የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 1/8 ገጽ 19-21
  • መድኃኒቶችን በአግባቡ ተጠቀምባቸው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መድኃኒቶችን በአግባቡ ተጠቀምባቸው
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጥቅሙንና ጉዳቱን ማመዛዘን
  • አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች— ጠንካራና ደካማ ጎናቸው
  • ከኪኒኖች ይልቅ በመርፌ የሚሰጡ መድኃኒቶች ይሻላሉን?
  • የሐሰት መድኃኒቶች
  • ድህነት የሚያስከትለው ችግር
  • በእርግጥ መድኃኒት ያስፈልግሃልን?
  • ከዕፅ ጋር የሚደረገውን ውጊያ በድል አድራጊነት ማጠናቀቅ ይቻል ይሆን?
    ንቁ!—1999
  • ለጥሩ ሕይወት ቁልፉ አደንዛዥ መድኃኒቶች ናቸውን?
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
  • መድኃኒቶችን በአግባብ መውሰድና አላግባብ መጠቀም
    ንቁ!—2009
  • ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት እነማን ናቸው?
    ንቁ!—2001
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 1/8 ገጽ 19-21

መድኃኒቶችን በአግባቡ ተጠቀምባቸው

በናይጄርያ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ሴትየዋ ራስ ምታት እንዳለባትና ሆዷን እንደሚያማት ተናገረች። ዶክተሩ ለአጭር ጊዜ አነጋገራት። ከዚያ በኋላ ለወባ የሦስት ቀን መርፌ፣ ራስ ምታቱ እንዲሻላት ፓራሲታሞል (አሲታሚኖፌን)፣ የጨጓራ ቁስለት ሊሆን ይችላል በሚል ሁለት ዓይነት መድኃኒቶች፣ ለጭንቀቷ የማስታገሻ መድኃኒትና ከእነዚህ መድኃኒቶች በተጨማሪ ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ የሚወሰዱ መልቲቫይታሚኖች አዘዘላት። ወጪው በጣም ብዙ ቢሆንም ሴትየዋ አልተቃወመችም። መድኃኒቶቹ እንደሚያሽሏት በመተማመን ደስ ብሏት ሄደች።

እንደዚህ ዓይነቱ የመድኃኒት ትእዛዝ በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ያልተለመደ አይደለም። በምዕራብ አፍሪካ በሚገኝ አንድ ትልቅ አገር ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በጤና ጣቢያዎች የሚሠሩ የሕክምና ባለ ሙያዎች እያንዳንዱ በሽተኛ ወደ እነሱ በመጣ ቁጥር በአማካይ 3.8 ዓይነት የተለያዩ መድኃኒቶች ያዙለታል። እንዲያውም ብዙ ሰዎች ጥሩ ዶክተር የሚሉት ብዙ መድኃኒቶች የሚያዝላቸውን ነው።

በምዕራብ አፍሪካ ከነበረው የጤና ሁኔታ አንፃር እዚያ የሚኖሩ ሰዎች በመድኃኒት ላይ እንዲህ ያለ እምነት ለምን እንዳሳደሩ ሊገባን ይችላል። ከ40 ዓመታት በፊት ጆን ጉንተር የተባሉ ደራሲ ቀደም ሲል ስለ ነበረው ሁኔታ ሲጽፉ እንዲህ ብለዋል:- “በዚህ የባሪያ ንግድ ይካሄድበት በነበረ ቦታ የሞቱት ጥቁሮች ብቻ አይደሉም፤ ነጮችም ሞተዋል፤ በአፈ ታሪክ ‘የነጮች መቃብር’ በመባል የሚታወቀው ይህ የአፍሪካ ክፍል ነው። የወባ ትንኝ ለብዙ መቶ ዓመታት ማንም ሊቋቋመው የማይችል ንጉሥ ሆኖ በጊኒ ጠረፍ ሲገዛ ቆይቷል። ቢጫ ወባ፣ ብላክ ዎተር ፊቨርና ወባ የዚህ ንጉሥ የተመረጡና ክፉ መሣሪያዎች ነበሩ። የምዕራቡ ባሕር ጠረፍ አየር ንብረት ለሕይወት አስጊ የነበረ መሆኑ የጥንት ታሪክ ሳይሆን ምን ጊዜም ከአእምሮ የማይጠፋ ትዝታ ነው። አንድ የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ሹም ወደ ናይጄርያ እንደተዛወሩ ሲነገራቸው ስለ ጡረታቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚገልጽ ትንሽ ቆየት ያለና ተወዳጅ የሆነ ተረት አለ። የቅኝ ገዢዎች ሹም የሆኑት አለቃቸው ‘ጡረታ?’ ሲሉ ጠየቁ። ‘ወንድሜ ወደ ናይጄርያ የሄደ ማንም ሰው ጡረታ እስኪወጣ ድረስ በሕይወት አይቆይም።’”

