ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ኃጢአቴን መናዘዝ አለብኝን?
“በጣም ያሳፍረኛል፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም። ለወላጆቼ መናገር እፈልጋለሁ፤ ግን በጣም ያሳፍረኛል።”—ሊዛa
ይህን የጻፈችው የምታደርገው ጠፍቷት የተጨነቀች አንዲት ወጣት ናት። ይህች ወጣት አንድ የማያምን ሰው አፍቅራ በጓደኝነት ጥቂት ዓመታት ካሳለፈች በኋላ አንድ ቀን በአልኮል ግፊት የጾታ ብልግና ፈጸመች።
እንዲህ ዓይነቱ ነገር በክርስቲያን ወጣቶች ዘንድ ሳይቀር አልፎ አልፎ መከሰቱ የሚያሳዝን ነው። በዕድሜ ብዙም ያልበሰልንና ተሞክሮ የሌለን በሆንን መጠን ስህተት የመሥራት አጋጣሚያችንም የዚያኑ ያህል ሰፊ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም ጥቃቅን ስህተቶችን መሥራት አንድ ነገር ሆኖ ሳለ እንደ ጾታ ብልግና ያሉ ከባድ ኃጢአቶችን መሥራት ደግሞ ጨርሶ ሌላ ነገር ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ አንድ ወጣት እርዳታ ማግኘት ያስፈልገዋል። ችግሩ ግን የሠሩትን መጥፎ ነገር መናዘዝ ቀላል አይደለም።
አንዲት ክርስቲያን ወጣት ከጋብቻ በፊት የጾታ ብልግና ፈጸመች። የምትናገርበትን ቀን ሳይቀር በመመደብ የሠራችውን ኃጢአት በጉባኤዋ ለሚገኙ ሽማግሌዎች ለመናዘዝ ወሰነች። ሆኖም ቀኑን ለሌላ ጊዜ አራዘመችው። አሁንም እንደገና ለሌላ ጊዜ አራዘመችው። በዚህ ሁኔታ ሳይታሰብ አንድ ዓመት አለፈ!
“የተሰወረ የለም”
ከባድ ኃጢአት ሠርቶ ደብቆ ዝም ማለት በጣም መጥፎ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብሃል። አንደኛ ነገር ሐቁ በዚያም ሆነ በዚህ አንድ ቀን ገሀድ መውጣቱ አይቀርም። ማርክ ልጅ በነበረበት ጊዜ ከሸክላ የተሠራ አንድ የግድግዳ ጌጥ ሰበረ። “በጥንቃቄ እንደነበረ በሙጫ በማስቲሽ ላጣብቀው ሞክሬ ነበር፤ ግን ምን ያደርጋል ወላጆቼ የተሰነጣጠቀውን ወዲያው አዩት” በማለት ያስታውሳል። እርግጥ ነው አሁን አንተ ልጅ አይደለህም። ሆኖም ልጆች የሆነ ነገር ሲያጠፉ አብዛኞቹ ወላጆች ሊታወቃቸው ይችላል።
“ችግሬን በመዋሸት ለመሸፋፈን ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም ነገሮች ይበልጥ እንዲባባሱ ከማድረግ በቀር ያተረፍኩት ነገር የለም” በማለት የ15 ዓመቷ አን ሐቁን ተናግራለች። ውሸት ብዙውን ጊዜ መጋለጡ አይቀርም። ወላጆችህ እንደዋሸሃቸው ካወቁ ደግሞ የሠራኸውን ስህተት በቀጥታ ብትነግራቸው ከሚናደዱት ይበልጥ ሊናደዱ ይችላሉ።
ከሁሉም በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፣ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም” ይላል። (ሉቃስ 8:17) ይሖዋ የሠራነውንም ሆነ እየሠራን ያለነውን ያውቃል። አዳም እንኳ የሠራውን ኃጢአት መደበቅ አልቻለም። (ዘፍጥረት 3:8-11) የሠራኸው ኃጢአት ውሎ አድሮ በሌሎች ዘንድም ገሃድ ሊወጣ ይችላል።—1 ጢሞቴዎስ 5:24
