የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 9/8 ገጽ 15-19
  • አምላክ ፈልገን እንድናገኘው አድርጎናል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ ፈልገን እንድናገኘው አድርጎናል
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስለ የይሖዋ ምሥክሮች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
  • ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘን
  • መንፈሳዊ ምግብ ተመገብን
  • በመንፈሳዊ እድገት አደረግን
  • ስቲቭ ሞስኮ ሊሄድ የቻለበት ምክንያት
  • ረጅም ጊዜ የፈጀው የፍርድ ቤት ክርክር በድል ተቋጨ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ንቁ!—1998
g98 9/8 ገጽ 15-19

አምላክ ፈልገን እንድናገኘው አድርጎናል

ንጉሥ ዳዊት በትረ መንግሥቱን ለልጁ ለሰሎሞን ሲያስረክብ የሚከተለውን ምክር ሰጥቶት ነበር:- “እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፣ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘላለም ይጥልሃል።”—1 ዜና መዋዕል 28:9

ይህ ጥቅስ ለእኛም እውነት ሆኖ አግኝተነዋል። አምላክን ፈልገን አግኝተነዋል። ሆኖም አምላክን ያገኘነው በተለያዩ የሃሰት መንገዶች ከባዘንን በኋላ ነበር። ይሖዋ መላው አስተሳሰባችን በእርሱና በአገልግሎቱ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዳተኮረ ስለተረዳ እንድናገኘው አድርጎናል ብለን እናምናለን። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ እንግለጽላችሁ።

አራት ወንድማማቾች ስንሆን ያደግነውም በፍሎሪዳ ዩ ኤስ ኤ ነው። አባታችን ቤተሰባችንን ለማስተዳደር በወጥ ቤትነት ረዥም ሰዓት ይሠራ ነበር። እናታችን የቤት እመቤት ስትሆን የቀረነው አራት ልጆች ደግሞ እንደ ሣር ማጨድና ጋዜጣ ማደል የመሰሉ ለቤተሰባችን ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ የተለያዩ ሥራዎች እንሠራ ነበር። እናታችን ካቶሊክ ስትሆን አባታችን ደግሞ ባፕቲስት ነበር። ሁላችንም በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ እናምን የነበረ ቢሆንም የምናውቀው ነገር ግን አልነበረም። አልፎ አልፎ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄድ ነበር። ወቅቱ በ1970ዎቹ መግቢያ ላይ ሲሆን ሰላም የሰፈነበት፣ ቤልባልት ሱሪ፣ ፀጉር ማስረዘምና የሮክ ሙዚቃ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያገኙበት ጊዜ ነበር። እነዚህ ሁሉ በሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድረውብናል።

በ1982 ሁለታችን ማለትም ስኮት እና ስቲቭ በ24 እና በ17 ዓመት ዕድሜያችን መጽሐፍ ቅዱስን የመመርመር ፍላጎት ያደረብን ከመሆኑም በላይ ወደ አዘቅት እየወረደ ያለው የዓለም ሁኔታ ያሳስበን ጀመር። ስኮት የራሱ የሆነ የግንባታ ሥራ የሚያካሄድ ድርጅት ነበረው። ሥራው ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ስለነበር በአንድ አፓርታማ ውስጥ አብረን መኖር ጀመርን። በየመጠጥ ቤቱ ጊዜያችንን ማሳለፉ በጣም አሰለቸን። ከዚህ የተሻለ የሕይወት መንገድ መኖር አለበት ብለን አሰብን። መንፈሳዊ ነገሮችን የመመገብ ፍላጎታችን እያየለ መጣ። መጽሐፍ ቅዱሳችንን አዘውትረን ማንበባችን ተጨማሪ እውቀት የመሰብሰብና የአምላክን ቃል በጥልቅ የማወቅ ፍላጎት እንዲያድርብን አድርጎናል።