ዛሬ ሁኔታው ተለውጧል። በዛሬው ጊዜ በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚሰራጩትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በሽታዎችንም ጭምር ለመከላከል የሚያስችሉ መድኃኒቶች አሉ። ኩፍኝ፣ ትክትክ፣ መንጋጋ ቆልፍና ዘጊ አናዳ የተባሉት በሽታዎች በክትባት ብቻ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንሱ ተደርጓል። በክትባት ብቻ የፈንጣጣ በሽታ ጠፍቷል። የልጅነት ልምሻም በቅርቡ የተረሳ ሊሆን ይችላል።

በዛሬው ጊዜ ብዙ አፍሪካውያን በመድኃኒት ጠቀሜታ ላይ ከፍተኛ እምነት ያላቸው መሆኑ ምንም አያስገርምም። እርግጥ እንዲህ ዓይነቱ እምነት በምዕራብ አፍሪካ ብቻ ያለ አይደለም። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ዶክተሮች በየዓመቱ ከ55 ቢልዮን በላይ የመድኃኒት ማዘዣዎች ይጽፋሉ። በፈረንሳይ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው በየዓመቱ በአማካይ 50 ፓኬት ኪኒኖች ይገዛል። በጃፓን ውስጥ ደግሞ እያንዳንዱ ግለሰብ በየዓመቱ በአማካይ ከ400 የአሜሪካ ዶላር በላይ ለመድኃኒት ያወጣል።

ጥቅሙንና ጉዳቱን ማመዛዘን

ዘመናዊ መድኃኒቶች የሰውን ልጅ በጣም ረድተውታል። መድኃኒቶችን በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው ጥሩ ጤንነት እንዲኖረን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሲሆን አለአግባብ ከተጠቀምንባቸው ደግሞ ሊጎዱን እንዲያውም ሊገድሉን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየዓመቱ መድኃኒቶች ባስከተሉባቸው ችግር ምክንያት 300,000 የሚያህሉ ሰዎች ታመው ሆስፒታል ከመግባታቸውም በላይ 18,000 ሰዎች ይሞታሉ።

መድኃኒቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ስናስብ ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ማንኛውም መድኃኒት አስፕሪን እንኳ ሳይቀር አንዳንድ ጉዳቶች ሊያስከትል ይችላል። በአንድ ጊዜ ብዙ ዓይነት መድኃኒቶችን ከወሰድክ ደግሞ ጉዳት ሊደርስ የሚችልበት መጠን ይበልጥ ከፍተኛ ይሆናል። በተጨማሪም የምትመገበው ምግብና የምትጠጣቸው ነገሮች መድኃኒቶች በአካልህ ውስጥ በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ሲሆን መድኃኒቱ ይበልጥ ኃይል እንዲኖረው ወይም እንዲዳከም ሊያደርጉ ይችላሉ።

ሌሎች አደጋዎችም አሉ። አንዳንድ መድኃኒቶች አለርጂ ሊያስከትሉብህ ይችላሉ። መድኃኒቶችን በተገቢው መጠንና ለታዘዙልህ ቀናት በሙሉ ካልወሰድክ ላይጠቅሙህ እንዲያውም ሊጎዱህ ይችላሉ። ሐኪምህ የተሳሳቱ ወይም የማያስፈልጉ መድኃኒቶች ካዘዘልህም ተመሳሳይ ነገር ሊያጋጥምህ ይችላል። በተጨማሪም ጊዜ ያለፈባቸው፣ ደረጃቸው አነስተኛ የሆኑ ወይም የሐሰት መድኃኒቶችን ከወሰድክ ትጎዳለህ።

ሊደርሱብህ የሚችሉትን አደጋዎች ለመቀነስ ስለምትወስደው ስለ እያንዳንዱ መድኃኒት የምትችለውን ያህል ማወቅ አለብህ። አንዳንድ እውነታዎችን ማወቅህ በጣም ሊጠቅምህ ይችላል።

አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች— ጠንካራና ደካማ ጎናቸው

አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ከ50 ዓመት በፊት መመረት ከጀመሩ ወዲህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አድነዋል። እንደ ሥጋ ደዌ፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ የሳንባ ምች፣ ስካርሌት ፊቨር እና ቂጥኝ ያሉትን አስፈሪ በሽታዎች እንዲቀንሱ አድርገዋል። ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን በማዳን ረገድም ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ በቱፊት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት የመድኃኒት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ስትዋርት ሌቪ እንዲህ ብለዋል:- “[አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች] በሕክምና ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል። የሕክምናን ታሪክ የእነርሱን ያህል የለወጠው ነገር የለም።” ሌላ የሕክምና ምሁር “ለዘመናዊ ሕክምና የማዕዘን ድንጋይ ሆነዋል” ብለዋል።

ሆኖም ቶሎ ወደ ሐኪምህ ሄደህ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች እንዲያዝልህ ከመጠየቅህ በፊት መጥፎ ጎናቸውን አስብ። አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን አለአግባብ ከተጠቀምክባቸው አንተን ከመጥቀም ይልቅ ሊጎዱህ ይችላሉ። ይህ የሆነው አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች የሚሠሩት በሰውነት ውስጥ የሚገኙትን ባክቴሪያዎች በማጥቃትና በማጥፋት ስለሆነ ነው። ሆኖም ሁልጊዜ ሁሉንም ጎጂ ባክቴሪያዎች አያጠፉም፤ አንዳንድ የባክቴሪያ ዝርያዎች ጥቃቱን ይቋቋማሉ። እነዚህ መድኃኒቶችን የመቋቋም ችሎታ ያላቸው ዝርያዎች በሕይወት ከመትረፋቸውም በተጨማሪ ተራብተው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ይተላለፋሉ።

ለምሳሌ ያህል ፔኒሲሊን በአንድ ወቅት ኢንፌክሽንን በማዳን ረገድ በጣም ውጤታማ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ፔኒሲሊንን መቋቋም የሚችሉ የባክቴሪያ ዝርያዎች እየጨመሩ በመሄዳቸው የመድኃኒት ፋብሪካዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የፔኒሲሊን ዓይነቶችን በገበያ ላይ አውለዋል።

ችግሮች እንዳይፈጠሩ ምን ልታደርግ ትችላለህ? አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች በእርግጥ የሚያስፈልጉህ ከሆነ ብቃት ያለው ሐኪም ያዘዛቸውና ከትክክለኛ ምንጭ የተገኙ መሆናቸውን አረጋግጥ። ዶክተርህ ቶሎ አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን እንዲያዝልህ አትጫነው፤ እሱ ወይም እሷ የሚያዙልህ መድኃኒት ለበሽታህ የሚስማማ መሆኑን ለማረጋገጥ የላቦራቶሪ ምርመራ እንዲካሄድ ይፈልጉ ይሆናል።

በተጨማሪም በየቀኑ ትክክለኛውን መጠን ለታዘዙልህ ቀናት በሙሉ መውሰድህ በጣም አስፈላጊ ነው። መድኃኒቱ ሳያልቅ ቢሻልህም እንኳ የታዘዙልህን አንቲባዮቲክ መድኃኒቶች በሙሉ እስኪያልቁ ድረስ መውሰድ አለብህ።

ከኪኒኖች ይልቅ በመርፌ የሚሰጡ መድኃኒቶች ይሻላሉን?

“መርፌ ነው የምፈልገው!” በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ብዙ የጤና ባለሙያዎች እነዚህን ቃላት ይሰማሉ። ሰዎች እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የሚያቀርቡት መድኃኒቱ በቀጥታ ወደ ደም ስለሚገባ ከኪኒኖች የተሻለ ፈውስ ያስገኛል የሚል እምነት ስላላቸው ነው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ በየገበያ ቦታው ፈቃድ የሌላቸው ‘መርፌ ወጊ ሐኪሞች’ ማየት የተለመደ ነው።

መርፌ መወጋት ኪኒኖች የማያስከትሏቸውን ችግሮች ሊያመጣ ይችላል። መርፌው ንጹሕ ካልሆነ በሽተኛው ሄፓታይተስ፣ መንጋጋ ቆልፍ፣ ኤድስም እንኳ ሳይቀር ሊይዘው ይችላል። ቆሻሻ መርፌ የሚያሠቃይ እባጭ ሊያስይዝ ይችላል። መርፌ የሚወጋው ለሥራው ብቃት ያለው ሰው ካልሆነ ደግሞ ይበልጥ አደገኛ ነው።

መርፌ መወጋት በእርግጥ የሚያስፈልግህ ከሆነ መርፌ የሚወጋህ ሰው የሕክምና ባለ ሙያ መሆኑን አረጋግጥ። አደጋ እንዳያስከትልብህ መርፌውም ሆነ ሲሪንጋው በሽታ ከሚያስተላልፉ ሕዋሳት ሙሉ በሙሉ ንጹሕ መሆናቸውን አረጋግጥ።

