የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 2/8 ገጽ 30-31
  • ከዓለም አካባቢ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከዓለም አካባቢ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በአፍላ ጉርምስና የሚፈጸም ወሲብ
  • ኢ ኮሊ 0157:H7 ከተባለው ባክቴሪያ ተጠንቀቅ
  • እጅህን ታጠብ
  • በልጆች ላይ የሚፈጸም በደልና በሽታ የመከላከል አቅም
  • ጠበኛ ተሳፋሪዎች
  • ማስጠንቀቂያ:- ስልክ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል
  • ኤድስና እስያ
  • ለትንባሆ ጭስ መጋለጥ ዕድሜ ያሳጥራል
  • ምግብ ማብሰል—እየተረሳ ያለ ሙያ
  • አሁንም አሁንም መብላትና የጥርስ መበስበስ
  • ኤድስ በአፍሪካ እየተዛመተ ነው
    ንቁ!—2002
  • ኤድስን እንዴት መከላከል ይቻላል?
    ንቁ!—1999
  • በኤች አይ ቪ ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆኑ የተረጋገጠ ደም አስተማማኝ ነው ሊባል ይችላል?
    ንቁ!—2008
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2000
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 2/8 ገጽ 30-31

ከዓለም አካባቢ

በአፍላ ጉርምስና የሚፈጸም ወሲብ

ዊክኤንድ ኮንኮርድ የተባለ አንድ የናይጄርያ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት “የናይጄርያ ወጣቶች በዓለም ካሉት ወጣቶች ከፍተኛ ወሲባዊ ፍላጎት በማሳየት የቀዳሚነቱን ደረጃ ከያዙት መካከል ሆነዋል።” ከ14 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወንዶች መካከል 68 ከመቶ የሚሆኑት፣ ከሴቶች መካከል ደግሞ 43 በመቶ የሚሆኑት “ወደ ጉርምስና ዕድሜ እንደገቡ ሩካቤ ሥጋ” እንደፈጸሙ አምነዋል። በዚህ ምክንያት ያልተፈለጉ እርግዝናዎች ቁጥር በጣም ከፍ ብሏል። ከዚህ ጥናት ጋር ግንኙነት በሌለው ሌላ ጥናት መሠረት “በናይጄርያ ከ19 ዓመት ዕድሜ በታች ከሚገኙ ወጣት ሴቶች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱት ከውርጃ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ነው” ይላል ኮንኮርድ።

ኢ ኮሊ 0157:H7 ከተባለው ባክቴሪያ ተጠንቀቅ

ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “በጣም አስፈሪ ከሆኑ የኢ ኮሊ ባክቴሪያ ዓይነቶች የሚመጣ የምግብ መመረዝ . . . በመላው ዓለም በመስፋፋት ላይ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል። “በመላው ዓለም መርዝ ተሸካሚ የሆኑ ባክቴሪያዎች ብዛትም ሆነ በመርዙ የሚለከፉና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።” 0157:H7 የሚል መጠሪያ የተሰጠው የባክቴሪያ ዓይነት ችግር እንደሚያስከትል ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በ1982 ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የባክቴሪያ ዓይነት ከዚያ ጊዜ ወዲህ ለሺጌላ ተቅማጥ መንስኤ የሆነውን የሺጋ መርዝ የሚሠራ አዲስ ጂን ተውሶ ተገኝቷል። ተቅማጡ በጊዜ ሕክምና ካልተደረገለት የአንጀት መድማት፣ የኩላሊት መበላሸትና ሞት ሊያስከትል ይችላል። በ1993 በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል 700 ሰዎች በአንድ የታወቀ ምግብ ቤት በደንብ ያልበሰለ ሃምበርገር ከበሉ በኋላ የታመሙ ሲሆን አራቱ ሞተዋል። በተጨማሪም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ በሽታ በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በጃፓን በጣም ተስፋፍቷል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ኢ ኮሊ 0157:H7 በየዓመቱ ለ20,000 ሰዎች መታመምና ከ250 እስከ 500 ለሚደርሱ ሰዎች መሞት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። “ሸማቾች የሚመገቡትን ሥጋ፣ በተለይም የተፈጨ ሥጋ የውስጥ ሙቀቱ 70 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ እስኪደርስ በደንብ በማብሰል በባክቴሪያው የመለከፍ ዕድላቸውን በእጅጉ ሊቀንሱ ይችላሉ” ይላል ታይምስ።

