የወጣቶች ጥያቄ . . .
ወላጆቼን መታዘዝ ያለብኝ ለምንድን ነው?
ስታን ያደገው ፈሪሃ አምላክ ባላቸው ወላጆች ነበር። ይሁን እንጂ 16 ዓመት ሲሆነው ለወላጆቹ ለመታዘዝ አሻፈረኝ አለ። “ከሰዎች ጋር ለመገናኘትና በእነርሱም ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ፈለግሁ። ሌሎች ሰዎች ያላቸውን ነገር ሁሉ ለማግኘት ፈለግሁ” በማለት ስታን ገልጿል። ስታን ዕፅ አዘዋዋሪ በመሆን እነዚህን ፍላጎቶቹን ለማሳካት አቀደ። የት ውሎ እንደሚመጣና ወደ ቤት ይዞት የሚመጣውን ገንዘብ ከየት እንደሚያመጣው ሲጠየቅ የግድ መዋሸት ነበረበት። “ሕሊናዬ ደንዝዞ ነበር” በማለት ስታን ያስታውሳል።
ጆን ክርስቲያን ሆኖ የተጠመቀው በ11 ዓመቱ ነበር። “እውነት ግን ወደ ልቤ ዘልቆ አልገባም ነበር” በማለት እውነቱን ሳይሸሽግ ተናግሯል። “ይህን እርምጃ የወሰድኩት ቤተሰቤ ይህን እንዳደርግ ይጠብቅብኝ ስለነበረ ነው። ወደ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስገባ ዓመፀኛ እየሆንኩ መጣሁ። የሮክ ሙዚቃም መጥፎ ተጽእኖ አሳድሮብኝ ነበር። የባሕር ላይ ስፖርት መጫወትና ወደ ባሕር ዳርቻ እየሄድኩ አብዛኛውን ጊዜዬን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከማይመሩ ወጣቶች ጋር ማሳለፍ ጀመርኩ። እዚያ ደግሞ ብዙ አደንዛዥ ዕፆች ነበሩ።” ብዙም ሳይቆይ ከወላጆቹ ቤት ወጣ፤ ከዚያም ከተማረው ነገር ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ኑሮ መኖር ጀመረ።
የሚያምፁበት ምክንያት
ወጣቶች አቅማቸውን ለመፈተንና የተወሰነ ነጻነት ለማግኘት መሞከራቸው የተለመደ ነገር ነው። ይሁን እንጂ የዓመፀኝነት፣ የክፋትና በራስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያመጣ ጠባይ ደግሞ ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው። ይህን የሚያመጣው ምንድን ነው? ምክንያቶቹ ብዙና የተለያዩ ናቸው። “በወጣትነታችሁ ዘመን የሚያስደስታችሁ ነገር ማግኘት ትፈልጋላችሁ። መዝናናት ትፈልጋላችሁ” በማለት ጆን ገልጿል። ይሁን እንጂ ወጣቶች የሕይወት ተሞክሯቸው አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ሁልጊዜ የተሻለውን ውሳኔ ያደርጋሉ ማለት አይቻልም። (ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ አስተዋይ የሆኑ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ምክንያታዊ የሆነ ገደብ ያበጃሉ፤ ይህን ደግሞ አንዳንድ ወጣቶች ክፉኛ ይቃወሙታል።
የሚያሳዝነው አንዳንድ ወጣቶች ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወላጆቻቸው የሰጧቸውን ሥልጠና ወደ ጎን ገሸሽ አድርገውታል። (ኤፌሶን 6:1–4) ክርስትና ‘ጠባብና ቀጭን’ የሕይወት መንገድ እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:13, 14) ስለዚህ ክርስቲያን ወጣቶች ብዙውን ጊዜ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው የሚያደርጉትን ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። አብዛኛዎቹ ክርስቲያን ወጣቶች የአምላክ ሕጎች ከባዶች እንዳልሆኑ በመገንዘብ የተጣሉባቸውን ገደቦች ያከብራሉ። (1 ዮሐንስ 5:3) በእርግጥም እነዚህ ሕጎች ወጣቶችን ከጋብቻ በፊት ከማርገዝ፣ ዕፅን አላግባብ ከመጠቀም፣ በጾታ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎችና ከመሳሰሉት ችግሮች ይጠብቋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አንዳንድ ወጣቶች ግን ነገሮችን በዚህ መንገድ ለመመልከት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋት የሚፈልጉትን ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ እንዳይከተሉ እንቅፋት እንደሆኑባቸው ይሰማቸዋል።
