የወጣቶች ጥያቄ . .
ሁለት ዓይነት ኑሮ ለማን ማሳወቅ ይገባል?
“አባዬና እማዬ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይወስዱኝ ስለነበረ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይቼ አውቅ ነበር” ይላል ሮበርት። “እኔ ግን በትምህርት ቤት ባሉት ልጆች እንድወደድና ተቀባይነት እንዳገኝ ፈለግሁ። ተወዳጅ ለመሆን ስለፈለግሁ ገና ስድስተኛ ክፍል ሳለሁ ማጨስ ጀመርሁ። ሰባተኛ ክፍል ስደርስ ኤል ኤስ ዲ መውሰድና ፖት የተባለውን አደንዛዥ ዕፅ ማጨስ ጀመርኩ። ስምንተኛ ክፍል ስደርስ ስፒድ የሚባል አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። ሁሉንም ሰው ማሞኘት ችዬ ነበር። እኔ ግን ምንም ዓይነት ደስታ አላገኘሁም።”
በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች፣ ክርስቲያን ወላጆች ያሳደጓቸው አንዳንድ ወጣቶች ጭምር፣ ሁለት ዓይነት ኑሮ ይኖራሉ። ሁሉም እንደ ሮበርት አደንዛዥ ዕፅ ላይወስዱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ወጣቶች ከወላጆቻቸው በስተ ጀርባ በድብቅ ይጠጣሉ፣ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ይቀጣጠራሉ፣ ቅጥ የለሽ ልብስ ይለብሳሉ፣ ልቅ የሆነ ሙዚቃ ያዳምጣሉ፣ ከሥርዓት ውጭ በሆኑ ፓርቲዎች ላይ ይገኛሉ፣ ወላጆቻቸው በማይደሰቱባቸው ወይም በሚከለክሏቸው ሌሎች ብዙ ተግባሮች ይካፈላሉ። አንተስ እንዲህ ባለው አኗኗር በመላለስ ላይ ነህን?
እንዲህ ባለ አኗኗር የምትመላለስ ከሆንክ የምታደርገው ነገር ስህተት መሆኑን ታውቅ ይሆናል። እንዲያውም እንደ ሮበርት የበደለኛነት ስሜት እየተሰማህ ሕሊናህ ይወቅስህ ይሆናል። (ሮሜ 2:15) ሆኖም ግን መጥፎ ድርጊትህን ለወላጆችህ መግለጽ ጥሩ ነገር መስሎ አይታይህም። ለወላጆችህ መናገር የሚያስከትለውን ውጤት ስታስብ ‘ወላጆቼ የማያውቁት ነገር አይጎዳቸውም’ የሚለው ሰበብ ምክንያታዊ ሆኖ ይታይህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ወላጆችህን መጉዳቱ አይቀርም።
የተሳሳተ አስተሳሰብ
ለምሳሌ ያህል ወላጆች ስለሚያደርጓቸው አንዳንድ ነገሮች ቅር እንድትሰኝ የሚያደርግህ ትክክለኛ ምክንያት እንዳለ ይሰማህ ይሆናል። ቅር ልትሰኝም ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ ከመጠን በላይ ሐሳበ ግትሮች፣ ወይም ሐሳባቸውን የማይገልጹ፣ ወይም ምክንያተ ቢሶች ቢሆኑ ወላጆችህን እንዳትታዘዝ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ይሆናልን? የአምላክ ቃል እንደሚለው ከሆነ በቂ ምክንያት አይሆንም። የአምላክ ቃል “ልጆች ሆይ፣ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ሲል ይመክራል። (ቆላስይስ 3:20) በወላጆችህ ላይ እንድትቆጣ የሚያደርግ በቂ ምክንያት እንዳለህ ሆኖ ከተሰማህስ? አምላክ የሰጠውን ትእዛዛት በድብቅ በመጣስ ይህን የተሰማህን ቁጣ መወጣት ምክንያታዊ ነውን? ይህን ብታደርግ ‘ልብህ በይሖዋ ላይ እንዲቆጣ አደረግህ’ ማለት ነው። (ምሳሌ 19:3) ትክክለኛው ነገር ወደ ወላጆችህ ቀርበህ ስለተሰማህ ቅሬታ በርጋታ መወያየት ነው።ምሳሌ 15:22