ኃጢአትን ደብቆ ዝም ማለት ሌላም ጉዳት አለው። መዝሙራዊው ዳዊት “ሁልጊዜ ከመጮኼ የተነሣ ዝም ባልሁ ጊዜ አጥንቶቼ ተበላሹ፤ በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 32:3, 4) አንድን ነገር በምስጢር አምቆ መያዝ የሚያስከትለው ውጥረት ከፍተኛ የስሜት መታወክ ሊፈጥር ይችላል። ጭንቀትና የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሁም እጋለጣለሁ የሚል ፍርሃት ውስጥ ውስጥህን ሊያሰቃይህ ይችላል። ከጓደኛም ሆነ ከቤተሰብ ራስህን ማግለል ልትጀምር ትችላለህ። ከአምላክ ጋር ያለህ ግንኙነትም ጨርሶ እንደተቋረጠ ሊሰማህ ይችላል! አንድሩ የተባለ ወጣት “ይሖዋን ማሳዘኔ ካስከተለብኝ የሕሊና ወቀሳ ጋር ስታገል ነበር። ውስጥ ውስጤን ያሰቃየኝ ነበር” ሲል ጽፏል።
በድፍረት አውጥቶ መናገር
ከዚህ ዓይነቱ የስሜት መታወክ እፎይታ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ አለን? አዎን፣ አለ! መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “ኃጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፣ በደሌንም አልሸፈንሁም፤ . . . አንተም የልቤን ኃጢአት ተውህልኝ።” (መዝሙር 32:5፤ ከ1 ዮሐንስ 1:9 ጋር አወዳድር።) አንድሩ ልክ እንደ መዝሙራዊው ኃጢአቱን በመናዘዝ እፎይታ አግኝቷል። “በጸሎት ወደ ይሖዋ ቀርቤ ኃጢአቴን ይቅር እንዲልልኝ ከልብ ተማጸንኩት” ሲል ተናግሯል።
አንተም እንደዚህ ልታደርግ ትችላለህ። ወደ ይሖዋ ጸልይ። ይሖዋ ምን እንደሠራህ ያውቃል፤ ቢሆንም ግን የሠራኸውን ኃጢአት በጸሎት አማካኝነት በትሕትና ንገረው። እኔ ምንም ተስፋ የሌለኝ ክፉ ሰው ነኝ ብለህ ወደኋላ ሳትል ኃጢአትህን ይቅር እንዲልልህ ጠይቀው። ኢየሱስ የሞተው ፍጹማን ባንሆንም እንኳ በአምላክ ፊት ጥሩ አቋም መያዝ እንድንችል ሲል ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) በተጨማሪም አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ማድረግ የሚያስችል ብርታት ለማግኘት ልትለምን ትችላለህ። በተለይ ደግሞ መዝሙር 51ን ማንበብ በዚህ መንገድ ወደ አምላክ እንድትቀርብ ሊረዳህ ይችላል።
ለወላጆችህ መናገር
ሆኖም ኃጢአትን ለአምላክ ከመናዘዝ በተጨማሪ ሌላም የሚያስፈልግ ነገር አለ። ኃጢአትህን ለወላጆችህ የመናገር ግዴታ አለብህ። ወላጆችህ አንተን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” የማሳደግ ኃላፊነት አምላክ ሰጥቷቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ የአንተን ችግር ካወቁ ብቻ ነው። ለወላጆችህ መናገርም ቢሆን አስቸጋሪ ወይም የማያስደስት ሊሆን ይችላል። ሆኖም ገና ሲሰሙ ነው እንጂ ከዚያ በኋላ ስሜታቸውን መቆጣጠራቸው አይቀርም። እንዲያውም ችግርህን ግልጽ አድርገህ በመንገር በእነሱ ላይ በጣም እንደምትመካ በማሳየትህ ሊደሰቱ ይችላሉ። ኢየሱስ ስለ ኮብላዩ ልጅ የተናገረው ምሳሌ የጾታ ብልግና ስለፈጸመ አንድ ወጣት ይገልጻል። ያም ሆኖ ግን ይህ ወጣት ኃጢአቱን በመናዘዝ በተመለሰ ጊዜ አባቱ በደስታ እጁን ዘርግቶ ተቀብሎታል! (ሉቃስ 15:11-24) አንተንም ቢሆን ወላጆች እንደሚረዱህ ምንም ጥርጥር የለውም። ደግሞም እኮ ወላጆችህ አሁንም ቢሆን ይወዱሃል።
