መሃይማንን እንዲያነቡ መርዳት
ማንበብና መጻፍ የማይችሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? በአብዛኛው ኃላፊነት የሚሰማቸውና ሥራቸውን በትጋት የሚያከናውኑ ዜጎች ናቸው። በታዳጊ አገሮች ለሚኖረው ለአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚያስፈልገውን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ የሚያቀርቡት እነዚህ ዜጎች ናቸው። በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ሌሎች ሰዎች ንክች እንኳ ሊያደርጓቸው የማይፈልጓቸውን ለኅብረተሰቡ ግን የግድ አስፈላጊ የሆኑ አድካሚ፣ አሰልቺና ዝቅተኛ መስለው የሚታዩ ሥራዎችን የሚሠሩት እነዚህ ሰዎች ናቸው።
ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የማንበብና የመጻፍ ችሎታ የማይኖራቸው አጋጣሚውን ባለማግኘታቸው ነው። መሃይማን በቡድን ደረጃ ደደቦች፣ ደንቆሮዎች ወይም ምንም ዓይነት ችሎታ የሌላቸው አይደሉም። መሠረተ ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኝ አንድ ሰው “የማሰብ ችግር የለብኝም። የኔ ችግር ማንበብ ብቻ ነው” ብሏል።
አጋጣሚ አለማግኘት
ለብዙ ሰዎች መሃይምነት ከድህነት ጋር ቁርኝት ይኖረዋል። ድህነት ሲኖር ቤተሰቦችን በይበልጥ የሚያሳስባቸው ትምህርት የማግኘት ጉዳይ ሳይሆን የሚቀመስ ነገር ማግኘት ይሆናል። ልጆች ለቤት ውስጥ ሥራ ስለሚፈለጉ ትምህርት ቤት አይሄዱም። ቢሄዱም ትምህርታቸውን መቀጠል አይችሉም።
ድህነት በብሔራዊ ደረጃም የሚያስከትለው ጉዳት አለ። በታዳጊ አገሮች ከውጭ አገሮች የተበደሯቸው ዕዳዎች ስለሚጫናቸው ለትምህርት የሚመድቡትን በጀት ለመቀነስ ይገደዳሉ። ለምሳሌ ያህል በአፍሪካ በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ላይ ለትምህርት የዋለው ገንዘብ በ30 በመቶ ቀንሷል። የበለጸጉ አገሮች ለእያንዳንዱ ተማሪ በዓመት ከ6,000 ዶላር (የአሜሪካ) የሚበልጥ ገንዘብ ሲመድቡ በአፍሪካና በደቡባዊ እስያ የሚገኙ ድሃ አገሮች ግን ለእያንዳንዱ ተማሪ የመደቡት ገንዘብ ከ2 ዶላር (የአሜሪካ) አላለፈም። በዚህ ምክንያት የትምህርት ቤቶችና የመምህራን ቁጥር አንሶ ተማሪዎች በጣም በተጣበቡ ክፍሎች ውስጥ ታጭቀው ለመማር ይገደዳሉ።
ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭትም ለመሃይምነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ሰባት ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እንደ ልብ በማይገኝባቸው የስደተኛ ካምፖች ውስጥ እንደሚማቅቁ ይገምታል። በአንድ የአፍሪካ አገር ብቻ 1.2 ሚልዮን የሚያክሉ 15 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ትምህርት ለመከታተል አልቻሉም።