የሐሰት መድኃኒቶች

የዓለም የጤና ድርጅት በገለጸው መሠረት የዓለም የመድኃኒት ኢንዱስትሪ በየዓመቱ 170 ቢልዮን የሚያህል የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኝ ትልቅ ንግድ ያካሂዳል። ስለ ሌላው ደንታ የሌላቸው ሰዎች ሁኔታው በፈጠረው አጋጣሚ በመጠቀም አስመስለው የተሠሩ መድኃኒቶችን ያመርታሉ። አስመስለው የተሠሩ መድኃኒቶች መጠቅለያቸውንና የተለጠፈባቸውን ምልክት ጨምሮ በሁሉም ነገር እውነተኛ መድኃኒቶችን የሚመስሉ ቢሆኑም ምንም አይጠቅሙም።

የሐሰት መድኃኒቶች በየትኛውም አገር ያሉ ቢሆንም በተለይ በታዳጊ አገሮች በብዛት ይገኛሉ። እነዚህ መድኃኒቶች አሳዛኝ ውጤቶች በማስከተል ላይ ናቸው። በናይጄርያ ለሥቃይ ማስታገሻ ተብሎ የተሰጣቸውን የኢንዱስትሪ ኬሚካል ያለበት ሽሮፕ በመጠጣታቸው 109 ሕፃናት ኩላሊታቸው መሥራት አቁሞ ሞተዋል። በሜክሲኮ ውስጥ የእሳት ቃጠሎ የደረሰባቸው ሰዎች ያሽለናል ብለው የእንጨት ብናኝ፣ ቡናና ጭቃ የተቀላቀለበት ነገር ቆዳቸውን በመቀባታቸው ኃይለኛ የቆዳ ኢንፌክሽን ይዟቸዋል። በርማ ውስጥ በአንድ መንደር የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ወባን መከላከል የማይችል የሐሰት መድኃኒት ወስደው በወባ በሽታ ሳይሞቱ አልቀሩም። የዓለም የጤና ድርጅት “አሁንም ቢሆን ከሁሉ ይበልጥ አደጋ የሚደርስባቸው በአንድ ጥሩ ኩባንያ የተመረተ የሚመስል መድኃኒት ሲገዙ ጥሩ መድኃኒት በርካሽ ዋጋ አገኘን ብለው የሚያስቡ በጣም ድሀ የሆኑ ሰዎች ናቸው” ሲል ይገልጻል።

ከሐሰት መድኃኒቶች ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? መድኃኒት ስትገዛ በሆስፒታል እንደሚገኙት መድኃኒት ቤቶች ጥሩ ስም ካላቸው ቦታዎች ግዛ። መንገድ ላይ ከሚቸረችሩ ሰዎች አትግዛ። በናይጄርያ ውስጥ በቤኒን ከተማ የሚኖር አንድ ፋርማሲስት እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “መንገድ ላይ መድኃኒት የሚቸረችሩ ሰዎች የሚሸጡት ለንግድ ነው። ከረሜላ ወይም ብስኩት የሆኑ ይመስል መድኃኒቶችን መንገድ ላይ ይቸረችራሉ። አብዛኛውን ጊዜ የሚቸረችሯቸው መድኃኒቶች ጊዜ ያለፈባቸው ወይም የሐሰት መድኃኒቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ስለሚሸጧቸው መድኃኒቶች ምንም እውቀት የላቸውም።”

ድህነት የሚያስከትለው ችግር

ብዙውን ጊዜ አንድ ግለሰብ የሚያገኘው ሕክምና ባለው የገንዘብ አቅም ላይ የተመካ ነው። በታዳጊ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ወጪ ለመቀነስና ጊዜ ለማዳን ሲሉ ወደ ሐኪም ሳይሄዱ በቀጥታ ወደ መድኃኒት ቤቱ ሄደው በሕግ ያለ ሐኪም ትእዛዝ የማይሰጡትን መድኃኒቶች ይገዛሉ። ቀደም ሲል መድኃኒቱን ወስደው ስለ ነበር ወይም ደግሞ ጓደኞቻቸው እንዲወስዱት ስላበረታቷቸው ለበሽታቸው መውሰድ የሚፈልጉትን መድኃኒት ያውቃሉ። ሆኖም መውሰድ ያለባቸው መድኃኒት እነሱ የፈለጉት ዓይነት ላይሆን ይችላል።

