የቤተሰብን ብዛት መወሰን ያለበት ማን ነው?
በብራዚል የሚገኝ የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ከተወለደ ሦስት ቀን ብቻ የሆነው ሕፃን በፌስታል ተከቶ በባቡር ጣቢያ ተጥሎ ተገኝቷል። ያም ሆኖ በርካታ ቤተሰቦች ሕፃኑን ለማሳደግ ጥያቄ ማቅረባቸውን አንድ የብራዚል ጋዜጣ ዘግቧል።
ምንም እንኳ ልክ ይህን የሚመስል ነገር ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ባይሆንም የማይፈለጉና ተጥለው የሚገኙ ሕፃናት ቁጥር በመላው ዓለም እያደገ መጥቷል። የወላጅነትን ኃላፊነት የመቀበል ፍላጎት እየጠፋ ነው። መፍትሔው የወሊድ ቁጥጥር ማድረግ ነውን? የቤተሰብን ብዛት አቅዶ መመጠን ስሕተት ነውን?
በዓለም ዙሪያ 50 በመቶ የሚያክሉት እርግዝናዎች ያለ እቅድ የሚመጡ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ብዙው እርግዝና ያልታቀደ ብቻ ሳይሆን የማይፈለግም ነው።
ብዙ ሰዎች በጤንነት፣ በመኖሪያ ቤት ወይም ከሥራ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት እርግዝናን ለመከላከል ይፈልጋሉ። ስለዚህ እንደ ክኒን ወይም ኮንዶም የመሳሰሉ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን መጠቀም በጣም የተለመደ ነገር ሆኗል። ውርጃና የመውለድ ችሎታን ማምከንም የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ተደርገው ይሠራባቸዋል። ኦ ኤስታዶ ደ ሳን ፓውሎ የተባለ አንድ የብራዚል ጋዜጣ ውርጃን አስመልክቶ “በብራዚል ውስጥ በያመቱ ከሚያረግዙት 13 ሚልዮን ሴቶች መካከል 5 ሚልዮን የሚያክሉት በምስጢር እንደሚያስወርዱ የዓለም ጤና ድርጅት ይገምታል” ሲል አትቷል። ከዚህም በተጨማሪ ታይም የተባለ መጽሔት ከትዳር ጓደኛ ጋር ከሚኖሩት ለአካለ መጠን የደረሱ የብራዚል ሴቶች መካከል 71 በመቶዎቹ የወሊድ ቁጥጥር ያደርጋሉ። ከእነዚህ ውስጥ 41 ከመቶ የሚሆኑት በክኒን ሲጠቀሙ፣ 44 ከመቶዎቹ ደግሞ የመውለድ ችሎታን የማምከን ዘዴ ይጠቀማሉ።
በተደረገው ጥናት መሠረት 75 ከመቶ የሚሆኑት ብራዚላውያን መጥኖ መውለድ አስፈላጊ ነው ይላሉ። ሌሎች ግን ከተወሰነው ዕድል ማምለጥ አይቻልም ብለው ስለሚያምኑ ወይም አንድ ቤተሰብ አምላክ የሰጠውን ያህል ብዙ ልጆች ማፍራቱ የእርሱ ፈቃድ ነው ብለው ስለሚያስቡ የቤተሰብን ምጣኔ ይቃወማሉ። ታዲያ የቤተሰቡን ብዛት መወሰን ያለበት ማን ነው? ባልና ሚስት ናቸው ወይስ የመንግሥትና የሃይማኖት ፍላጎት በጉዳዩ ውስጥ መግባት አለበት?
የወሊድ ቁጥጥር ለምን ያወዛግባል?
