ፒግሚዎች የጫካ ሕዝቦች
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
ና አገራችን በሆነችው በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ከሚኖሩት ፒግሚዎች ወይም ባቢንጋዎች ጋር ተዋወቅ። ስለ ፒግሚዎች የሰማኸው ወይም ያነበብከው ነገር ባይጠፋም ፊት ለፊት አግኝተሃቸው አታውቅ ይሆናል። ዋና ከተማ የሆነችውን ባንግዊን በምትጎበኝበት ጊዜ ከሁለት ሰዓት ከማያልፍ ጉዞ በኋላ ፒግሚዎች የሚኖሩበትን አካባቢ ልታገኝ ትችላለህ።
የይሖዋ ምሥክሮች ለሁሉም ብሔሮች፣ ነገዶች፣ ዘሮችና ጎሣዎች መድረስ የሚገባው አስፈላጊ የሆነ መልእክት አላቸው። በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያችን ለሁሉም ዓይነት ሕዝቦች እንሰብካለን። ፒግሚዎች ከእነዚህ አንዱ ናቸው።—ራእይ 14:6
ስለዚህ እባክህ አብረኸን ተጓዝና እንዴት እንደሚኖሩ፣ ምድርን ገነት ስለሚያደርገው የአምላክ መንግሥት ለሚነገራቸው ምሥራች እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ ተመልከት። በጣም አስደሳችና አስደናቂ ቀን ይሆንልሃል።
ስለ ፒግሚዎች ማጥናት
ጉዟችንን ከመጀመራችን በፊት ስለምንጎበኛቸው ሕዝቦች መጠነኛ ጥናት ብናደርግ ተገቢ ይሆናል። ለበርካታ ወራት ኑሯቸውን ከፒግሚዎች ጋር አድርገው ባሕላቸውን፣ ሃይማኖታቸውንና ልማዳቸውን ያጠኑ ሰዎች የጻፏቸው መጻሕፍት አሉ።
ስለነዚህ ሰላማዊና ሰው ወዳድ ሰዎች ማንበብና እነርሱን መጎብኘት እንደሚከተሉት ላሉት በርካታ ጥያቄዎች መልስ እንድናገኝ ያስችለናል:- ፒግሚዎች ከየት መጡ? ከእነርሱስ ምን ልንማር እንችላለን? የሚኖሩት የት ነው? ከሌሎች የአፍሪካ ጎሣዎች ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ከቀሩት ሕዝቦች ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩት እንዴት ነው?
ዌብስተርስ ሰርድ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ፒግሚዎች “በአፍሪካ የምድር ሰቅ አካባቢ የሚኖሩ ከአንድ ሜትር ተኩል የማይበልጥ ቁመት ያላቸው . . . የቅርብ ጎረቤቶቻቸውን ቋንቋ የሚናገሩ” እንደሆኑ ይገልጻል። የአፍሪካ ፒግሚዎች አመጣጥ በኦሺንያ እና በደቡብ ምሥራቅ እስያ ክልል ከሚገኙት ኔግሪቶስ (“ትናንሽ ኔግሮዎች”) አመጣጥ የተለየ እንደሆነ ይገመታል።
“ፒግሚ” የሚለው ቃል የተገኘው “ከክርን እስከ ዓጥቅ ያለው ርቀት” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል ነው። ፒግሚዎች በአደንና በመለቃቀም እንደሚተዳደሩ ይታወቃል። በመላው ዓለም የሚኖሩ ፒግሚዎች ከ200,000 ብዙም እንደማይበልጡ ይገመታል።
ሴርዥ ባሁሼ እና ጊ ፊሊፓር ደ ፉዋ የተባሉት ሰዎች ፒግሜ፣ ፐፕል ደ ላ ፎሬ (ፒግሚዎች—የጫካ ሕዝቦች) በተባለው መጽሐፋቸው ስለ ፒግሚዎች በጣም የሚያስደስቱ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን ይነግሩናል። ፒግሚዎች በኮንጎ ሪፑብሊክ፣ በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ፣ በጋቦን፣ በካሜሩንና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ በሚገኙ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች እንዲያውም ወደ ምሥራቅ ሻገር ብሎ በሩዋንዳና በቡሩንዲ ሳይቀር እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
