የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 7/8 ገጽ 28-29
  • የአራዊት የማንቀላፋት ምሥጢር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአራዊት የማንቀላፋት ምሥጢር
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የእንቅልፍ ባለ ክብረ ወሰኖች
  • ‘እየበረሩ’ ማንቀላፋት
  • በባሕር ውስጥ ማሸለብ
  • ሁልጊዜ አንድ ዓይን ገልጦ መጠባበቅ
  • ሰውነትህ እንቅልፍ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1995
  • በቂ እንቅልፍ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?
    የወጣቶች ጥያቄ
  • እንቅልፍ ቅንጦት ነው ወይስ የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር?
    ንቁ!—2003
  • እንቅልፍ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
    ንቁ!—2011
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 7/8 ገጽ 28-29

የአራዊት የማንቀላፋት ምሥጢር

ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

እንቅልፍ—የዕድሜያችንን አንድ ሦስተኛ በመተኛት የምናሳልፍበት የእረፍት ጊዜ ነው። እንቅልፍ የጊዜ ማባከኛ ሳይሆን በርካታ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ፍላጎቶቻችንን የሚያሟላልን ነው። ስለዚህ እንቅልፍ ከአምላክ የተገኘ ውድ ስጦታ ነው ሊባል ይችላል—ከመዝሙር 127:2 ጋር አወዳድር።

እንቅልፍ በአራዊት ዓለምም ሳይቀር እጅግ አስፈላጊ ሚና የሚጫወት መሆኑም የሚያስገርም አይደለም። እንዲያውም አንዳንድ የአራዊት ዝርያዎች የሚያሸልቡበት መንገድ በጣም የሚያስደንቅ ሲሆን የሌሎቹ ደግሞ የሚያስቅና የሚያስገርም ነው። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

የእንቅልፍ ባለ ክብረ ወሰኖች

በአፍሪካ የቀትር ፀሐይ በጀርባው ተንጋልሎና እግሩን ወደ ሰማይ ሰቅሎ እንቅልፉን የሚለጥጥ አንበሳ የተመለከተ ሰው ይህ አውሬ ልክ እንደ ድመት ገራምና ለማዳ ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል። ከውጭ የሚታዩ ሁኔታዎች አሳሳቾች ናቸው። ቶማስ ካምፕዮን የተባለው የ17ኛው መቶ ዘመን ደራሲ “የተኛን አንበሳ ለመቀስቀስ የሚደፍር ማን ነው?” ሲል ጽፏል። አዎን፣ ጉልበተኛው አንበሳ እንኳን የሚተዳደርበትን የአደን ሥራ ለማከናወን በቀን ውስጥ የ20 ሰዓት እንቅልፍ ያስፈልገዋል።

በኒው ዚላንድ የምትገኘውን ቱዋታራ የምትባል እንሽላሊት መሳይ ቀሰስተኛ እንስሳ እንመልከት። ከዓመት ውስጥ ግማሹን የምታሳልፈው በማሸለብ ነው። እንዲያውም ቱዋታራ በጣም እንቅልፋም ከመሆኗ የተነሳ ምግቧን እያላመጠች እያለ እንኳ እንቅልፍ ይወስዳታል! ሳይንቲስቶች አንዳንድ ቱዋታራዎች 100 ዓመት ያክል እንደሚኖሩ መገመታቸው ይህ ሁሉ እንቅልፍ ከፍተኛ ጥቅም እንዳስገኘላቸው ግልጽ ነው።

ሌሎች ፍጥረታትም ሪፕ ቫን ዊንክል እንደሚባለው የተረት ሰው ለረዥም ጊዜ ያንቀላፋሉ። ብዙዎቹ ፍጥረታት የቅዝቃዜ ወራቶችን ተቋቁመው የሚያልፉት በእንቅልፍ አማካኝነት ነው። እነዚህ እንስሳት ለክረምቱ ወራት ለመዘጋጀት በሰውነታቸው ውስጥ ወፍራም የስብ ክምችት ያዘጋጃሉ። አንቀላፍተው በሚቆዩባቸው በእነዚያ በርካታ ወራት ይህን ስብ እየተመገቡ ይከርማሉ። ይሁን እንጂ በእንቅልፍ ላይ ያለው እንስሳ በቅዝቃዜ እንዳይሞት የሚከላከልለት ምንድን ነው? ኢንሳይድ ዚ አኒማል ወርልድ የተባለው መጽሐፍ እንደሚያስረዳው የእንስሳው አንጎል በደሙ ውስጥ ኬሚካላዊ ለውጥ እንዲካሄድ በማድረግ ቅዝቃዜውን እንዲቋቋም የሚረዳ ቅመም ይፈጥራል። የእንስሳው የሰውነት ሙቀት በጣም ዝቅ ብሎ ወደ ዜሮ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሲጠጋ የልቡ ትርታና አተነፋፈሱ በጣም ይቀንሳል። ከዚያም በጣም ከባድ እንቅልፍ ይወስደውና ለበርካታ ሳምንታት እንዳንቀላፋ ይቆያል።

