የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 7/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጊዜው እልም የሚለው ለምንድን ነው?
  • በደፈጣ ውጊያ ላይ የተሠማሩ ልጆች
  • የአፍ ንጽሕና ለአረጋውያን
  • የተፈጥሮ የጽዳት ሠራተኞች
  • በጭንቅላታቸው በመሸከም
  • “የይሖዋ ምሥክሮች የታደሉ ናቸው”
  • የአእምሮ በሽታ እየጨመረ ነው
  • ለእግር ኳስ ተጨዋቾች የሚሆን ማስጠንቀቂያ
  • ማሰብ እንድትችል ጠጣ
  • ልባዊ ፈገግታዎች ይተላለፋሉ
  • መመሪያዎቹ ከየት መጡ?
    የሕይወት አመጣጥ​—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
  • ሴሎችህ—ሕያው ቤተ መጻሕፍት!
    ንቁ!—2015
  • ዲ ኤን ኤ ያለው መረጃ የመያዝ አቅም
    ንቁ!—2013
  • ማስረጃውን መርምር
    ንቁ!—2011
ንቁ!—1996
g96 7/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

ጊዜው እልም የሚለው ለምንድን ነው?

ብዙ ሰዎች ቀኑ ከምኔው እልም ይላል? በማለት በመገረም መልክ ይጠይቃሉ፤ ሆኖም በቅርቡ የተካሄደ አንድ ጥናት ለዚህ ጥያቄ ሳይንሳዊ የሆነ ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል። ዩ ኤስ ኤ ኢሊኖይስ ውስጥ የሚገኝ ጥናት የሚያካሂድ አንድ ድርጅት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት እንዴት እንደሆነ በየዕለቱ መዝግበው እንዲይዙ ጥያቄ በቀረበላቸው ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ የሦስት ዓመት ጥናት አካሂዷል። ሰዎቹ ከ18 እስከ 90 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ከተለያዩ የኑሮ ደረጃዎች የተውጣጡ ናቸው። በአንደኛ ደረጃ ብዙ ሰዓት የሚጠፋው በእንቅልፍ ነው። ከዚህ በመቀጠል በቀን በአማካይ 184 ደቂቃዎችን በመውሰድ ተከታዩን ደረጃ የያዘው ሥራ ነው። 154 ደቂቃዎችን በመውሰድ ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የያዘው ደግሞ ቴሌቪዥንና ቪዲዮ ለመመልከት የሚውለው ጊዜ ነው። ለቤት ውስጥ ሥራዎች 66 ደቂቃ፣ ለጉዞ 51 ደቂቃ፣ ለመቆነጃጀት 49 ደቂቃና ለልጆችና ለቤት ውስጥ እንስሳ ለሚደረገው እንክብካቤ 25 ደቂቃ ይውላል። በወጣው ዝርዝር ላይ ወደ መጨረሻ አካባቢ የሠፈረው አምልኮ ሲሆን እሱም በቀን የሚወስደው ጊዜ በአማካይ 15 ደቂቃ ነው።

በደፈጣ ውጊያ ላይ የተሠማሩ ልጆች

በዓለም ዙሪያ በደፈጣ ውጊያ ላይ የተሠማሩ ልጆችን ማየቱ የተለመደ ነገር ሆኗል። ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን እንዳለው ልጆች እንዴት መግደል እንደሚቻል በፍጥነት ይማራሉ፤ እንደ ቤተሰብ አድርጎ ሊይዛቸው በሚችል በማንኛውም ወታደራዊ አንጃ ተቀባይነት ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት መልካሙንና ክፉውን ለይቶ ለማወቅ ካላቸው ችሎታ የላቀ ነው። “በሩዋንዳና በሌሎች ቦታዎች ከተፈጸሙት እጅግ አሠቃቂ ድርጊቶች መካከል አንዳንዶቹ የተፈጸሙት በልጆች ነው” ሲሉ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይ ተናግረዋል። “ከተሰለፉለት አንጃ ጎን መቆማቸውን ማሳየትና መወደስ ይፈልጋሉ፤ በእኩዮቻቸው ዘንድ አድናቆት ሊያተርፉ የሚችሉት ደግሞ ከአዋቂዎቹ የላቀ ጀብዱ ወይም የጭካኔ ድርጊት በመፈጸም ሊሆን ይችላል።” በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ በሚካሄድ ግጭት ገና በስምንት ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ትንንሽ ልጆች ሳይቀሩ የራሳቸውን ወላጆች በጥይት መግደልና አንገታቸውን ማረድ የመሳሰሉ ዘግናኝ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ይሠለጥናሉ፤ እንዲሁም ይገደዳሉ። ታፍነው የተወሰዱ ልጃገረዶች ምግብ እንዲያበስሉ፣ እንዲያጸዱና የወንዶቹን የጾታ ስሜት እንዲያረኩ ይደረጋል። “በአሁኑ ጊዜ በ24 ግጭቶች ውስጥ በጦር ግንባር የሚገኙ ልጆች ቁጥር ከ50,000 እስከ 200,000 እንደሚደርስ ይገመታል” ሲል ኒውስዊክ የተባለው መጽሔት ገልጿል።

