ደስታ የሰፈነበት ቤት ሁለቱ አንድ በሚሆኑበት ጊዜ
ጠንካራ፣ አስተማማኝና ምቹ ቤት መሥራት ከፈለግክ እንዴት ባሉ የግንባታ ዕቃዎች ትጠቀማለህ? በእንጨት፣ በጡብ ወይስ በድንጋይ? የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል። “ቤት በጥበብ ይሠራል፣ በማስተዋልም ይጸናል። በእውቀት ከከበረውና ካማረው ሀብት ሁሉ ጓዳዎች ይሞላሉ።” (ምሳሌ 24:3, 4) አዎን፣ ደስታ የሰፈነበት ቤት ለመገንባት ጥበብ፣ ማስተዋልና እውቀት ያስፈልጋል።
ቤቱን የሚገነባው ማን ነው? “ብልሃተኛ ሴት ቤትዋን ትሠራለች፣ ሰነፍ ሴት ግን በእጅዋ ታፈርሠዋለች።” (ምሳሌ 14:1) ሁኔታው ለወንዱም ቢሆን ከዚህ የተለየ አይደለም። ትዳሩን ጠንካራና ደስታ የሰፈነበት አለበለዚያም ደካማና ምሬት የሞላበት ሊያደርግ ይችላል። ልዩነት የሚያመጣው ምንድን ነው? አንዳንድ ዘመናዊ የጋብቻ አማካሪዎች የሚሰጡት ምክር በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከተጻፉት ዘመን የማይሽራቸው የአምላክ ቃል ምክሮች ጋር በጣም የሚቀራረብ መሆኑ ያስገርማል።
ማዳመጥ:- ስለ ጋብቻ ምክር የሚሰጥ አንድ መጽሐፍ “ለአንድ ሰው አክብሮት እንዳላችሁ ከምታሳዩባቸው ትላልቅ መንገዶችና የተቀራረበ ዝምድና ለመመስረት ከሚያስችሏችሁ ወሳኝ ነገሮች አንዱ ማዳመጥ ነው” ይላል። የምሳሌ መጽሐፍ “የጠቢባን ጆሮ እውቀትን ትፈልጋለች” ይላል። (ምሳሌ 18:15) የጆሮ ክፍት መሆን እንደ ዓይንና አፍ በግልጽ ሊታይ ስለማይችል የትዳር ጓደኛችሁን እንደምታዳምጡ እንዴት ማሳየት ትችላላችሁ? አንደኛው መንገድ የምታዳምጡ መሆናችሁን የሚያሳይ አካላዊ ወይም የቃል መግለጫ መስጠት ነው።— በገጽ 11 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
ግልጽ መሆንና መቀራረብ:- ዋን ቱ ዋን— አንደርስታንዲንግ ፐርሰናል ሪለሽንሽፕስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል። “ባሕላችን ግልጽነትን ይቃወማል። ከልጅነታችን ጀምሮ በሰው ጉዳይ ውስጥ እንዳንገባ፣ ገንዘብን፣ አስተሳሰብንና ስሜትን . . . በጠቅላላው የግል ጉዳዮችን ስለሚመለከቱ ነገሮች ምሥጢረኞች እንድንሆን ይነገረናል። ይህ ትምህርት የምንወደው የትዳር ጓደኛ በምናገኝበት ጊዜም ጥሎን አይሄድም። ግልጽ ለመሆን የማያቋርጥ ጥረት ካልተደረገ የተቀራረበ ዝምድና ሊኖር አይችልም።” የምሳሌ መጽሐፍ “የምሥጢር ውይይት ካልኖረ የታቀደው አይሳካም። በሚመካከሩ ዘንድ ግን ጥበብ ይኖራል” ይላል።— ምሳሌ 13:10፤ 15:22 አዓት
መተማመን:- ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ ለመሆን በአምላክ ፊት ምለዋል። የትዳር ጓደኞች አንዳቸው ለሌላው የተወሰኑ እንደሆኑና ታማኝ የመሆን ግዴታ እንዳለባቸው እርግጠኛ ሲሆኑ በመካከላቸው ያለው ፍቅር በጥርጣሬ፣ በኩራት፣ በፉክክር መንፈስ፣ የየበኩል ድርሻ ለማግኘት በሚደረግ ትግል አይቆረቁዝም።
