የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g97 1/8 ገጽ 15-18
  • አካለ ደካማ፣ ጠንካራ ተጓዥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አካለ ደካማ፣ ጠንካራ ተጓዥ
  • ንቁ!—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በቀላሉ የሚቀነጠስ አካል ያላት ውብ ፍጥረት
  • አስደናቂ በረራዎች
  • በብዛት ሆነው የሚያደርጉት ጉዞ
  • መድረሻቸው
  • የሞናርክ ቢራቢሮ ፍልሰት
    ንድፍ አውጪ አለው?
  • ቢራቢሮ የሚጓዝበትን አቅጣጫ የሚያውቅበት ዘዴ
    ንቁ!—2008
  • የአንድ ቀን ውሎ በቢራቢሮ ሕይወት ውስጥ
    ንቁ!—1994
  • በቀለማት ያሸበረቀች እመቤት—ሚስጥሩ ተገለጠ
    ንቁ!—2013
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1997
g97 1/8 ገጽ 15-18

አካለ ደካማ፣ ጠንካራ ተጓዥ

ሠዓሊዎች ይስሏቸዋል፤ ገጣሚዎችም ስለ እነርሱ ይደርሳሉ። ዝናብ በሚበዛባቸው የሐሩር አካባቢዎች ዓይነታቸው የተለያየ ነው። ብዙዎች በጫካ፣ በሜዳ፣ ረጃጅም ሣር በሚበቅልባቸው ሜዳዎች ይገኛሉ። አንዳንዶች በተራራ ጫፍ ላይ ያለውን ብርድ ወይም የምድረ በዳን ሙቀት ተቋቁመው ይኖራሉ። ከበራሪ ነፍሳት ሁሉ በውበታቸው እጅግ ማራኪ ከሆኑት መካከል ተመድበዋል።

ካናዳ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ይህችን በጣም ደስ የሚል ውበት ያላትን ፍጥረት፣ ቢራቢሮን፣ አይተህ እንደምታውቅ አያጠራጥርም። በተለይ ግን አንዷ የቢራቢሮ ዝርያ በአስደናቂ የበረራ ችሎታዋ ምክንያት በዓለም ዙሪያ ዝናን አትርፋለች። ይህች አካለ ደካማ ነገር ግን ጠንካራ ተጓዥ የሆነችው ቢራቢሮ ሞናርክ (የሁሉ የበላይ ንግሥት) የሚል ስም ወጥቶላታል። እስቲ ውብ ፍጥረት የሆነችውን ይህችን ቢራቢሮና ከቦታ ቦታ የምታደርገውን እጅግ አስገራሚ የሆነ ጉዞ ጠጋ ብለን እንመርምር።

በቀላሉ የሚቀነጠስ አካል ያላት ውብ ፍጥረት

ሞቃታማ በሆነ ብሩህ ቀን በሣር በተሸፈነ ለጥ ያለ ሜዳ ላይ እንዳለህ አድርገህ አስብ። በሜዳ አበቦች መካከል ውር ውር እያሉ ያለ ማቋረጥ ምግብና መጠጥ የሚፈልጉትን ባለ ክንፍ አስደናቂ ፍጥረታት ልብ ብለህ ተመልከት። እጆችህን ዘርግተህ ምንም ሳትንቀሳቀስ ቁም። አንዷ ጠጋ ትላለች። ያስደንቃል፣ እጅህ ላይ ልታርፍ ነው። ምንም ሳይሰማህ ቁጭ እንደምትል አስተውል።