የአፍ ንጽሕና ለአረጋውያን

“የአፍ ንጽሕና ለአረጋውያን የሕይወትና የሞት ጉዳይ ሊሆን ይችላል” ሲል አሳሂ ኢቭኒንግ ኒውስ ዘግቧል። የጃፓን ሳይንቲስቶች “አረጋውያን ጥርሳቸውን በመቦረሽ ብቻ በኒሞኒያ በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸውን መቀነስ ይችላሉ” ሲሉ ገልጸዋል። በ46 አረጋውያን ላይ በተካሄደ አንድ ጥናት ሀያ አንዱ ጥርሳቸው በነርሶች አማካኝነት በየዕለቱ ከምሳ በኋላ በደንብ እንዲቦረሽ ተደረገ። በተጨማሪም በሳምንት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ የጥርስ ንጽሕና ምርመራ ተደረገላቸው። ከሦስት ወራት በኋላ እንደታየው እነዚህ ሀያ አንዱ ሰዎች ትኩሳት የነበራቸው እንዲህ ዓይነቱን ክትትል ካላደረጉት 25 ሰዎች በአሥር ቀናት ላነሰ ጊዜ ነው። በአፍ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎችን በማስወገድ የተሻለ ጤንነት ማግኘት ተችሏል። ቀደም ሲል የተደረገ አንድ ጥናት “ምራቅ ወይም የምግብ ፍርፋሪዎች ድንገት ሳንባ ውስጥ ገብተው ኒሞኒያ ያመጣሉ” ሲል መግለጹን ጋዜጣው ዘግቧል።

የተፈጥሮ የጽዳት ሠራተኞች

አንዳንድ የአበባ ተክሎች በዘይት የተበከለን የበረሃ አፈር የማጽዳትና ወደ ቀድሞው ሁኔታ የመመለስ አስደናቂ ችሎታ አላቸው ሲል በለንደን እየታተመ የሚወጣው ዘ ታይምስ ዘግቧል። ሳይንቲስቶች ዘይቱ ከአሸዋው ክብደት ከ10 በመቶ ያነሰ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ ተክሎች ማደግና ሥሮቻቸውም ሙሉ በሙሉ ንጹሕ ሆነው መኖር ይችላሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? በተክሎቹ ሥሮች ዙሪያ የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች ዘይቱን በመመገብ ምንም ጉዳት የማያስከትል ንጥረ ነገር እንዲሆን ያደርጉታል። እነዚህ ተክሎች ኮምፖዚቴ ተብለው በሚጠሩት የተክል ዓይነቶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ዳዚየስና አስተርስ የሚባሉት ተክሎችና ሌሎችም ብዙ አረሞች በእነዚህ የተክል ዓይነቶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ሳይንቲስቶች በኩዌት ውስጥ ያለውን በረሃ ለማጽዳት የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን እነዚህ ተክሎች እንዲተከሉ ሐሳብ አቅርበዋል። ከኢራቅ ጋር ጦርነት ከተደረገ ከአራት ዓመታት በኋላ 32 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆነው በረሃ አሁንም እንደተበከለ ይገኛል።

በጭንቅላታቸው በመሸከም

“የአፍሪካ ሴቶች ውኃ የያዙ ከባድ እንስራዎች ወይም እህል የያዙ ማሰሮዎች ጭንቅላታቸው ላይ አስቀምጠው ረጅም ርቀት ሲጓዙ ምንም ነገር የያዙ አይመስሉም” ሲል ዲስከቨር የተባለው መጽሔት ገልጿል። “ሴቶቹ ምንም ዓይነት ተጨማሪ ኃይል ሳይጠቀሙ በጭንቅላታቸው ከባድ ሸክም መሸከም እንደሚችሉ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል።” አንዳንድ የኬንያ ሴቶች ሌላ ምን ዓይነት ኃይል ሳይጠቀሙ የራሳቸውን ክብደት 20 በመቶ የሚሆን ሸክም በጭንቅላታቸው ላይ መሸከም ይችላሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? “በጭንቅላታቸው ላይ የመሸከም ልምድ ከሌላቸውና በጀርባቸው ላይ ከባድ ዕቃዎችን ከሚሸከሙ ሰዎች በተሻለ ቅልጥፍና ሸክማቸውን” በጭንቅላታቸው ላይ በመሸከም ነው ሲል ኒው ሳይንቲስት መልስ ሰጥቷል። “ተመራማሪዎቹ ለዚህ ነገር ቁልፉ ሴቶቹ የፔንዱለም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው እንደሆነ ያምናሉ።” ስንራመድ ልክ እንደ ፔንዱለም ወዲያ ወዲህ እንወዛወዛለን፤ የተወሰነ ኃይል አግኝተን ወደ ሚቀጥለው እርምጃችን እንሻገራለን። አውሮፓውያን ግን ክብደቱ በጨመረ መጠን ሰውነታቸውን እንደ ፈለጉ የማዘዝ ቅልጥፍናቸው ይቀንሳል። በጭንቅላታቸው ላይ የሚሸከሙ የአፍሪካ ሴቶች ቅልጥፍናቸው ስለሚጨምር ጡንቻዎቻቸው ተጨማሪ ሥራ መሥራት አያስፈልጋቸውም። ሆኖም ይህን ዘዴ ሙሉ በሙሉ መካን የሚቻለው በርከት ካሉ ዓመታት በኋላ ነው።