አድራጎትህን በምሥጢር ብትይዝ ወላጆችህን ከብስጭት ታድናለህ የሚለው አስተሳሰብም ቢሆን የተሳሳተ ነው። አንድ የ16 ዓመት ልጅ “ወላጆቼን የሚያበሳጭ ነገር ፈጽሞ አልናገርም” ብሏል። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብም ቢሆን ራስን ከማታለል አያልፍም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው እንዲህ የሚያስብ ሰው “በአንደበቱ ሸንግሎአልና፤ ኃጢአቱ ባገኘችው ጊዜ ይጠላታል።” (መዝሙር 36:2) በእውነት ስለ ወላጆችህ ስሜት የምታስብ ከሆንክ መጀመሪያውኑ ትእዛዛቸውን አትጥስም። ከዚህም በላይ ሌሎች ሰዎች ስለ ስውር ኑሮህ ማወቃቸው ስለማይቀር ከእነርሱ መደበቅ አያዛልቅም።
ተሰውሮ የሚቀር ነገር የለም
የጥንቶቹ እስራኤላውያን ተሰውረው የፈጸሙት በደል ተደብቆ እንዲቀር በሞከሩ ጊዜ ይህን ሐቅ ተገንዝበዋል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት አስጠነቀቃቸው:- “ምክራቸውን ጥልቅ አድርገው ከእግዚአብሔር ለሚሰውሩ ሥራቸውንም በጨለማ ውስጥ አድርገው ማን ያየናል? ወይስ ማን ያውቀናል? ለሚሉ ወዮላቸው።” (ኢሳይያስ 29:15) እስራኤላውያን አምላክ መጥፎ ድርጊታቸውን እንደሚመለከት ዘንግተው ነበር። ራሱ በወሰነው ጊዜ የበደላቸውን ብድራት እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ በነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችም ላይ ተመሳሳይ ነገር ተፈጽሟል። በሐዋርያት ሥራ 5:1–11 ላይ የሚገኘውን ስለ ሐናንያና ስለ ሚስቱ ሰጲራ የሚናገረውን ታሪክ አንብብ። ለችግረኛ ክርስቲያኖች መርጃ የሚውል ገንዘብ ማዋጣት ባስፈለገ ጊዜ ሐናንያ መሬቱን ሸጦ የሸጠበትን ገንዘብ በሙሉ እንደሰጠ በድፍረት ተናገረ። ሐናንያ ግን የገንዘቡን እኩሌታ ለራሱ አስቀርቶ ነበር። ታዲያ አምላክ እንዲህ ባለው የይስሙላ ልግስና ተታልሎ ነበርን? በፍጹም አልተታለለም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም” አለው። “ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ፣ ሞተም።” የባልዋ ተባባሪ የነበረችው ሰጲራም ብዙ ሳትቆይ ተቀስፋ ሞተች። ሁለቱም አምላክ “ልብ የሰወረውን” እንደሚያውቅ ዘንግተው ነበር።መዝሙር 44:21
