ከምግብ ወለድ በሽታ ራሳችሁን ጠብቁ
“ለአሥራ ሁለት ሰዓታት ያህል ከመጸዳጃ ቤት መውጣት እንኳ አልቻልኩም” አለች ቤኪ። “ይህ ነው የማይባል ቁርጠት ይሰማኝ ነበር። በተጨማሪም በሰውነቴ ውስጥ ያለው ፈሳሽ እያለቀ ስለሄደ በአንድ ሆስፒታል ድንገተኛ ክፍል ውስጥ በደም ሥሬ ፈሳሽ ተሰጠኝ። ጤንነቴ የተመለሰልኝ ከሁለት ወይም ከሦስት ሳምንታት በኋላ ነበር።”
ቤኪ የተመረዘ ምግብ በመብላቷ ምክንያት ምግብ ወለድ በሽታ ይዟት ነበር። እንደ አብዛኞቹ የዚህ በሽታ ተጠቂዎች ሁሉ ቤኪ በሕይወት ለመትረፍ ችላለች። ሆኖም የደረሰባት ሥቃይ እስካሁን ከአእምሮዋ አልጠፋም። “የተመረዘ ምግብ ይህን ያህል ሕመም የሚያስከትል አይመስለኝም ነበር” ብላለች።
እንደዚህ ያሉና ከዚህ የባሱ ሁኔታዎች ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥሙ ከመሆናቸውም በላይ ስሜትን ይረብሻሉ። ምግባችንን ሊመርዙ የሚችሉ በርካታ የባክቴሪያ፣ የቫይረስና የልዩ ልዩ ጥገኛ ሕዋሳት ዓይነቶች አሉ። በተጨማሪም በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች አንዳንድ ምግብ ወለድ በሽታዎች በቅርብ ዓመታት የቀነሱ ቢሆንም ዎርልድ ሄልዝ የተባለ መጽሔት “ሳልሞኔላ በሚባሉትና በሌሎች ባክቴሪያዎች የሚመጡትን በሽታዎች መቆጣጠር በጣም አዳጋች ሆኗል” በማለት ዘግቧል።
ብዙዎቹ ሁኔታዎች ሪፖርት ስለማይደረጉ የተመረዘ ምግብ መብላት የሚያስከትለው ችግር ምን ያህል ስፋት እንዳለው በትክክል ለማወቅ ያዳግታል። በአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ጄን ኮለር “የተመረዘ ምግብ በመብላት ምን ያህል ሰዎች እየተሠቃዩ እንዳሉ እምብዛም አናውቅም” ብለዋል።
የምግብ ወለድ በሽታ መንስኤዎች ምንድን ናቸው? ብዙውን ጊዜ ችግሩ የሚጀምረው ምግቡ ለገበያ ከመቅረቡ ከረጅም ጊዜ በፊት መሆኑን ስታውቁ ትገረሙ ይሆናል።
የእንስሳት እርባታ ዘዴዎች በሽታ ያስተላልፋሉ
ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ዘዴዎች በሽታ አስተላላፊ ሕዋሳት ከከብት ወደ ከብት እንዲተላለፉ አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ በግምት 900,000 ከሚሆኑ የእርባታ ጣቢያዎች ለእርድ የሚመጡ ጥጃዎች ከመቶ በሚያንሱ ቄራዎች ውስጥ አንድ ላይ ይቀላቀላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ቅልቅል ከአንዱ እርባታ ጣቢያ የመጣው ተላላፊ በሽታ ወደ ሌሎቹ ከብቶች እንዲዛመት ሊያደርግ ይችላል።
ከዚህም በላይ የዩናይትድ ስቴትስ የእንስሳት ሐኪሞች ብሔራዊ ማኅበር ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ኤድዋርድ ኤል ሜኒ “ከእንስሳት መኖ ውስጥ ሰላሣ በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነው በበሽታ አስተላላፊ ሕዋሳት የተመረዘ ነው” ብለዋል። አንዳንድ ጊዜ የእንስሳት መኖ ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት እንዲኖረው ሲባል የቄራዎች ተረፈ ምርት ይጨመርበታል። ይህ ልማድ ሳልሞኔላ የተባለው ባክቴሪያና ሌሎች ጀርሞች እንዲሰራጩ ሊያደርግ ይችላል። እንስሳትን ለማደለብ ሲባል አንቲባዮቲኮችን በአነስተኛ መጠን