ማካፈል:- በባልና ሚስት መካከል ያለው ዝምድና ጥልቀት እያገኘ የሚሄደው አብረው በሚያሳልፏቸው ተሞክሮዎች ነው። ከጊዜ በኋላ እያንዳንዳቸው በደስታ የሚያስታውሷቸው በርካታ ትዝታዎች ይኖሯቸዋል። ይህን የመሰለውን ጠንካራ ዝምድና ማፍረስ ሊያስቡት እንኳን የማይችሉት ነገር ይሆናል። “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ።”— ምሳሌ 18:24
ደግነትና ርህራሄ:- ደግነት በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ግጭቶች ከመቀነሱም በላይ የኩራትን መንፈስ ያረግባል። ደግነት የተለመደና ሥር የሰደደ የዘወትር ባሕርይ ከሆነ አለመግባባት ተፈጥሮ የስሜት መጋጋል በሚኖርበት ጊዜ እንኳን ጸንቶ ስለሚኖር በተፈጠረው አለመግባባት የሚከሰተው ጉዳት በጣም አነስተኛ ይሆናል። ርህራሄ ፍቅር ሊያድግ የሚችልበት ሞቅ ያለ ሁኔታ እንዲኖር ያስችላል። የርህራሄና የፍቅር ጠባይ ማሳየት በተለይ ለወንዶች አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስ “ከምድራዊ ሰው የሚፈለገው ፍቅራዊ ቸርነት ነው” ይላል። (ምሳሌ 19:22 አዓት) ጥሩ ሚስት ደግሞ “የርህራሄ ሕግ በምላስዋ” ይኖራል።— ምሳሌ 31:26
ትህትና:- ትህትና የኩራትን መርዝ የሚያረክስ መድኃኒት ሲሆን ይቅርታ ለመጠየቅ ፈጣኖች ለመሆንና አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ያነሳሳናል። ፈጸማችሁ ስለተባላችሁት ጥፋት ፈጽሞ የምታውቁት ነገር ካልኖረስ? ለምን በደግነት “ይህን ያህል ስለ ተሰማህ/ሽ በጣም አዝናለሁ” አትሉም? ስለ ትዳር ጓደኛችሁ ስሜት የምታስቡ መሆናችሁን ከገለጻችሁ በኋላ የተፈጠረውን ችግር እንዴት ልታስወግዱ እንደምትችሉ አብራችሁ ተወያዩ። “ከክርክር ይርቅ ዘንድ ለሰው ክብሩ ነው።”— ምሳሌ 20:3
መከባበር:- “ከትዳር ጓደኛችን ጋር ያለንን ልዩነት ለመገንዘብና ችግሮች ሲነሱ አብረን ለመፍታት የሚያስችለን ቁልፍ መከባበር ነው። ለአንደኛው የትዳር ጓደኛ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነገር ለሌላኛው በጣም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። ቢሆንም አንደኛው የትዳር ጓደኛ ሁልጊዜ የሌላውን አመለካከት ማክበር ይኖርበታል።” (ኪፒንግ ዩር ፋምሊ ቱጌዘር ዌን ዘ ወርልድ ኢዝ ፎሊንግ አፓርት) “በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፣ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት።”— ምሳሌ 13:10
በራስ ስህተት የመሳቅ ችሎታ:- በጣም ከባድ የሆነ የግጭት ጭጋግ ከልብ በመነጨ ስሜት አብሮ በመሳቅ ሊወገድ ይችላል። የፍቅርን ሰንሰለት ከማጠንከሩም በላይ የማሰብ ችሎታችንን የሚያዳክምብንን ውጥረት ያረግብልናል። “ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል።”— ምሳሌ 15:13
