የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 1/8 ገጽ 28-29
  • የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “ዋነኛው አንቀሳቃሽ ኃይል”
  • ኢየሱስ የሰሎሞን ግኝት ትክክል መሆኑን አረጋግጧል
  • የሕይወትን ትርጉም ማግኘት
  • ‘የሰው ሁለንተናዊ ግዴታ’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • የሕይወትህ ዓላማ ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው ምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ሕይወት ዓላማ አለውን?
    የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1996
g96 1/8 ገጽ 28-29

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?

“የዳርዊን ተከታዮች ተፈጥሮ የተሻሉትን ሕያዋን ነገሮች እየመረጠ ደካማዎቹን ግን እያከሰመ አሁን ወዳሉበት ደረጃ እንዲደርሱ አስችሏል የሚለው ንድፈ ሐሳብ (ናቹራል ሴሌክሽን) ሕይወት ያላቸው ነገሮች በአዝጋሚ ለውጥ እንደተገኙ ያረጋግጣል ይላሉ። ሆኖም አንድ ሕይወት ያለው ነገር ከቀላልነት ወደ ውስብስብነት፣ ራሱን ይበልጥ ወደማወቅና ወደበለጠ የብልህነት ደረጃ የሚያድገው እነዚህ ባሕርያት አስፈላጊ በመሆናቸው እንጂ በመመረጣቸው አይደለም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።”— ዲለን ቶማስ (1914-53 የዌልስ ባለቅኔና ደራሲ።)

የመኖርን ትርጉም ለማግኘት ጥረት ማድረግ አዲስ ነገር አይደለም። ለብዙ መቶ ዘመናት የእውቀት ጥማት ባላቸው ሰዎች አእምሮ ውስጥ ሲጉላላ የቆየ ነገር ነው። በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው ኒው ዚላንዳውያን በአሁኑ ጊዜ የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ ያላቸው ፍላጎት ከአሥር ዓመት በፊት ከነበራቸው ፍላጎት የላቀ ነው። ሊስነር የተባለ መጽሔት ሪፖርት እንዳደረገው 15 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆናቸው ሰዎች ውስጥ አርባ ዘጠኝ ከመቶ የሚሆኑት “ብዙውን ጊዜ ስለ ሕይወት ትርጉም ያስባሉ።” ይህም በ1985 በተደረገው ተመሳሳይ ጥናት ከተገኘው ቁጥር ከፍ ያለ ነው። በዚያን ጊዜ ስለ ሕይወት ትርጉም ያስቡ የነበሩት 32 ከመቶ ነበሩ።

በሌሎች አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታም ከኒው ዚላንዳውያኑ ጋር ይመሳሰላል። ሊስነር የተባለው መጽሔት በመቀጠል “የመኖራችን ትርጉም ምን እንደሆነ የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ይህ ጉዳይ ከ80ዎቹ ዓመታት ይልቅ አሁን እያሳሰበን እንዳለና ይበልጥ ግራ እንደተጋባን ሊጠቁም ይችላል” ብሏል።

የዝግመተ ለውጥ አማኞች የምንኖረው ለምንድን ነው? ለሚለው ምድር አቀፍ ጥያቄ የሚሰጧቸው መልሶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ ያሉትን በርካታ ጠያቂዎች እንዳላረኩ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው የሚኖረው ለምን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችለውን ትክክለኛ አቅጣጫ ሊያመለክት ይችላልን?

“ዋነኛው አንቀሳቃሽ ኃይል”

በምድር ላይ ከሚኖሩት ፍጥረታት መካከል ስለ ሕይወት ዓላማ የሚያስበው ሰው ብቻ ነው። ለምን እንዲህ እንደሆነ ታውቃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ በመክብብ 3:11 ላይ አንዱን ምክንያት ይነግረናል። ጥቅሱ “ሰዎች ያለፈውንና የወደፊቱን ጊዜ እንዲያስተውሉ አደረጋቸው” በማለት ስለ ፈጣሪ ይናገራል። (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ሁሉም ሕያዋን ፍጥረታት ከፍተኛ የሆነ የመኖር ፍላጎት ቢኖራቸውም ስላለፈው፣ ስለአሁኑና ስለሚመጣው ጊዜ የማወቅ ችሎታ ያለው ሰው ብቻ ይመስላል። ሰው ስላለፈው ጊዜ ሊያሰላስልና ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ ሊያወጣ፣ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ሊጠባበቅ ይችላል፤ እንዲያውም በወደፊቱ ጊዜ ተሳታፊ የመሆን ጠንካራ ፍላጎቶች ሊያድርበት ይችላል። በተጨማሪም በዕድሜው አጭርነት ምክንያት የተመኘው ነገር ሳይሳካለት ሲቀር ይበሳጫል።

በዚህ የተነሳ ከየት መጣሁ? የምሄደውስ ወዴት ነው? ብሎ የሚጠይቀው ሰው ብቻ ነው። የሥነ አእምሮ ሊቅ የሆኑት ቪክቶር ፍራንክል እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የሕይወትን ትርጉም ለማወቅ ጥረት ማድረግ በሰው ውስጥ የሚገኝ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው። . . . ሕይወት ትርጉም እንዳለው የማወቅን ያህል በጣም አስከፊ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ኃይል የለም ለማለት እደፍራለሁ።”