ፒግሚዎች ከየት ወይም መቼ እንደመጡ በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም። ራሳቸውን “ፒግሚ” ብለው አይጠሩም። በአብዛኛው በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ባቢንጋ ተብለው ሲጠሩ በሌሎች አገሮች ግን ባኮላ፣ ባቦንጎ፣ ባአካ፣ ባምቤንዜል፣ ባትዋ እና ባምቡቲ በመባል ይታወቃሉ።
የመጀመሪያው ጉብኝት
በላንድ ክሩዘር ተሳፍረን ጠዋት በአንድ ሰዓት አካባቢ ከባንግዊ እንነሳና በደቡብ አቅጣጫ ወደ ምባኢኪ/ሞንጉምባ እንጓዛለን። የአስፋልት መንገድ የምናገኘው በመጀመሪያዎቹ 100 ኪሎ ሜትሮች ብቻ ነው። ባለፈው ሌሊት ዝናብ በመዝነቡ ምክንያት መንገዱ ስለሚያንሸራትት በባለ ሁለት ዲፈረንሽያል መኪና መጓዛችን ጥሩ ነው።
በለመለመና አረንጓዴ መስክ በተነጠፈበት ገጠራማ ጥቅጥቅ ያለ ደን መካከል፣ ሰዎች በየመንገዱ ዳር በተቀመጡ ትናንሽ ጠረጴዛዎች ላይ ሙዝ፣ አናናስ፣ ማንዮክ፣ በቆሎ፣ ዱባና ኦቾሎኒ ደርድረው ለመሸጥ በሚጠባበቁባቸው መንደሮች እናልፋለን። እዚህ ረሀብ የሚባል ነገር አይታወቅም። ለም የሆነው አፈርና እርጥበት የማያጣው የአየር ሁኔታ የተለያዩና በርካታ የሆኑ ምግቦች ያስገኛል። ከዚያ በኋላ በድንገት የመጀመሪያውን የባቢንጋ “መንደር” ወይም ሠፈር እናገኛለን።
የሚኖሩት በእንብርክክ ሊያስገባ የሚችል አንድ በር ብቻ ባላቸው ትናንሽ ጎጆዎች ውስጥ ነው። በአካባቢው ከሚገኙ ጭራሮዎችና ቅጠሎች ጎጆዎቹን የሚሠሩት ሴቶቹ ናቸው። ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ጎጆዎች ዙሪያውን ተሠርተዋል። ጎጆዎቹ የሚያገለግሉት ለመኝታና ከባድ ዝናብ ሲመጣ ለመጠለል ብቻ ነው። የዕለታዊ ኑሮ ጉዳዮች የሚከናወኑት ከቤት ውጭ ነው።
ከመኪናው ወጣንና ሕፃን ላዘሉ ሴቶች ሰላምታ ሰጠን። አንዳንድ ወንዶች የመኪናችንን ድምፅ ሰምተው ማን እንደሆንና ምን እንደምንፈልግ ለማወቅ እየሮጡ መጡ። አንገታቸው ላይ ትናንሽ ቃጭሎች የተንጠለጠሉባቸው ውሾች ተከትለዋቸዋል።
ፒግሚዎች ከውሻ በስተቀር ምንም ዓይነት የቤት እንስሳ እንደማያረቡ ቀደም ብለን ካደረግነው ጥናት አስታወስን። ውሾች የአደን ባልደረቦቻቸው ናቸው። ከአፈሩ ጀምሮ እስከ ዛፎች አናት ድረስ ብዙ የሚታደኑ እንስሳት አሉ። ፒግሜ፣ ፐፕል ደ ላ ፎሬ የተባለው መጽሐፍ እንደሚያብራራው ወፎችን፣ ዝንጀሮዎችን፣ ዝሆኖችን፣ ጎሾችን፣ አይጦችን፣ ድኩላዎችን፣ የዱር ዓሣማዎችን፣ ሙጭጭላዎችንና ሌሎችንም ያድናሉ። እያንዳንዱ አዳኝ ታማኝ የሆነ ውሻ የግድ ያስፈልገዋል።
እነዚህን ሰዎች ስናነጋግር የምንጠቀመው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ በተባለው መጽሐፍና በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው ብሮሹር ነው።a እነዚህ ጽሑፎች በቅርቡ ምድር ውብ የሆኑ ደኖች ያሉባትና በሽታና ሞት የማይኖርባት ውብ ገነት እንደምትሆን በሥዕላዊ መግለጫዎች ያሳያሉ። (ራእይ 21:4, 5) ሁለቱም ጽሑፎች ፒግሚዎችን ጨምሮ 90 በመቶ የሚሆኑት የአካባቢው ኗሪዎች በሚናገሩት በሳንጎ ቋንቋ ታትመዋል። እነዚህ ሰላም ወዳድ ሕዝቦች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የአፍሪካውያን ጎረቤቶቻቸውን ቋንቋ ይናገራሉ። የንግድ ሸሪኮቻቸው ስለሆኑ ቋንቋቸውን መልመድ የግድ ያስፈልጋቸዋል።