እንዲወስዱ ሲደረግ ጀርሞች መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ሊያዳብሩ ይችላሉ። የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሮበርት ቪ ቶክስ እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው አንቲባዮቲኮችን የመቋቋም ኃይሉ እየጨመረ የሄደው ሳልሞኔላ የተባለው ባክቴሪያ ነው። ይህ የሆነው ለሚደልቡ እንስሳት ወይም ለዶሮዎች አንቲባዮቲክ ስለሚሰጣቸው ነው የሚል ግምት አለን። ሌሎች ባክቴሪያዎችም አንቲባዮቲኮችን መቋቋም የቻሉት በዚህ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።”
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከእርባታ ጣቢያ ወደ ቄራዎች ሲላኩ በአንጀታቸው ውስጥ ሳልሞኔላ የተባለው ባክቴሪያ የተገኘባቸው ዶሮዎች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም ማይክሮባዮሎጂስት የሆኑት ኔልሰን ኮክስ “ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በሚጓጓዙበት ወቅት ይህ ቁጥር ወዲያውኑ ከሃያ እስከ ሃያ አምስት በመቶ ይጨምራል” ብለዋል። ዶሮዎች ከሽቦ በተሠሩ ትናንሽ ጎጆዎች ውስጥ ሲታጨቁ በቀላሉ በበሽታ ሊለከፉ ይችላሉ። በከፍተኛ ፍጥነት የሚከናወነው የእርድና የዝግጅት ሂደት አደጋው እንዲጨምር ያደርጋል። ማይክሮባዮሎጂስት የሆኑት ጄራልድ ኩስተር እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ዶሮዎቹ በመጨረሻ ለተጠቃሚዎች ዝግጁ በሚሆኑበት ወቅት የሚኖራቸው የንጽሕና ደረጃ በቆሻሻ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ቢነከሩ ከሚኖራቸው ንጽሕና የተሻለ አይደለም። ታጥበው ሊሆኑ ቢችሉም ጀርሞቹ አይወገዱም።”
በተመሳሳይም ብዙ እንስሳትን አንድ ላይ አርዶ ሥጋቸውን ለበላተኛ ማዘጋጀቱ አደገኛ ነው። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ኮመን ዲዝዝስ የተባለው መጽሐፍ “በዘመናዊ የምግብ ማዘጋጃ ፋብሪካዎች የሚገኙ የምግብ ክምችቶች በጣም ከፍተኛ ከመሆናቸው የተነሣ አንድ ወይም ሁለት የተበከለ ምግብ ሲመጣ ቀደም ሲል የተመረተውን በብዙ ቶን የሚቆጠር ምግብ ሊመርዘው ይችላል” ብሏል። ለምሳሌ ያህል በአንድ የተበከለ ቁራጭ ሥጋ ሳቢያ በማሽኑ ከተፈጨው ሥጋ የተዘጋጀው ሐምበርገር በሙሉ ሊበከል ይችላል። ከዚህም በላይ በአንድ ማዕከላዊ ስፍራ የተዘጋጀ ምግብ ወደ ሱቆችና ሬስቶራንቶች በሚላክበት ወቅት ተገቢው የሙቀት መጠን ካልተጠበቀ ለብክለት የተጋለጠ ሊሆን ይችላል።
ለገበያ ከሚቀርበው ምግብ ውስጥ ለዚህ አደጋ የሚጋለጠው ምን ያህሉ ነው? ዶክተር ሜኒ “በችርቻሮ ከሚሸጠው ውስጥ ቢያንስ 60 በመቶ የሚያክለው ይበከላል” ብለዋል። ሆኖም ራስህን ከምግብ ወለድ በሽታ ለመጠበቅ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ። ኤፍ ዲ ኤ ኮንስዩመር የተባለው መጽሔት እንደገለጸው “ከእነዚህ በሽታዎች ውስጥ 30 በመቶዎቹ የሚመጡት በቤት ውስጥ ምግብ በተገቢው ሁኔታ ባለመያዙ ምክንያት ነው።” ይህ እንዳይሆን ምን ጥንቃቄዎችን ማድረግ ትችላላችሁ?
ምግቡን ከመግዛታችሁ በፊት . . .