ትልቋ የብራዚል ሃይማኖት ማለትም የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቀን በመቁጠር የሚደረገውን የወሊድ ቁጥጥር ስትፈቅድ ውርጃንና ሌሎችን ዘዴዎች በሙሉ ትቃወማለች። ጳጳስ ጳውሎስ 6ኛ “ማንኛውም ግብረ ሥጋ ሕይወትን እንዳያስተላልፍ የሚያግደው ነገር መኖር የለበትም” ብለው ነበር። ጳጳስ ዮሐንስ ዳግማዊም “የወሊድ ቁጥጥር፣ ባልተዛባ ዓይን ስንመለከተው ምንም ዓይነት ምክንያት ቢቀርብ፣ በምንም መንገድ ትክክል ሊሆን አይችልም” ብለዋል። በዚህ ምክንያት ብዙ ካቶሊኮች የወሊድ ቁጥጥርን እንደ ኃጢአት አድርገው ስለሚመለከቱ የቤተሰባቸውን ብዛት ለመወሰን ያመነታሉ።
በሌላው በኩል ደግሞ ላንሴት የተባለው የሕክምና ጋዜጣ እንዲህ ብሏል:- “በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመማር ሳይታደሉ፣ ሥራ ሳያገኙ፣ በደሳሳ ቤት ተቆራምደው፣ በጣም መሠረታዊ የሆነ የጤና፣ የጽዳትና የበጎ አድራጎት አገልግሎት ሳያገኙ ሕይወታቸው ታልፋለች። ለዚህ አንዱ ዐቢይ ምክንያት የሕዝብ ቁጥር ያለ ገደብ መጨመሩ ነው።” ስለሆነም አንዳንድ መንግሥታት በሕዝብ ብዛት መጥለቅለቅንና ድህነትን በመስጋት የቤተ ክርስቲያንን ተቃውሞ ወደኋላ ትተው በእቅድ መጥኖ መውለድን ያበረታታሉ። ለምሳሌ ያህል “ኮስታሪካ [በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ] የልጆችን አማካይ ብዛት ከ7 ወደ 3 ዝቅ እንዲል አድርጋለች” በማለት የሥነ ሕይወት ምሁር ፖል ኧህርሲሽ ተናግረዋል።
የሕይወት እውነታዎች፤ ለማስረዳት ያለው ችግር (Facts for Life— A Communication Challenge) የተባለ በተባበሩት መንግሥታት የሚታተም ጽሑፍ የሚከተለውን ብሏል:- “አንዲት ሴት 4 ልጆች ከወለደች በኋላ ብታረግዝ ለእርሷም ሆነ ለሕፃኑ ሕይወትና ጤንነት አደገኛ ነው። በተለይ ፊተኞቹ እርግዝናዎች ከሁለት ዓመት በላይ ካልተራራቁ የአንዲት ሴት አካል በእርግዝና፣ በወሊድ፣ በማጥባትና ትንንሽ ሕፃናትን በማሳደግ ድግግሞሽ ሊዝል ይችላል።”
በለጋነታቸው የሚቀጩት ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች፣ በተለይ በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ የገጠር አካባቢዎች፣ ብዙ ልጅ መውለድ ዛሬም የተለመደ ነገር ነው። ለምን? ብዙዎቹ ስለ ወሊድ ቁጥጥር ዘዴዎች ምንም ስለማያውቁ ነው። በሌሎች አካባቢዎች ግን አንዱ የችግሩ ምክንያት አንድ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል እንደተናገሩት ነው:- “አንድ ወንድ ራሱን በትክክል ወንድ እንደሆነ አድርጎ የሚያስበው ሚስቱ በያመቱ ካረገዘችለት ነው።” ዦርናል ዳ ታርድ በሴቶች በኩል ያለውን ሌላውን ችግር ሲገልጽ “ልጅ መውለድ ለአንዲት ሴት ደስታ ከሚያመጡላት በጣም ብርቅ ነገሮች አንዱ ሲሆን ሕይወቷ እንደተሳካላት አድርጋ ታስባለች” ብሏል። ከዚህም ሌላ የቀድሞው የብራዚል የአካባቢ ሚኒስትር ፓውሎ ኖጋር ኔቶ እንደተናገሩት “ለድሃው ሕዝብ ልጅ መውለድ ማለት የችግር ጊዜ አለኝታ ማግኘት ማለት ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የአምላክ ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ብዛት መመጠንን በተመለከተ ውሳኔውን ለባልና ሚስቱ እንደተወው ታውቅ ነበርን? ከዚህም ሌላ ልጅ ለመውለድ አስቦም ይሁን ክብር ባለው ሩካቤ ሥጋ አማካኝነት ፍቅር ለመገላለጽ በማሰብ የሚደረገው ጋብቻ ምንም ስሕተት እንደሌለው ያስረዳል።— 1 ቆሮንቶስ 7:3-5፤ ዕብራውያን 13:4