ወዲያው ብዙ ሳይቆይ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ዙሪያችንን ከበው የምንሰጠውን መግለጫ እያዳመጡ ሥዕሎቹን በጉጉት መመልከት ጀመሩ። ቀደም ሲል ከጥቂት ዓመታት በፊት ተጎብኝተው ስለነበር የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ያውቃሉ። ጽሑፎቹን ለመውሰድ ደስተኞች ናቸው። ችግሩ ግን ማንበብ የማይችሉ መሆናቸው ነው። መንግሥትና ሌሎች ተቋሞች እነሱን ማንበብና መጻፍ ለማስተማር ለበርካታ ዓመታት ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ተከፍተውላቸው ነበር። ትምህርት ቤቶቹ ለተወሰነ ጊዜ ከሠሩ በኋላ ልጆቹ ቀስ በቀስ ትምህርታቸውን አቋርጠው ይሄዳሉ። በፒግሚዎች መካከል ለብዙ ዘመናት የሠሩ አንድ መምህር “በክፍል ውስጥ በጣም አስደናቂ የሆነ የመማር ችሎታ ቢኖራቸውም ለበርካታ ወራት ሲማሩ ከቆዩ በኋላ ይጠፋሉ” ብለዋል። ቢሆንም የአካባቢው ባለ ሥልጣኖችና ሌሎች ድርጅቶች መደበኛ ትምህርት ለመስጠት የሚያደርጉትን ጥረት አላቆሙም።
የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ ቃል ፍላጎት የሚያሳዩ ሰዎችን ደጋግመው እንደሚጠይቁ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ባቢንጋዎች ዓመቱን በሙሉ ከቦታ ወደ ቦታ ስለሚዘዋወሩ ሌላ ጊዜ ስንመጣ እነዚያኑ ሰዎች እንደማናገኝ እናውቃለን። ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ወደሚገኘው ቤታቸው ይጠፉና ለበርካታ ወራት በዚያ ይኖራሉ። ቋሚ መኖሪያ እንዲኖራቸው የተደረገው ጥረት ሁሉ አልተሳካም። በእርግጥም የጫካ ሰዎች ናቸው። መዘዋወርና አደን የሕይወታቸው ክፍል በመሆኑ ምንም ነገር አኗኗራቸውን ሊለውጥ አልቻለም።
ዕለታዊ ኑሮ፣ ጋብቻና ቤተሰብ
በመሠረቱ አዳኞቹ ወንዶቹ ሲሆኑ ሴቶቹ ለቃሚዎች ናቸው። እንጉዳዮችን፣ ስራስሮችን፣ ፍራ ፍሬዎችን፣ ቅጠላ ቅጠሎችን፣ ኦቾሎኒ፣ ነፍሳትን፣ ምስጦችን፣ የጫካ ማር፣ እንዲሁም በጣም የሚወዷቸውን አባጨጓሬዎችን፣ በጠቅላላው በጫካው ውስጥ ያገኙትን ሁሉ ይለቅማሉ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ለምግብነትና ለንግድ የሚፈለጉ ናቸው። ሌ ግራን ንዋር (ረዥሞቹ ጥቁሮች) ተብለው የሚጠሩት የፒግሚዎቹ አፍሪካውያን ጎረቤቶች እነዚህን ነገሮች የሚያገኙት በአብዛኛው ከፒግሚዎች ነው። በለውጡ ማሰሮዎችን፣ መጥበሻዎችን፣ ገጀራዎችንና እንደ መጥረቢያና ቢላዋ የመሰሉትን መሣሪያዎች፣ ጨው፣ ዘይት፣ ማንዮክ፣ ሙዝ እንዲሁም የሚያሳዝን ቢሆንም ትንባሆ፣ በአካባቢው የሚዘጋጅ የአልኮል መጠጥና ሐሺሽ ይሸጡላቸዋል። የመጨረሻዎቹ ሦስት ሸቀጦች በእነዚህ ድሃ ሕዝቦች ላይ ከባድ ችግር አስከትለዋል። ብዙ ጊዜ እነዚህን ለማግኘት ዕዳ ውስጥ ይገቡና ቀስ በቀስ መላ ሕይወታቸውን ያበላሻሉ።
አብዛኛውን ጊዜ ወንዶቹ በአንድ ሚስት ብቻ የተወሰኑ ናቸው። ቢሆንም ከሌላ ሴት ጋር ለመኖር ሲሉ በቀላሉ ከሚስታቸው ይፋታሉ ወይም ይለያያሉ። በሠፈሩ ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ክብር የሚሰጠው ለአባትዬው ወይም በዕድሜ ለሚበልጠው ሰው ነው። እንዲህ አድርጉ ብሎ ባያዝም የሚሰጠው ምክር አብዛኛውን ጊዜ ተቀባይነት ያገኛል። ፒግሚዎች ልጆቻቸውን እንደሚወዱ መመልከት ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ አባቶችም ሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን ይይዛሉ። ሁለቱም ወላጆች የትም ቢሆኑ፣ ምንም ቢያደርጉ፣ አደንም ላይ ሆኑ ጭፈራ ላይ ከልጆቻቸው አይነጠሉም።
ሕፃናት ማታ የሚተኙት በወላጆች መካከል ነው። ቀን ቀን ሕፃናት በወላጆች፣ በወንድሞች፣ በእህቶች፣ በአጎቶችና በአያቶች የሚጠበቁ ሲሆን የመላው ሠፈረተኛ ጥበቃ አይለያቸውም። ወላጆችና ዘመዳሞች አዘውትረው ይጠያየቃሉ። በዚህ ምክንያት ቤተሰቦች በጣም ይቀራረባሉ። በምዕራቡ ዓለም የቤተሰብ ግንኙነት በጣም የላላ፣ እንዲያውም የሌለ ቢሆንም እዚህ ግን ሁኔታው በጣም የተለየ ነው።