ወላጆቼን አናድዳቸዋለሁ ብለህ መፍራትህ አይቀርም። ሆኖም ወላጆችህን የሚያናድዳቸው ኃጢአትህን መናዘዝህ ሳይሆን ኃጢአቱን መሥራትህ ነው! ኃጢአትህን መናዘዝህ ደግሞ ንዴታቸው እንዲበርድ የሚያደርግ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው አን ለወላጆቿ በመናገር ትልቅ እፎይታ አግኝታለች።b
ኃጢአትህን እንዳትናዘዝ እንቅፋት የሚሆንብህ ሌላው ነገር ሐፍረት ነው። ታማኙ ጸሐፊ ዕዝራ እሱ ራሱ ኃጢአት ባይፈጽምም ሌሎች አይሁዶች የፈጸሟቸውን ኃጢአቶች በሚናዘዝበት ጊዜ “አምላኬ ሆይ፣ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ” ሲል ተናግሯል። (ዕዝራ 9:6) አንድ መጥፎ ነገር ከሠራህ በኋላ ማፈር ትክክለኛ ስሜት ነው። ኅሊናህ አሁንም እየሠራ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እንዲህ ዓይነቱ የሐፍረት ስሜት ከጊዜ በኋላ ይቀንሳል። አንድሩ እንደሚከተለው ሲል ገልጾታል:- “ኃጢአትን መናዘዝ በጣም ከባድና የሚያሳፍር ነገር ነው። ሆኖም ይሖዋ ይቅርታው ብዙ እንደሆነ ማወቅ ትልቅ እፎይታ ያስገኛል።”
ሽማግሌዎችን መጥራት
ክርስቲያን ከሆንክ ጉዳዩን ለወላጆችህ በመንገር ብቻ አያበቃም። አንድሩ እንዲህ ይላል:- “ችግሬን ለጉባኤ ሽማግሌዎች መንገር እንዳለብኝ አውቅ ነበር። ሽማግሌዎች እኔን ለመርዳት የቆሙ መሆናቸውን ማወቅ ምንኛ እፎይታ የሚሰጥ ነበር!” አዎን፣ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ ወጣቶች እርዳታና ማበረታቻ ለማግኘት ወደ ጉባኤ ሽማግሌዎች መሄድ ይችላሉ፤ ደግሞም አለባቸው። ሆኖም ችግሩን ለይሖዋ ከተናዘዝክና ኃጢአት መሥራትህን ካቆምክ አይበቃምን? አይበቃም፤ ምክንያቱም ሽማግሌዎች “የነፍስህ ጠባቂዎች” እንዲሆኑ ይሖዋ አደራ ሰጥቷቸዋል። (ዕብራውያን 13:17 NW) ድጋሚ በኃጢአት እንዳትወድቅ ሊረዱህ ይችላሉ።—ከያዕቆብ 5:14-16 ጋር አወዳድር።
ራሴን በራሴ እረዳለሁ እያልክ ፈጽሞ ራስህን አታታልል። ይህን ማድረግ የሚያስችል ጥንካሬ ቢኖርህ ኖሮ መጀመሪያውኑስ ኃጢአት ትሠራ ነበርን? የሌላ ሰው እርዳታ መፈለግ እንዳለብህ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድሩ በቆራጥነት ይህን አድረጓል። ለሌሎች ምን ምክር ይሰጣል? “ከባድ ኃጢአት እየፈጸመ ያለ ወይም ደግሞ ከዚህ በፊት የፈጸመ ማንም ሰው ቢሆን ልቡን ለይሖዋና ይሖዋ ከሾማቸው እረኞች መካከል ለአንዱ እንዲከፍት አበረታታለሁ።”
ሆኖም አንድን ሽማግሌ ማነጋገር የምትችለው እንዴት ነው? ይበልጥ ወደምትቀርበው ሽማግሌ ሂድ። ከዚያም “አንድ ነገር ልነግርህ እፈልጋለሁ” ወይም “አንድ ችግር አለብኝ” አሊያም ደግሞ “የሆነ ችግር አለብኝ፤ የአንተን እርዳታ እፈልጋለሁ” በማለት ልትጀምር ትችላለህ። ሐቀኛና ግልጽ መሆንህ ንስሐ ለመግባትና ለመለወጥ እንደምትፈልግ የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው።
‘እወገዳለሁ ብዬ እፈራለሁ’