ምግቡ በታሸገበት ዕቃ ላይ የተጻፈውን አንብቡ። ምግቡ የተሠራው ከምን ከምን ነገሮች ነው? ለምሳሌ በሰላጣ ማባያ ወይም በማዮኒዝ ላይ እንደሚደረገው ያልተቀቀለ እንቁላል ተጨምሮ ከሆነ ጥንቃቄ አድርጉ። በወተትና በቺዝ ማሸጊያ ዕቃ ላይ “ፓስቸራይዝድ” የሚል ጽሑፍ መኖር አለበት። ምግቡ ለምን ያህል ጊዜ ‘ሳይበላሽ እንደሚቆይ የተሰጠውን መግለጫ’ ተመልከቱ። ምግቡ ኬሚካል እንዳልተጨመረበት የሚገልጽ ማስታወቂያ ቢኖርም በጤንነት ላይ ምንም ጉዳት አያስከትልም ብላችሁ አታስቡ፤ ኬሚካሎች ሊከላከሏቸው ይችሉ ለነበሩት አደጋዎች ሊያጋልጣችሁ ይችላል።
ምግቡንና ማሸጊያውን በጥንቃቄ መርምሩ። የተበላሸ ከመሰላችሁ ምግቡን አትግዙ። ዓሣ በምትገዙበት ወቅት በአጠቃላይ ዓሣው ጥርት ያሉ ዓይኖችና ቀይ ስንጥቦች ያሉት እንዲሁም ሥጋው ጠንካራ፣ ፈካ ያለና የሚያብለጨልጭ መሆን ይኖርበታል፤ በተጨማሪም ኃይለኛና ደስ የማይል ሽታ ሊኖረው አይገባም። ለሽያጭ የቀረበ ዓሣ በበረዶ ላይ ወይም በማቀዝቀዣ ዕቃ ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል። የተጠበሰና ያልተጠበሰ ዓሣ አንድ ላይ ተቀምጠው ከሆነ አንዱ ሌላውን ሊበክል ይችላል። ከዚህም በላይ የተበሱ፣ የተሰረጎዱ፣ የተጣመሙ ወይም በሌላ መንገድ የተጎዱ ቆርቆሮዎችና ዕቃዎች አደገኛ የምግብ መመረዝ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህ የሚያጋጥመው አልፎ አልፎ ብቻ ቢሆንም ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት የሞት አደጋ ያስከትላል።
ምግቡን ከመብላታችሁ በፊት . . .
በደንብ አብስሉት። ይህ ጎጂ ሕዋሳትን ለመከላከል ከሚያስችሉት ዋና ዋና መንገዶች አንዱ ነው። “እያንዳንዱ የእንስሳ ተዋጽኦ የሆነ ምግብ እንደተበከለ አድርጋችሁ አስቡና አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጉ” በማለት ዶክተር ኮሄን ምክር ይሰጣሉ። እንቁላል አስኳሉና ነጩ ክፍል ከፈሳሽነት ወደ ጠጣርነት እስኪለወጡ ድረስ መቀቀል ይኖርበታል። ከ4 እስከ 60 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ድረስ ባለው ሙቀት ውስጥ ባክቴሪያዎች ማደግ ስለሚችሉ የከብት ሥጋ እስከ 71 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የዶሮ ሥጋ ደግሞ እስከ 82 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ድረስ መብሰል አለበት።
ምግብን በንጽሕና የማዘጋጀት ልማድ ይኑራችሁ። እያንዳንዱን ዕቃ ከተጠቀማችሁበት በኋላ በደንብ ማጽዳት ይኖርባችኋል። አንዳንዶች የእንጨት መክተፊያ ለባክቴሪያዎች አመቺ የመራቢያ ቦታ ይሆናል ቢሉም አንድ ጥናት ከፕላስቲክ መክተፊያ እንደሚሻል አሳይቷል።a መክተፊያችሁ የትኛውም ዓይነት ይሁን በሳሙናና በሙቅ ውኃ ሙልጭ አድርጋችሁ እጠቡት። አንዳንዶች ጀርሞችን ለመግደል በኬሚካል መጠቀም ጥሩ እንደሆነ ይናገራሉ። የምትነኩትን ነገር ሁሉ ሊበክል ስለሚችል የከብትም ሆነ የዶሮ ጥሬ ሥጋ ከነካችሁ በኋላ እጃችሁን ታጠቡ።
ሰዓቱን ተመልከቱ። ከግሮሰሪ የተገዙ ምግቦችን በተቻለ መጠን ወዲያውኑ ወደ ቤት ውሰዷቸው። ከዚህም በላይ የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ጌል ኤ ሌቪ እንዲህ ብለዋል:- “ጥሬም ይሁን የበሰለ ማንኛውም ምግብ ከሁለት ሰዓት በላይ ከማቀዝቀዣው ውጪ መቆየት የለበትም። የውጪው ሙቀት ከ32 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ከሆነ ደግሞ ከአንድ ሰዓት በላይ አታቆዩት።”
ምግቡን ከማስቀመጣችሁ በፊት . . .