“የይሖዋ ምሥክሮች የታደሉ ናቸው”

በብዙዎቹ አገሮች ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ በኢጣሊያ ውስጥም ከደም ጋር በተያያዘ ሁኔታ አሳፋሪ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው። በብዙ ሺህ ሊትር የሚቆጠር ደም በቂ ምርመራ ወይም ተገቢው ጥንቃቄ ሳይደረግለት ደም ወደሚሰጡ ማዕከላት እንደተሰራጨ ይወራል። ይህም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደ ኤድስና ሄፓታይተስ ለመሳሰሉ በሽታዎች እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል። ትርፍ ለማጋበስ ሲባል የሰዎችን ጤንነት አደጋ ላይ የጣለውን ይህን ሁኔታ አስመልክቶ ኢል ማኒፌስቶ የተባለው የኢጣሊያ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆኑት ሉዊጂ ፒንተር አስተያየት ሲሰጡ በጽሑፋቸው መግቢያ ላይ ያሰፈሯቸው ቃላት እንዲህ ይላሉ:- “ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ምክንያት ደም አንወስድም የሚሉት . . . የይሖዋ ምሥክሮች የታደሉ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ጋዜጦችን ሲያነቡ ደም፣ ፕላዝማና ሌሎች የደም ተዋጽኦዎችን ለሰዎች በሚሸጡና በሚሰጡ ማዕከላትና ክሊኒኮች ውስጥ እየተፈጸመ ያለው ነገር . . . የማያስጨንቃቸው ሰዎች እነሱ ብቻ ናቸው።”

የአእምሮ በሽታ እየጨመረ ነው

ዓለም አቀፍ የጤና ጠበብቶችን ያቀፈ አንድ ቡድን “በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የአእምሮ በሽታ በአስደንጋጭ መጠን እየጨመረ መሆኑን” በመግለጽ ማስጠንቀቁን ፈርስት ኮል ፎር ችልድረን የተባለ መጽሔት ዘግቧል። በሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ተመራማሪዎች “በጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በሴቶችና በልጆች ላይ በሚፈጸም አስነዋሪ ድርጊትና ግድያ እንዲሁም በሥነ ሕዝብ ጉዳዮች፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ለውጥ ሳቢያ የሚመጡ” ብዛት ያላቸው ከፍተኛ የአእምሮ ሕመሞችን መዝግበዋል። በተጨማሪም አነስተኛ ገቢ ባላቸው ኅብረተሰቦች ውስጥ የሚገኙ የአእምሮ ድኹርነትና የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ከሦስት እስከ አምስት እጥፍ በልጦ ተገኝቷል፤ እንዲሁም አብዛኞቹ ወጣቶች የሚሞቱት የራሳቸውን ሕይወት በማጥፋት እንደሆነ ታውቋል። ቡድኑን የሚመሩት ዶክተር አርተር ክሌንማን እንዳሉት ከሆነ የአእምሮ ጤንነት ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። “ድሃ የሆኑትም ሆኑ የበለጸጉት አገሮች የአእምሮ ጤንነትን ለመጠበቅና ችግሩ ያለባቸውን ሰዎች ጤንነት ለማስተካከል የሚያስፈልገውን መዋዕለ ንዋይ አልመደቡም” ሲሉ ተናግረዋል።

