ሥራ አጥነት እንዴት ሊመጣ ቻለ?
በአንዳንድ አገሮች ብዙ ሰዎች ለረጅም ሰዓታት፣ አድካሚ የሆነና ምንም ፋታ የማይሰጥ ከባድ የጉልበት ሥራ በትንሽ ደሞዝ በመሥራት ኑሯቸውን ለመግፋት ተገደዋል። አንዳንዴም በትንሽ ደሞዝ ተቀጥረው ለጤናና ለሕይወት አደገኛ የሆነ ሥራ ሲሠሩ ይታያሉ። በሌሎች አገሮች የሚገኙ ብዙ ሰዎች ደግሞ አንድ ሰው በአንድ ትልቅ ኩባንያ ወይም በመንግሥት መሥሪያ ቤት ከተቀጠረ ጡረታ እስኪወጣ ድረስ የሥራ ዋስትና ይኖረዋል ብለው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያስቡ ነበር። ዛሬ እንደሚታየው ግን የፈለጉትን ዓይነት ሥራ ወይም ዋስትና መስጠት የሚችል የንግድ ድርጅትም ሆነ ኩባንያ የለም። ለምን?
የችግሩ ምክንያቶች
በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች፣ ዲግሪ ይኑራቸውም አይኑራቸው፣ የመጀመሪያዋን ሥራ እንኳን መያዝ ተስኗቸዋል። ለምሳሌ ያህል በኢጣሊያ ውስጥ ሥራ ከሌላቸው መካከል ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚሆኑት በ15 እና በ24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸው። ቀደም ሲል በሥራ ገበታ ላይ የነበሩትና ይህን ሥራቸውን ሙጥኝ ብለው የያዙት ሰዎች አማካይ ዕድሜያቸው ከፍ እያለ ሄዷል፤ በመሆኑም ወጣቱ ወደ ሥራው ዓለም ለመግባት ያለው ዕድል ጠባብ እየሆነበት መጥቷል። ወደ ጉልበት ሥራ በብዛት እየተሰማሩ ባሉት ወጣት ሴቶችም ዘንድ የሥራ አጦቹ ብዛት ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ባሁኑ ጊዜ ሥራ ለመያዝ ትግል ውስጥ የገባው አዲስ የሠራተኞች ሠራዊት እጅግ ብዙ ነው።
የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ማሽን ከተሠራበት ጊዜ ወዲህ ብዙ አዳዲስ መሣሪያዎች ስለተፈለሰፉ ለአንድ ፋብሪካ የሚያስፈልጉት ሠራተኞች ብዛት በእጅጉ ቀንሷል። የፈረቃ ሠራተኞች እጅግ ከፍተኛ ድካም ይሰማቸው ስለነበር ማሽኖች ሥራ እንደሚቀንሱላቸው፤ እንዲያውም ጨርሶ እንደሚያስቀሩላቸው ተስፋ አድርገው ነበር። እርግጥ፣ ማሽኖች ምርትን አሳድገዋል፤ ብዙ አደጋዎችንም አስቀርተዋል፣ የዚያኑ ያህል ደግሞ ክፍት የሥራ ቦታ አስዘግተዋል። ከሥራ የተቀነሱ ሰዎች አዲስ ሞያ ካልተማሩ በስተቀር ለረጅም ጊዜ ሥራ አጥ ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ።