አንድ ወጣት ተግሣጽንና መዝናኛን በመሳሰሉ ጉዳዮች ረገድ ወላጆቹ ችክ ያለ አቋም እንዳላቸው ሆኖ ከተሰማው ብስጭቱ ሥር እየሰደደ ይሄዳል። “ወላጆቼ በጣም ጥብቅ የሆኑብን ይመስለኛል” በማለት አንዲት ወጣት ሴት የተሰማትን ቅሬታ ገልጻለች። እውነት ነው፣ ሌሎች ክርስቲያን ወላጆች የሚፈቅዱትን ነገር አንተ እንዳታደርግ ስትከለከል ቅር ሊያሰኝ ይችላል። (ቆላስይስ 3:21) አንዳንድ ወጣቶች የተሰማቸውን ብስጭት ለመታዘዝ ፈቃደኛ ባለመሆን ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው አምላክ ላወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ምንም ዓይነት አክብሮት ስለማያሳዩ እነርሱን ለመታዘዝ እምቢተኞች ይሆናሉ። “አባዬ የአልኮል ሱሰኛ ነበር” በማለት ጆን ያስታውሳል። “ብዙ ይጠጣ ስለ ነበር ከእማዬ ጋር ይጋጩ ነበር። ከእሱ ለመራቅ ስንል ብዙ ጊዜ ከቤት ወጥተን ነበር።” የአልኮል ሱሰኞችና ሌሎች ነገሮችን አለ አግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች ልጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አጥጋቢ በሆነ መንገድ ማሟላት አይችሉም። እንዲህ ባሉ ቤቶች ውስጥ የቃላት ዱላና ውርደት የአንድ ወጣት የዕለት ተዕለት ገጠመኙ ሊሆን ይችላል።
ሌሎች ወጣቶች ደግሞ የሚያምፁበት ምክንያት ወላጆቻቸው ስለሚተዉአቸው ወይም ችላ ስለሚሏቸው ነው። ማመፅ የወላጆቻቸውን ትኩረት የሚያገኙበት ወይም እነሱን የሚጎዱበት መንገድ መስሎ ሊታያቸው ይችላል። ከሀብታም ቤተሰብ የተወለደችው ወጣቷ ቴይለር “እስከማስታውሰው ድረስ ወላጆቼ ሁልጊዜ ብቻዬን ይተዉኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። “እኔ አንድ ልጃቸው ነኝ፤ ወላጆቼ ደግሞ ብዙ ጊዜ አብረውኝ ስለማይሆኑ ብዙ ገንዘብ ሰጥተውኝ ይሄዱ ነበር።” የሚቆጣጠራት ስላልነበረ ቴይለር በምሽት ወደ ዳንስ ቤቶች መሄድና መስከር ጀመረች። ጠጥታ ስትነዳ ተይዛ እስከታሰረችበት ጊዜ ድረስ ወላጆቿ ችግር እንደነበራት አልተገነዘቡም ነበር።
በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ:- “በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ?” በማለት አንድን የክርስቲያኖች ቡድን ሲጠይቅ የጠቆመው ሁኔታም አለ። (ገላትያ 5:7) ብዙ ጊዜ ችግሩ መጥፎ ባልንጀርነት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:33) አንዲት በአሥራዎቹ እድሜ ላይ የምትገኝ ኤልሳቤጥ የተባለች ልጅ “ከመጥፎ ልጆች ጋር ተጎዳኘሁ” ስትል ተናግራለች። “ሲጋራ ማጨስና አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ” የጀመረችው በእኩዮች ተጽእኖ እንደሆነ ገልጻለች። “ዝሙት ዘወትር የምፈጽመው ነገር ነበር” በማለት አክላ ተናግራለች።
ማመፅ ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው?