በየሳምንቱ እሁድ ወደተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች መሄድ ጀመርን። በአንድ ወቅት የሄድንበት ቤተ ክርስቲያን በፍሎሪዳ ሌክ ዎርዝ ውስጥ ከሚገኘው ቤታችን አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን እሁድ እሁድ ገንዘብ ማዋጣትን በሚመለከት ለ25 ደቂቃ ንግግር ይሰጥ ነበር። ሰባኪው አትራኖሱን ተደግፎ “ሳትሰስቱ ያላችሁን ስጡ” እያለ ይናገራል። በአንድ ስብሰባ ላይ ሙዳየ ምጽዋቱን ሦስት ጊዜ ያዞሩ ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ሰዎች ኪሳቸው ተራቁቶ ወደ ቤት ይመለሱ ነበር። ወደ ሌሎች በርካታ ቤተ ክርስቲያኖች ሄድን። ሆኖም ተጨማሪ ሙዳየ ምጽዋት ሲዞር ከመመልከትና አብሮ ከመብላትና ከመጠጣት የተለየ ነገር አልገጠመንም።

ስለ የይሖዋ ምሥክሮች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ናቸው ብለን ባሰብናቸው የሃይማኖት ትምህርቶች እንድናምን ተደርገን ነበር። አስተማሪዎቻችን ከመንፈሳዊ ትምህርት ቤት የተመረቁ ስለነበሩ ያለምንም ማንገራገር ትምህርቶቹን እንቀበል ነበር። ከትምህርቶቹ መካከል አንደ ኛው በአሜሪካ ስላሉ መናፍቃን የሚገልጽ ነበር። በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሱት ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ አያምኑም፣ የራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው፣ ወደ ሰማይ አይሄዱም፣ ሲኦል የለም ብለው ያምናሉ ተብሎ ማስጠንቀቂያ ተሰጠን። ይህ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳቱ ናቸው ብለን እንድናምን አደረገን።

በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ቅንዓት አድሮብን የነበረ ቢሆንም በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አልነበረም። (ሮሜ 10:2) ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ምሥራቹን መስበክና ደቀ መዛሙርት ማድረግ እንዳለብን እናውቅ ነበር። በዚህ ጊዜ 2,000 አባላት ባሉት ባይብል ታውን ተብሎ በሚታወቅ ቤተ ክርስቲያን እንሰበሰብ ነበር። በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከነበረውና ከ17 እስከ 30 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 100 የሚሆኑ አባላት ካሉት አንድ የወጣቶች ቡድን ጋር ተቀላቀልን። ስኮት አንድ ዓይነት የስብከት ሥራ እንዲያከናውኑ ለማድረግ ሙከራ ያደረገ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል።

ስለዚህ የራሳችንን የስብከት ሥራ ማከናወን ጀመርን። ስኮት በአካባቢያችን በሚገኝ በአንድ የገበያ ቦታ ትራክቶችንና መጽሐፍ ቅዱሶችን ደርድሮ ወደዚያ ቦታ ለሚመጡ ሰዎች የማደል ሐሳብ መጣለት። እንዳሰበውም አደረግን። በአካባቢያችን ወደሚገኝ አንድ “የክርስቲያን” መጻሕፍት መደብር ሄድንና በርካታ ትራክቶችንና መጽሐፍ ቅዱሶችን ገዛን። ከዚያም ወደ ገበያ ቦታው ሄደን ሁለት ጠረጴዛ ካስቀመጥን በኋላ የገዛናቸውን ትራክቶችና መጽሐፍ ቅዱሶች ላያቸው ላይ ደረደርናቸው። በዚህ መንገድ ‘ቃሉን የምንሰማ ብቻ ሳንሆን የምናደርግ’ ለመሆን ጥረት አደረግን።—ያዕቆብ 1:22

ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ የእንግሊዝኛና የስፓንኛ ጽሑፎችን በማደል በገበያ ሥፍራው የምናከናውነው አገልግሎት እያደገ ሄደ። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ 30 የተለያዩ ትራክቶችና ኮፍያዎች ላይ የሚሰኩ “አምላክ ይወድሃል” የሚል ጽሑፍ ያለባቸው አርማዎች እናድል ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስኮት አጫጭር የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶችን በካናቴራ ላይ የሚያትም አንድ ማሽን ገዛና “ዛሬ መጽሐፍ ቅዱስ አንብበሃል?” “ደስተኛ የሆንኩት ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ኢየሱስ በልቤ ውስጥ ስላለ ነው” የሚሉና ሌሎች መልእክቶችን ማተም ጀመርን። አንደኛው ደግሞ አራቱ ፈረሰኞች የተሳሉበትና “ራእይ” የሚል ጽሑፍ ያለበት ነበር።

እነዚህን ካናቴራዎች ለብሰን በተለያዩ ቦታዎች መታየታችን ድምፅ አልባ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችለናል የሚል እምነት ነበረን። በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ በገበያ ሥፍራው እንደምናገለግል ማንም ሰው በቀላሉ መረዳት ይችላል። መኪና በሚቆምባቸው ቦታዎች የምታልፉ ቢሆንና በቆሙት መኪናዎች ውስጥ ትራክት ተቀምጦ ብትመለከቱ ቀደም ብለን እዛ ነበርን ማለት ነው። ጹሑፎቹን የምናድለው ሰዎች መዋጮ እንዲያደርጉ በመጠየቅ የነበረ ቢሆንም የምናገኘው መዋጮ በጣም አነስተኛ ነበር። በአንድ ወቅት በዓመት ውስጥ ያወጣነውን ወጪ ስናሰላው ከ10,000 የአሜሪካን ዶላር በልጦ ነበር።

ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኘን

በአንድ ወቅት ቦኒተ ስፕሪንግስ ውስጥ ከሚገኙት የባሕር ዳርቻዎች በአንዱ እየዋኘን ሳለ አንድ በዕድሜ የገፋ ሰው ወደ እኛ መጣና በመኪናችን ላይ የተለጠፉ ጽሑፎች እንዳየና ካናቴራዎቻችንንም እንደተመለከተ ነገረን። ከዚያም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አነሳና ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ ማብራራት ጀመረ። ሥራ 2:31 ላይ የሰፈሩትን ሐሳቦች ጠቅሶ “ሲኦል ማቃጠያ ከሆ ነና እዛም የሚገቡት መጥፎ ሰዎች ከሆኑ ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ በሲኦል ውስጥ ገብቶ እንደነበር የሚናገረው ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀን። ሌሎች በርካታ ጥቅሶችን እየጠቀሰ ማብራሪያ መስጠቱን ቀጠለ። በመጨረሻ ስኮት “አንተ የይሖዋ ምሥክር ሳትሆን አትቀርም” አለው። ሰውዬውም “አዎን፣ ነኝ” በማለት መለሰ። ከዚያም ስኮት “እናንተ በኢየሱስ አታምኑም” አለው። ለተጨማሪ 20 ደቂቃ ምሥክሩ ስለ ኢየሱስ ማብራሪያ ቢሰጥም ሊያሳምነን ግን አልቻለም።

