ሥራህ አሰልቺ ሆኖብሃልን?
በቀን ስምንት ሰዓት ያህል ሳትሠራ አትቀርም። ሥራህ የሚሰለችህ ከሆነ ደግሞ ይህን የሚያክል ብዙ ሰዓት ሳትደሰትበት ያልፋል ማለት ነው! በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን አብዛኞቹ ሥራዎች አሰልቺ ሲሆኑ ለሚሠራቸው ሰው ትንሽ እንኳ እርካታ የሚሰጡ አይደሉም።
ስለዚህ ሥራህ አስደሳች እንዲሆንልህ ብታደርግ ብዙ ጥቅም ልታገኝ ትችላለህ። ከምትሠራው ሥራ ብዙ ደስታ ታገኛለህ፣ ወደፊት የሚያጋጥሙህንም ሥራዎች እንዴት አስደሳች ማድረግ እንደምትችል ትማራለህ። እንግዲያው ይህን ለማድረግ የሚያስችሉንን አንዳንድ ዘዴዎች እስቲ እንመልከት።
በጥሩ መንፈስ ለመሥራት ሞክር
አንዳንድ ጠበብት የምትሠራውን ሥራ እንዲያስደስትህ አድርገህ እንድትሠራ ይመክራሉ። እንዲህ ካደረግህ ሥራህ አስደሳች ሊሆንልህ ይችላል።
‘ይሁን እንጂ በምንም ዓይነት ሥራዬን በጥሩ ስሜት ልሠራው አልችልም’ ትል ይሆናል። ሥራህ ዕቃዎችን በየፈርጁ ማስቀመጥና ሠራተኞችን እንደማቀናጀት ያለ ከሆነ ተደጋጋሚና አሰልቺ ሊሆን ይችላል። ወይም ለብዙ ዓመታት አንድ ዓይነት ሥራ ስትሠራ ስለ ቆየህ አሁን ሥራውን እንደ አዲስ ልወደው አልችልም የሚል ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። ይሁን እንጂ ፈገግ እንደማለትና ቀጥ ብሎ እንደመቆም ያሉ ቀላል ዘዴዎች ለሥራህ ጥሩ ስሜት እንዲኖርህ ሊረዱህ ይችላሉ።
በተጨማሪም በምትሠራው ሥራ ላይ ሙሉ በሙሉ ማተኮር ሊረዳህ ይችላል። ሥራህን ስትሠራ ስሜት እንደሌለው መሣሪያ ሆነህ ወይም የምሳ ዕረፍትህን ወይም የሳምንቱን የመጨረሻ ቀኖች ወይም ልትሠራ ያሰብከውን ሌላ ሥራ እያሰብክ አትሥራ። አብዛኛውን ጊዜ ሙሉ ትኩረትህን በያዝከው ሥራ ላይ ብታደርግ ጥሩ ይሆናል። ውጤቱስ? በሥራህ መደሰት ስለምትጀምር የሥራ ሰዓትህ ሳይታወቅህ ፈጥኖ ያልፋል።
በጣም በምትወደው ሥራ ስትመሰጥ ሰዓቱ ሳይታወቅህ ያልፋል። የማያስደስትህን ሥራ በምትሠራበት ጊዜም ራስህን አስገድደህ በሥራው ላይ ሙሉ በሙሉ ብታተኩር በተመሳሳይ ሁኔታ ሳይታወቅህ ሰዓቱ ይሄዳል።
የተቻለህን ሁሉ አድርግ
አቅምህ የሚፈቅደውን ሁሉ ብታደርግ ከሥራህ እርካታ ለማግኘት ትችላለህ። እርግጥ፣ እንዲህ ያለው ምክር አንድን ሥራ የማያስደስት ሆኖ ካገኘኸው ራስህን ማስጨነቅ የለብህም ከሚለው የተለመደ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጭ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቸልተኝነት፣ ሥራን ለሌላ ጊዜ ማቆየትና በቂ ጥረት አለማድረግ አቅም ስለሚያሳጣህ ድካምና ጭንቀት ይጨምርብሃል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከሥራ ሲመጡ የሚደክማቸው፣ የሚጨንቃቸውና ውጥረት የሚሰማቸው ሥራቸውን በትጋት ሳይሠሩ በመቅረታቸው ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አንድን ሥራ በሙሉ ኃይል መሥራት የዕረፍት ጊዜን ጭምር አስደሳች ሊያደርግ ይችላል። “ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም።” (መክብብ 