አሁን ጠጋ ብለህ ተመልከታት። ግራና ቀኝ ሁለት ሁለት ሆነው የተዘረጉትን፣ ብናኝ ነገር የተሸፈኑ፣ በቀላሉ ሊበጠሱ የሚችሉ፣ ጠቃጠቆ ያለበት ብርቱካንማ ቀለም ያላቸው እንዲሁም ዙሪያውን ግሩም ዲዛይን የተነደፈባቸውን ክንፎች ተመልከት። ለእነዚህ ቢራቢሮዎች ሞናርክ የሚል ስም ያወጡት ወደ አሜሪካ የፈለሱት እንግሊዛውያን ሰፋሪዎች እንደሆኑ ይነገራል። ለቢራቢሮዋ ይህን ስም ያወጡት ዊልያም ኦቭ ኦሬንጅ የተባለ ንጉሠ ነገሥታቸውን ለማስታወስ ነው። እውነትም ይህች ቢራቢሮ ‘የሁሉም የበላይ የሆነች ንግሥት’ ናት። ይሁንና ይህች ግማሽ ግራም ብቻ የምትመዝንና ከዳር እስከ ዳር ከ8-10 ሴንቲ ሜትር ያህል የሚረዝሙ ክንፎች ያሏት አካለ ደካማ ውብ ፍጥረት ረጅምና አስቸጋሪ ጉዞ ማድረግ ትችላለች።

አስደናቂ በረራዎች

የክረምት ወራት ሊገባ ሲል ይበልጥ ሩቅ ወደሆነ ስፍራ መጓዝ የሚችሉ ሌሎች የቢራቢሮ ዝርያዎች ቢኖሩም ወደ ታወቀ አድራሻ ምንም ሳይሳሳቱ፣ በከፍተኛ አጀብ ረጅም ጉዞ ማድረግ የሚችሉት ሞናርክ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቢራቢሮዎች ብቻ ናቸው። በእውነትም ሞናርኮች የሚያደርጉት ጉዞ እጅግ አስገራሚ ነው። እነዚህ ጠንካራ ተጓዦች የሚያከናውኗቸውን አንዳንድ አስደናቂ በረራዎች እንመልከት።

በአውሮፓውያን የበልግ ወራት (መስከረም—ኅዳር) ከካናዳ በመነሳት ቀዝቃዛውን የክረምት ወራት ወደሚያሳልፉበት ወደ ካሊፎርኒያ ወይም ሜክሲኮ የሚያደርጉት ጉዞ 3,200 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት አለው። ታላላቅ ሐይቆችን፣ ወንዞችን፣ ሰፋፊ ሜዳዎችንና ተራሮችን ያቋርጣሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ቢራቢሮዎች እስከ ጉዞው ፍጻሜ ድረስ ይኸውም በሜክሲኮ መሐል አገር እስካሉት ሴራ ማድሬ ተራሮች ይበራሉ።

ወጣቶቹ ቢራቢሮዎች ከዚህ በፊት ይህን የመሰለ ጉዞ ጨርሶ አለማድረጋቸው፣ በከፊል በድን ሆነው የሚያሳልፉበትንም ስፍራ አይተውት የማያውቁ መሆናቸው ይህን በረራ ይበልጥ አስደናቂ ያደርገዋል። ያም ሆኖ ግን አቅጣጫቸውን ምንም ሳይስቱ ይጓዛሉ፤ የክረምት ማሳለፊያ ቦታቸው ላይ ሲደርሱም ያውቁታል። እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ?

ካነዲያን ጂኦግራፊክ የተባለ መጽሔት እንዲህ ብሏል:- “በትንሿ ጭንቅላታቸው ውስጥ በተፈጥሮ የተቀረጸ በጣም ውስብስብ የሆነ ፕሮግራም እንዳለ ግልጽ ነው። ልክ እንደ ንብ የፀሐይ ብርሃን ምን ያህል እንዳጋደለ ማንበብ የሚችል፣ ወፎችን የሚመራቸው ዓይነት የመሬትን ማግኔቲክ ፊልድ መለየት የሚችል ነገር ሳይኖራቸው አይቀርም። ወደ ግባቸው ሲደርሱ ይህን እንዲያውቁ የሚረዳ ትክክለኛውን ሙቀትና እርጥበት ለመለየት የሚያስችላቸው ውስጣዊ መሣሪያ ሳይኖር አይቀርም። ይሁን እንጂ የጥያቄው መልስ ለሳይንስ እስከ ዛሬ ድረስ አልተጨበጠለትም።” በመጽሐፍ ቅዱሱ የምሳሌ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሱት ፍጥረታት ሁሉ ቢራቢሮዎችም “እጅግ ጠቢባን ናቸው።”— ምሳሌ 30:24