የፋብሪካ ውጤቶች ገበያውን ከመጠን በላይ እንዳያጥለቀልቁት ያስፈራል። እንዲያውም የመጨረሻው የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሰናል የሚሉ አሉ። ከዚህም ሌላ ሥራ አጦች በበዙ ቁጥር የሸማቹ ሕዝብ ቁጥር ይቀንሳል። ስለዚህ ፋብሪካዎች ለገበያ የሚያቀርቡት ምርት መጠን ገበያተኞች መግዛት ከሚችሉት በላይ የተትረፈረፈ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ምርትን ማሳደግ እንዲችሉ ሆነው የተዘጋጁ ፋብሪካዎች ዕቃቸው ስለማይነሳላቸው ተዘግተዋል አለዚያም ሥራ ለውጠዋል። እንደነዚህ ላሉት አዝማሚያዎች ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች አሉ፤ እነርሱም ከሥራ የሚወጡት ናቸው። ገበያ በአጠቃላይ ሲቀዘቅዝ ሠራተኛ የመቅጠሩ አስፈላጊነት ይቀንሳል። በእንዲህ ዓይነቱ ቀውጢ ወቅት የሠራተኞች ቅነሳ ከተደረገ ጊዜው ተለውጦ ሥራው እንደገና ቢያንሰራራ እንኳ የፊተኞቹ የሥራ ቦታዎች ክፍት አይሆኑም። እንግዲያው የሥራ አጥነት መንስዔዎች በርካታ እንደሆኑ ግልጽ ነው።
ማኅበራዊ ቸነፈር
ሥራ አጥነት ማንንም ስለማይምር ማኅበራዊ ቸነፈር ነው ሊባል ይችላል። በሥራ ገበታ ላይ ያሉት በሥራቸው እንዲቀጥሉ ሲባል አንዳንድ ዘዴዎችን የቀየሱ አገሮች አሉ። ለምሳሌ ደሞዝና የሥራ ቀናትን የቀነሱ አሉ። ይህም ቢሆን ለሥራ ፈላጊዎች በር ይዘጋባቸዋል።
ከሥራ ጋር በተያያዙ ችግሮች ሳቢያ ሥራ ያላቸውም ሆኑ የሌላቸው ብዙ ጊዜ ተቃውሞአቸውን በልዩ ልዩ መንገድ ገልጸዋል። ሥራ አጦቹ ሥራ ይሰጠን ሲሉ ሥራ ላይ ያሉት ደግሞ የሥራ ዋስትናቸውን ለማስጠበቅ ይታገላሉ። ሁለቱ ዓላማዎች ደግሞ ሁልጊዜ አይጣጣሙም። “በሥራ ገበታ ላይ ያሉት የሥራ ሰዓታቸውን እንዲያራዝሙ ግብዣ ሲቀርብላቸው ከሥራ ውጭ ያሉት እዚያው ባሉበት እንዲቆዩ ይደረጋል። ኅብረተሰቡ ለሁለት እንዳይከፈል ያሰጋል። . . . አንደኛው ወገን ሥራ የበዛበት ሲሆን ሌላው ደግሞ ጨርሶ ከሥራ የተገለለውና የሌላው ተረጂ የሆነው ወገን ነው” ሲል ፓኖራማ የተባለ በኢጣሊያ የሚታተም መጽሔት አትቷል። በአውሮፓ ውስጥ የኢኮኖሚው ዕድገት የጠቀመው ሥራ አጦችን ሳይሆን በሥራ ላይ ያሉትን ሰዎች ነው የሚሉ ባለሞያዎችም አልጠፉም።
ከዚህም በላይ ሥራ አጥነት ከአካባቢው የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር የተያያዘ በመሆኑ እንደ ጀርመን፣ ኢጣሊያና ስፔይን በመሳሰሉት አገሮች ችግሩ ከአካባቢ ወደ አካባቢ ከፍተኛ ልዩነት ይታይበታል። ሠራተኞቹ በአዲስ ሞያ ለመሰልጠን ወይም ወደ ሌላ አካባቢ ወይም አገር ለመዛወር ፈቃደኛ ይሆናሉን? ይህ እርምጃ ብዙውን ጊዜ ችግሩን ለመቅረፍ አንዱ ወሳኝ ነገር ሊሆን ይችላል።
ከፊት ለፊታችን የሚታዩ መፍትሔዎች አሉን?