2:24) ይህ ለአንዳንዶች ዘመኑ ያለፈበት መፈክር ሆኖ ይታያቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህን ዘመን የማይሽረው መሠረታዊ ሥርዓት የሚከተሉ ብዙ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ድካማቸው ባስገኘላቸው ፍሬ ከመደሰት ‘የሚሻል ነገር’ እንደሌለ ይስማማሉ። ዘ ጆይ ኦቭ ዎርኪንግ የተባለው መጽሐፍ “በደንብ የተሠራ ሥራ ውስጣዊ የእርካታ ስሜት ያሳድራል” ይላል።
ስለዚህ ሥራህን ባለህ አቅም በሙሉ ጥሩ አድርገህ ብትሠራ ብርታት ይሰማሃል። ግዳጅህን ለመወጣት ያክል ብቻ ሳይሆን የበለጠ ለመሥራት ጥረት ብታደርግ ደስታ ልታገኝ ትችላለህ። ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ሥራዎች አስቀድመህ ጨርስ። እንዲህ ካደረግህ ዛሬ ነገ እሠራዋለሁ እያለ ራሱን በሐሳብ ከሚያደክም ሰው የበለጠ በምሳና በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ዕረፍትህ ትደሰታለህ።—ከአስቴር 10:2፤ ከሮሜ 12:11 እና ከ2 ጢሞቴዎስ 2:15 ጋር አወዳድር።
ከሌሎች ጋር ከመፎካከር ይልቅ የራስህን ችሎታዎች ለማሻሻል ተጣጣር። (ገላትያ 6:4) አዳዲስ ደረጃዎችና ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት አድርግ። ሁልጊዜ ካለፈው የተሻለ ሥራ ለመሥራት ተጣጣር። የአንዲት ሴት ሥራ ብዙዎች አሰልቺ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት ተደጋጋሚ የሆነ የስፌት ሥራ ነበር። ሥራዋን እንደ ጨዋታ በመውሰድ በየሰዓቱ ምን ያህል ጨርቅ ሰፍታ እንደጨረሰች መቁጠር ጀመረች። ከዚያም በየጊዜው የምትሰፋውን መጠን ለመጨመር ሞከረች። ጉልበቷን ሳትቆጥብ ስለምትሠራ በሥራዋ ትደሰታለች።—ምሳሌ 31:31
ሥራህን “አስጊጥ”
ዶክተር ዴንስ ቲ ጃፍ እና ዶክተር ሲንትያ ዲ ስኮት የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል:- “ሥራችሁን እንደ ባዶ ቤት አድርጋችሁ ውሰዱት። ወደ ቤቱ ትገቡና ቅርጹንና አቀማመጡን ትመለከታላችሁ። ከዚያም የፈጠራ ችሎታችሁን በመጠቀም ምን ያህል ቦታ እንዳላችሁ ካያችሁ በኋላ ቤቱን ታስጌጡና ባዶውን ቤት አስደሳች የመኖሪያ ቦታ ታደርጋላችሁ። በራሳችሁ ችሎታና ጥረት የግላችሁ መኖሪያ ታደርጉታላችሁ።”
አብዛኛውን ጊዜ ከሥራህ ጋር አብሮ የሚሰጥ የአሠራር ሕግና መመሪያ ይኖራል። የሚፈለግብህን ብቻ መሥራት በባዶ ቤት ውስጥ እንደመኖር ይቆጠራል። ቤቱ ምንም ዓይነት የራሱ መለያ የለውም። ይሁን እንጂ የራስህን ጌጥ በምትጨምርበት ጊዜ ሥራህ ይበልጥ አስደሳች ይሆንልሃል። የተለያዩ ሰዎች ሥራቸውን በተለያየ መንገድ “ያስጌጣሉ።” አንድ የምግብ ቤት አስተናጋጅ አዘውታሪ ደንበኞች ምን ዓይነት ምግብ እንደሚያዙ በቃል ያጠና ይሆናል። ሌላው ደግሞ ለየት ያለ ደግነትና ትህትና ይታይበታል። ሁለቱም ሥራቸውን በትጋትና ባላቸው ችሎታ በሙሉ የሚያከናውኑ በመሆናቸው በሚሠሩት ሥራ ይደሰታሉ።
ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ተማር