ምናልባት አንተም በሚያበሳጭ አልፎ ተርፎም በሚያስጨንቅ ሁኔታ ሥር እንዳለህ ሊሰማህ ይችላል። ሁኔታው በወላጆችህ ላይ እንድታምፅና ያሻህን ሁሉ እንድታደርግ ይፈትንህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለጻድቁ ሰው ለኢዮብ የተሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተከተል:- “ቁጣ ለእልህ [ድርጊት] እንዳያነሳሳህ ተጠንቀቅ። ራስህን የሚጎዳ ነገር ከማድረግ ተቆጠብ።”— ኢዮብ 36:18–21 አዓት
እልኸኝነትና መጥፎ ጠባይ ወላጆችህ ምላሽ እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል፤ የሚያሳዩት ምላሽ ግን የሚያስደስት አይሆንም። እንዲያውም ተጨማሪ እገዳዎችን ሊጥሉብህ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ያለው ጎጂ ጠባይ ወላጆችህን በጣም ያሳዝናቸዋል። (ምሳሌ 10:1) ይህ ታዲያ እንደምታፈቅራቸው ያሳያልን? ያለህበትን ሁኔታ ያሻሽለዋልን? በእነርሱ ላይ ትክክለኛ የሆነ ቅሬታ ካለህ ይበልጥ የተሻለው መንገድ ስለጉዳዩ ከእነርሱ ጋር መነጋገር ነው።a ምናልባት አንተን የሚይዙበትን መንገድ ለማስተካከል ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ።
ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ የምትወስዳቸው እርምጃዎች በአምላክ ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉት ስሜት ነው። ‘በአምላክ ላይ? ’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን፣ ምክንያቱም ወላጆችህን እንድታከብር ያዘዘህ እርሱ ስለሆነ በወላጆችህ ላይ ማመፅ በእርሱ ላይ እንደ ማመፅ ይቆጠራል። (ኤፌሶን 6:2) እንዲህ ያለው ያለመታዘዝ ጠባይ አምላክን እንዴት እንዲሰማው የሚያደርግ ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ የእስራኤልን ሕዝብ በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “በበረሓ ሳሉ ብዙ ጊዜ በእርሱ ላይ ዐመፁ።” ይህስ ምን ውጤት አስከተለ? “ብዙ ጊዜም [አምላክን] አሳዘኑት።” (መዝሙር 78:40 የ1980 ትርጉም ) እርግጥ ነው፣ ወላጆችህ ከሚገባው በላይ ጥብቅ እንደሆኑ ተሰምቶህ ትበሳጭ ይሆናል። ነገር ግን የሚወድህንና የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ የሚፈልገውን የይሖዋ አምላክን ልብ ማሳዘን ትፈልጋለህን?— ዮሐንስ 17:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4
“ነፃነት” የሚያመጣው መዘዝ
አፍቃሪ ሰማያዊ አባታችንን የምንሰማበት በቂ ምክንያት አለን። በሐሰት “የነፃነት” ተስፋ አትታለል። (ከ2 ጴጥሮስ 2:19 ጋር አወዳድር።) አንዳንድ ወጣቶች መጥፎ ጠባይ በማሳየታቸው የተጠቀሙ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ መዝሙራዊው:- “በክፉዎች ላይ አትቅና፣ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፣ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና” በማለት አስጠንቅቋል። (መዝሙር 37:1, 2) የሚያምፁ ወጣቶች ብዙውን ጊዜ እነርሱ ነፃነት ነው ብለው የሚያስቡት ነገር ከባድ መዘዝ ያስከትልባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በገላትያ 6:7 ላይ “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ይላል።