አብዛኞቹ ሰዎች ተስፋቸውን የጣሉት ኢኮኖሚው ከፍተኛ የመሻሻል ለውጥ ያደርግ ይሆናል በሚለው ተስፋ ላይ ነው። በዚህ እምብዛም ተስፋ የማይጥሉ ሰዎች ግን ይህ ዓይነቱ መሻሻል እስከ 2,000 ዓ.ም. ድረስ አይመጣም ብለው ያስባሉ። ኢኮኖሚው አሁንም ማገገም ጀምሯል የሚሉም አሉ፤ ይሁን እንጂ ውጤት በማሳየት በኩል አዝጋሚ ነው። ለምሳሌ በኢጣሊያ በቅርቡ የሠራተኛው ሕዝብ ቁጥር የማሽቆልቆል አዝማሚያ ታይቶበታል። ኢኮኖሚ ማገገሙ የሥራ አጦቹን ቁጥር ሁልጊዜ ላይቀንሰው ይችላል። መጠነኛ መሻሻል ቢመጣም የንግድ ድርጅቶች አዲስ ሠራተኞችን ከመቅጠር ይልቅ ባሉት ሠራተኞች በተሻለ ሁኔታ ተጠቅመው ሥራውን ማካሄድ ይመርጣሉ። በሌላ አባባል ‘የሥራ ዕድል የማይከፍት ዕድገት’ ይኖራል ማለት ነው። ከዚህም ሌላ የሥራ አጦች ቁጥር አዲስ ከሚፈጠሩት ሥራዎች ቁጥር ይልቅ በፍጥነት ያድጋል።
በዛሬው ጊዜ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ዘርፎች ዓለም አቀፋዊ መልክ እየያዙ መጥተዋል። አንዳንድ የኢኮኖሚ ጠበብት እንደ የሰሜን አሜሪካ ነፃ የንግድ ስምምነት (NAFTA) እና የእስያና ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (APEC) የመሳሰሉ ታላላቅና አዳዲስ ድንበር ዘለል የንግድ ቀጠናዎችን መፍጠሩ ለዓለም ኢኮኖሚ ትልቅ ድጋፍ ይሰጠዋል ብለው ያምናሉ። ይሁንና ይህ አካሄድ ታላላቅ የንግድ ድርጅቶች በትንሽ ደሞዝ ሠራተኛ መቅጠር ወደሚቻልበት አገር ተዛውረው ፋብሪካ እንዲያቋቁሙ ስለሚጋብዛቸው በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች ዜጎቻቸው ሥራ ያጣሉ። በዚያ ላይ ደግሞ በፊቱንም ዝቅተኛ ገቢ የነበራቸው ሠራተኞች ያችውም ትቀንስባቸዋለች። ስለዚህ በተለያዩ አገሮች ብዙ ሰዎች ለእነዚህ የንግድ ስምምነቶች ያላቸውን ተቃውሞ ኃይል በታከለበት መንገድ ጭምር መግለጻቸው ያጋጣሚ ነገር አይደለም።
የኢኮኖሚ ጠበብት ሥራ አጥነትን ለመዋጋት የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦች ያቀርባሉ። እነዚህ የመፍትሔ ሐሳቦች የመነጩት ከኢኮኖሚ ጠበብት ወይም ከፖለቲካውያን ወይም ከራሳቸው ከሠራተኞቹ ይሆንና አንዳንድ ጊዜ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ። ለኩባንያዎች ከባድ ሸክም የሆነባቸውን የመንግሥት ግብር በመቀነስ የሠራተኞቹ ብዛት እንዲጨምር ማበረታታት ይቻላል ብለው የሚያስቡም አሉ። አንዳንዶች ደግሞ መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ድጎማ በማድረግ እጁን ማስገባት አለበት ይላሉ። የሥራ ሰዓትን በመቀነስ ሥራውን ለተለያዩ ሰዎች ማከፋፈል ይበጃል የሚሉም አሉ። በርካታ ትልልቅ ኩባንያዎች ይኸኛውን ዘዴ እየሠሩበት ነው። እርግጥ በያዝነው መቶ ዘመን በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች ሁሉ የሳምንቱ የሥራ ቀናት በብልሃት እንዲቀነሱ ቢደረግም የሥራ አጥነት ችግር አልተቃለለም። ሬናቶ ብሩኔታ የተባሉት የኢኮኖሚ ምሁር “የትኛውም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዞሮ ዞሮ ውጤት አልባ ሆኖ ይገኛል፤ ከጥቅሙ ይልቅ የሚያስከትለው ኪሣራ ያመዝናል” ብለዋል።
ሌስፕሬሶ የተባለው ጋዜጣ “ራሳችንን አናታልል፤ ችግሩ ውስብስብ ነው” ሲል ደምድሟል። ለመፍታት የሚያዳግት ውስብስብ ችግር ነውን? ሥራ አጥነት መፍትሔ ያገኝ ይሆን?