ሞናርኮች ልዩ የበረራ ችሎታም አላቸው። ክንፋቸውን ሳያውለበልቡ አየር ላይ እየተንሳፈፉ በሰዓት 12 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላሉ። ወደ ላይ ሲመጥቁም በሰዓት 18 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላሉ። ቢራቢሮ ለመያዝ የሞከረ ማንኛውም ሰው እንደሚያውቀውም ከዚያ በበለጠ ፍጥነት፣ ይኸውም በሰዓት 35 ኪሎ ሜትር ያህል ወዲያና ወዲህ ይሯሯጣሉ። ነፋሱንም በብልሃት ለጉዟቸው እንዲያግዛቸው ይጠቀሙበታል። ወደ ምሥራቅ የሚነፍስ ኃይለኛ ነፋስም ቢሆን በተወሰነ አንግል ተንጋደው በመብረር በደቡብ ምዕራብ ወደሚገኘው መድረሻቸው ይጓዛሉ። ነፋስ ፍጥነቱንና አቅጣጫውን በሚለዋውጥበት ጊዜ ልዩና ውስብስብ በሆነ ዘዴ ይቋቋሙታል። ሞተር አልባ የሆነች ትንሽ አውሮፕላን የሚያበር ሰው ወይም ጭልፊቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ ቢራቢሮዎቹም ሞቃት አየር ወዳለበት ወደ ላይ ይመጥቁና በአየር ውስጥ ክንፋቸውን ዘርግተው ሳያውለበልቡት ይጓዛሉ። አንድ ተመራማሪ በተናገሩት መሠረት ሞናርኮች በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 200 ኪሎ ሜትር ድረስ መሄድ ይችላሉ። የሚበሩት ቀን ብቻ ነው። ሌሊት ሲሆን ያርፋሉ፤ ብዙውን ጊዜም በያመቱ የሚያድሩባቸው ቦታዎች አንድ ናቸው።

የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስት፣ ዴቪድ ጊቦ ሞናርክ ቢራቢሮ አልፎ አልፎ ወደላይ በመምጠቅና አየር ላይ እየተንሳፈፈ በመጓዝ ብቻ የተወሰነ ያለመሆኑን ተመልክተዋል። “ወደ ሌላ ስፍራ እየፈለሱ ካሉ ዝዮች በተሻለ ሁኔታ ነፋሱን በልዩ ብልሃት እንዳሻቸው ይጠቀሙበታል” በማለት ተናግረዋል። ሞናርኮች ክንፋቸውን እያውለበለቡ፣ ወደላይ እየመጠቁና ምግብ እየበሉ የሚያደርጉት በረራ እስከ ሜክሲኮ አድርሶ ክረምቱን የሚያወጣና በጸደይ ወራት ወደ ሰሜን የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያስጀምር ኃይል ሰጪ ቅባት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ፕሮፌሰር ጊቦ ጨምረው ሲናገሩ “አካላቸውና ጤናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ረጅሙን ጉዞ ለማጠናቀቅ የሚረዳቸው ክንፋቸውን ሳያውለበልቡ፣ እንዲሁ ዘርግተውት ብቻ አየር ላይ እየተንሸራተቱ ለመጓዝ መቻላቸው ነው” ብለዋል።

በብዛት ሆነው የሚያደርጉት ጉዞ

ከሮኪ ተራሮች በስተ ምዕራብ የሚገኙት ሞናርኮች ወደ ደቡብ አቅጣጫ በመፍለስ ክረምቱን ካሊፎርኒያ ላይ እንደሚያሳልፉ ከታወቀ ረጅም ጊዜ ሆኖታል። በደቡባዊ የካሊፎርኒያ የባሕር ጠረፍ በጥዶችና ባሕር ዛፎች ላይ እጅብ ብለው ይሰፍራሉ። በካናዳ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኙት እጅግ ብዙ ቢራቢሮዎች ግን ወዴት እንደሚፈልሱ ለተወሰነ ጊዜ ምስጢር ሆኖ ቆይቶ ነበር።