መስጠት:- የትዳር ጓደኛችሁን መልካም ጎን ፈልጉና አድናቆታችሁን በለጋስነት መንፈስ ግለጹ። ይህ ዓይነቱ የአድናቆት መግለጫ የክራባት ወይም የአበባ ስጦታ ከመስጠት የበለጠ ልባዊ ስሜት ሊቀሰቅስ ይችላል። እርግጥ አንዳችሁ ለሌላችሁ ስጦታ ልትገዙ ወይም ጥሩ ነገር ልታደርጉ ትችላላችሁ። ላይፍ ስኪልስ ፎር አደልት ችልድረን የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ግን “በጣም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች በስጦታ ወረቀት ተጠቅልለው የሚመጡ አይደሉም። ፍቅራችሁንና አድናቆታችሁን ከመግለጽ፣ ማበረታቻና እርዳታ ከመስጠት የበለጠ ስጦታ ሊኖር አይችልም” “በወቅቱ በትክክል የተነገረ ቃል በብር ላይ እንደፈሰሰ የወርቅ ጌጥ ውበት ይኖረዋል።”— ምሳሌ 25:11 የ1980 ትርጉም
እነዚህ የተለያዩ ባሕርያት የትዳር ሕንጻ በሚገነባባቸው ጡቦች ቢመሰሉ ጡቦቹን እርስ በርሳቸው የሚያያይዘው ሲሚንቶ ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት ነው። ስለዚህ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ባልና ሚስት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? ጌቲንግ ዘ ላቭ ዩ ዋንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “የትዳር ጓደኛችሁን የአመለካከት ልዩነት የግጭት ምክንያት እንደሆነ ሳይሆን . . . የእውቀት ምንጭ እንደሆነ አድርጋችሁ ቁጠሩ። . . . በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ዝርዝር ሁኔታዎች ተዝቆ የማያልቅ የእውቀት ማዕድን ይሆንላችኋል።”
እያንዳንዱን ያለመግባባት አጋጣሚ እንደ ጦርነት ጥሪ ሳይሆን ይህን የምትወዱትን/ዷትን ግለሰብ ይበልጥ ለማወቅ የሚያስችላችሁ አጋጣሚ አድርጋችሁ ተመልከቱ። በአንድነት ለሚያጋጥሟችሁ ችግሮች መፍትሔ እየፈለጋችሁ፣ ሰላምና አንድነት እየፈጠራችሁ ሁለት የተለያያችሁ ግለሰቦች የሆናችሁትን አንድ የሚያደርገውን ሰንሰለትና ፍቅር ይበልጥ ጥብቅ እንዲሆን ታደርጋላችሁ።
ይሖዋ በፍጥረቱ ውስጥ በሚታየው ትብብርና ቅንብር በጣም ይደሰታል። እጽዋትና እንስሳት በመሰጣጠትና በመቀባበል የኦክስጅን ዑደት ያካሂዳሉ፤ የጠፈር አካላት የተወሰነላቸውን ምሕዋር ሳይለቁ ይዞራሉ፤ አበቦችና ጥቃቅን ነፍሳት ተረዳድተውና ተጋግዘው ይኖራሉ። በጋብቻ ጥምረትም ውስጥ ባል በቃልም ሆነ በድርጊት ሚስቱን እንደሚወድ የሚያረጋግጥበትና አፍቃሪ የሆነች ሚስት ደግሞ የባልዋን አመራር በፍቅር የምትከተልበት ሞቅ ያለ ዑደት ሊኖር ይችላል። በዚህ መንገድ ሁለቱ የትዳር ጓደኞች ሁለት ከመሆን ይልቅ አንድ በመሆን አንዳቸው ሌላውንና የጋብቻ መሥራች የሆነውን ይሖዋ አምላክን ያስደስታሉ።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘እንዴት እንደምታዳምጡ ተጠንቀቁ።’— ሉቃስ 8:18
