያለውን አመለካከትና ስለምታመጣቸውም በረከቶች ለማስረዳት ችዬ ነበር። ሚስተር ቸርችል በጣም ትሑት ሰው ነበሩ፤ ሥራችንንም እንደሚያከብሩ ነገሩኝ።
አጋጣሚ ሆኖ ከዚያ በኋላ ፈጽሞ ላገኛቸው አልቻልኩም። ይሁን እንጂ ምንም ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ብሆንም ከአባቴ ባገኘሁት ስልጠናና ማበረታቻ አማካኝነት ታዋቂ የዓለም የፖለቲካ ሰው ለነበሩት ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ። — መዝሙር 119:46
እየሰፋ የሄደ አገልግሎት
በ1950 ግንቦት ወር ላይ እናቴ ወደ ካናዳ ለመሄድ እንዳሰበችና ከእርሷ ጋርም ትንሹን ወንድሜን ጆንን እንደምትወስደው በደብዳቤ ገለጸችልን። በዚያን ጊዜ ሁለቱ ወንድሞቼ ፒተርና ዴቪድ እራሳቸውን ችለው ነበር። በሥራው ዓለም ለ18 ዓመታት ያህል ከቆየ በኋላ (ስሙ በተቀጣሪዎች መዝገብ ላይ የቆየባቸውን የጦርነት ዓመታት ጨምሮ) አባቴ የሥራ መልቀቂያ ጥያቄውን አቅርቦ የዘወትር አቅኚ ለመሆን አመለከተ። ከዚያም በኒው ዮርክ በተደረገው ትልቅ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ እንደተመለሰ በነሐሴ 1950 የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ጀመረ። ከአንድ ዓመት ብዙም ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በኅዳር 1951 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመና ጉባኤዎችን ለማበረታታት ጉብኝቱን ጀመረ። እኔም እንደዚሁ በ1949 ማለቂያ ላይ በእንግሊዝ አገር በለንደን ከተማ ውስጥ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጠራሁ።
በዚያን ወቅት ሌላ ትልቅ በረከትም መጣ። አባቴና እኔ ኒው ዮርክ በሚገኘው የጊልያድ ሚስዮናውያን ትምህርት ቤት 20ኛ ክፍል እንድንካፈል ተጋበዝን። ስልጠናችንን በመስከረም 1952 ጀምረን በዚያው ዓመት በየካቲት ወር ተመረቅን። ከዚያ በኋላ ብሩክሊን ኒው ዮርከ በሚገኘው የዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ማገልገል ጀመርኩ። አባቴ ግን ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ወደ ኢንዲያና ተልኮ ነበር።
በኒው ዮርክ ከተማ በሐምሌ ወር በሚደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እንድንችል መላው የ20ኛው ክፍል ተመራቂዎች ወደ ሚስዮናዊ ምድባቸው ከመሄድ ዘግይተው ነበር። ከክፍል ጓደኞቼ አንዷን ኬይ ዊትሰንን በጣም ስለወደድኳት ለመጋባት ወሰንን። በሚቺጋን በተጓዥነት አገልግሎት ላይ ተመድበን ነበር፤ ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ በአየርላንድ ሰሜናዊ ክፍል በሚስዮናዊነት እንድናገለግል ተመደብን።
ይሁንና ወደ ምድብ ቦታችን ለመጓዝ ስንዘጋጅ ኬይ መፀነሷን አወቀች። ስለዚህ አባቴ እኔን እንዳሰለጠነኝ ሁሉ አንድ ወንድ ልጅና ሦስት ሴቶች ልጆችን የተሳካላቸው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እንዲሆኑ በማሳደግ ሌላ የሥራ ድርሻ ጀመርን። በኅዳር 1953 አባቴ ወደ አፍሪካ ለመሄድ ተነሥቶ ጥር 4, 1954 ወደ ተመደበበት ወደ ደቡብ ሮዴሺያ (አሁን ዚምባቡዌ) ደረሰ።
አባቴ ብዙ ነገሮች መማር ነበረበት ይኸውም:- አዲስ የአኗኗር ዘይቤ፣ አዲስ ባሕል እና አዳዲስ የእምነት ፈተናዎችን መልመድ ነበረበት። እስከ 1954 ድረስ ደቡብ ሮዴሺያ በምዕራቡ አካሄድ እምብዛም አልተነካችም ነበር። በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ካሳለፈ በኋለ የወረዳ የበላይ ተመልካች በመሆን በተጓዥነት እንዲያገለግል ተላከ። እንደገና በ1956 በቅርንጫፍ ቢሮው እንዲያገለግል ተጠርቶ እስከ ሞተበት እስከ ሐምሌ 5, 1991 ድረስ በዚያ አገልግሏል። በ1954 አምስት ብቻ የነበሩት የቅርንጫፍ ቢሮው አገልጋዮች ወደ 40 ከፍ ሲሉ እንዲሁም የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ9,000 ወደ 18,000 ሲያድግ ተመልክቷል።