ከሥራህ ደስታ የምታገኝበት ሌላው መንገድ ዘወትር መማር ነው። ቴንሽን ተርንአራውንድ የተባለው መጽሐፍ እያደግን ስንሄድ የአንጎላችን መረጃዎችን የማጠናቀር ችሎታ ይጨምራል በማለት ገልጿል። ባለፉት ጊዜያት ትኩረታችንን ይስቡ የነበሩ ነገሮች በአሁኑ ጊዜ አሰልቺ የሚሆኑብን በዚህ ምክንያት ነው። ለዚህ መፍትሔው አዳዲስ ነገሮችን በመማር አንጎል ለአዳዲስ መረጃዎች ያለውን ጥማት ማርካት ነው።
ስለ ሥራህ ያለህን እውቀት ዘወትር መጨመርህ ይበልጥ አስደሳች የሆነ ሥራ እንድታገኝ ያስችልህ ይሆናል። ይህም ባይሆን መማር ራሱ ሥራህን ይበልጥ አስደሳችና አርኪ ሊያደርግልህ ይችላል። ቻርልስ ካሜሮንና ሱዛን ኤሉሶር የተባሉት ደራሲዎች እንደሚከተለው ብለዋል:- “መማር ችሎታዎችህን በማሳደግ ይበልጥ በራስህ እንድትተማመን ከማስቻሉም በተጨማሪ ለሕይወት ባለህ አጠቃላይ አመለካከት ላይ ለውጥ በማስከተል ችግሮች ሊሸነፉ እንደሚችሉ፣ ፍርሐት ሊቀንስ እንደሚችልና ከምትገምተው በላይ ብዙ ነገሮች ማከናወን እንደሚቻል ያሳምንሃል።”
‘ይሁን እንጂ ስለ ሥራዬ መማር የሚቻለውን ሁሉ አውቄ ከጨረስኩ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል!’ ትል ይሆናል። እንዲህ ከሆነ ከሥራህ ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ የሌላቸውን ነገሮች ለመማር ትችል ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሰብዓዊ ግንኙነቶች ወይም ስለምትሠራበት መሣሪያ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ትወስን ይሆናል። ሰርኩላር ደብዳቤዎችን እንዴት ጥሩ አድርገህ እንደምትጽፍ ወይም የስብሰባ አመራር ችሎታህን እንዴት እንደምታሻሽል መማር ትችል ይሆናል። ከሥራ ኃላፊዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር የምትችልባቸውን መንገዶችም ልትማር ትችላለህ።
ታዲያ እነዚህን ነገሮች እንዴት ትማራለህ? የምትሠራበት ኩባንያ አንተም ልትካፈል የምትችልበት ኮርስ ያዘጋጅ ይሆናል። አለበለዚያም የሚያስፈልግህን መጽሐፍ ከቤተ መጻሕፍት ማግኘት ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ እምብዛም ያልተለመዱ የመረጃ ምንጮችን ችላ አትበል። ሰዎችን በሥራቸው ላይ እንዳሉ መመልከትና ደካማና ጠንካራ ጎናቸውን ማስተዋል ራሱ ጥሩ የትምህርት ምንጭ ነው። ከሠራሃቸው ስህተቶች ልትማር ትችላለህ፤ በትክክል የሠራሃቸውን ነገሮች በመመርመር ካገኘሃቸው የተሳኩ ውጤቶች ትምህርት ልታገኝ ትችላለህ። ከራስህ ተሞክሮም ሆነ ሌሎችን በመመልከት የምትማራቸውን ነገሮች መጻሕፍት በማንበብ ወይም ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ በመማር ፈጽሞ ሊገኙ የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ።
ጥቂት የመጨረሻ ምክሮች
