የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 7/8 ገጽ 15-17
  • በቀይ ባሕር ውስጥ የሚገኙ አስደናቂ ነገሮች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቀይ ባሕር ውስጥ የሚገኙ አስደናቂ ነገሮች
  • ንቁ!—1995
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዓሣ መብላት ለሕመም ሲዳርግህ
    ንቁ!—2006
  • አስደናቂው ክላውን ፊሽ
    ንቁ!—2016
  • ፓሮት ፊሽ–አሸዋ አምራች ማሽን
    ንቁ!—2015
  • ዓሣ ማጥመድ፣ በአእዋፍ ዓለም
    ንቁ!—2011
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1995
g95 7/8 ገጽ 15-17

በቀይ ባሕር ውስጥ የሚገኙ አስደናቂ ነገሮች

ሰዎች ውበት ከቆዳ አያልፍም ይላሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ እውነተኛ ውበት የሚገኘው ላይ ላዩን ከሚታየው ገጽታ በታች ነው። ይህ ደግሞ የሚሠራው ለሰዎች ብቻ አይደለም። በቀይ ባሕር ያለው ሁኔታም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ተገንዝቤአለሁ። ምድረ በዳ የሆነው የባሕሩ ዳርቻ የታደለ ዋናተኛ በቀይ ባሕር ውስጥ ሊመለከት ከሚችለው ዕፁብ ድንቅ ውበት ፈጽሞ የተለየ ነው።

ቀይ ባሕር አስደናቂ ዛጎላማ አለቶች ሊታዩ ከሚችሉባቸው እጅግ ማራኪ የሆኑ ስፍራዎች አንዱ እንደሆነ ይነገርለታል። ስለዚህ በመጀመሪያ ለማወቅ የጓጓሁት ይህ ዝናው ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ነበር።

ከባሕሩ በታች ያለውን ዓለም ካየሁ በኋላ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት ፈለግሁ። በቀይ ባሕር ውስጥ ያለውን ሕይወት የሚያጠኑ የባሕር ሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት አሮን ሚሮዝ የነበሩኝን ጥያቄዎች መልሰውልኛል።

በቀይ ባሕር ውስጥ በጣም ብዙ የባሕር ፍጥረታት የሚገኙት ለምንድን ነው?

“ቀይ ባሕር ለመላው የሕንድ ውቅያኖስ እንደ ጠርሙስ አንገት ስለሆነ በርካታ ዓሣዎች ይሰበሰቡበታል። ከዚህም በላይ ብዛት ያላቸው አስደናቂ ዛጎሎች አሉን። ብዙውን ጊዜ አንድ ካሬ ሜትር በማያክል ቋጥኝ ላይ ብቻ 20 የሚያክሉ የተለያየ ዓይነት ዝርያዎች ያሏቸው ዛጎሎች አድገው ታገኛለህ። ዛጎሎች በብዛት እንዲያድጉ የሚያደርገው በዓመቱ ውስጥ ብዙ መለዋወጥ የማይታይበትና በጣም ጥሩ የሆነው የውኃ ሙቀት ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው የሚዘንበው ዝናብ አነስተኛ መጠን ያለው በመሆኑ ባሕሩ ውስጥ ብዙ ደለል አይገባም። ይህም የባሕሩን ብክለት መጠን ይቀንሳል፤ ሆኖም ባለፉት 15 ዓመታት ሁኔታው እየተበላሸ መምጣቱ ያሳዝነኛል።”

ይህን ውድ የባሕር ሀብት በመጠበቅ ረገድ ያጋጠሙት ችግሮች ምንድን ናቸው?

“በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ አልተበላሹም በሚባሉት የባሕር ፍጥረታት መኖሪያዎች ላይ ያለው ከፍተኛ ችግር ብክለት ነው። በቀይ ባሕር ውስጥ ውኃውን የሚበክሉት ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ናቸው፤ እነሱም:- ፎስፈረስ የያዙ ንጥረ ነገሮች፣ ከዓሣ ማርቢያ ጣቢያዎችና በጠረፍ አካባቢ ከሚገኙ ከተማዎች የሚመጡ ፍሳሾች ናቸው። ባሕር ጠላቂ ዋናተኞች የሚያዘወትሯቸው ስፍራዎች መኖራቸውም ችግር ሊፈጥር ይችላል። ተሰባሪ የሆነው ዛጎላማ አለት ግዴለሽ በሆኑ ባሕር ጠላቂዎች ሊጎዳ ይችላል።”

በቀይ ባሕር ውስጥ ያሉትን ዛጎላማ አለቶች ለብዙ ዓመታት ሲያጠኑ ቆይተዋል። በጥናት ከደረሱባቸው ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

