ወጣቶች የሚጠይቋቸውጥያቄዎች . . .
አምላክ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ የፈቀደው ለምንድን ነው?
ቀደም ሲል ዩጎዝላቭያ ተብሎ ይጠራ በነበረው አገሯ ጦርነት ሲፈነዳ ሊድያ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ትገኝ ነበር። “ጨለማ በወረሰው መጠለያ ለበርካታ ቀኖችና ሌሊቶች ቆየሁ” በማለት ትናገራለች። “ውጭ ብወጣ እንደምገደል ባውቅም ሮጬ ለመውጣት የፈለግኩባቸው በርካታ ጊዜያት ነበሩ! ይህ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የፈለግነውን ነገር ሁሉ እናገኝ ነበር። አሁን ግን በሕይወት መኖራችን ብቻ እንደ ትልቅ ነገር ይቆጠራል።”
ጦርነቱ ባስከተለው ውጥረትና ጭንቀት ምክንያት የሊድያ መንፈሳዊነት መጎዳት ጀመረ። “ለበርካታ ሳምንታት ለስብከትም ሆነ ለስብሰባ መውጣት አልቻልንም ነበር። ይሖዋ ጨርሶ ትቶናል ብዬ አሰብኩ። ‘እንዲህ ባለው ጊዜ የማይረዳን ለምንድን ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቅ ነበር” ትላለች።
ጦርነት፣ ወንጀል፣ ዓመፅ፣ በሽታ፣ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች እንዲሁም እነዚህን የመሰሉ መጥፎ ነገሮች በወጣቶች ላይ እንኳን ሊደርሱ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉት አሳዛኝ ሁኔታዎች አንተን በግል የሚነኩ በሚሆኑበት ጊዜ ‘አምላክ እንደነዚህ ያሉ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ብለህ መጠየቅህ እንግዳ ነገር ሊሆን አይችልም።
የጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦችም ይህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ጠይቀው ነበር። ለምሳሌ ያህል ነቢዩ ዕንባቆም የአምላክ ሕዝቦች የወደቁበትን አሳዛኝ ሁኔታ ሲመለከት እንዲህ በማለት የተሰማውን መሪር ሐዘን ገልጿል:- “አቤቱ፣ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ስለ ግፍ ወደ አንተ እጮኻለሁ፣ አንተም አታድንም። በደልንስ ስለ ምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ?” (ዕንባቆም 1:2, 3) ዛሬም አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ጭንቀት ይሰማቸዋል።
አንዲት ወጣት ክርስቲያን አባትዋ ድንገት በመሞቱ ምክንያት እንዴት እንደተሰማት እንመልከት። እንዲህ ትላለች:- “የማደርገው ጠፍቶኝ መስኮት ከፍቼ በይሖዋ ላይ ጮህኩ። . . . ለደረሰብኝ ነገር ሁሉ ይሖዋን አማረርኩ። እንዴት እንዲህ ያለ ነገር ሊደርስ ይችላል? እንደ አባዬ ያለ አባት አይገኝም። በጣም አፍቃሪ ባል ነበር። አሁን ግን ይኸው ሞተ። ይሖዋ ግድ የለውም ማለት ነው?” እንዲህ ባለው ሁኔታ ግራ መጋባት፣ ቁጣና የስሜት መጎዳት ቢኖር እንደ እንግዳ ነገር ሊቆጠር አይችልም። ታማኙ ነቢይ ዕንባቆምም ክፋት እንዲቀጥል በመፈቀዱ ምክንያት ስሜቱ ተረብሾ እንደነበረ ትዝ ይበልህ። ይሁን እንጂ እንድ ሰው የምሬት ስሜቱን ቶሎ ብሎ ካላሸነፈ አደገኛ ሊሆንበት ይችላል። “በእግዚአብሔር ላይ ሊቆጣ” ይችላል።— ምሳሌ 19:3
ታዲያ ለቁጣና ለምሬት ከመሸነፍ ልትጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ መጥፎ ነገሮች የሚመጡት ከማን እንደሆነ ማስተዋል ይኖርብሃል።