በልጅነታቸው የመማር አጋጣሚ ካላገኙ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ካደጉ በኋላ ማንበብና መጻፍ የመማር አጋጣሚ ቢያገኙም የመማሩ አስፈላጊነት የሚታያቸው ሁሉም አይደሉም። አደልት ኢዱኬሽን ፎር ደቨሎፒንግ ካንትሪስ የተባለው መጽሐፍ በገጠር አካባቢዎች ስለሚኖሩ መሃይማን እንዲህ ብሏል:- “ማንበብና መጻፍ ሳይችል ኑሮውን ማሸነፍ የቻለ ሰው በጣም ልዩ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ካልሆነ በስተቀር ከፍተኛ የሆነ ማንበብና መጻፍ የመቻል ፍላጎት አያድርበትም። . . . በሚኖርበት ሁኔታና ደረጃ ሙሉ በሙሉ ረክቷል ማለት ፍጹም ስህተት ቢሆንም አለመርካቱ ሁኔታውን የሚለውጥ ነገር እንዲያደርግ የሚያነሳሳ ጥንካሬ አይኖረውም።”
ይሁን እንጂ ራሳቸውን ለማሻሻል ጠንካራ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። እርግጥ ማንበብና መጻፍ ለመቻል የሚነሳሱበት ዓላማ የተለያየ ይሆናል። አንዳንዶች የሚፈልጉት እውቀታቸውንና በሰዎች ዘንድ የሚኖራቸውን ግምት ለማሻሻል ብቻ ነው። ሌሎች ደግሞ የሚነሳሱት ገንዘብ ለማግኘት ነው። ሥራ የሌላቸው መጻፍና ማንበብ ቢችሉ ሥራ እንደሚያገኙ ሲያስቡ ሥራ ያላቸው ደግሞ የተሻለ ሥራ ለማግኘት ሲሉ ይማራሉ።
መንግሥታትና ድርጅቶች ማንበብና መጻፍ መቻል በግለሰብም ሆነ በአገር ደረጃ የሚያስገኘውን እድገት በመገንዘባቸው የመሠረተ ትምህርት ፕሮግራሞችን ለጎልማሶች መስጠት ጀምረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ቀላል ሥራ አይደለም። አስተማሪው ራሱን በጎልማሳው ተማሪ ቦታ አድርጎ እንዲመለከትና የተማሪውን ልዩ የሆነ ባሕርይ እንዲረዳ ይጠይቅበታል።
የጎልማሳ ተማሪ ልዩ ባሕርይ
ጎልማሶችን የሚያስተምሩ ሰዎች በጎልማሳ ተማሪዎችና በሕፃናት ተማሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የጎልማሶች ባሕርይ፣ ልማድ፣ ዝንባሌና ፍላጎት ከልጆች ይበልጥ ሥር የሰደደ ስለሚሆን ለውጥ ለማድረግ ለጎለመሰ ሰው ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆንበታል። በሌላ በኩል ግን ጎልማሶች የበለጸገ ተሞክሮ ስለሚኖራቸው ልጆችን ሊያደናግሩ የሚችሉ ጭብጦችንና ጽንሰ ሐሳቦችን ለመረዳት ይችላሉ። አብዛኛውን ጊዜ የልጆችን ያህል ብዙ ትርፍ ጊዜ አይኖራቸውም። ሌላው ትልቅ ልዩነት ደግሞ ጎልማሳ ተማሪዎች ከልጆች በተለየ መንገድ ትምህርታቸውን በፈለጉበት ጊዜ ለማቋረጥ ነጻነት አላቸው።
ብዙ ጎልማሳ መሃይማን ባላቸው ልዩ ተሰጥኦ በአንዳንድ የኑሮ መስኮች የተሳካ ውጤት ስለሚያገኙ የማንበብና የመጻፍ ችሎታቸውን አያዳብሩም። የመሠረተ ትምህርት መምህሩ በሌሎች የኑሮ መስኮች ያሳዩትን ጽናት፣ የፈጠራና ከሁኔታዎች ጋር የመላመድ ችሎታቸውን በዚህ የትምህርት ጊዜያቸውም ወቅት እንዲጠቀሙበት ሊያበረታታቸው ይገባል።