ጥንታዊ ችግር
ሥራ አጥነት ከጥንት የነበረ ችግር ነው። ሰዎች ያለ ውዴታቸው ሥራ የፈቱባቸው በርካታ መቶ ዘመናት አልፈዋል። በትላልቅ የግንባታ ፕሮጄክቶች ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ብዙ ሺህ ሠራተኞች ሥራው ሲጠናቀቅ ሥራ አልባ ይሆናሉ። ሌላው ቢቀር ሌላ ሥራ እስኪያገኙ ድረስ ሥራ አጥ ይሆናሉ። ሥራ እስኪያገኙ ድረስ ደግሞ አስተማማኝ ያልሆነ ኑሮ ይገፋሉ።
በመካከለኛው መቶ ዘመናት “ሥራ አጥነት በዘመናዊ መልኩ ያልነበረ” ቢሆንም ሥራ አጦች ግን ነበሩ። (La disoccupazione nella storia [ሥራ አጥነት በዘመናት ታሪክ] የተባለ መጽሐፍ) ይሁን እንጂ በእነዚያ ዘመናት ሥራ የማይሠሩ ሰዎች የማይረቡና ወሮበላ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር። እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች “ሥራ የሌላቸው ሰዎች ሥራ ፈቶችና የጐዳና ተዳዳሪ ተደርገው ይታዩ ነበር” ሲሉ ፕሮፌሰር ጆን በርኔት ሥራ የፈቱ እጆች (Idle Hands) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸዋል።
“የሥራ አጥነት ችግር መኖሩ የተነቃው” በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ወይም በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ነው። ችግሩን ለማጥናትና መፍትሔ ለመፈለግ የመንግሥት ኮሚሽኖች ተቋቁመዋል። ለምሳሌ በ1895 በእንግሊዝ አገር “በሥራ ዕጦት የሚመጣን ጭንቀት” ለማጥናት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ኮሚቴ ተሰይሞ ነበር።” በወቅቱ ሥራ አጥነት ማኅበራዊ ቸነፈር ሆኖ ነበር።
ይህ አዲስ ግንዛቤ በተለይ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። ያ ጦርነት የጦር መሣሪያ ለማምረት የሞት ሽረት ሩጫ የሚደረግበት ጊዜ ስለነበረ ሥራ አጥነትን አጥፍቶት ነበር ለማለት ይቻላል። በኋላ ግን ከ1920ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በምዕራባውያን አገሮች በየቦታው የንግድ ዕቃዎች ገበያ እየቀዘቀዘ ሄደ። ይህ ሂደት በ1929 የጀመረውን ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት አስከተለና በዓለም ዙሪያ በኢንዱስትሪ ላይ የተገነቡ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን አደቀቀ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ አገሮች አዲስ የኢኮኖሚ ምጥቀት አገኙና ሥራ አጥነት ዝቅ አለ። “አሁን ያለው ሥራ አጥነት ግን ወደኋላ መለስ ብለን ስናጠናው ችግሩ የተነሳው ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ነው” በማለት የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት ገልጿል። በ1970ዎቹ ዓመታት የነዳጅ ዋጋ ባስከተለው ውዝግብ ሳቢያ እንዲሁም በኮምፒዩተር አማካኝነት የኢንፎርሜሽን ልውውጥ እንደ አሸን በመፍላቱ ምክንያት የሥራው መስክ አዲስ ችግር ገጠመውና የሠራተኞች ቅነሳ መጣ። ሥራ አጥነት ወደ ላይ አሻቅቦ በመሄድ ምንም ነገር አይነካቸውም ይባሉ በነበሩት የቢሮ ሠራተኞችና በአስተዳደር አካባቢ ባሉት አለቆች ላይ ቀስቱን አነጣጥሯል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሥራ ይሰጠን ብሎ መጠየቅ ብቻውን የሥራ አጥነቱን ችግር አይፈታውም
[ምንጭ]
Reuters/Bettmann