ቅዳሜና እሁድ ወደ ገበያ ቦታው እየሄድን መስበካችንን ቀጠልን። ይህንንም ለሦስት ዓመታት ያህል ያደረግን ሲሆን ያንን ሁሉ ዓመት እውነትን እንደያዝንና ትክክለኛውን ነገር እያደረግን እንዳለን ሆኖ ይሰማን ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን በየሳምንቱ እሁድ አመሻሹ ላይ ወደ ተለያዩ ቤተ ክርስቲያን መሄዳችንን የቀጠልን ሲሆን አንዱም ግን አላረካንም። አሉ የተባሉትን ቤተ ክርስቲያኖች ሁሉ ካዳረስን በኋላ አንድ ቀን ምሽት ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች ቤተ ክርስቲያን” ብለን ከምንጠራቸው ቦታዎች ወደ አንዱ ለመሄድ ወሰንን። እዚያ ለመሄድ ያሰብነው ስለ ኢየሱስ ለመስበክ ነበር። ከስልክ ቁጥር ማውጫ ላይ አድራሻ ካገኘን በኋላ አንድ እሁድ ምሽት ላይ ወደዚያው ሄድን። እንደ ሌሎቹ ቤተ ክርስቲያኖች እሁድ ምሽት ላይ የሚደረግ ስብሰባ አለመኖሩን ስንረዳ በኢየሱስ አያምኑም ወደሚለው ድምዳሜ ላይ ደረስን። ስብሰባ የሚደረግበትን ቀንና ሰዓት በሚገልጸው ማስታወቂያ ላይ ሰኞ ማታ የመጽሐፍ ጥናት እንደሚደረግ አነበብን። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱሳችንን ይዘንና ካናቴራዎቻችንን ለብሰን እንደገና ተመልሰን ሄድን። የትኛውን ካናቴራ እንደምንለብስና ጥሩ ምሥክርነት ሊሰጥ የሚችለው የትኛው እንደሆነ ለመወሰን ጥቂት ደቂቃዎች እንደወሰደብን ትዝ ይለናል። የደረስነው ትንሽ ቀደም ብለን ስለነበር ጥቂት ወንድሞች ቀርበው አነጋገሩን። ሞቅ ባለ ወዳጃዊ ስሜት አነጋገሩን። ወዲያው የራእይ መጽሐፍን በተመለከተ የጦፈ ውይይት ውስጥ ገባን። ስብሰባው እስኪያልቅ ድረስ እንድንቆይ ጋበዙን። የአምልኮ አንድነት የተባለ መጽሐፍ ሰጡንና ተቀመጥን። ከዚያም አንድ ወንድም ስብሰባውን በጸሎት ከፈተ።

ጸሎቱን በጥሞና አዳመጥን። በመደምደሚያው ላይ “በኢየሱስ ስም፣ አሜን” አለ። ሁለታችንም ተገርመን እርስ በርሳችን ተያየን። “ጆሯችን ነው? የጸለየው እኮ በኢየሱስ ስም ነው!” በዚያች ቅጽበት ከዓይናችን ላይ ቅርፊት ወድቆ አጥርተን ማየት እንደጀመርን ያክል ሆኖ ተሰማን። ልባችን ጥሩ ከሆነ መስማት የምንችልበት ጥሩ አጋጣሚ ይህ ወቅት ነበር። ስብሰባውን የሚመራው ወንድም የአምልኮ አንድነት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 21 ላይ እንዲያወጡ ጋበዘ። ይህ ምዕራፍ ስለ ኢየሱስና የዓለም ክፍል ስላለመሆን የሚናገር ነበር። እንዲህ በመሰለው ስብሰባ ላይ መገኘት በእርግጥም ተገቢ ነበር። ትምህርቱ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት፣ ስለ መጨረሻ ቀኖችና ስለ ገለልተኝነት የሚገልጽ ነበር። ትንንሽ ልጆች እኛ ጨርሶ በማናውቃቸው ብዙ ነጥቦች ላይ ሐሳብ ሲሰጡ ሰማን። ከዚያም በስብሰባው መደምደሚያ ላይ ወንድም በኢየሱስ ስም ጸለየ!