ግን፣ አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ ሳሉ አምላክ “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም መሉአት” ብሏቸው አልነበረምን? (ዘፍጥረት 1:28) አዎን፣ ብሏቸው ነበር፤ ቢሆንም ያ ትእዛዝ ዛሬም የሚሠራ መሆኑን የሚጠቁም ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም። ሪካርዶ ሊስካኖ የተባሉ ጸሐፊ እንደገለጹት “የፕላኔታችን ብቸኛ ኗሪዎች ለነበሩት ሁለት ሰዎች የተሰጠውን ትእዛዝ ዛሬ ባሉት [በቢልዮን በሚቆጠሩ] ሰዎች ላይ እንዲሠራ ማድረግ እርስ በርሱ የሚቃረን ሐሳብ ይመስላል።” ባልና ሚስቱ ምንም ልጅ ላለመውለድ ቢወስኑም ይህ መብታቸው ሊከበርላቸው የሚገባ የግል ምርጫቸው ነው።
ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ የይሖዋ ምሥክሮች አቋም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተገንዝቧል። እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “የባልና ሚስቱ ውሳኔ ነው ብለው ከሚተዉት የወሊድ ቁጥጥር በቀር በሩካቤ ሥጋና በጾታ ላይ ያላቸው አቋም በጣም ድርቅ ያለ ነው።” በማከልም “መጽሐፍ ቅዱስን ብቸኛው የእምነታቸው መሠረትና የሥነ ምግባር መመሪያ አድርገው ይመለከቱታል” ብሏል።
የቤተሰብን ብዛት ለመወሰን የሚሠራባቸው ዘዴዎች ሁሉ ትክክል ናቸው ማለት ነውን? አይደለም። አምላክ ለእሥራኤል የሰጠው ሕግ አንድ ወንድ አንዲትን ሴት እንድትጨነግፍ የሚያደርግ ጉዳት ቢያደርስባት ነፍሰ ገዳይ ነው ብሎ ደንግጎ ነበር። (ዘጸአት 20:13፤ 21:22, 23) በሕክምና አማካኝነት የመውለድ ችሎታን ማምከንን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀጥታ የተሰጠ ትእዛዝ ስለሌለ ይህ ግለሰቡ በሕሊናው ተመርቶ የሚወስነው ጉዳይ ነው። “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና።” (ገላትያ 6:5)a በርካታ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ስላሉ አንድ ባልና ሚስት በየትኛው እንደሚጠቀሙ ለመወሰን ሐኪሞችን ማማከር ይችላሉ።
የሚያዋጣችሁን ውሳኔ አድርጉ
በሕይወት ውስጥ እያንዳንዱ ነገር በእቅድ የሚመጣ አይደለም። ይሁን እንጂ ግራና ቀኙን በጥሞና ሳትመለከት መኪና ወይም ቤት ትገዛለህን? መኪናና ቤት መልሶ መሸጥ ይቻላል፤ ልጆችን ግን መመለስ አይቻልም። እንግዲያው ባልና ሚስት ልጅ ለመውለድ የሚያቅዱ ከሆነ ለሕይወት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማቅረብ የመቻላቸውን ጉዳይ ሊያስቡበት አይገባም?