‘እየበረሩ’ ማንቀላፋት

የአንዳንድ እንስሳት አተኛኘት ደግሞ በጣም እንግዳ ነው። ሱቲ ተርን የምትባለውን የባሕር ወፍ እንውሰድ። አንዲት ወጣት ሱቲ ተርን ከጎጆዋ ከወጣች በኋላ ወደ ባሕር ታቀናና ለሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት እንደ በረረች ትኖራለች! ላባዎች በውኃ የሚረጥቡ በመሆናቸውና በውኃ ላይ ሊያርፉ እንደሚችሉት ሌሎች የተርን ወፍ ዝርያዎች ውኃ ሊቀዝፍ የሚችል እግር ስለሌላት በባሕር ውስጥ እንዳትጠልቅ ትጠነቀቃለች። ከውኃው ውስጥ ብቅ የሚሉ ትናንሽ ዓሣዎችን በአፍዋ ቆንጥጣ በማውጣት ምግቧን ታገኛለች።

ታዲያ የምትተኛው ምን ጊዜ ነው? ወተር፣ ፕሬይ፣ ኤንድ ጌም በርድስ ኦቭ ኖርዝ አሜሪካ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ላባቸው በውኃ ስለሚርስ ባሕር ላይ ይተኛሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ወፎቹ እየበረሩ ሳያንቀላፉ አይቀርም በማለት አንዳንድ ሳይንቲስቶች ሐሳብ ይሰጣሉ።”

በባሕር ውስጥ ማሸለብ

ዓሣዎች ያንቀላፋሉ? ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ እንደሚለው ከሆነ የጀርባ አጥንት ካላቸው እንስሳት መካከል “የአንጎል ሞገድ ለውጥ የሚያስከትል እውነተኛ እንቅልፍ የሚተኙት በጀርባ የሚሳቡ እንስሳት፣ አእዋፍና አጥቢ እንስሳት ብቻ ናቸው።” ሆኖም ብዙዎቹ ዓሦች ዓይናቸውን መክደን ባይችሉም በማንቀላፋት ዕረፍት የሚወስዱበት ጊዜ አለ።

አንዳንድ ዓሦች በጎናቸው ሆነው ሲያንቀላፉ፣ ሌሎች ደግሞ ቁልቁል ተዘቅዝቀው ወይም ወደ ላይ ቀጥ ብለው ያንቀላፋሉ። እንደ ፍላውንደር ያሉ አንዳንድ ጠፍጣፋ ዓሣዎች የሚኖሩት ከባሕር በታች ባለው መሬት ላይ ነው። እንቅልፍ ሲወስዳቸው ግን ከመሬቱ ጥቂት ሳንቲ ሜትር ከፍ ብለው ይንሳፈፋሉ።

ባለ ደማቅ ቀለሟ ፓሮት ፊሽ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የመኝታ ዝግጅት ታደርጋለች። “የሌሊት ልብስ” ትለብሳለች። የምትተኛበት ጊዜ ሲቃረብ አካሏን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍንላት ንፍጥ መሳይ ዝልግልግ ነገር ታመነጫለች። ይህን የምታደርገው ለምንድን ነው? “በላተኞች እንዳያገኟት ለማድረግ ሳይሆን አይቀርም” ይላሉ ስለ ተፈጥሮ የሚጽፉት ዱግ ስትዋርት። ከእንቅልፏ ስትነቃ ካጠለቀችው የልፋጭ ሸማ ትወጣለች።

ሲሎችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አስደናቂ የመኝታ ዝግጅት ያደርጋሉ። ጉሮሮአቸውን እንደ ፊኛ ይነፉና በውኃ ላይ የሚያንሳፍፋቸው መሣሪያ ያዘጋጃሉ። በዚህ መንገድ ይንሳፈፉና አፍንጫቸውን ከባሕሩ ወጣ አድርገው እየተነፈሱ ያንቀላፋሉ።

ሁልጊዜ አንድ ዓይን ገልጦ መጠባበቅ

አንድ እንስሳ በዱር ውስጥ እንዳለ እንቅልፍ ሲተኛ ራሱን ለአዳኞች ማጋለጡ የማይቀር ነው። በዚህ ምክንያት ብዙ እንስሳት እንቅልፍ የሚተኙት በምሳሌያዊ አነጋገር አንድ ዓይናቸውን ሳይከድኑ ነው። በሚተኙበት ጊዜ አእምሮአቸው መጠነኛ ንቃት ስለሚኖረው አንድ ዓይነት አደጋ እንዳለ የሚያመለክት ድምፅ ሲሰሙ ወዲያው ይነቃሉ። ሌሎች ፍጥረታት ደግሞ በተወሰነ የጊዜ ርዝመት ውስጥ ነቃ እያሉ አካባቢያቸውን በመቃኘት ራሳቸውን ከአደጋ ይጠብቃሉ። ለምሳሌ አንድ ላይ እጅብ ብለው የሚያንቀላፉ ወፎች በየጊዜው ዓይናቸውን ገለጥ እያደረጉ አካባቢያቸውን ይቃኛሉ።

በአፍሪካ የሚኖሩ ድኩላዎችና የሜዳ አህዮች በተመሳሳይ ሁኔታ እንቅልፍ በሚተኙበት ጊዜ በየተራ እየተፈራረቁ ዘብ ይቆማሉ። የመንጋው አባሎች በሙሉ መሬት ላይ ተኝተው ሙሉ በሙሉ ሳያንቀላፉ ከራሳቸው ቀና ብለው አካባቢያቸውን የሚቆጣጠሩበት ጊዜም አለ። አልፎ አልፎ ከመካከላቸው አንዱ በጎኑ ይተኛና ኃይለኛ እንቅልፍ ይወስደዋል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የሌላ እንስሳ ተራ ይደርስና በተራው ድብን ያለ እንቅልፍ ይተኛል።

ዝሆኖችም የሚያንቀላፉት አንድ ላይ እጅብ ብለው ነው። ይሁን እንጂ ትላልቆቹ ዝሆኖች አብዛኛውን ጊዜ የሚያሸልቡት በእግራቸው እንደቆሙ ሲሆን በየጊዜው ዓይናቸውን ገለጥ ያደርጉና ግዙፍ ጆሯቸውን ቀና አድርገው በማዳመጥ በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ ይቆጣጠራሉ። ጥጃዎቹ ዝሆኖች እነዚህ ግዙፍ ዘበኞች ጥላ ስለሚሆኗቸው አላንዳች ስጋት በጎናቸው ተጋድመው ለጥ ብለው ይተኛሉ። ሲንትያ ሞስ የተባሉት ደራሲ ኤሌፋንት ሜሞሪስ በተባለው መጽሐፋቸው አንድ የዝሆኖች መንጋ ሲተኛ የተመለከቱትን ጽፈዋል:- “መጀመሪያ ግልገሎቹ፣ ቀጥሎ ጥጆቹ፣ በመጨረሻም ትላልቆቹ ዝሆኖች ተጋደሙና አንቀላፉ። በጨረቃ ብርሃን ሲታዩ ግራጫ ቀለም ያለው ትልቅ ቋጥኝ ይመስሉ ነበር። ከባድ እንቅልፍ ወስዷቸው በሰላም የሚያንኮራፉ ዝሆኖች አይመስሉም ነበር።”

ስለ እንስሳት እንቅልፍ የመተኛት ልማድ ገና ያላወቅናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ይሁን እንጂ እስካሁን ልናገኝ የቻልነው ጥቂት እውቀት እንኳን ‘ሁሉን የፈጠረው’ አምላክ ያለውን አስደናቂ ጥበብ እንድናደንቅ አይገፋፋንምን?—ራእይ 4:11

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