የአባቴና የእናቴ የመጨረሻ ዓመታት
እናቴና አባቴ ፈጽመው አልተፋቱም። እናታችን ከእንግሊዝ አገር ከሄደች በኋላ በካናዳ ትንሽ ቆይታ ከጆን ጋር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደች። ከወንድሞቼ መካከል ምሥክር የሆነ የለም። ይሁን እንጂ እናቴ በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ከምሥክሮች ጋር ተገናኘች። በ1966 ወደ ኬንያ ሞምባሳ ሄዳ በዚያ ጥናቷን እንደገና ጀመራ ነበር። ነገር ግን በተከታዩ ዓመት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያዛት።
ወንድሞቼ ፒተርና ዴቪድ ሕክምና ወዳገኘችበት ወደ እንግሊዝ አገር ወሰዷት። ከሕመሟ ስታገግም እንደገና ጥናቷን ቀጠለች። እናቴ በ1972 በለንደን በሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ልጠመቅ ነው ብላ ስትጽፍለት አባቴ የተሰማውን ደስታ መገመት ትችላላችሁ። በምትጠመቅበት ጊዜ ከእርሷ ጋር በዚያ ለመገኘት እኔና ሚስቴ ከአሜሪካ ሄድን።
በሚቀጥለው ዓመት አባቴ እረፍት አግኝቶ ወደ እንግሊዝ አገር ሲሄድ ከእናቴ ጋር ከቤት ወደ ቤት ለማገልገል የሚያስችለውን አስደሳች አጋጣሚ አግኝቶ ነበር። ከዚያ ሲመለስም ቤተሰባችንን ለመጎብኘት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መጥቶ ነበር። አባዬና እማዬ መልሰው ስለመታረቃቸውም ተነጋግረው ነበር እርሷ ግን:- “እስካሁን ለረዥም ጊዜ ተለያይተን ቆይተናል። አሁን አስቸጋሪ ነው። ሁሉም ነገር የሚስተካከልበት አዲስ ዓለም እስኪመጣ ድረስ እንጠብቅ” አለችው። ስለዚህ አባቴ ወደ ምድብ ቦታው ተመለሰ። እናቴ ኬኒያ እያለች የያዛት በሽታ ጨርሶ ስላልተዋት ውሎ አድሮ በሞት እስካንቀላፋችበት እስከ 1985 ድረስ ተኝታ ወደቆየችበት ሆስፒታል መግባቷ ግድ ነበር።
በ1986 አባቴ በጣም ስለታመመ እኔና ፒተር ዚምባቡዌ የሚገኘው ቤቱ ድረስ ሄደን ጠየቅነው። ይህ በጣም አበረታትቶት ስለነበር አዲስ የሕይወት ኮንትራት የገባ ያህል ነበር። የሌስተር ልጅ ስለሆንኩ የአፍሪካ ወንድሞች ከዚያ ይበልጥ ቢያደርጉልኝም ደስ ባላቸው ነበር። እውነቱን ለመናገር የአባቴ ምሳሌ ከእርሱ ጋር ግንኙነት በነበራቸው በሁሉም ላይ ጥሩ ስሜት አሳድሯል።
አሁን እኔ እራሴም ታምሜያለሁ። ሐኪሞች ካሁን በኋላ የምኖረው ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደሆነ ነግረውኛል። የያዘኝ አሚሎዪዶሲስ የሚባል አልፎ አልፎ የሚከሰትና የሚገድል በሽታ ነው። እኔ የታማኝ አባቴን ምሳሌ እንደተከተልኩ ሁሉ ልጆቼም የኔን ምሳሌ እየተከተሉ በመሆናቸው ደስ ይለኛል። ሁሉም ከእኛ ጋር ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው። ፈቃዱን በታማኝነት በመፈጸማችን ብንሞትም ሆነ ብንኖር ከአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን በሚመጡት የተትረፈረፉ በረከቶች ለዘላለም እየተደሰትን የመኖር ተስፋ ማግኘታችን እንዴት የሚያጽናና ነው! (ዕብራውያን 6:10)—በ ሚካኤል ዴቪይ እንደተነገረው።a
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህ ዘገባ ሲጠናቀቅ ሰኔ 22, 1993 ሚካኤል ዴቪ በሞት አንቀላፍቷል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በግራ በኩል:- ወላጆቼ ከታላቅ ወንድሜና ከእኔ ጋር
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለዊንስተን ቸርችል ስለ አምላክ መንግሥት በሰፊው ለመናገር ችዬ ነበር
[ምንጭ]
USAF Photo
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቴ ሌስቴር ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከኬይ ጋር