እጅህን ታጠብ

ኮሪየር ዴላ ሴራ የተባለው የኢጣሊያ ጋዜጣ “የበርካታ ተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት እጅ የመታጠብን ያህል ጥሩ፣ ቀላልና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ዘዴ የለም” ይላል። ይሁን እንጂ “ከ10 ኢጣሊያውያን መካከል ከ3 የሚበልጡት ወዲያው የሚመገቡ ቢሆኑም እንኳ መጸዳጃ ቤት ከገቡ በኋላ እጃቸውን አይታጠቡም።” የዚህ ጥናት ውጤት በሌሎች አገሮች ከተደረጉ ሌሎች ጥናቶች ከተገኘው ውጤት ጋር ተመሳሳይ ነው። ኤንሪኮ ማግሊያኖ የተባሉት ማይክሮባዮሎጂስት እንዳብራሩት “እጆች ጀርሞችን ወደ ምግቦች ሊያስተላልፉና የማይቋረጥ የበሽታ ሰንሰለት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።” ታዲያ ይህን ሰንሰለት እንዴት መበጠስ ይቻላል? ቢያንስ ለ30 ሴኮንድ ያህል እጅህን (ከዚህ ባነሰ ጊዜ ባክቴሪያዎች አይወገዱም) የጥፍሮችህን ውስጦች ጭምር በሳሙናና በሙቅ ወይም ለብ ባለ ውኃ በመታጠብ ነው። ከ10 እስከ 15 ሴኮንድ ያህል እጆችን እርስበርስ ማሸትና ከዚያ በኋላ ከክንድ ጀምሮ ወደታች እስከ ጣቶች ድረስ አለቅልቆ ማድረቅ ያስፈልጋል በማለት ጽሑፉ ያብራራል።

በልጆች ላይ የሚፈጸም በደልና በሽታ የመከላከል አቅም

በጃፓን አገር በማይ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች አንድ ሕፃን ረዘም ላለ ጊዜ በደል ሲፈጸምበት በሽታ የመከላከል አቅሙ በጣም ስለሚመናመን ለብዙ በሽታዎች የተጋለጠ እንደሚሆን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ደማቸው አንጎላቸው ውስጥ በመፍሰሱ ምክንያት ወይም ሌላ ዓይነት አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው በሞቱ ከአንድ ወር እስከ ዘጠኝ ዓመት ዕድሜ የሆናቸው 50 ልጆች አስከሬን ላይ ጥናት አድርጓል። ማይኒቺ ዴይሊ ኒውስ የልጆቹን “በሽታ የመከላከል ኃይል የሚቆጣጠረው ታይመስ የተባለው ዕጢ መንምኖ ከመደበኛ ክብደቱ ከግማሽ በላይ ቀንሶ እንደተገኘ” ዘግቧል። በደሉ የተፈጸመባቸው ጊዜ በረዘመ መጠን የዕጢው መመናመን ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል። እንዲያውም “ከስድስት ወራት በላይ በደል የተፈጸመበት ሕፃን ታይመስ ዕጢ ምንም በደል ያልተፈጸመበትን ሕፃን አንድ አሥራ ስድስተኛ ያህል ክብደት ኖሮታል” ይላል ጋዜጣው። ሥነ-አእምሯዊ በደል የደረሰባቸውና ወላጆቻቸው በቂ ምግብ ሳያቀርቡላቸው በመቅረታቸው ምክንያት የአመጋገብ ጉድለት ያጋጠማቸው ሕፃናት በተመሳሳይ ዕጢያቸው መንምኖ እንደተገኘ ተመራማሪዎች አረጋግጠዋል።

ጠበኛ ተሳፋሪዎች

የተበሳጩ ተሳፋሪዎች የሚያሳዩት የጠበኝነት ባሕርይ በጣም እየጨመረ መምጣቱን የንግድ አየር መንገዶች ይናገራሉ። ተሳፋሪዎች በበረራ ሰዓት መጓተት፣ በዕቃ መጥፋትና በመሳሰሉት ምክንያቶች ስለሚቆጡ “በበረራ አስተናጋጆች ላይ ይተፋሉ፣ አንዳንድ ጊዜም የበሉበትን ሳህን ይወረውራሉ፣ ሠራተኞችን ይማታሉ። አብራሪዎችን እስከ መደብደብ የሚደርሱበትም ጊዜ አለ” ይላል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ። በተለይ እንዲህ ያለው ጥቃት በአየር ላይ በሚገኝ አውሮፕላን ውስጥ የሚፈጸም መሆኑ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ባለ ሥልጣኖችን ኣሳስቧቸዋል። አንድ አየር መንገድ በየወሩ እስከ 100 የሚደርሱ የአፍ ወይም የእጅ እልፊት እንደሚያጋጥመው ሪፖርት አድርጓል። “ረብሸኛ ተሳፋሪዎች በጾታ፣ በቆዳ ቀለም ወይም በዕድሜ የተወሰኑ አይደሉም። በአንደኛም ሆነ በሦስተኛ ማዕረግ ክፍሎች ይገኛሉ። ከሦስቱ አንዱ በመጠጥ ኃይል የሚገፋ ነው” ይላል ታይምስ።