በ1976 ምስጢሩ ታወቀ። የክረምት ማሳለፊያ ቦታቸው ሜክሲኮ በሚገኙት ሴራ ማድሬ ተራሮች ውስጥ በጫካ የተሸፈነ የአንድ ተራራ ጫፍ ሆኖ ተገኘ። በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ቢራቢሮዎች ረጃጅም በሆኑና ግራጫና አረንጓዴ ቀለም ባላቸው ከዓመት እስከ ዓመት በማይደርቁ ዛፎች ላይ በየቅርንጫፉና ግንዱ ላይ ተነባብረው እንደሚሰፍሩ ተደረሰበት። ይህ እጅግ አስደናቂ የሆነ ትርዒት ዛሬም ለጐብኚዎች ግሩም መስህብ ነው።

በካናዳ ውስጥ ሞናርክ ቢራቢሮዎችን አንድ ላይ እጅብ ብለው ማየት ከሚቻልባቸው ጥሩ ቦታዎች አንዱ በኦንታሪዮ ከተማ የሚገኘው ፖይንት ፔሌ ብሔራዊ ፓርክ ነው። ወደ ደቡብ ለሚያደርጉት ፍልሰት ዝግጅት እዚህ ቦታ ላይ እጅግ በጣም ብዙ ሆነው ይከማቻሉ። በጋው ሊገባደድ ሲል በዚህ በደቡባዊ ካናዳ በሚገኝ ቦታ፣ በኢሪ ሐይቅ ሰሜናዊ ዳርቻ ላይ ተሰባስበው ጉዞ የሚጀምሩበትን ጊዜ ይጠብቃሉ። ከዚያም የነፋሱና የሙቀቱ ሁኔታ ተስማሚ ሲሆን የክረምቱን ጊዜ ወደሚያሳልፉበት ወደ ሜክሲኮ ለመድረስ በደቡብ በኩል መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።

መድረሻቸው

ከፖይንት ፔሌ በመነሳት በኢሪ ሐይቅ ላይ በሰልፍ ከደሴት ወደ ደሴት እየተሻገሩ ዩናይትድ ስቴትስን ለማቋረጥ ረጅሙን ጉዞ ይያያዙታል። መንገድ ላይ ሌሎች የሞናርክ ቡድኖችን ያገኙና ከእነርሱ ጋር ተቀላቅለው ይጓዛሉ። በሜክሲኮ ሲቲ ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኙ ተራሮች ላይ በግምት አንድ መቶ ሚልዮን የሚሆኑ ቢራቢሮዎች አንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ክረምቱን ያሳልፋሉ።

ሌሎች ቡድኖች ደግሞ በፍሎሪዳና ካሪቢያን በኩል አቋርጠው በዩካታን ልሳነ ምድር ወይም በጓቴማላ ውስጥ ገና በውል ወዳልታወቀ መድረሻቸው ይጓዛሉ። ሞናርክ ቢራቢሮዎች በሜክሲኮም ይሁን በሌሎች መጠለያዎች ሲቆዩ ከቁጥራቸው አንፃር ሲታይ በጥቂት ጫካዎች ላይ አንድ ላይ እጅብ ብለው ይቀመጣሉ።

ረጅም ጉዞ አድርገው ክረምቱን ወደሚያሳልፉበት ስፍራ ሲደርሱ ሙቀትና ፀሐይ ወዳለበት የዕረፍት ቦታ እንደመጡ አድርገን እናስብ ይሆናል። ነገሩ እንደዚያ አይደለም። ቢራቢሮዎቹ የሚሄዱበት አያሌ እሳተ ጎሞራዎች የነበሩበት የተራሮች ሰንሰለት ቀዝቃዛ ነው። ሆኖም በተራሮቹ ጫፍ ላይ ያለው የአየር ንብረት ክረምቱን ለማሳለፍ በጣም ተስማሚ ነው። በሌላውም በኩል ቅዝቃዜው ኃይለኛ ስለሆነ ጊዜውን የበድን ያህል ሆነው እንዲያሳልፉ ያስገድዳቸዋል። በዚህ መንገድ ዕድሜያቸው ከስምንት እስከ አሥር ወራት ይራዘምላቸዋል። ይህም ወደ ሜክሲኮ ሄደው ክረምቱን እዚያው እንዲያሳልፉና ወደመጡበት ለመመለስ ጉዞ እንዲጀምሩ ያስችላቸዋል። የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ዓይነት ነው ለማለት ይቻላል።