ስለ ሥራህ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት ሊኖርህ ይችላል። የተሻለ ነገር ሲመጣ ሁልጊዜ ለሌሎች እንደሚሰጥና የምትወደውን ሥራ የመሥራት አጋጣሚ ፈጽሞ አግኝተህ እንደማታውቅ ልታስብ ትችላለህ። ይህን አስተሳሰብህን ከሚደግፉልህ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ተነጋግረህ ይህ ሁሉ ትክክል እንደሆነ ታምን ይሆናል።
ይሁን እንጂ ይህ እውነት ላይሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች በሥራቸው መደሰት የቻሉት የአመለካከት ለውጥ ለማድረግ በመማራቸው ነው። የቤት ንድፍ በማውጣት የሚደሰት ሰው የአውቶቡስ ሾፌርም ሆኖ ሊደሰት ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ከሥራው ደስታና እርካታ እንዲያገኝ የሚያስችለው ለሥራው ያለው አመለካከት ነው።
ስለዚህ የሳምንቱ የሥራ ቀናት ከቅዳሜና እሁድ ጋር ሲነጻጸሩ የበለጠ የጨለሙ ሆነው እንዲታዩህ የሚያደርገውን አፍራሽ አስተሳሰብ አስወግድ። ባለፉት ጊዜያት ያልተሳኩልህን ነገሮች እያሰብክ ወደፊት ደግሞ ምን ስህተት እሠራ ይሆን ብለህ በማሰብ ጊዜህን አታባክን። ሌሎች ስለ አንተ የሚኖራቸው ግምት አያስጨንቅህ። ከፊትህ ስላለው ሥራ ብቻ አስብ። ሙሉ ትኩረት ስጠው። በትርፍ ጊዜህ የምትሠራውን በጣም የምትወደውን ሥራ በፍላጎት እንደምትሠራ ሁሉ ለመደበኛ ሥራህም ተመሳሳይ ፍላጎት ይኑርህ። አቅምህ የሚችለውን ሁሉ አድርግ። በሚገባ በተሠራ ሥራ ተደሰት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሥራህን ችላ አትበል
መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 27:23, 24 ላይ “የበጎችህን መልክ አስተውለህ እወቅ፣ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር። ባለጠግነት ለዘላለም አይኖርምና፣ ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና” ይላል። ይህ ምን ማለት ነው?
ሀብት (ባለጠግነት) እና ማዕረግ (ዘውድ) ሊገኝ ቢችል እንኳን ዘላለማዊ አይደለም ማለት ነው። ስለዚህ አንድ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሚኖር እረኛ በጎቹን ተግቶ ቢጠብቅ፣ ወይም ‘በከብቶቹ ላይ ልቡን ቢያኖር’ ጥበበኛ ይሆናል። የሚቀጥሉት ሦስት ቁጥሮች እንደሚያመለክቱት እንዲህ ማድረጉ ለሠራተኛውም ሆነ ለቤተሰቡ በቂ መተዳደሪያ ያስገኛል።—ምሳሌ 27:25-27
ዛሬስ? ብዙ ሰዎች አሁን ከሚሠሩት ሥራ እንዲገላግላቸው በማሰብ ሀብትና ትልቅ ቦታ ለማግኘት ይጣጣራሉ። አንዳንዶች ከነባራዊ ሁኔታዎች ያልራቀ እቅድ ሲያወጡ ሌሎች ግን የቁም ቅዠት ይቃዣሉ። በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን አንድ ሰው የሚተዳደርበትን ሞያ ባይንቅ ወይም ችላ ባይል ጥሩ ይሆናል። ከማንኛውም ሥራ የበለጠ አስተማማኝ ገቢ የሚያስገኝለት ይህ ሥራ ነው። ማንኛውም ሰው ልቡን ‘በከብቶቹ’ ላይ ቢያኖር ማለትም አስተማማኝ በሆነው ሥራው ላይ ሙሉ በሙሉ ቢያተኩር በጣም የተሻለ ይሆናል። ይህን ማድረጉ አሁንም ሆነ ወደፊት አስተማማኝ መተዳደሪያ ሊያስገኝለት ይችላል።