በቂ የምግብ ማስቀመጫዎችን ተጠቀሙ። ቶሎ ለመቀዝቀዝ እንዲችሉ ትኩስ ምግቦችን በትናንሽ ዕቃዎች ከፋፍላችሁ አስቀምጧቸው። በማቀዝቀዣው ወይም በበረዶው ቤት ውስጥ ያለው ሙቀት ከፍ እንዳይል በዕቃዎቹ መካከል በቂ ክፍተት በመፍጠር አየር እንደልብ እንዲዘዋወር አድርጉ። አንዱ ዕቃ በሌላው ዕቃ ውስጥ የሚገኘውን ምግብ እንዳይበክል ሁሉም ዕቃዎች መሸፈን አለባቸው።
በማቀዝቀዣው ውስጥ ያለውን ሁኔታ ተከታተሉ። የበረዶው ቤት የቅዝቃዜ መጠን ከዜሮ በታች ከ18 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መብለጥ የሌለበት ሲሆን ማቀዝቀዣው ደግሞ ከ4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች መሆን አለበት። የዶሮና የከብት ሥጋ በበረዶ ቤት ውስጥ ለብዙ ወራት ሊቀመጥ ቢችልም በማቀዝቀዣው ውስጥ ከሆነ ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሊበላሽ ይችላል። እንቁላሎች ከሦስት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በጥቅም ላይ መዋል አለባቸው። እንቁላሎቹ እንዳይሰነጠቁና እንዲቀዘቅዙ ለማድረግ ማቀዝቀዣው በይበልጥ በሚሞቅበት በበሩ ውስጥ በሚገኘው የእንቁላል ማስቀመጫ ውስጥ ከማድረግ ይልቅ መጀመሪያ በነበሩበት ካርቶኖች አድርጎ በማቀዝቀዣው ዋነኛ ክፍል ውስጥ ማስቀመጥ ይሻላል።
እነዚህ ሁሉ ጥንቃቄዎች ከተደረጉ በኋላም ቢሆን ስታዩት ወይም ስታሸቱት የሚያጠራጥር ከሆነ ምግቡን ጣሉት! ብዙውን ጊዜ ምግብ ወለድ በሽታ ከባድ ጉዳት ሳያስከትል የሚያልፍ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ በተለይ ልጆችን፣ አረጋውያንንና በሽታን የመከላከል አቅም የሌላቸው ሰዎችን ሊገድል ይችላል።b
“እንስሳትን፣ አእዋፍንና ዓሦችን ሁሉ፣ . . . ምግብ እንዲሆኑህ ሰጥቼሃለሁ” በማለት አምላክ ለኖኅ ከነገረው በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። (ዘፍጥረት 9:2, 3፣ ቱዴይስ እንግሊሽ ቨርሽን) የጅምላ እርድ፣ የተማከለ የማምረት ሂደትና ከፍተኛ የምርት ስርጭት መኖሩ በእንስሳት ምግቦች ምክንያት በሽታ የሚከሰትበት አጋጣሚ ከፍ እንዲል ያደርጋል። ስለዚህ የምርቱ ተጠቃሚ እንደመሆናችሁ መጠን በበኩላችሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጉ። ምግብ ስትገበዩ፣ ስታበስሉና ስታስቀምጡ ጥንቃቄ አድርጉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ታኅሣሥ 8, 1993 የእንግሊዝኛ ንቁ! ገጽ 28 ተመልከቱ።
b ምግብ ወለድ በሽታ ከያዛችሁ ብዙ እረፍት አድርጉ፤ እንደ ጭማቂ፣ ሾርባ ወይም ለስላሳ መጠጥ ያሉትን መጠጦች ውሰዱ። ከነርቭ ጋር ግንኙነት ያላቸው ችግሮች እንደተፈጠሩ የሚያሳይ ምልክት ከታየ ወይም ትኩሳት፣ ማዞር፣ ትውከት፣ ደም የተቀለቀለበት ዓይነ ምድር ወይም የማያቋርጥ ከባድ ሥቃይ ከተከሰተ ወይም ደግሞ ከፍተኛ አደጋ ሊያጋጥማቸው ከሚችሉት ሰዎች መካከል ከሆናችሁ ሐኪም ማማከራችሁ ተገቢ ሊሆን ይችላል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቤት ውጭ የምትበሉ ከሆነ