ሰዎች በሌሎች መንገዶችም ወጪያቸውን ለመቀነስ ይሞክራሉ። አንድ ሐኪም የላቦራቶሪ ምርመራ ካደረገ በኋላ የተወሰኑ መድኃኒቶችን ያዝላቸዋል። በሽተኛው የሐኪሙን ትእዛዝ ይዞ ወደ መድኃኒት ቤት ሲሄድ መድኃኒቱ በጣም ውድ መሆኑን ይገነዘባል። ስለዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ገንዘብ ከመፈለግ ይልቅ ርካሽ መድኃኒት ይገዛሉ ወይም ከታዘዙላቸው መድኃኒቶች ውስጥ በከፊል ብቻ ይገዛሉ።

በእርግጥ መድኃኒት ያስፈልግሃልን?

መድኃኒት በእርግጥ የሚያስፈልግህ ከሆነ ስለምትወስደው መድኃኒት ለማወቅ ሞክር። ሐኪሙን ወይም ፋርማሲስቱን ስለታዘዘልህ መድኃኒት አንዳንድ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ አትፈር። የማወቅ መብት አለህ። ደግሞም እኮ ሊጎዳ የሚችለው የአንተ አካል ነው።

የታዘዘልህን መድኃኒት በትክክል ካልተጠቀምክበት ላይሻልህ ይችላል። በአንድ ጊዜ ምን ያህል ኪኒን መውሰድ እንዳለብህ፣ መቼ እንደምትወስደውና ለምን ያህል ጊዜ መውሰድ እንዳለብህ ማወቅ ያስፈልግሃል። በተጨማሪም መድኃኒቱን በምትወስድበት ወቅት ከየትኞቹ ምግቦች፣ መጠጦችና ሌሎች መድኃኒቶች መቆጠብ እንዳለብህ ወይም የትኞቹን እንቅስቃሴዎች ማድረግ እንደሌለብህ ማወቅ ያስፈልግሃል። ከዚህም በላይ መድኃኒቱ በአካልህ ላይ ሊያስከትል የሚችላቸውን ችግሮችና እነዚህ ችግሮች ሲከሰቱ ምን ማድረግ እንዳለብህ ማወቅ ያስፈልግሃል።

በተጨማሪም መድኃኒቶች ለሁሉም የጤንነት ችግሮች መፍትሔ እንደማያስገኙ አትርሳ። መድኃኒት ፈጽሞ ላያስፈልግህ ይችላል። ዎርልድ ሄልዝ የተባለው የዓለም የጤና ድርጅት እያሳተመ የሚያወጣው መጽሔት እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “መድኃኒት ሲያስፈልግህ ብቻ ውሰድ። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው እረፍት ማድረጉ፣ ጥሩ ምግብ መመገቡና ብዙ ውኃ መጠጣቱ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል።”

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“አንድ ሺህ በሽታዎች አንድ ሺህ ፈውሶች ያስፈልጋቸዋል” ሲል አንድ ሮማዊ ባለቅኔ ከ2,000 ዓመታት በፊት ጽፏል። በዛሬው ጊዜ ቢኖር ኖሮ ባለቅኔው ‘አንድ ሺህ በሽታዎች አንድ ሺህ ኪኒኖች ያስፈልጋቸዋል’ ብሎ ሊጽፍ ይችል ነበር! በእርግጥም ለእያንዳንዱ በውን የተከሰተም ሆነ በምናብ ለተፈጠረ በሽታ አንድ ኪኒን ያለ ይመስላል። የዓለም ባንክ እንዳለው ከሆነ በመላው ዓለም ከ5,000 በላይ ከሆኑ መድኃኒትነት ካላቸው ንጥረ ነገሮች የሚቀመሙ 100,000 የሚያህሉ የተለያዩ የመድኃኒት ዓይነቶች አሉ።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አስተዋይነት የተሞላበት የመድኃኒት አጠቃቀም

1. ጊዜ ያለፈባቸውን መድኃኒቶች አትውሰድ።

2. ጥሩ ስም ካተረፈ መድኃኒት ቤት ግዛ። መንገድ ላይ ከሚቸረችሩ ሰዎች አትግዛ።

3. መመሪያዎቹን በትክክል መረዳትህንና መከተልህን አረጋግጥ።

4. ለሌላ ሰው የታዘዙ መድኃኒቶችን አትውሰድ።

5. መርፌ መወጋት አለብኝ አትበል። ብዙውን ጊዜ በአፍ የሚወሰዱ መድኃኒቶችም ተመሳሳይ ውጤት ያስገኛሉ።

6. መድኃኒቶችን ልጆች በማይደርሱበት ቀዝቃዛ ቦታ አስቀምጣቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