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ስታንን ተመልከቱ። ልክ እንደተመኘው በአልባሌ ጓደኞቹ ዘንድ ተወዳጅነትን አተረፈ። “ተቀባይነት እንዳገኘሁ ተሰማኝ” በማለት ያሳለፈውን ሁኔታ በማስታወስ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ነገሮች እየከፉ ሄዱ። እንዲህ አለ:- “አንድ ጊዜ በጥይት ተመትቻለሁ፤ ለጥቂት ጊዜም ታስሬ ነበር። አሁን ደግሞ ወደ ወህኒ ልወርድ ነው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ለራሴ ያቀረብኩት ጥያቄ ‘ይህ ሁሉ መሥዋዕት ሊከፈልለት የሚገባው ነገር ነውን?’ የሚል ነበር።”
ጆን “ነፃነት” ለማግኘት ያደረገው ጥረትስ ያተረፈለት ነገር ምንድን ነው? አደንዛዥ ዕፅ ይዞ በመገኘቱ ከታሰረ በኋላ ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ። ከዚያ በኋላ ይበልጥ የከፋ ድርጊት ውስጥ ተዘፈቀ። ጆን የፈጸመውን ድርጊት ሲናዘዝ “ገንዘብ ለማግኘት መኪናዎች እሰርቅ ነበር። በጣም ዓመፀኛ ነበርኩ።” ጆን ወንጀል በመፈጸም ብዙ ገንዘብ አካበተ። ይሁን እንጂ ያሳለፈውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ብሏል:- “ሁሉንም አባከንኩት። እንወስደው የነበረው ዕፅ መጠን ፈጽሞ የሚታመን አልነበረም።” ጆን በማይደባደብበት፣ በማይሰርቅበትና በማይሰክርበት ጊዜም እንኳ ዕረፍት አልነበረውም፤ ምክንያቱም ከፖሊሶች ይሸሽ ነበር። “ወደ 50 ጊዜ ያህል ታስሬ ነበር። ብዙውን ጊዜ ለክስ የሚሆን በቂ መረጃ አያገኙብኝም ነበር፤ ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ ዓመቱን ሙሉ በእስር አሳልፌአለሁ።” አዎን፣ ጆን ነፃነት ያገኘ ሰው ከመሆን ይልቅ ‘በሰይጣን ጥልቅ ነገር’ መጠመዱን ተገነዘበ።— ራእይ 2:24
ስለ ኤልሳቤጥም እንዲሁ ሊባል ይቻላል። ከዓለማዊ ጓደኞቿ ጋር ያሳለፈችው ጊዜ መጨረሻ ለእስር ዳረጋት። የሆነውን ሁኔታ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ይባስ ብሎ አረገዝኩ፤ አደንዛዥ ዕፅ እጠቀም ስለነበረ አስወረደኝ። አደንዛዥ ዕፅ ሕይወቴ ነበር፤ በውስጤ የሚፈጥረውን ስሜት ለማግኘት እጓጓ ነበር። በመጨረሻም ከምኖርበት አፓርታማ ተባረርኩ። ወደ ቤት ተመልሼ መሄድ አልችልም፤ ይሖዋ እንዲረዳኝ ለመጠየቅ እንኳ አፈርኩ።”
አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ወደ ጎን ገሸሽ በማድረጋቸው አስከፊ መዘዝ የደረሰባቸው ወጣቶችን በተመለከተ ብዙ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንተ ‘ትክክለኛ መንገድ ነው’ ብለህ የምታስበው ወደሞት ይመራህ ይሆናል።” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 14:12 የ1980 ትርጉም ) ስለዚህ ልትወስደው የሚገባህ የጥበብ እርምጃ ከወላጆችህ ጋር ወዳጃዊ ግንኙነት ለመፍጠር መሞከር ነው። ትክክል አይደለም ብለህ የምታስበውን ገደብ ከመጣስ ይልቅ ከእነርሱ ጋር መወያየቱ የተሻለ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች ]
a በዚህ ጉዳይ ላይ በርከት ያሉ ጽሑፎች ጠቃሚ ሐሳቦችን አቅርበዋል። ለምሳሌ ያህል በጥር 8, 1985፣ በነሐሴ 8, 1992 እና በኅዳር 8, 1992 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትሞቻችን ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚለው ርዕስ ሥር የወጡትን ትምህርቶች ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በወላጆችህ ላይ ማመፅ የበለጠ “ነፃነት” ይሰጥህ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሚያስከትለውን መዘዝ አስበህበታልን?