ለእግር ኳስ ተጨዋቾች የሚሆን ማስጠንቀቂያ

በዓለም ላይ እጅግ ተወዳጅ ስፖርት በሆነው በእግር ኳስ ጨዋታ ተጨዋቾች ኳሱን በጭንቅላታቸው መምታት ይችላሉ። ይሁን እንጂ አንድ ተጨዋች ኳስን በተደጋጋሚ በጭንቅላቱ የሚመታ ከሆነ በአእምሮው ላይ ጉዳት ሊያስከትልበት ይችላል ሲል ጆርናል ዱ ብራዚል የተባለው ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ እግር ኳስ ተጨዋቾች ኳስ በጭንቅላት መምታታቸው የማስታወስ ችግርና የአእምሮ ችሎታ መቀነስ ሊያመጣባቸው ይችላል። ያን ያህል የከፋ ባይሆንም እንኳ በጭንቅላታቸው ላይ የሚደርሰው ጉዳት ጭንቅላታቸው ላይ በተደጋጋሚ ቡጢ ያረፈባቸው ቦክሰኞች ከሚደርስባቸው ጉዳት ጋር ተመሳሳይ ነው። ፓውሎ ኒምየር ፊሎ የተባሉ ኒውሮሎጂስት ወደ ላይ ተነስቶ በከፍተኛ ኃይል የሚመለስን ኳስ በጭንቅላታቸው መምታት እንደሌለባቸውና እርጥበት በሚኖርበት ጊዜም የኳሱ ክብደት ስለሚጨምር ኳሱን በጭንቅላት ከመግጨት መቆጠብ እንዳለባቸው ተናግረዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ጠበብቶች ኳስን በጭንቅላት በኃይል መግጨት የተጨዋቾችን የማየት ችሎታ ሊጎዳ እንደሚችል ያምናሉ።

ማሰብ እንድትችል ጠጣ

ሐሳብህን አሰባስበህ በአንድ ነገር ላይ ማተኮር ያስቸግርሃልን? ምናልባት ብዙ ውኃ መጠጣት ያስፈልግህ ይሆናል ሲል ኤሽያዊክ ሐሳብ ያቀርባል። መጽሔቱ በቅርቡ በሆንግ ኮንግ ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን የሚያስተምሩ መምህራንና የተማሪዎቹ ወላጆች ብዙ ውኃ መጠጣት በትኩረት የማዳመጥ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች እንደሚረዳ ተነግሯቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸው በቀን ከ8 እስከ 15 ብርጭቆ ውኃ መጠጣት እንዳለባቸው ተነግሯቸዋል። ሪፖርቱ ዘ ለርኒንግ ብሬን የተባለውን መጽሐፍ በመጥቀስ የሰውነት ፈሳሽ ማለቅ የመማር አቅምን ሊያዳክም እንደሚችል የሚጠቁሙ ጥናቶችን አመልክቷል። ንጹሕ ውኃ መጠጣት ሰውነታችን የያዘውን ፈሳሽ እንዲያስወጣ ሊያነሳሱ የሚችሉትን ለስላሳ መጠጦች፣ ቡና፣ ሻይ አልፎ ተርፎም ጭማቂዎች ከመጠጣት የተሻለ ጥቅም አለው ሲል ኤሽያዊክ ገልጿል።

ልባዊ ፈገግታዎች ይተላለፋሉ

በታምፐር ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ዶክተር ጃሪ ሂታነንና በሄልሲንኪ ዩኒቨርሲቲ በባዮሜዲሲን ኢንስቲትዩት ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ቬይኮ ሱራካ የተባሉ ፊንላንዳውያን ተመራማሪዎች እንዳሉት ከሆነ ሁለት ዓይነት ፈገግታዎች አሉ። አንዱን የፈገግታ ዓይነት ጠበብቶቹ የይስሙላ ፈገግታ ብለው ይጠሩታል። ይህ እንዲሁ ማድረግ ያለብን ሆኖ ስለተሰማን የምናደርገውና የጉንጭ ጡንቻዎችን ብቻ የሚያንቀሳቅስ የፈገግታ ዓይነት ነው። በአንጻሩ ልባዊ ፈገግታ እውነተኛ የደስታ ስሜት የሚገለጽበትና የጉንጭን ጡንቻዎች ጭምር ብቻ ሳይሆን በዓይን አካባቢ ያሉ ጡንቻዎችንም የሚያንቀሳቅስ ነው። በቅርቡ በፊንላንድ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ልባዊ ፈገግታዎች ከአንዱ ወደ ሌላው ይተላለፋሉ። ተመራማሪዎች ጥቃቅን የጡንቻ እንቅስቃሴዎችን በመከታተልና በመመዝገብ ጥናቱን ያካሄዱባቸው ሰዎች ልባዊ ፈገግታ ያሳየ ፎቶግራፍ ገና ሲመለከቱ እነሱም ፈገግ ሊሉ እንደቻሉ መረዳት ችለዋል። እነዚህ ሰዎች የይስሙላ ፈገግታ እያሳዩ የተነሱ ሰዎችን ፎቶግራፍ ሲመለከቱ ግን ይህን ዓይነት ምላሽ አላሳዩም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