በሽርሽር ጊዜ። በበረዶ የተሞላ የሙቀት መከላከያ ያለው የፕላስቲክ ማቀዝቀዣ ተጠቀሙ። ማቀዝቀዣውን በመኪናው ኮፈን ውስጥ ከምታስቀምጡት ይልቅ በተሳፋሪዎች መቀመጫ አካባቢ ብታደርጉት የተሻለ ሊሆን ይችላል። በሽርሽሩ ቦታ ስትደርሱ የማቀዝቀዣው ክዳን መዘጋት ይኖርበታል። ያልበሰሉ ምግቦችን ከሌሎች ምግቦች ለይታችሁ አስቀምጧቸው። ምግብ ሙሉ በሙሉ ካልበሰለ ባክቴሪያዎች እንዲያድጉ አመቺ ሁኔታ ስለሚፈጥር በቤት ውስጥ በከፊል ካበሰሉ በኋላ በሽርሽሩ ቦታ ማጠናቀቅ ጥሩ አይደለም።
ምግብ ቤቶች። “ንጹሕ ያልሆኑ ምግብ ቤቶች ውስጥ አትግቡ” ሲሉ ዶክተር ጆናታን ኤድሎ አስጠንቀቀዋል። “የመመገቢያው ክፍል ቆሻሻ ከሆነ ወጥ ቤቱም ጭምር ቆሻሻ ሳይሆን አይቀርም።” ማንኛውንም ትኩስ ያልሆነ ወይም በደንብ ያልበሰለ ምግብ መልሱ። የመበላሸት ሁኔታ የሚታይበት ዶሮ ወጥ አትብሉ። የእንቁላል ጥብስ በሁለቱም ወገን በደንብ መብሰል ይኖርበታል። “እንቁላሉ በደንብ ካልበሰለ የሚያስከትለው አደጋም ያንኑ ያህል ከፍ ይላል” በማለት ኤፍ ዲ ኤ ኮንስዩመር የተባለ መጽሔት አስጠንቅቋል።
የሰላጣ መሸጫ ቤቶች። የተለያዩ የማብሰያና የማቀዝቀዣ ደረጃዎችን የሚጠይቁ ምግቦችን ቀላቅለው የሚያዘጋጁ በመሆናቸው ምክንያት ኒውስ ዊክ መጽሔት የሰላጣ መሸጫ ቤቶችን “ለማይክሮቦች በጣም አመቺ የሆኑ የመራቢያ ቦታዎች” በማለት ጠርቷቸዋል። የሰላጣ መሸጫ ቤቶቹን ንጽሕናና መቀዝቀዝ ያለባቸው ምግቦች በበረዶ ውስጥ መቀመጣቸውን አረጋግጡ። የሰላጣ መሸጫ ቤቶች ንጽሕናቸው በደንብ የተጠበቀ ቢሆንም እንኳ ጀርሞች ከአንዱ ደንበኛ ወደ ሌላው ደንበኛ ሊተላለፉ ይችላሉ። ማይክሮባዮሎጂስት የሆኑት ማይክል ፓሪሳ እንዳሉት “የሰላጣ ማባያውን ጭልፋ በመጨረሻ የነካው ማን እንደሆነ አታውቅም።”
ድግስና ሐዘን ቤት። ዶክተር ኤድሎ ምግብ በቡፌ መልክ በሚቀርብበት ወቅት ጋባዡ “ጠረጴዛው ላይ በአንድ ጊዜ ብዙ ምግብ ለረጅም ሰዓት ከማስቀመጥ ይልቅ አነስተኛ ምግብ ካስቀመጠ በኋላ ማለቁን እየተከታተለ ከማቀዝቀዣው ወይም ከማሞቂያው እያነሣ ቢጨምር የተሻለ” እንደሆነ ተናግረዋል። ቀዝቃዛ ምግቦችን ከ4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች ትኩስ ምግቦችን ደግሞ ከ60 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ በሆነ ቦታ አስቀምጧቸው። በሌላ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል ሲባል የተቀቀለ ሥጋ ወዲያውኑ በማቀዝቀዣ ውስጥ መቀመጥ ያለበት ሲሆን ለጉዞ እስኪዘጋጅ ድረስ በዚሁ ሁኔታ መቀመጥ ይኖርበታል። ምግቡ ከመበላቱ በፊት በደንብ ሊሞቅ ይችላል።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተበላሸ ከመሰላችሁ አትግዙት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሆቴል የምትመገቡ ከሆነ ወጥ ቤቱ ንጹሕ ነውን?