“ዓሣዎች የሚመገቡበት ፕሮግራም እንዳላቸው ተገንዝበናል። አንዳንዶቹ ጠዋት በአንድ ሰዓት ይጀምሩና ለሦስት ሰዓት ይመገባሉ፤ ከዚያም እረፍት ያደርጉና ከሰዓት በኋላ ተጨማሪ ሦስት ሰዓት ይመገባሉ። አንዳንዶች በሌሊት ብቻ ይመገባሉ። እነዚህ ፕሮግራሞች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ትናንሽ ዓሣዎች ቀኑን በሙሉ የሚታደኑ ቢሆኑ ኖሮ ራሳቸውን መመገብ ያስቸግራቸው ነበር። ዓሣዎችም እንደ ሰዎች ምግብ ያማርጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በሰውነቱ ላይ ሰማያዊ ነጠብጣብ ያለው ግሩፐር የተባለው ዓሣ በተለይ በቀይ ባሕር ውስጥ በብዛት የሚገኙትን ፌሪ ባስሌትስ የተባሉትን ዓሣዎች መብላት ይመርጣል። በገንዳ ውስጥ የምናረባቸው ዓሣዎቻችንም የየራሳቸው የምግብ ምርጫ አላቸው፤ አንዳንዶች ቱና የሚባሉትን ትላልቅ ዓሣዎች ሲመርጡ ሌሎች ደግሞ ሰርዲን የሚባሉትን ትናንሽ ዓሣዎች ይመርጣሉ።

“ዓሣዎች ሰውን ከሰው አይለዩም ብለህ ታስብ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚህ አይደለም። የጀርባ አጥንት የሌላቸው ዓሣዎች እንኳ ሰዎችን ለይተው ያውቃሉ። ከሥራ ባልደረቦቻችን አንዱ አንድን ኦክተፐስ ለጨዋታ ያህል መታ መታ ያደረገበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። ዓሣው መመታቱን አልወደደም፤ ስለዚህ ከዚያ ቀን ወዲህ ከዚያ ሰው እጅ ምግብ አልቀበልም አለ። በነገራችን ላይ ገር ሰዎች ከዓሣዎች ጋር ይበልጥ ሲስማሙ ኃይለኛ ወይም ትዕግሥት የለሽ ሰዎች ግን ዓሣዎችን እንደሚያበሳጯቸው ተገንዝበናል።”

አንድን ባሕር ጠላቂ እጅግ የሚማርከው ዕፁብ ድንቅ የሆነው ውበትና ልዩ ልዩ የቀለም ዓይነት ነው።

“በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ዓሣዎች በጣም እንደሚያስደንቁ እሙን ነው። ሆኖም አንዳንድ ዓሣዎች ቀለሞቻቸውን እንደ ትራፊክ መብራቶች በምልክትነት እንደሚጠቀሙባቸው ብዙዎች አይገነዘቡም። ለምሳሌ ያህል፣ ሬድ ግሩፐር የተባለው ዓሣ እንዲሁ ክልሉን ከሚቃኝበት ጊዜ ይልቅ አደን ላይ በሚሆንበት ጊዜ መልኩ ጠቆር ይላል። ግሩፐር በተባለው ዓሣ የሚታደነው ክላውን ፊሽ የግሩፐርን ቀለም በማየት ግሩፐር ‘አደን ላይ እንዳልሆነ’ መለየት ይችላል። በእነዚህ አደጋ በሌለባቸው ጊዜያት ክላውን ፊሽ ክልሉን የወረረውን ግሩፐር በድፍረት ይከተለዋል።”

እጅግ አስገራሚ በሆነው የአምላክ ፍጥረት የሚታየው ውበት ባልጠበቅንባቸው ብዙ ቦታዎች ሊገኝ እንደሚችል አያጠራጥርም። የዚህን ውበት ቅንጣት ናሙና ብቻ በመመርመር ሕይወቴ ታድሷል። በዚህ የአጭር ጊዜ ቆይታ ከባሕር በታች ባለው ዓለም የተመለከትኩት ነገር ፕላኔታችን የያዘችውን ውድ የተፈጥሮ ሀብት በእጅጉ እንዳደንቅ አድርጎኛል።— በአንድ ግለሰብ የተጠናቀረ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ላየንፊሽ የባሕር እንስሳት አድነው ይበሉኛል የሚል ስጋት ሳይኖርበት ተዝናንቶ ይዋኛል። እሾሃማ ክንፎቹ መርዝ የተሞሉ ስለሆኑ አዳኞቹ አይቀርቡትም

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክላውን ፊሽ በአንድ ትልቅ የባሕር ተክል መካከል ከሚገኘው መኖሪያው እምብዛም አይርቅም። ከመኖሪያው ከተለየ በጠላቶቹ በቀላሉ ሊያዝ ይችላል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተርፍላይ ፊሽ የሚባሉት ዓሣዎች ብዙ ዓይነት ቀለም አላቸው። ጠፍጣፋ ሰውነታቸው ሲወዛወዝ ቢራቢሮን አስታወሰኝ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢምፐረር ኤንጅልፊሽ እያደገ ሲሄድ የሚለዋወጥ ብዙ ዓይነት የቆዳ ቀለምና መልክ አለው

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፒካሶ ፊሽ አካል ላይ ያሉት ብልጭልጭ መስመሮችና በከንፈሮቹ ላይ ያለው ደማቅ ቢጫ ቀለም በጥሩ ሠዓሊ የተሳለን ረቂቅ ሥዕል አስታውሶኛል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