መጥፎ ነገሮች የሚመጡት ከአምላክ አይደለም
አምላክ መጀመሪያውንም ቢሆን መከራ እንዲደርስብን ዓላማው እንዳልነበረ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያመለክታል። የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ያኖረው ምንም ዓይነት መከራና ሥቃይ በሌለበት ገነት ውስጥ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28) ነገሮች እንዴት እንደተበላሹ እንደምታውቅ የተረጋገጠ ነው። በኋላ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚል ስያሜ ያተረፈ አንድ የማይታይ መንፈሳዊ ፍጡር አዳምና ሔዋን የአምላክን ትዕዛዝ እንዲጥሱ አደረገ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 3፤ ራእይ 12:9) አዳም እንዲህ በማድረጉ ልጆቹ በሙሉ የኃጢአትና በኃጢአት ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶች ኩነኔ ደረሰባቸው።— ሮሜ 5:12
በሰው ልጆች ላይ መጥፎ ነገሮች እንዲደርሱ ያደረገው ሰው ራሱ እንጂ አምላክ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (ዘዳግም 32:5፤ መክብብ 7:29) በእርግጥም በአሁኑ ጊዜ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱት መከራዎች በሙሉ ማለትም በሽታ፣ ሞት፣ ጦርነትና የፍትሕ መጓደል አዳም ሆን ብሎ የአምላክን ትዕዛዝ በማፍረሱ ምክንያት የመጡ ናቸው። ከዚህም በላይ ሁላችንም “ጊዜና አጋጣሚ” ለሚያመጧቸው ነገሮች የተጋለጥን ነን። (መክብብ 9:11 NW) ያልታሰቡ አደጋዎችና አሳዛኝ ሁኔታዎች በክፉዎችም በጻድቃንም ላይ ይደርሳሉ።
አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበት ምክንያት
የክፋት ምንጭ አምላክ አለመሆኑን ማወቅ የሚያጽናና ቢሆንም ‘ክፋት እስካሁን ድረስ እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ብለህ መጠየቅህ አይቀርም። የዚህን መልስ ለማግኘት በኤደን ወደተነሳው አከራካሪ ሁኔታ መመለስ ያስፈልገናል። አምላክ፣ አዳም ትዕዛዙን ካልጠበቀ እንደሚሞት ነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) ዲያብሎስ ደግሞ ሔዋን ከተከለከለው ዛፍ ብትበላ እንደማትሞት ነግሯታል። (ዘፍጥረት 3:1-5) ሰይጣን እንዲህ ሲል አምላክን ውሸታም ነው ማለቱ ነበር። ከዚህም በላይ ሰይጣን፣ ሰው አምላክ ያዘዘውን ከማድረግ ይልቅ ራሱ የፈለገውን ቢያደርግ የተሻለ ኑሮ እንደሚኖር የሚጠቁም ነገር ተናግሯል!
አምላክ እነዚህን ክሶች ችላ ብሎ ማለፍ አይችልም። አንድ የክፍል ጓደኛህ የአስተማሪህን ሥልጣን ሲገዳደር ተመልክተህ ታውቃለህ? አስተማሪው የዲስፕሊን እርምጃ ባይወስድበት ሌሎቹ ተማሪዎች እንደርሱ ማድረግ ይጀምራሉ። በተመሳሳይ መንገድ ይሖዋም ለሰይጣን ግድድር ፊት ለፊት ምላሽ ባይሰጥ ኖሮ በመላው ጽንፈ ዓለም ሁከት ይነግሥ ነበር። ይሖዋ ለሰይጣን ግድድር ምላሽ የሰጠው የሰው ልጅ የሰይጣንን መንገድ እንዲከተል በመፍቀድ ነው። ታዲያ የሰው ልጅ ሰይጣን እንዳለው እንደ አምላክ ያለ ነጻነት አግኝቷልን? በፍጹም አላገኘም። የሰይጣን አገዛዝ ከፍተኛ ጥፋትና ሐዘን አስከትሏል። በዚህም ሰይጣን የለየለት ቀጣፊ መሆኑ ተረጋግጧል!