ማስጠንቀቂያ:- ስልክ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል ይችላል

መኪና በማሽከርከር ላይ እያለህ በስልክ ከተጠቀምክ ማለት ነው። ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲስን ላይ የወጣ ጥናት እንደሚያመለክተው በመኪናቸው ውስጥ በሚገኝ ስልክ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎች አደጋ የማድረስ ዕድላቸው ትኩረታቸውን በማሽከርከር ላይ ብቻ ካደረጉት በአራት እጥፍ ይበልጣል። ስልክ እየተነጋገሩ ማሽከርከር አደገኛነቱ በደም ውስጥ 0.1 በመቶ የአልኮል መጠን እያለ የማሽከርከርን ያህል ነው ለማለት ይቻላል። ከዚህም በላይ ተለጣፊ መነጋገሪያ ያላቸው አሽከርካሪዎች የስልኩን መነጋገሪያ በእጃቸው ይዘው ከሚነጋገሩት ተሽለው አልተገኙም። ለአደጋው ምክንያት የሆኑት ስልኮቹ ራሳቸው ሳይሆኑ ለአሽከርካሪዎቹ መዘናጋት ወይም መጨቃጨቅ ምክንያት መሆናቸው እንደሆነ አጥኚዎቹ ገልጸዋል። ከዚህም በላይ አደጋ ከደረሰባቸው አሽከርካሪዎች መካከል 39 በመቶ የሚሆኑት ከአደጋው በኋላ በስልካቸው ተጠቅመው እርዳታ እንዲደርስላቸው ጥሪ አድርገዋል። የመኪና ውስጥ ስልክ ያላቸው ሁሉ በሚያሽከረክሩበት ጊዜ አስፈላጊ ያልሆኑ የስልክ ጥሪዎችን እንዳያደርጉና ጭውውታቸውንም አጭር እንዲያደርጉ ተመክረዋል። እንደ ብራዚል፣ ስዊዘርላንድና እስራኤል ያሉ አገሮች አሽከርካሪዎች በተንቀሳቃሽ ስልክ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ሕግ አውጥተዋል።

ኤድስና እስያ

በአንዳንድ ምዕራባዊ አገሮች የተረጋገጡ የኤድስ በሽተኞች ቁጥር በጥቂቱ የቀነሰ ቢሆንም በብዙ የእስያ አገሮች ወረርሽኙ በጣም ተባብሷል። በሕንድ በ1990ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አጋማሽ ላይ የኤድስ በሽተኞች ቁጥር 71 ጊዜ እንደጨመረ ኤዥያዊክ ዘግቧል። በ1990 ከዓለም በ57ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ የነበረችው ታይላንድ በ1990ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ 5ኛ ሆናለች። ካምቦዲያ ከ173ኛ ደረጃ ተነስታ 59ኛ ሆናለች። ፊሊፒንስ ደግሞ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 131 በመቶ ጭማሪ አሳይታለች። ለዚህ በከፊል ምክንያት የሚሆነው ከእነዚህ አገሮች በብዙዎቹ የዝሙት አዳሪ ሕፃናት ንግድ እየተስፋፋ መሄዱ እንደሆነ ብዙዎች ተገንዝበዋል። ይሁን እንጂ ኤዥያዊክ እንደሚለው ፖለቲከኞች “አገሮቻቸው ከቱሪስቶች የሚያገኙት ገንዘብ በጣም ስለሚያስፈልጋቸው . . . ይህን የሚያግድ ቁርጥ ያለ እርምጃ ለመውሰድ ያመነታሉ።”