አንድ መሃይም የሆነ ሰው ፍላጎቱን ገልጾ እርዳታ እንዲደረግለት ለመጠየቅ ድፍረት ያስፈልገዋል። ሁኔታዎችና ግለሰቦች የተለያዩ ቢሆኑም አብዛኞቹ ጎልማሶች የመሠረተ ትምህርት ሥልጠና መጀመር የሚያስፈራና በራሳቸው እንዳይተማመኑ የሚያደርጋቸው ይሆንባቸዋል። አንዳንዶቹ ብዙ ጊዜ ለመማር ሞክረው ሳይሳካላቸው የቀሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ስላረጁ ምንም ዓይነት አዲስ ነገር ሊማሩ የሚችሉ አይመስላቸውም። አንድ የናይጄርያ ተረት “ካረጁ በኋላ ግራኝ መሆን አይቻልም” ይላል።
አስተማሪዎች ተማሪዎቹ ያሳዩትን እድገት በመናገርና በማመስገን በራሳቸው እንዲተማመኑና ፍላጎታቸው እንዳይቀዘቅዝ ለመርዳት ይችላሉ። ትምህርቱ በተቻለ መጠን ቀለል ብሎና በየጊዜው በተወሰኑ የመማር ግቦች ላይ እንዲደርሱ በሚያስችላቸው መንገድ መንደፍ ይኖርበታል። ጎልማሶችን ማስተማር የተባለው ጽሑፍ “የተማሪው ፍላጎት ሳይቀዘቅዝ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ ተማሪው ጥረቱ እየተሳካለት እንዳለ ማወቁ ሳይሆን አይቀርም” ይላል።
ጎልማሶች በአጠቃላይ ከትምህርታቸው ምን ውጤት ማግኘት እንደሚፈልጉ ስለሚያውቁ እዚህ ግባቸው ላይ የሚያደርሳቸውን ዕድገት ወዲያውኑ ማየት ይፈልጋሉ። አንድ በአፍሪካ የሚኖሩ የጎልማሶች ትምህርት ባለሞያ “ክፍል ገብተው በተቻለ ፍጥነት ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን አውቀው ለመገላገል ይፈልጋሉ” ብለዋል።
አንዳንድ ጊዜ ተማሪዎች ለራሳቸው የሚያወጡት ግብ በቀላሉ ሊደረስበት የማይችል ይሆናል። አስተማሪው ከመጀመሪያ አንስቶ ተማሪው መለስተኛ የሆነ የአጭር ጊዜ ግቦችን እንዲያወጣና እነዚህ ግቦች ላይ እንዲደርስ መርዳት ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ማንበብ ስለፈለገ ማንበብና መጻፍ መማር ጀመረ እንበል። ይህ ግብ የረዥም ጊዜ ግብ ነው። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ በሚማርበት ጊዜ አስተማሪው ፊደሎችን በሙሉ እንደማወቅ፣ የተወሰኑ ጥቅሶችን አውጥቶ እንደማንበብና ቀለል ያሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንደማንበብ ያሉ መለስተኛ ግቦችን እንዲያወጣ ሊያበረታታው ይችላል። በየጊዜው ካወጣቸው ግቦች ላይ ለመድረስ መቻሉ የተማሪው ፍላጎት እንዳይቀዘቅዝና በትምህርቱ እንዲቀጥል ይረዳዋል።
ውጤታማ የሆኑ አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን በማበረታታትና በማመስገን እንዲሁም ተግባራዊ የሆኑና ሊደረስባቸው በሚችሉ ግቦች ላይ እንዲደርሱ በመርዳት ፍላጎታቸውን ሊያነሳሱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ጎልማሳ ተማሪዎች እድገት እንዲኖራቸው ከፈለጉ ሁልጊዜ አጉራሽ እንደሚያስፈልጋቸው ሆኖ ሊሰማቸው አይገባም። ለራሳቸው ትምህርት ኃላፊዎቹ እነርሱ እንደሆኑ ሊሰማቸውና በራሳቸው ተጣጥረው ለመማር ፈቃደኛ ሊሆኑ ያስፈልጋል። እንዲህ ካደረጉ ማንበብና መጻፍ ይችላሉ። ይህ ችሎታ ደግሞ በሕይወታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣላቸዋል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ጎልማሶችን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር የሚረዱ መመሪያዎች