መንፈሳዊ ምግብ ተመገብን

ወደ አዳራሹ የገባነው እውነትን ተጠምተን ነበር፤ የፈለግነውን እውነት እዛው አገኘነው። ወደ ቤት ስንመለስ በመንፈሳዊ በደንብ እንደ ተመገብን ተሰምቶን ነበር፤ በመሆኑም ከዚያ ጊዜ አንስቶ ወደየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ዝር አላልንም። በቀጣዩ ምሽት በልብስ ማጠቢያ ማሽን ልብሳችንን እያጠብን ሳለ በዱቄት ሳሙና ማሽኑ አጠገብ 150 የሚሆኑ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች አገኘን። እንደ ቀድሞው ቢሆን ኖሮ አናነባቸውም ነበር። አሁን ግን እላያቸው ላይ በሰፈሩት ብዙ ርዕሶች ስለተማረክን ሰብስበን ወሰድናቸው።

ከርዕሶቹ መካከል አንደኛው “በሥላሴ ታምናለህን?” የሚል ነበር። ሌላኛው ደግሞ “በእርግጥ ሲኦል አለን?” ይላል። አንደኛው የንቁ! መጽሔት ደግሞ ስለ ምስሎች የሚናገር ርዕስ ነበረው። በዚያች ምሽት ስቲቭ ስለ ሥላሴ የሚናገረውን መጽሔት አነበበ፣ ጥቅሶቹን በሙሉ እያወጣ በደንብ ከመረመረ በኋላ ያነበበው ነገር በጣም ስለነካው ከሌሊቱ 6 ሰዓት ተኩል ላይ ስኮትን ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው። በቀጣዩ ቀን ረቡዕ ዕለት ስቲቭ ከሥራ ከተመለሰ በኋላ ስለ ሲኦል የሚናገረውን ርዕስ አነበበ። ኢየሱስ፣ አልዓዛር እንደተኛ አድርጎ የተናገረበትን ዮሐንስ 11:11⁠ን የሚያብራራ ነበር። ስቲቭ ስኮትን ሲያገኘው “የኔ መጽሐፍ ቅዱስ እሳታማ ሲኦል አለ ብሎ አያስተምርም” አለው። ስለ ምስልና ስለተለያዩ የመስቀል ዓይነቶች የሚናገረውን ንቁ! ካነበብን በኋላ ያሉንን ምስሎች ሁሉ ሰብስበን በቆሻሻ መጣያ መኪና ውስጥ ጥለን መኪናው ይዟቸው ሲሄድ ቆመን ተመለከትናቸው። እርስ በርሳችን ተያየንና ራሳችንን እየነቀነቅን ፈገግ አልን። አንድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነገር ማለትም እውነትን እንዳገኘን አውቀን ነበር።

ከአንድ ቀን በኋላ ሁለት ካርቶኖች ደረሱን። ንሥሐ ካልገባህ ሲኦል ትገባለህ የሚል ሐሳብ የሠፈረባቸው 5,000 ትራክቶች ካርቶኖቹ ውስጥ ታጭቀዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት እነዚህ ትራክቶች ትክክል አለመሆናቸውን በዚህ ወቅት አውቀን ነበር። ትንሽ ግር ስላለን በርካታዎቹን ትራክቶች ይዘን ሰኞ ማታ ወደሚደረገው የመጽሐፍ ጥናት በድጋሚ ሄድን። “ይህን እንዴት ትመለከቱታላችሁ?” ብለን ጠየቅናቸው። አንድ ቀን ማታ ላይ ሁሉንም አንድ በአንድ መረመርናቸው። ወዲያውኑ አንድ በአንድ የጣልናቸው ትራክቶች መሬቱ ላይ ተቆለሉ። አንዳቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚስማሙ አልነበሩም። ሁሉንም አስወገድናቸው። ያገኘነው አዲሱ እምነት የእኛንም ሆነ የምንሰብክላቸውን ሰዎች ሕይወት በእጅጉ እንደሚነካ ተገንዝበን ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ምንም ነገር እንዲያስተጓጉልብን ስላልፈለግን ቦታ ለመቀየር ወሰንን።