ታዲያ አምላክ ክፋት ለዘላለም እንዲቀጥል ይፈቅዳል? በፍጹም አይፈቅድም። አምላክ ሰይጣን ያነሳውን ክርክር እልባት ላይ ለማድረስ ሲል በቅርቡ ክፋትን በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል። (መዝሙር 37:10) ይህ እስከሚሆን ግን የሚደርሱብንን መጥፎ ሁኔታዎች እንዴት መቋቋም እንችላለን?
አንተንም ጭምር የሚመለከት ጥያቄ
በመጀመሪያ ደረጃ ይህ በአምላክና በሰይጣን መካከል የተነሳው ክርክር አንተንም የሚመለከት መሆኑን ተገንዘብ! እንዴት? በጻድቁ ኢዮብ ስም የተጠራውን መጽሐፍ ተመልከት። ኢዮብ በታማኝ አምላኪነቱ በአርዓያነት የሚጠቀስ እንደሆነ አምላክ በተናገረ ጊዜ “ኢዮብ ጥቅም ባያገኝ ኖሮ የሚያመልክህ ይመስልሃል?” ሲል መልሶለታል። (ኢዮብ 1:9፤ ቱደይ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ሰይጣን ተጽእኖ እንዲያሳድር ቢፈቀድለት ማንንም ሰው አምላክን ከማገልገል ዞር ሊያደርግ እንደሚችል መከራከሩ ነበር!— ኢዮብ 2:4, 5
ሰይጣን በዚህም መንገድ ፈሪሐ አምላክ ያላቸውን ሰዎች ስም አጥፍቷል። ይሁን እንጂ ምሳሌ 27:11 “ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው። ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” ይላል። አዎን፣ የደረሰብህን ችግር በሙሉ ተቋቁመህ አምላክን ስታገለግል የሰይጣንን ውሸታምነት ለማረጋገጥ አንድ አስተዋጽኦ ታደርጋለህ።
መጥፎ ነገር ሲደርስብህ የተነሳውን ግድድር ለማሰብ ቀላል እንደማይሆን የታወቀ ነው። እናቷ በሞተችባት ጊዜ የአሥር ዓመት ልጅ የነበረችው ዳያን “በሕይወቴ ውስጥ የደረሱብኝ ፈተናዎች እንድማረር ወይም ልቤ እንዲደነድን ያደርጉ ይሆናል ብዬ ሰግቼ ነበር” ትላለች። ይሁን እንጂ አምላክ ክፋት እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያት ማወቋ ለችግሮቿ ጤናማ አመለካከት እንዲኖራት አስችሏታል። በአሁኑ ጊዜ “በሕይወቴ ውስጥ ለመቋቋም የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙኝም የይሖዋ እጅ ከእኔ አልራቀም ነበር” ትላለች።
ዳያን አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ቁም ነገር ታስታውሰናለች። ይሖዋ እነዚህን ችግሮች ለብቻችን እንድንሸከም አይጠብቅብንም። መዝሙር 55:22 የሚከተለውን ዋስትና ይሰጠናል:- “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።” ወጣቷ ኮቶዮ ይህ እውነት መሆኑን አረጋግጣለች። በ1995 በኮቤ ጃፓን በደረሰው የምድር መናወጥ ወላጆቿ ሞተውባት ነበር። ስለ ራስዋና ስለ ታናናሽ እህቶቿ ስትናገር “እናቴ በይሖዋ ላይ እንድንታመን አስተምራን ስለ ነበረ ችግራችንን ልንቋቋም እንችላለን” ብላለች።
በመግቢያችን ላይ የጠቀስናት ወጣቷ ሊድያስ? ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ፈጽሞ እንዳልተዋት ለመገንዘብ ቻለች። በአሁኑ ወቅት “ይሖዋ ምን ጊዜም ከእኛ አይለይም። አካሄዳችንን ይመራናል” ትላለች።
