“ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ”
“ለየት ያሉ ጉንዳኖች”—ይህ አባባል በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለተገነባ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ የሚናገር መጣጥፍ በቀረበበት ከጥቂት ዓመታት በፊት በወጣ አንድ ጋዜጣ ላይ የሰፈረ እንግዳ የሆነ ርዕስ ነው። ጋዜጣው በዚህ ርዕስ ለመጻፍ ያነሳሳው ምንድን ነው? በግንባታ ላይ የሚገኝ ሕንፃ የሚያሳየውን ከአየር ላይ የተነሳውን ፎቶግራፍ ስትመለከት ጋዜጣው እንደዚህ ያለው ለምን እንደሆነ መረዳት አያስቸግርህም። ይህ ርዕስ በወጣበት ጋዜጣ ላይ የሚገኝ አንድ ንዑስ ርዕስ “አምስት መቶ የይሖዋ ምሥክሮች በግንባታ ላይ— አስገራሚ የጉንዳን ኩይሳ” ይላል።
የቀረበው ንጽጽር ምናልባትም ዜና ዘጋቢው ካሰበው በላይ ከሁኔታው ጋር የሚስማማ ነው። በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በግንባታ ቦታ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ከላይ በርቀት ለሚመለከታቸው በኩይሳ ላይ ያሉ ጉንዳኖች መስለው እንደሚታዩ እሙን ነው። ሆኖም በመካከላቸው ያለው ተመሳሳይነት ከውጪያዊ ገጽታ አልፎ ይሄዳል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች በምሳሌ 6:6 ላይ የሚገኘውን “ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ፣ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አክብደው ይመለከቱታል። አንድ ሰው ጉንዳን በመመልከት ጠቢብ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ ጉንዳኖች ብዙ ይሠራሉ። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል:- “በደመ ነፍስ ለወደፊቱ ጊዜ ዝግጅት ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን ጽናታቸውና ቁርጠኝነታቸውም ያስደንቃል። ብዙውን ጊዜ ከራሳቸው ክብደት እጥፍ የሚሆኑ ነገሮችን ይሸከማሉ ወይም ባለ በሌለ ኃይላቸው ተጠቅመው ይጎትታሉ፤ ሥራቸውን ለመወጣት የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ቢወድቁም፣ ቢንሸራተቱም ወይም ከከፍታ ቦታ ላይ ቢንከባለሉም እንኳ ወደ ኋላ አይመለሱም።”a
ምንም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች የራሳቸውን ክብደት እጥፍ የሚመዝን የግንባታ ቁሳቁስ ባይሸከሙም ሰዎች እስኪገረሙ ድረስ ግንባታቸውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቃቸው ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። የመንግሥት አዳራሻቸው መሠረቱ በተጣለ በሁለት ወይም ሦስት ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ማየቱ የተለመደ ነው!
ይህን ለማከናወን የቻሉት እንዴት ነው? የጉንዳኖችን ቁልፍ ጠባይ በመኮረጅ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (የእንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ጉንዳኖችን በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “አስገራሚ የትብብር መንፈስ አላቸው። ጎጆአቸውን በንጽሕና ከመያዛቸውም በተጨማሪ ለባልደረቦቻቸው አሳቢነት ያሳያሉ። አንዳንድ ጊዜ አደጋ የደረሰባቸውን ወይም የደከሙ ጉንዳኖችን ወደ ጎጆአቸው በመመለስ ይረዷቸዋል።” መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ዜና ዘጋቢ በምሥክሮቹ መካከል ባለው ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የትብብር መንፈስ የተገረመ ይመስላል። እንዲህ አለ:- “በግንባታው ላይ ከሁሉም ዓይነት የግንባታ ዘርፎች የተውጣጡ 80 ባለሙያዎች በ400 ፈቃደኛ ሠራተኞች እየታገዙ በጣም ተደስተውና ተዝናንተው አስደናቂ ሥራ አከናውነዋል።”
ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾቻቸውን ሲሠሩ የሚያፈሱት ጉልበትና የሚያሳዩት የትብብር መንፈስ አዳራሾቹ ተሠርተው ካለቁ በኋላ ባሉት ዓመታት በአዳራሾቹ ውስጥ ለሚፈጸሙ ነገሮች ቅምሻ ነው። በአዳራሾቹ ውስጥ ጠንክረው መሥራታቸውንና እርስ በርስ መተባበራቸውን ይቀጥላሉ፣ የትምህርትና የስብከት ሥራቸውን ያደራጃሉ እንዲሁም የሚያንጹና ትምህርት ሰጪ የሆኑ ስብሰባዎች ያካሂዳሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ለተከታዮቹ ያሳየውን ዓይነት ፍቅራዊ አሳቢነት አንዳቸው ለሌላው ለማሳየት ይጥራሉ።— ዮሐንስ 13:34, 35
አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ተመልክተህ በውስጡ ምን እንደሚካሄድ ለማወቅ ፈልገህ ከነበረ ራስህ መጥተህ እንድታየው ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። ሞቅ ያለ አቀባበል እንደሚደረግልህና አዲስ ነገር እንደምትቀስም እርግጠኞች ነን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፈረንሳይ ኦሪያክ ከተማ በአጭር ጊዜ የተገነባ የመንግሥት አዳራሽ
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል13]
የጉንዳኖቹ ሥዕል:- Pharaoh’s ant. Lydekker