ስለዚህም ወደ አላስካ ሄድን። ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ እንደተገኘን ከእኛ ጋር በየቀኑ ማጥናት ይችል እንደሆነ አንዱን ሽማግሌ ጠየቅነው። የተናገርነውን ስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ የሰሙት ይመስለኛል። ጥሩ እድገት አደረግንና ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ አጥንተን ጨረስን። ለሁ ለት ቀናት ከሚካሄዱት ትልልቅ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ለመጠመቅ ፈልገን ነበር። ሆኖም ትንሽ መቆየት ነበረብን። ግባችን አቅኚ መሆን ነበር። አባታችን በድንገት ስለታመመ እርሱን ለማስታመም ስንል ወደ ፍሎሪዳ ለመመለስ ተገደድን።

በመንፈሳዊ እድገት አደረግን

በፍሎሪዳም ጥሩ እድገት አደረግንና የአምልኮ አንድነት የተባለውን መጽሐፍ አጥንተን ጨረስን። ከዚያም በ1987 ተጠመቅን። ጥናት ከጀመርን 11 ወራት ሆኖን ነበር። ወዲያውኑ ለስድስት ወራት ረዳት አቅኚ ሆነን ካገለገልን በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆንን። ከተጠመቅን አንድ ዓመት ከስድስት ወር እንደሆነን ሁለታችንም የጉባኤ አገልጋዮች ሆነን እንድናገለግል ተሾምን። ከተጠመቅን ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል ጀመርን። ስኮት እስከ አሁን ድረስ እዚያው እያገለገለ ሲሆን ለሁለት ዓመታት ያክል የቻይንኛን ቋንቋ ሲያጠና ቆይቷል። ስቲቭ ደግሞ ሩስያ ውስጥ በሞስኮ ከተማ የዘወትር አቅኚ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ሁለታችንም እውነትን ያገኘን ሲሆን እውነትን ለማግኘት ያደረግነው ፍለጋ ልክ ምሳሌ 2:1–5 ላይ እንደተገለጸው ነው:- “ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፣ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፣ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፣ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፣ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፣ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።”

ስቲቭ ሞስኮ ሊሄድ የቻለበት ምክንያት

ሌላ ቋንቋ ማወቅ በኒው ዮርክ የሚደረገውን የስብከት ሥራ ይበልጥ አስደሳች የሚያደርገው ከመሆኑም በላይ ምናልባት ይሖዋ በቅርቡ በሩስያ ለስብከቱ ሥራ በር ይከፍት ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ የሩስያ ቋንቋ ለመማር ወሰንኩ። በብሩክሊን ቤቴል እያገለገልኩ በሩስያ ቋንቋ በሚመራ አንድ የመጽሐፍ ጥናት ላይ መገኘት ጀመርኩ። በየሳምንቱ ዓርብ ዓርብ በሩስያ ቋንቋ የሚካሄድ አንድ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ብቻ ነበር። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ በዚህ የሩስያ ቋንቋ ቡድን ውስጥ የማደርገውን እንቅስቃሴ ከፍ ማድረግ ጀመርኩ። በስብከቱ ሥራ አብሬያቸው መካፈል ጀመርኩ። ሩስያውያን የሚያሳዩት ሞቅ ያለ የተግባቢነት መንፈስ የስብከት ሥራውን አስደሳች አደረገልኝ። ወደዚህ የሩስያ ቋንቋ ቡድን እንዲያዘዋውሩኝ ለአገልግሎት ክፍል ማመልከቻ አስገባሁ። በጥያቄዬ እንደተስማሙ ሳውቅ በጣም ተደሰትኩ።