ፒግሚዎች ከአፍሪካውያን ጎረቤቶቻቸው ተነጥለው ቢኖሩም የኢኮኖሚ ግንኙነት አላቸው። በንግድ ምክንያት እርስ በርስ ከመገናኘታቸው በተጨማሪ በቡናና በካካዋ ማሳዎች ተቀጥረው እንዲሠሩ ይጠየቃሉ። ለጥቂት ሳምንታት ሠርተው ደመወዛቸውን ከተቀበሉ በኋላ ወደ ደናቸው ገብተው ረዥም ጊዜ ያሳልፋሉ። ማን ያውቃል? ዛሬ ጠዋት የጠጣኸው ቡና በማዕከላዊ አፍሪካ ፒግሚዎች እጅ ያለፈ ሊሆን ይችላል።
ሃይማኖት
ባቢንጋዎች ሃይማኖተኞች ቢሆኑም ሃይማኖታዊ ሕይወታቸውን የሚገዛው አጉል እምነትና ወግ ነው። ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚፈጽሙት በሙዚቃ፣ በዝማሬና (ድምፅ ከፍ በማድረግ) በጭፈራ ታጅበው ነው። ኤትኒ—ድርዋ ደ ሎም ኤ ፐፕል ኦቶክቶን (ጎሣዎች—ሰብዓዊ መብትና አገር በቀል ሕዝቦች) የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን መግለጫ ይሰጣል:- “ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች እንደሚያምኑት አምላክ ዓለምን ማለትም ጫካን ፈጠረ። የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት ከፈጠረ በኋላ . . . ወደ ሰማይ ተመለሰና የሰዎችን ጉዳይ ፈጽሞ ተወ። በአሁኑ ጊዜ የእሱ ወኪል ሆኖ የሚሠራው የጫካ አምላክ የሆነው ኃያል መንፈስ ነው።” በእርግጥ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ ዓላማው ከሚሰጠው መግለጫ ፈጽሞ የተለየ ነው።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 1, 2፤ መዝሙር 37:10, 11, 29
ብልህ ሕዝቦች
አንዳንድ ሰዎች ፒግሚዎችን ከሌላ ሕዝቦች ያነሰ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ናቸው ወይም ደደቦች ናቸው ብለው መናቃቸውና ማዋረዳቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። ይሁን እንጂ በእንግሊዝ አገር የሊድስ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮፊዝክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፓትሪክ መረዲት እንዲህ ብለዋል:- “ፒግሚዎች በተፈጥሮ አካባቢያቸው ሆነው ከቃጫ ድልድይ ሲሠሩ ወይም የተሳካ ኑሮ ሲመሩ ብትመለከቱ ታዲያ ከዚህ ወዲያ ብልህነት ምንድን ነው ብላችሁ መጠየቃችሁ አይቀርም።”
ሰዎች በሙሉ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የአዳምና የሔዋን ዝርያዎች እንደሆኑ እናውቃለን። የሐዋርያት ሥራ 17:26 (በ1980 ትርጉም) “[እግዚአብሔር] የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው [ከአዳም] ፈጠረ፤ በምድር ሁሉ ላይም እንዲኖር አደረገ” ይላል። በተጨማሪም ሥራ 10:34, 35 “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ይላል። በዚህ ምክንያት እነዚህም ሕዝቦች መላይቱ ምድር ብዙ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ያሉባት የተዋበች ገነት በምትሆንበት ጊዜ በሕይወት የመኖር ተስፋ ለማግኘት እንዲችሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ልናደርስላቸው እንፈልጋለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብና ትራክት ማኅበር የተዘጋጁ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
1. የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለፒግሚዎች ማካፈል፣ 2. ፒግሚ እንጨት ጠራቢ፣ 3. የፒግሚዎች መኖሪያ