ምናልባት ብወገድስ? አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት መሥራቱ እንዲወገድ ሊያደርገው እንደሚችል የታወቀ ነው፤ ሆኖም የግድ ይህ እርምጃ ይወሰዳል ማለት አይደለም። የውገዳ እርምጃ የሚወሰደው ንስሐ ለመግባት ማለትም ልበ ደንዳና በመሆን ለመለወጥ አሻፈረኝ በሚሉ ሰዎች ላይ ነው። ምሳሌ 28:13 “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል” ይላል። እርዳታ ለመጠየቅ ወደ ሽማግሌዎች መቅረብህ ለመለወጥ ያለህን ፍላጎት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የሽማግሌዎች ተቀዳሚ ተግባር መቅጣት ሳይሆን የታመመውን መፈወስ ነው። የአምላክን ሕዝብ በደግነትና በአክብሮት የመያዝ ግዴት አለባቸው። ‘ለእግርህ ቅን መንገድ በማድረግ’ ሊረዱህ ይፈልጋሉ።—ዕብራውያን 12:13
ለማታለል ከተሞከረ ወይም ከባድ ኃጢአት የመሥራት ሥር የሰደደ ልማድ ካለ “ለንስሐ የሚገባ ነገር” በማድረግ ረገድ ችግር መኖሩ የማይካድ ነው። (ሥራ 26:20) ይህ ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ ውገዳ ሊያስከትል ይችላል። እንዲሁም ኃጢአት የሠራው ሰው ንስሐ ቢገባም እንኳ ሽማግሌዎች አንድ ዓይነት ተግሣጽ ለመስጠት ይገደዳሉ። በዚህ ውሳኔ ልትቆጣ ወይም ልትናደድ ይገባሃልን? በዕብራውያን 12:5, 6 ላይ ጳውሎስ እንዲህ በማለት አጥብቆ ይመክራል:- “ልጄ ሆይ፣ የጌታን ቅጣት አታቅልል፣ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፣ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል።” ማንኛውም ዓይነት ተግሣጽ ቢሰጥህ ይሖዋ እንደሚወድህ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ አድርገህ ተቀበለው። ከልብ ንስሐ መግባት መሐሪ ከሆነው አባታችን ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖርህ እንደሚያደርግ መዘንጋት የለብህም።
ጥፋትን አምኖ መቀበል ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም እንዲህ ማድረግህ ከወላጆችህ ጋር ብቻ ሳይሆን ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህን ግንኙነት ጭምር ለማስተካከል ያስችልሃል። ፍርሃት፣ ኩራት ወይም ሐፍረት አስፈላጊውን እርዳታ ከማግኘት ወደኋላ እንድትል አያድርግህ። ይሖዋ ‘ይቅርታው ብዙ’ መሆኑን አስታውስ።—ኢሳይያስ 55:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
b ወላጆችን ቀርቦ ስለማነጋገር ሐሳብ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ተመልከት።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ኃጢአት የሠራ ማንኛውም ሰው ልቡን ለይሖዋ እንዲከፍት አበረታታዋለሁ።’—አንድሩ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኃጢአትን ለወላጆች መናዘዝ በመንፈሳዊ ለማገገም ሊረዳ ይችላል