አንድ ቀን በቤቴል የማለዳ አምልኮ ላይ ሳለን የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሚልተን ጂ ሄንሼል አንድ ልዩ ሪፖርት እንደሚቀርብ ለቤተሰቡ ተናገረ። ከዚያም በሩስያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና እንዳገኙና ወንድሞቻችንም በነፃነት አምልኳቸውን እንደሚያከናውኑ አስታወቀ። እንዲህ ያለውን አስደሳች ዜና ስንሰማ የተሰማንን ደስታ በዚያ ማለዳ የተገኘ ማንኛውም ቤቴላዊ ይዘነጋዋል ብዬ ፈጽሞ አላስብም። በዚያ ሰፊ አዲስ የአገልግሎት ክልል ከሚያገለግሉት ጋር አብሮ መሥራት ታላቅ መብት መሆኑን ያሰብኩት በዚያች ቅጽበት ነበር።

ሩስያ ውስጥ በክራስነዳር ከሚኖር ቨሎድየ ከሚባል አንድ ሩስያዊ ወንድም ጋር መጻጻፍ ጀመርኩ። እርሱም ሩስያን እንድጎበኝ ጋበዘኝ። ስለዚህም ሰኔ 1992 ሻንጣዎቼን ጭኜ ወደ ሞስኮ አመራሁ። እዛም እንደደረስኩ ወንድም ቨሎድየ እኔን ለመቀበል አውሮፕላን ማረፊያው ድረስ በመምጣቱ ደስ አለኝ። ከዚያም 45 ዓመታት በእውነት ቤት ውስጥ ባሳለፈው በወንድም ስቴፋን ለቪንስኪ ቤት አረፍኩኝ። ሞስኮ ውስጥ በመጀመሪያ ያገኘሁት ምሥክር እርሱ ነበር። ለእውነት በነበረው የጸና አቋም ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ታስሯል። ወንድሞች ያሳዩኝ የነበረው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በጣም የሚደነቅ ነው።

ቋንቋውን እምብዛም ባላውቅም የሞስኮ ኑሮዬን ተያያዝኩት። በዚያን ጊዜ በሞስኮ የነበሩት ጉባኤዎች ብዛት አራት ብቻ ሲሆን ሁሉም ወንድሞች እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁ ያክል ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀምኩ የመኖሪያ ፈቃዴን ማራዘም ችያለሁ። ወጪዎቼን ለመሸፈን ስል አልፎ አልፎ እሠራለሁ። ትልቁ ችግሬ ለመግባቢያ የሚሆነኝንና በስብሰባ ላይ በመንፈሳዊ በደንብ ለመመገብ የሚያስችለኝን የሩስያኛ ቋንቋ ጠንቅቆ ማወቁ ነበር። ቀስ በቀስ ቋንቋውን መናገር ቻልኩ፤ እርግጥ አሁንም ቢሆን ገና ይቀረኛል።

በተለያዩ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የመገኘትና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሲጠመቁ የመመልከት መብት አግኝቻለሁ። እዚህ ያሉ ወንድሞች የሚያሳዩትን ከፍተኛ የቅንዓት መንፈስ መመልከቱ እምነትን እጅግ የሚያጠነክር ነው። ይህንን በምንም ነገር ልለውጠው አልፈልግም። ወደዚህ ስመጣ ገና ጥናቶች ወይም አዲስ ተጠማቂዎች የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወንድሞችና እህቶች አሁን የሙሉ ጊዜ አቅኚዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች ወይም ደግሞ ሩስያ ውስጥ በሴንት ፒተርዝበርግ አቅራቢያ በሶልኔችኖዬ ቤቴላውያን ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።