ቤተሰባችን በምግብ እንዲቸገር ወይም በሌሎች ላይ ሸክም ለመሆን እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ልጆች ከምግብና ከመጠለያ በተጨማሪ ትምህርት ቤት መግባት፣ የሥነ ምግባር መመሪያና ፍቅር ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።
ልጅ መውለድ የሚጠይቀው ሥራ፣ ገንዘብና ትዕግሥት ብቻ ሳይሆን የሚስቲቱ ጤንነትም ሊታሰብበት ይገባል። እርግዝናን ማራራቅ ከሕልፈተ ሕይወት ያድናል፤ ለመልካም ጤንነትም ይረዳል። የሕይወት እውነታዎች (Facts for Life) የተባለው ጽሑፍ እንዲህ ብሏል:- “በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት በእናቲቱም ይሁን በሕፃኑ ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን አደጋዎች መቀነስ ከሚቻልባቸው በጣም ውጤታማ መንገዶች አንዱ አራርቆ ለመውለድ ማቀድ ነው። የወላዷ ዕድሜ ከ18 በታች ወይም ከ35 ዓመት በላይ ከሆነ ወይም ከዚህ በፊት አራት ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ አርግዛ ከነበረና በመካከሉ ያለው ርቀት ከሁለት ዓመት በታች ከሆነ ወሊድ ብዙ አደጋዎች አሉት።”
ልጅ ለመውለድ እያሰቡ ያሉ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው በዙሪያችን ያለው ዓለም በወንጀል፣ በራብ፣ በጦርነትና በማያስተማምን የኢኮኖሚ ሁኔታ የተሞላ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም። (ማቴዎስ 24:3-12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13፤ ራእይ 6:5, 6) ወላጆች ለልጆቻቸው ያላቸው እውነተኛ ፍቅር ስለምንኖርበት ዓለም ተጨባጩን ሁኔታ ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ያስገድዳቸዋል፤ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ልጅ ማሳደግ ከባድ ትግል እንደሚጠይቅ ይገነዘባሉ። ስለሆነም ሁሉም ነገር ትክክል ይመጣል ብለው ተስፋ በማድረግ በዘፈቀደ ከመውለድ ይልቅ ብዙዎቹ ወላጆች ልጆቻቸው የሚቻለውን ያህል ደስታና የኑሮ ዋስትና እንዲኖራቸው ሲሉ መጥኖ መውለድን ይመርጣሉ።
የአምላክ ቃል ቤተሰብን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጥበባዊ ውሳኔ እንድናደርግ ከመርዳቱም ሌላ ስለወደፊቱ ጊዜ ጠንካራ መሠረት ያለው ተስፋ ይሰጠናል። የሰው ልጆች ገነት በምትሆን ምድር ላይ ለዘላለም በሰላምና በደስታ ይኖሩ ዘንድ የፈጣሪያችን ዓላማ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። አምላክ ይህን ዓላማውን እውን ለማድረግ በቅርቡ ያሁኑን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ያጠፋል። ከዚያ በኋላ ድህነትና በሕዝብ ብዛት መጨናነቅ የማይኖርበት ጻድቅና አዲስ የሆነ ዓለም ሲመጣ የማይፈለጉ ልጆች ተጣሉ የሚባል ነገር ፈጽሞ የማይሰማ ይሆናል።— ኢሳይያስ 45:18፤ 65:17, 20-25፤ ማቴዎስ 6:9, 10
እንግዲያው አንድ ባልና ሚስት እርስ በርስ መተሳሰባቸውና ስለ ልጆቻቸው ደኅንነት የሚጨነቁ መሆናቸው እንዲሁም ስለ ወሊድ ትክክለኛ አመለካከት መያዛቸው የቤተሰባቸውን ብዛት ለመመጠን እንዲወስኑ ያደርጋቸዋል። ባወጣ ያውጣው በማለት ፈንታ በጸሎት አምላክ እንዲመራቸው ይጠይቁታል። “የእግዚአብሔር በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ ኀዘንንም ከእርሷ ጋር አይጨምርም።”— ምሳሌ 10:22
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ግንቦት 1, 1985 የወጣውን የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31 ተመልከት።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት ይጣላሉ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሕፃናት ፍቅራዊ እንክብካቤ ያሻቸዋል