1. የተማሪውን ፍላጎት ማነሳሳት በጣም አስፈላጊ ነው። ከመጀመሪያው የትምህርት ወቅት ጀምረህ ማንበብና መጻፍ የሚያስገኘውን ጥቅም ጠበቅ አድርገህ ግለጽ። ተማሪው ምክንያታዊ የሆነ የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ ግብ እንዲያወጣ አበረታታው።
2. ተማሪው እድገት እንዲኖረው ከተፈለገ በሳምንቱ ውስጥ በርከት ያሉ የትምህርት ወቅቶች መመደብ ያስፈልጋል። በሳምንት አንድ ጊዜ አይበቃም። ተማሪው በየትምህርቶቹ መካከል የቤት ሥራ መሥራት አለበት።
3. ተማሪውን የሚከብድ ነገር በመጠየቅ ወይም በአንድ የትምህርት ወቅት በጣም ብዙ ነገር በማስተማር አታስደንግጠው። ይህ ተስፋ እንዲቆርጥና መማሩን እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል።
4. ሁልጊዜ የምታበረታታና በጎው ጎን የሚታይህ ሁን። የማንበብና የመጻፍ ችሎታ የሚገኘው ትናንሽና ተከታታይ በሆኑ ቀስ በቀስ በሚሰጡ ስልጠናዎች ነው። ተማሪው በሚያደርገው እድገትና መሻሻል መርካት ይኖርበታል።
5. ተማሪው የሚማራቸውን ነገሮች በተቻለ ፍጥነት በዕለታዊ ኑሮው ሥራ ላይ እንዲያውል አበረታታ።
6. ከትምህርቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላቸው ጉዳዮች ላይ ብዙ ጊዜ አታባክን። ጎልማሶች ብዙ ሥራ ያለባቸው ሰዎች ናቸው። የትምህርቱን ክፍለ ጊዜ በአብዛኛው አስፈላጊዎቹን ነገሮች ለማስተማር ተጠቀምበት።
7. ሁልጊዜ ለተማሪው የሚገባውን ክብር ስጥ። ፈጽሞ አታዋርደው ወይም አታሳፍረው።
8. ለሚያጋጥሟቸው ግላዊ ችግሮች ንቁዎች ሁኑ። አንድ ተማሪ መነጽር ስለሚያስፈልገው ጥቃቅን ፊደላትን ማንበብ ያቅተው ይሆናል። ሌላው ደግሞ አጥርቶ የመስማት ችግር ይኖርበትና ትክክለኛውን የቃላት አጠራር መስማት ያስቸግረው ይሆናል።
9. ፊደላት እርስ በርሳቸው ተቀጣጥለው የሚጻፉ ከሆነ ተማሪው ቀጣጥሎ መጻፍ ከመሞከሩ በፊት ነጣጥሎ መጻፍ መማር አለበት። ተነጣጥለው የተጻፉ ሆሄያት ለመማርም ሆነ ለመጻፍ ቀላል ከመሆናቸውም በላይ በጽሑፎች ላይ ከሚወጡት ሆሄያት ጋር በጣም ይመሳሰላሉ።
10. ተማሪው የተጻፉ ፊደላት ላይ ስስ ወረቀት አስደግፎ እንዲገለብጥ ማድረግ መጻፍ ለማስተማር የሚያስችል ጥሩ መንገድ ነው። ፊደላቱ ላይ አስደግፎ ደጋግሞ ከገለበጠ በኋላ በሌላ ወረቀት ላይ በራሱ መጻፍ ሊሞክር ይችላል።
11. አብዛኛውን ጊዜ ከመጻፍ ይልቅ ማንበብ በፍጥነት ይለመዳል። ተማሪው በጽሑፍ የተሰጠውን የቤት ሥራ ጽፎ አልመጣም ብለህ ወደ አዳዲስ የማንበብ ትምህርቶች እንዳይዛወር አታድርግ። በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ፊደላትን ለማወቅና ለማስታወስ ቀላል የሚሆነው ተማሪዎቹ እየጻፉ ሲለማመዷቸው ነው።
12. ጎልማሳው ተማሪ በጣቶቹ የረቀቁ ሥራዎችን ለመሥራት የሚችል ቢሆንም በብዕር ወይም በእርሳስ ተጠቅሞ መጻፍ ተስፋ አስቆራጭና አስቸጋሪ ሥራ ሊሆንበት ይችላል። ጥርት ያሉ ፊደላት ካልጻፍክ ብለህ አታስገድደው።