ባለሁበት ጉባኤ በየሳምንቱ እሁድ 530 ተሰብሳቢዎች የሚገኙ ሲሆን በየወሩ በአማካይ 12 ሰዎች ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ይሆናሉ። በአሁኑ ጊዜ 380 አስፋፊዎች፣ 3 ሽማግሌዎችና 7 የጉባኤ አገልጋዮች በጉባኤያችን አሉ። ጉባኤያችን ከ486 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ሪፖርት ያደርጋል። በየካቲት 1995 የአገልግሎት ንግግር ለመስጠት 29 የመጽሐፍ ጥናት ቡድኖቻችንን የመጎብኘት መብት አግቼ ነበር። በአንድ ሳምንት ውስጥ አራት ቡድኖችን እጎበኝ ነበር። እያንዳንዱ ትልቅ ስብሰባ ሲደርስ አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናሳልፈው የጥምቀት እጩዎችን በመጠየቅ ነው። ግንቦት 1995 ባደረግነው የልዩ ስብሰባ ቀን ላይ 30 የሚሆኑ ሰዎች ከጉባኤያችን ተጠምቀዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ 10,000 የሚያክሉ ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን 607 ተጠምቀዋል። በ1995 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተጠመቁት 877 ሰዎች መካከል 24ቱ የእኛ ጉባኤ አባላት ናቸው! በጉባኤያችን 13 አቅኚዎችና 3 ልዩ አቅኚዎች አሉ። አቅኚዎቹ በድምሩ 110 የሚያክሉ ጥናቶችን ሪፖርት አድርገዋል! በአሁኑ ጊዜ ጉባኤያችን 132 የሚያክሉ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች አሉት።

በ1995 ባደረግነው የመታሰቢያው በዓል ላይ 1,012 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር! በቅርቡ ማኅበሩ ማቲሽ የተባለ አንድ ፖላንዳዊ ወንድም ወደ ጉባኤያችን ልኳል። ይህ ወንድም ከአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቀ ሲሆን ለጉባኤያችንም ከፍተኛ እገዛ ያበረክታል። አሁን ሦስት ሽማግሌዎች አሉን። ስለዚህም አንድ ተጨማሪ ጉባኤ ይመሠረታል። አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ያሉት የአገልግሎት ክልላችን ለሁለት ይከፈላል። ሁለቱ ጉባኤዎች እያንዳንዳቸው 200 የሚጠጉ አስፋፊዎች ይኖሯቸዋል። አንደኛው ጉባኤ ሁለት ሽማግሌዎች ሲኖሩት ሌላኛው ደግሞ አንድ ሽማግሌ ይኖረዋል። ሌላ ትልቅ ስብሰባ የምናደርግበት ጊዜ እየተቃረበ ያለ ሲሆን በዚያ ስብሰባ ላይ የሚጠመቁትን 44 የሚያክሉ አስፋፊዎች ለጥምቀት እጩዎች የተዘጋጁትን ጥያቄዎች መጠየቅ አለብን። ሁኔታው በጣም አስገራሚ ነው! በእርግጥም መንፈሳዊ ገነት ነው! እጅግ የሚያስደንቅ ነው! ይሖዋ ሥራውን እየደገፈው እንዳለ የሚያሳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ሰረገላ በሩስያ ውስጥ በታላቅ ፍጥነት እየተጓዘ ያለ ይመስላል። ከጥቅምት 1995 ጀምሮ በሞስኮ ያሉት የጉባኤዎች ብዛት 40 ሲሆን በቂ ቁጥር ያላቸው ሽማግሌዎች ቢኖሩ ኖሮ ቁጥሩ ከእዚህ በእጥፍ ይበልጥ ነበር።

በገበያ ቦታ እናደርግ የነበረው የስብከት ሥራ ረዥም ጊዜ አልፎታል። ስኮት በብሩክሊን ቤቴል እያገለገለ ሲሆን ስቲቭ ደግሞ ሞስኮ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። አምላክ እርሱን እንድናገኘው ስላደረገን ሁለታችንም በጣም አመስጋኞች ነን። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አምላክን እንዲፈልጉትና እንዲያገኙት ጸሎታችን ነው።—ስኮት እና ስቲቭ ዴቪስ እንደተናገሩት

[የግርጌ ማስታወሻ]

ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስኮት

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስቲቭ

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሞስኮ በሚገኝ በአንድ ጉባኤ በየሳምንቱ እሁድ ከ530 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ይገኛሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