ጸደይ ይገባል፤ ሞናርኮችም እንደገና መንቀሳቀስ ይጀምራሉ። ከሌሊቱ ይልቅ የቀኑ ርዝመት እየበለጠ ሲሄድ ቢራቢሮዎቹ በፀሐይ ብርሃን ላይ ክንፋቸውን ማውለብለብ ይጀምራሉ፣ ይራባሉ፣ ከዚያም ወደመጡበት ለመመለስ ሰሜናዊ ጉዞአቸውን ይጀምራሉ። አንዳንዶቹ ቢራቢሮዎች የደርሶ መልሱን ጉዞ አሟልተው ይፈጽማሉ ተብሎ ይታመናል። በአጠቃላይ ሲታይ ግን በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ክፍል ወደሚገኙት ተራሮች የሚደርሱት ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ብቻ ናቸው። ከዕንቁላል ወደ አባ ጨጓሬነት፣ ፒዩፓነትና ቢራቢሮነት የተለወጡ ሦስት ወይም አራት ትውልዶች ወደ ሰሜን አቅጣጫ ተጉዘው የመጀመሪያዎቹ ቢራቢሮዎች ወደተነሱበት ቦታ ይደርሳሉ። ሊፈለፈሉ የተዘጋጁ አንድ መቶ ወይም ከዚያ በላይ ዕንቁላሎች የተሸከመችው ሴቷ ቢራቢሮ ከቅጠሎች በታች ክንፎቿን በማራገብ ዕንቁላሎቿን አንድ በአንድ ታስቀምጣለች። ዑደቱ በዚሁ መንገድ ይቀጥልና ሞናርኮች በጋውን ወደሚያሳልፉበት ስፍራ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ።

በእውነቱ ሞናርክ የተባለችው ቢራቢሮ አስደናቂ ፍጥረት ናት። ሰዎች እንቅስቃሴዎቿን ለመከታተልና ለማጥናት እንዴት ግሩም አጋጣሚ አላቸው። ይሁንና ግን ለረጅም ጊዜ ምስጢር ሆኖ የነበረው ሜክሲኮ የሚገኘው የቢራቢሮዋ የክረምት ማሳለፊያም ሆነ ሌላው ከለላዋ የካሊፎርኒያ አካባቢ በሰብዓዊ የሥራ እንቅስቃሴዎች ሳቢያ ለብልሽት ተዳርጓል። እነዚህ አቅም የሌላቸው ውብ ፍጥረታት ወደ ሌላ ቦታ ሊሄዱ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ጨርሶ ወደ መጥፋት ሊያደርሳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ዕጣ እንዳይደርስባቸው ለመከላከል የሚያስመሰግኑ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ ናቸው። ፈጣሪያችን ምድር ወደ ገነትነት እንደምትለወጥ የገባልን ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ቅርብ ሲሆን በዚያን ጊዜ ይህች አቅም የሌላት ጠንካራ ተጓዥ አስተማማኝ መጠለያ የምታገኝ መሆኗ እንዴት ግሩም ነገር ነው!

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ቢራቢሮ:- Parks Canada/J. N. Flynn

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ገጽ 16 ላይኛውና ታችኛው ሥዕል:- Parks Canada/J. N. Flynn; የመካከለኛው ሥዕል:- Parks Canada/D. A. Wilkes; ገጽ 17 የላይኛው ሥዕል:- Parks Canada/J. N. Flynn; የመካከለኛውና የታችኛው ሥዕል:- Parks Canada/J. R. Graham

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