ዛሬም ቢሆን የሠራኸውን መጥፎ ድርጊት ከወላጆችህ ለመሸሸግ ብትችልም እንኳን ይህን ተግባርህን ሁሉን ማየት ከሚችለው የይሖዋ ዓይን መሸሸግ አትችልም። ዕብራውያን 4:13 “እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ይላል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የተሸሸገው ኃጢአትህ ለሌሎች ሰዎችም ግልጽ ሆኖ ይታያል። ምሳሌ 20:11 “ሕፃን ቅንና ንጹሕ መሆኑ በሚያደርገው ሥራ ይታወቃል” ይላል። ሌላው ምሳሌ ደግሞ “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፣ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል” ይላል።ምሳሌ 28:13
ታሚ የተባለች አንዲት ወጣት ሴት ይህ እውነት መሆኑን ያወቀችው ገና አፍላ ወጣት ሳለች ነበር። ወላጆችዋ ክርስቲያኖች ቢሆኑም ማጨስ፣ መጠጣትና ከማያምኑ ወንዶች ጋር መቀጣጠር ጀመረች። ታሚ መጥፎ ሥራዋን ደብቃ ለማቆየት ሞክራ ነበር። ይሁን እንጂ ራስዋ አስታውሳ እንደተናገረችው “ወላጆቼ ወዲያው አንድ ዓይነት ለውጥ ያለኝ መሆኑን አስተዋሉ። የዓመፀኝነትና በራሴ ፈቃድ የመመራት ዝንባሌ አደረብኝ። አንድ ሰው ሁለት ዓይነት ኑሮ መኖር ከጀመረ ፈጥኖም ሆነ ዘግይቶ መጋለጡ አይቀርም። የእኔ መጋለጥ ግን አልዘገየም። አባቴ በአቅራቢያዬ በሚገኘው ትምህርት ቤት ከሚማረው ወንድ ጓደኛዬ ጋር ሆኜ አየኝ።”
ይሖዋ እንዴት ይሰማዋል?
ስለዚህ ወላጆችህ የማያውቁት ነገር ይዋል ይደር እንጂ እነርሱን ማሳዘኑ አይቀርም። ከዚህ ይበልጥ ደግሞ ራስህን ‘በውሸት ኑሮ የሚመላለሱትን ይሖዋ እንዴት ይመለከታቸዋል?’ ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህን? መዝሙር 5:5, 6 መልሱን ይሰጣል። “ክፉ አድራጊዎችን ጠላህ። ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ። ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል።” በሃይማኖታዊ ስብሰባዎች በምትገኝበት ጊዜ ብቻ ለአምላክ ያደርክ ሰው መስለህ በመታየት አምላክን ለማስደሰት የምትችል መስሎህ ራስህን አታታልል። ‘በከንፈራቸው የሚያከብሩትንና ልባቸው ግን ከእርሱ የራቁትን ሰዎች’ ያውቃቸዋል።ማርቆስ 7:6
የፆታ ርኩሰት የፈጸመ ሪካርዶ የተባለ ወጣት “አንድ ሰው ይሖዋን እንዳሳዘነ ሲያውቅ በጣም መጥፎ ስሜት ይሰማዋል” ሲል ተናዟል። ይሁን እንጂ እውነት ይሖዋን ማሳዘን ይቻላል? በእርግጥ ይቻላል። የጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ የአምላክን ሕግ በተወ ጊዜ “የእስራኤልን ቅዱስ አሳዝነውት ነበር።’ (መዝሙር 78:41) ዛሬም “በእግዚአብሔር ተግሣጽና ምክር” ያደጉ ልጆች በድብቅ የተሳሳተ ድርጊት ሲፈጽሙ አምላክ ምን ያህል ያዝን!ኤፌሶን 6:4
በወላጆች ላይ የሚደርስ ጉዳት
