የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 7/8 ገጽ 10-11
  • ለዘላለም መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለዘላለም መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ዓላማ
  • ለዘላለም መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?
  • የዘላለም ሕይወት ማግኘት በእርግጥ ይቻላልን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ለዘላለም መኖር ሕልም አይደለም
    በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ
  • አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?
    አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?
  • ሕይወት ታላቅ ዓላማ አለው
    የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 7/8 ገጽ 10-11

ለዘላለም መኖር የምትችለው እንዴት ነው?

የሰው ልጅ አካል ሰዎች አሁን ከሚኖሩበት ዕድሜ በጣም የሚረዝም ዕድሜ የመኖር አቅም ያለው በመሆኑ አንዳንድ ሰዎች ሳይንስ ለዘላለም የምንኖርበትን ምሥጢር ያገኛል በማለት እምነታቸውን በሳይንስ ላይ ይጥላሉ። ዶክተር አልቭን ሲልቨርስታይን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የአካላችንን ኬሚካሎችና እርስ በርስ የሚፈጥሩትን ውህደት ይበልጥ በተሟላ መንገድ ስናውቅ የሕይወትን ምሥጢር መፍታት እንችላለን። ሰው እንዴት እንደሚያረጅ . . . መረዳት እንችላለን።”

ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? ሲልቨርስታይን “በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል” ብለዋል። “ሞትን ድል ለመንሳት የሚያስችለው እውቀት ዘላለማዊ ወጣትነት ጭምር ስለሚያስገኝ ‘ያረጁ’ ሰዎች አይኖሩም።”

ታዲያ የሰው ልጆች ይህን ማድረግ ይችላሉን? መጽሐፍ ቅዱስ “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ። ነፍሱ ትወጣለች፣ ወደ መሬቱም ይመለሳል። ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል” በማለት ይመክራል። (መዝሙር 146:3, 4) ቀደም ብለን እንደተመለከትነው የሰው ልጆች ለሞትና እርጅና ምክንያት የሆነውን በዘር የሚወረስ ጉድለት ማስተካከል ይቅርና ምክንያቱን ለይተው ማወቅ እንኳን አልሆነላቸውም። ይህን ማድረግ የሚችለው ፈጣሪያችን ብቻ ነው።

ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ለዘላለም በምድር ላይ እንዲኖሩ የአምላክ ፈቃድ ነውን?

የአምላክ ዓላማ

ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስቶች ያኖረው የት ነበር? በምድራዊ ገነት ውስጥ ነበር። በተጨማሪም “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) አዎን፣ የአምላክ ዓላማ መላዋ ምድር በሰላምና በደስታ በሚኖሩ ጻድቅ ሰብዓዊ ቤተሰቦች ቀስ በቀስ እንድትሞላ ነበር።—ኢሳይያስ 45:18

አዳም የአምላክን ትእዛዝ በመጣሱ ምክንያት የሞት ፍርድ የተወሰነበት ቢሆንም አምላክ የሰው ልጆች በምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም እንደሚኖሩ አስቀድሞ ያወጣው ዓላማ አልተለወጠም። (ዘፍጥረት 3:17-19) አምላክ “ተናግሬአለሁ፣ እፈጽምማለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢሳይያስ 46:11፤ 55:11) “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ለምድር ያለው ዓላማ ያልተለወጠ መሆኑን አመልክቷል።—መዝሙር 37:29

አምላክ ፈጣሪያችን በመሆኑ የሰው ልጆች እንዲያረጁና እንዲሞቱ የሚያደርጋቸውን ጉድለት ማስተካከል ይችላል። ታዲያ ይህን የሚያደርገው በምን መሠረት ነው? ይህ ጉድለት የመጀመሪያ ሰው ከሆነው ከአዳም የተወረሰ በመሆኑ አምላክ የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍጹም ሕይወት “በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ እንዳይሞት” ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል።—ዮሐንስ 3:16፤ ማቴዎስ 20:28

በዚህ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያው አዳም ምትክ በመሆን አባታችን ወይም ሕይወት ሰጪያችን ይሆናል። ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ “የኋለኛው አዳም” ተብሎ የተጠራው በዚህ ምክንያት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ስለዚህ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የኃጢአተኛው አዳም ልጆች በመሆናቸው ለሞት ኩነኔ የተገዙ ከመሆን ይልቅ “የዘላለም አባት” የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች በመሆን የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የበቁ ሆነው ይቆጠራሉ።—ኢሳይያስ 9:6

እርግጥ፣ “የዘላለም ንጉሥ” እና “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት” ይሖዋ አምላክ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ራእይ 15:3፤ ቆላስይስ 1:3) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ “የዘላለም አባት” እና “መድኃኒት” ሆኖ የተሰጠን ከመሆኑ በተጨማሪ ‘የሰላም ገዥ’ ነው። (ሉቃስ 2:11) ክርስቶስ የአባቱ ወኪል በመሆን በመስፍናዊ ሥልጣኑ በምድር ላይ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።—መዝሙር 72:1-8፤ 110:1, 2፤ ዕብራውያን 1:3, 4

የታጣችው ምድራዊ ገነት በኢየሱስ ክርስቶስ ግዛት ሥር ተመልሳ ትቋቋማለች። ይህ የሚሆነው ኢየሱስ እንዳለው “በዳግመኛ ልደት፣ የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ” ነው። (ማቴዎስ 19:28) በጠቅላላው 144,000 የሚሆኑት የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ከኢየሱስ ጋር ይገዛሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:11, 12፤ ራእይ 5:10፤ 14:1, 3) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ በመኖር ከዚህ የጽድቅ አገዛዝ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል በኢየሱስ ጎን የሞተውና ኢየሱስ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ብሎ ቃል የገባለት ወንጀለኛ ይገኛል።—ሉቃስ 23:43

ስለዚህ ጻድቃን ያልነበሩ ሙታን እንኳን ተነስተው በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ብቁ የመሆን አጋጣሚ ያገኛሉ። (ሥራ 24:15) መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፣ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን፣ ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም። የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” በማለት በሽታ፣ እርጅናና ሞት እንደሚወገዱ በጣም ውብ በሆኑ ቃላት ይናገራል።—ራእይ 21:3, 4

ለዘላለም መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

ምድርን ከሚወርሱትና በእርስዋም ለዘላለም ከሚኖሩት ሰዎች መካከል ለመሆን እንደምትፈልግ የተረጋገጠ ነው። እንግዲያው በገነት ዘላለም ለመኖር የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ማሟላት ይኖርብሃል። ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን፣ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ሲል ወደ ሰማያዊ አባቱ በመጸለይ አንዱን መሠረታዊ ብቃት ገልጿል።—ዮሐንስ 17:3

የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሕይወት ሰጪ እውቀት እንድታገኝ በደስታ ይረዱሃል። ከጠየቅካቸው በሚያመችህ ጊዜ መጥተው አለ ምንም ክፍያ አምላክ የሰው ልጆችን ወደ መንፈሳዊና አካላዊ ፍጽምና እንዴት እንደሚያደርስ ያብራሩልሃል። ሁሉን የሚችለው ፈጣሪያችን ለእርጅናና ለሞት ምክንያት የሆነውን በዘር የተወረሰ ጉድለት ለማስተካከል እንደሚችል እርግጠኛ ሁን። ሕይወት እንደ አሁኑ አጭር የማይሆንበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል። ይሖዋ ለሕዝቦቹ ‘የዘላለም ሕይወት’ በመስጠት ይባርካቸዋል።—መዝሙር 133:3

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በክርስቶስ መስፍናዊ ግዛት እርጅናና ሞት ድል ይነሳሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