ይሖዋ የሚያስብልን አፍቃሪ አምላክ ነው
አንተም መጥፎ ነገር በሚደርስብህ ጊዜ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ትችላለህ። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ስለ አንተ ያስባል! በጥሩ ሰዎች ላይ መጥፎ ነገር እንዲደርስ ቢፈቅድም ፍቅራዊ ማጽናኛም ይሰጣቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ማጽናኛ ለመስጠት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ የክርስቲያን ጉባኤ ነው። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ችግር በሚያጋጥምህ ጊዜ የሚያበረቱህ ‘ከወንድም ይበልጥ የሚቀርቡ ወዳጆች’ ታገኛለህ። (ምሳሌ 18:24) ኮቶዮ እንዲህ ብላለች:- “የምድር መንቀጥቀጡ ከደረሰበት ማግስት ጀምሮ ወንድሞች ወደሚሰበሰቡበት ቦታ ሄድን። በዚያም ማበረታቻና የሚያስፈልጉንን ነገሮች አገኘን። አረጋጉን። ይሖዋና ወንድሞች ከጎናችን እስካሉ ድረስ ማንኛውንም ነገር መቋቋም እንችላለን።”
በተጨማሪም ይሖዋ የእያንዳንዳችን ሁኔታ ስለሚያውቅ መጥፎ ነገር በሚደርስብህ ጊዜ የሚያስፈልግህን ነገር ሊያሟላልህ ይችላል። ዳንኤል የአባቱን ሞት እንዴት ሊቋቋም እንደቻለ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ይሖዋ አባት ሆኖኛል። በድርጅቱ ውስጥ በአርዓያነት የሚታዩ መንፈሳዊ ሰዎች አሉ። ይሖዋ ሁልጊዜ ከአባቴ ጋር መወያየት ለሚኖርብኝ ጥያቄዎች መልስ እንዳገኝ ይረዳኝ ነበር።” ዳያንም በተመሳሳይ እናትዋ ከሞተች ጀምሮ የይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ እንዳልተለያት ስትገልጽ:- “ይሖዋ ማበረታቻ፣ አመራርና ምክር በሰጡኝ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ክርስቲያኖች አማካኝነት መርቶኛል እንዲሁም ያጋጠመኝን ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሙሉ እንዳሸንፍ ረድቶኛል” ብላለች።
እርግጥ መጥፎ ነገር መድረሱ አያስደስትም። ቢሆንም አምላክ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱ የሚፈቅድበትን ምክንያት ማወቅህ ሊያጽናናህ ይገባል። ሁልጊዜ አምላክ እነዚህን ነገሮች በቅርቡ እንደሚያስወግድ አስታውስ። እንዲያውም የደረሱብን መጥፎ ነገሮች በሙሉ አሻራቸው እንኳን እስከማይገኝ ድረስ ተጠራርገው ይጠፋሉ! (ኢሳይያስ 65:17፤ 1 ዮሐንስ 3:8) አምላክ ባዘጋጃቸው ዝግጅቶች በሙሉ እየተጠቀምክ የሚደርሱብህን ችግሮች ስትቋቋም የሰይጣንን ውሸታምነት በማረጋገጥ ረገድ የበኩልህን አስተዋጽኦ ታበረክታለህ። በቅርቡ አምላክ ‘እንባዎችን ሁሉ ከዐይኖችህ ያብሳል።’— ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በቅርቡ መጥፎ ነገሮችን በሙሉ ያስወግዳል