ስለዚህ ለሁልጊዜ እንደተደበቅህ ልትኖር እንደማትችል ተገንዘብ። በድብቅ ስትሠራ የነበረውን ድርጊት ተናዝዘህ ራስህን ንጹሕ ለማድረግ በአምላክ፣ በወላጆችህና በራስህ ፊት ኃላፊነት አለብህ። ይህን ማድረግ ሊያሳፍርህና አንዳንድ የማይፈለጉ ውጤቶችን ሊያስከትልብህ እንደሚችል አይካድም። (ዕብራውያን 12:10, 11) በውሸትና በሽንገላ ኑሮ ስትመላለስ የቆየህ ከሆንክ ወላጆችህ በአንተ ላይ የነበራቸውን ትምክህት አጉድለሃል። ስለዚህ ከበፊቱ ይበልጥ ጥብቅ ሆነው ቢቆጣጠሩህ ሊገርምህ አይገባም። ታሚ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ከወንድ ጓደኛዬ ጋር ሆኜ ካየኝ በኋላ አባቴ ብርቱ ስጋት አደረበት። አሁን እምነት ሊጣልብኝ የምችል እንዳልሆንኩ ተገነዘበ። ዘወትር ይከታተለኝ ጀመረ።” ይሁን እንጂ ታሚ የዘራችውን ማጨዷ እንደነበረ ተገንዝባለች።ገላትያ 6:7
በተጨማሪም ወላጆችህ በጣም እንደሚቆጡና እንደሚያዝኑ ልትጠብቅ ትችላለህ። ዝናቸውና መልካም ስማቸው ተበላሽቷል። (ከዘፍጥረት 34:30 ጋር አወዳድር።) አባትህ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ አንዳንድ የጉባኤ መብቶቹን እንዲተው ሊገደድ ይችላል። (ቲቶ 1:5–7ን) አዎን፣ ምሳሌ 17:25 እንደሚለው ዓመፀኛ የሆነ ወጣት ልጅ “ለአባቱ ፀፀት ነው፣ ለወለደችውም ምሬት ነው።”
ጆይ ፒ ጌጅ የተባሉት ደራሲ ወላጆች ልጆቻቸው ዓመፀኛ ሲሆኑባቸው የሚሰማቸውን ምሬት በሚከተሉት ቃላት ገልጸዋል:- “አንዳንዶች ድምፃቸውን ሳያሰሙ ያነባሉ። አንዳንዶች በራቸውን ዘግተው ብቻቸውን ያለቅሳሉ። ያሳለፉት ዘመን በሙሉ ከንቱ ስለሆነባቸው ያለቅሳሉ። ለነገ የነበራቸው ተስፋ በሙሉ በድንገት በመጥፋቱ ያለቅሳሉ። ስለቀረባቸው ነገር ያለቅሳሉ። ወደፊት መሆኑ ስለማይቀረው ነገር ያለቅሳሉ። ከቁጣቸው የተነሣ ያለቅሳሉ። ከብስጭታቸው የተነሣ ያለቅሳሉ።” በዚህ ዓለም ከሚኖር ከማንኛውም ሰው ይበልጥ የሚወዱህን እነኚህን ሁለት ሰዎች ማሳዘን በጣም ከባድ ነገር ሆኖ እንደሚታይህ የታወቀ ነው። ታሚ “ወደ ኋላ መለስ ብዬ አስብና ምነው ይህን ያህል አባቴንና እናቴን ባላሳዘንኩ ኖሮ እላለሁ” ብላለች።
ይሁን እንጂ ወደ ኋላ ተመልሰህ የሆነውን ነገር እንዳልሆነ ለማድረግ አትችልም። ሁኔታው በጣም አስቸጋሪና የሚያሳዝን ቢሆንም ነገሩን የማስተካከል ግዴታ አለብህ። (ከኢሳይያስ 1:18 ጋር አወዳድር።) ለወላጆችህ እውነቱን መናገር፣ ማዘናቸውና መቆጣታቸው ተገቢ መሆኑን መቀበልና የሚሰጡህን ማንኛውም ዓይነት ተግሣጽና ቅጣት መቀበል ይኖርብሃል። እውነቱን መናገርህ የወላጆችህንና የይሖዋን ልብ የሚያስደስት፣ ለአንተም ከንጹሕ ሕሊና የሚገኘውን ደስታ የሚያመጣልህ የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል።ምሳሌ 27:11፤ 2 ቆሮንቶስ 4:2
ይሁን እንጂ ለወላጆችህ የምትነግራቸው እንዴት ነው? ሁለት ዓይነት ኑሮ ከመኖር ለመላቀቅ የምትችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው እትማችን ይብራራሉ።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነቱን መናገር አንተንም ሆነ ወላጆችህን ከጭንቀት ሊያድን ይቸላል