ኢየሱስ የሰሎሞን ግኝት ትክክል መሆኑን አረጋግጧል

የጥንት ሰዎች የመኖርን ትርጉም ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አድሮባቸው ነበር። እስኪ ሦስት ሺህ ዓመት ወደ ኋላ መለስ እንበልና በሰሎሞን የሚመራውን የእስራኤል መንግሥት እንመልከት። የሳባ ንግሥት ስለ ሰሎሞን ስትናገር እንዲህ ብላ ነበር:- “ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው። እኔም መጥቼ በዓይኔ እስካይ ድረስ የነገሩኝን አላመንሁም ነበር፤ እነሆም፣ እኩሌታውን አልነገሩኝም ነበር፤ ጥበብህና ሥራህ ከሰማሁት ዝና ይበልጣል።”— 1 ነገሥት 10:6, 7

ንጉሥ ሰሎሞን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የመክብብ መጽሐፍ በመጻፍ አንባቢዎቹ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ አድርጎት ከነበረው ሙከራ የተገኘውን ውጤት እንዲያውቁ አድርጓል። ሙከራው በጥንታዊው ምሥራቅ የሚኖር ንጉሥ ሊያገኝ በሚችላቸው የደስታ አጋጣሚዎች ላይ የተደረገ ነበር። ሰሎሞን በምዕራፍ 2 ከቁጥር 1-10 ላይ በዛሬው ጊዜ ይገኛል ተብሎ ስለማይታሰብ የፈንጠዝያ ሕይወት ገልጿል። ቁሳዊ ሀብትና ሥጋዊ ተድላ ሊያስገኙ የሚችሉትን ደስታ በሙሉ ለማግኘት ጥረት አድርጎ ነበር። እነዚህን ነገሮች ማሳደድ ምን ስሜት እንደሚሰጥ ተናግሯል? የተናገረው ቃል በእነዚህ ነገሮች የሚመኩ ሰዎችን የሚያስደነግጥ ነው።

ያደረጋቸውን ነገሮች መለስ ብሎ ሲመለከት ሁሉም ከንቱ ሆነው አገኛቸው። ከንቱዎችና ጊዜ የሚያባክኑ ነበሩ። “እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ እነሆ፣ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፣ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም” በማለት ጽፏል።— መክብብ 2:11

ምድራዊ ተድላ የሚያስገኘው ጥቅም ጊዜያዊ ከሆነ ደስታ እንደማያልፍ ደርሶበታል። ሰብዓዊ ጥበብ ሰው በሕይወቱ ከሚያጋጥመው ሥቃይና ጭንቀት እንኳ እረፍት ሊያስገኝለት አይችልም።

ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሰው ማግኘት ስለሚኖርበት የቁሳዊ ሀብት ውርስ ከሚገባ በላይ ተጨንቆ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ለተሰበሰበው ሕዝብ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” በማለት ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል።— ሉቃስ 12:15

የሰዎችን የዕለት ተዕለት ችግር ሙሉ በሙሉ ማስወገድና ኑሯቸው ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ስለዚህ ያለ አምላክ ሕይወት ከንቱ ነው። ሰሎሞን በመክብብ 12:13 ላይ “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ” በማለት ተናግሯል።

የሕይወትን ትርጉም ማግኘት

ሰሎሞን የመኖር ትርጉምና ለአምላክ ጤናማ ፍርሃት ማሳየት የማይነጣጠሉ ነገሮች እንደሆኑ ሊገነዘብ ችሏል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ እውነት መሆኑን በተደጋጋሚ አረጋግጧል። ኢየሱስ ከአምላክ ቃል በመጥቀስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ብሏል። (ማቴዎስ 4:4፤ ዘዳግም 8:3) አዎን፣ እርካታ ያለው ኑሮ ለመኖር የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መንፈሳዊ ነገሮችን ችላ ለማለት አይችልም። በተጨማሪም ኢየሱስ ስለ ራሱ ሲናገር “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጸም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) ኢየሱስ ሰማያዊ አባቱን በፈቃደኝነት ማገልገሉ የደስታና የእርካታ ምንጭ ሆኖለት ነበር። እንደ ምግብና መጠጥ ሰውነቱን አድሶለታል። ሕይወቱ ዓላማ ያለው እንዲሆን አድርጎለታል።

ስለዚህ ከአምላክ ውጪ የሆነ ሕይወት የተሟላ ሊሆን ይችላልን? አይችልም! ታሪክ ጸሐፊው አርኖልድ ቶይንቢ አንድ ጊዜ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የአንድ ታላቅ ሃይማኖት እውነተኛ ዓላማ ብዙ ነፍሳት ወደ ትክክለኛው የሰው ልጅ ግብ ለመድረስ የሚያስችላቸውንና የአንድ ሃይማኖት መግለጫ የሆኑትን መንፈሳዊ ምክሮችና እውነቶች ለበርካታ ሰዎች ማዳረስ ነው። የሰው ሕይወት እውነተኛ ግብ አምላክን ማወደስና ለዘላለም ከእርሱ ጋር ተስማምቶ መኖር ነው።” ነቢዩ ሚልክያስ “ተመልሳችሁም በጻድቁና በኃጢአተኛው መካከል፣ ለእግዚአብሔር በሚገዛውና በማይገዛው መካከል ትለያላችሁ” በማለት አምላክ ያለውን አመለካከት ገልጿል።— ሚልክያስ 3:18

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በሐሳብ የተዋጠው” በሮዲን የተሠራ

[ምንጭ]

Scala/Art Resource, N.Y.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