ንቁ አድማጭ መሆን ተናጋሪና አድማጭ በእርግጥ የተግባቡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል። ንቁ አድማጭ መሆን አንዳንድ ጊዜ በእንግሊዝኛ ሚረሪንግ ይባላል። እንዲህ የሚባለው አድማጩ የሚሰማቸውን ቃላትና ያገኘውን ግንዛቤ ልክ እንደመስተዋት ለማንጸባረቅ ስለሚሞክር ነው። ይህን ለማድረግ የሚያስችሉ መሠረታዊ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው:-
1. የሚነገረውን በጥሞና መከታተል፤ አስፈላጊ የሆኑ መልእክቶችን ማዳመጥ።
2. ከቃሎቹ በስተጀርባ ያለውን ስሜት ማዳመጥ።
3. የሰማኸውን ለተናጋሪው መድገም። ተናጋሪውን አትተች፣ አትፍረድ ወይም አትቃወም። መልእክቱን በትክክል እንደተረዳህ ብቻ እንዲያውቅ አድርግ። ስሜቱን እንደምትረዳ ግለጽ።
4. ተናጋሪው በትክክል እንደተረዳህ ያረጋግጥልሃል ወይም የተናገርኸውን ካስተካከለ በኋላ ተጨማሪ መግለጫ ይሰጥ ይሆናል።
5. ያንተ ግንዛቤ ትክክል ካልነበረ በድጋሚ ሞክር።
በተለይ በንቃት ማዳመጥ ትችት መስማት የሚያስከተለውን ሕመም በእጅጉ ይቀንሳል። ትችት የሚሰነዘረው አብዛኛውን ጊዜ በተወሰነ እውነት ላይ ተመሥርቶ መሆኑን መቀበል ያስፈልግሃል። ትችቱ የቀረበው በሚያሳምም መንገድ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ራስን በመከላከል መንፈስ ተቺውን በዚያው መጠን ለማሳመም ከመሞከር ይልቅ በንቃት በማዳመጥ ሁኔታውን ብታረግቡ የተሻለ አይሆንም? ለምንም ዓይነት ሁኔታ ኃላፊ እንደሆናችሁ ቢነገር ነገሩን እንደተረዳችሁ በመግለጽ ለተፈጠረው ሁኔታ መፍትሔ የሚገኝበትን መንገድ አስቡ።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
‘ቅር የተሰኛችሁበት ነገር ቢኖር’— ቆላስይስ 3:13
ቅር የተሰኛችሁበት ነገር ቢኖር ጦርነት ሳታስነሱ ቅሬታችሁን ማሰማት የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ የትዳር ጓደኛችሁ መጥፎ ዓላማ ወይም ፍላጎት እንደሌለው/ላት ተናገሩ። አሳቢነት የጎደለው/ላት፣ ችኩል፣ ጥበብ የሌለው/ላት ሆኖ ወይም ሆና ይታያችሁ/ትታያችሁ ይሆናል። ቢሆንም በአጠቃላይ ሲታይ ታስቦ የተደረገ ወይም ለመጉዳት ታቅዶ የተደረገ አይሆንም። የክስ ቃል ሳትጠቀሙ በእርጋታ ስሜታችሁን መግለጽ ትችላላችሁ። “እንዲህ በማድረግህ/ሽ . . . ተሰማኝ” ቢባል ምንም ክርክር ወይም ጭቅጭቅ የሚያስነሳ ነገር አይኖርም። ይህ አነጋገር የሚገልጸው ስሜታችሁን ብቻ ስለሆነ በትዳር ጓደኛችሁ ላይ የተሰነዘረ ክስ አይሆንም። ግለሰቡ/ቧ ቀድሞውንም ቢሆን እናንተን ለማበሳጨት ሆን ብሎ/ላ ያደረገው/ችው ነገር ስለሌለ እንዲህ አላደረግኩም ሊል/ልትል ወይም ሰበብ ሊያቀርብ/ልታቀርብ ይችላል/ትችላለች። ይሁን እንጂ ትኩረታችሁን ችግሩ ላይ በማድረግ መፍትሔ ለመጠቆም ዝግጁ ሁኑ።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለአንድ ሰው አክብሮት እንዳላችሁ ከምታሳዩባቸው ትላልቅ መንገዶች አንዱ ማዳመጥ ነው