ለትንባሆ ጭስ መጋለጥ ዕድሜ ያሳጥራል

ጉድ ሃውስኪፒንግ የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ መጽሔት ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደዘገበው “በየዓመቱ ከ50,000 የሚበልጡ ሰዎች ለትንባሆ ጭስ በመጋለጣቸው፣ ማለትም ሌሎች ያጨሱትን የትንባሆ ጭስ ወደ ሰውነታቸው በማስገባታቸው ምክንያት በመጣባቸው የልብና የደም ሥር በሽታ” ሳቢያ ይሞታሉ። በተጨማሪም ትንባሆ በሚጨስበት አካባቢ አዘውትረው ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ የማያጨሱ ሰዎች በብሮንካይትና በሳንባ ምች እንዲሁም በተለያዩ ዓይነት ካንሰሮች የመያዛቸው ዕድል ከፍተኛ ነው። ትንባሆ በተጨሰበት ክፍል ውስጥ ለበርካታ ቀናት የሚቆየው ደስ የማይል ጠረን አደገኛ ነው ተብሎ አይታሰብም ነበር። ይሁን እንጂ ጽሑፉ እንዳለው “በጭስ በተሞሉ ክፍሎች ውስጥ የሚኖረው የአየር ብክለት መጠን ተሽከርካሪዎች በሚበዙባቸው አውራ ጎዳናዎች ከሚኖረው ብክለት ከስድስት ጊዜ እጥፍ ይበልጣል።” በተጨማሪም “በትንባሆ ጠንቅ ከሚሞቱ ስምንት ሰዎች መካከል አንዱ የሚሞተው ለትንባሆ ጭስ በመጋለጡ ምክንያት ነው” ይላል።

ምግብ ማብሰል—እየተረሳ ያለ ሙያ

በአውስትራሊያ አገር ኩዊንስላንድ በሚባል ግዛት 12 ወራት የፈጀ በአመጋገብ ልማድ ላይ የተደረገ ጥናት ምግብ ማብሰል እየተረሳ ያለ ሙያ ሳይሆን እንደማይቀር ገልጿል። ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች የሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች ለራሳቸው የሚመገቡትን ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስችል በቂ የሆነ ችሎታ እንደሌላቸው ዘ ኮሪየር ሜይል ሪፖርት አድርጓል። የሕዝብ ጤና አስተማሪና የጥናቱ አዘጋጅ የሆኑት ማርጋሬት ዊንጌት ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ወጣቶች በተለይም ልጃገረዶች ምግብ ማብሰልን እቤታቸው ከእናቶቻቸው አሊያም በትምህርት ቤት ይማሩ ነበር ብለዋል። ይሁን እንጂ ልጃገረዶችን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ብዙ ወጣቶች ምግብ እንዴት ማብሰል እንደሚቻል አያውቁም እንዲሁም ለመማር አይፈልጉም። ብዙዎቹ የታሸጉ ወይም ፈጣን ምግቦችን መመገብ ይመርጣሉ። አንዳንዶች እንዲህ ያለው የአመጋገብ ልማድ ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለስኳርና ለልብ በሽታ እንደሚዳርግ ያምናሉ።

አሁንም አሁንም መብላትና የጥርስ መበስበስ

ስኳርነት ያላቸውን ምግቦች አሁንም አሁንም ከመብላት መቆጠብ ጥርስ እንዳይበሰብስ ሊረዳ እንደሚችል ከታወቀ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ሃው ቱ ኪፕ ዩር ፋምሊ ስማይሊንግ የተባለው የጥርስ ጤንነት መመሪያ እንደሚለው መቼና ስንት ጊዜ እንደምንበላ ጥንቃቄ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ስኳርነት ወይም የተጣሩ ካርቦሃይድሬትነት ያላቸው ምግቦች ጥርስ ላይ ከሚገኝ ችክ ጋር በሚገናኙበት ጊዜ አሲድ ይፈጠራል። ብሮሹሩ እንደሚለው ይህ አሲድ ኢናመል የሚባለውን የጥርሳችሁን የውጭ ሽፋን 20 ደቂቃ ለሚያክል ጊዜ ይቦረቡራል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጥርሳችሁ ቀዳዳ ሊያበጅ ይችላል። ከዚህም በላይ “ይህ የሚሆነው ጣፋጭ ወይም ስታርችነት ያለው ምግብ በተመገባችሁ ቁጥር ነው።” ስለዚህ አሁንም አሁንም ከመብላት “አንድ ጊዜ ጨርሶ መብላት የተሻለ” ይሆናል። ምክንያቱም ጥርሳችሁ ለአሲድ የሚጋለጠው አንድ ጊዜ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። አንዱን ምግብ እየቆያችሁ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጎረስ የምታደርጉ ከሆነ አሲዱ ጥርሳችሁን የሚቦረቡርበት ጊዜ ይራዘማል። ጥርሳችሁ እንዳይበሰብስ ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ጥርሳችሁን እንድትቦርሹ የጥርስ ሐኪሞች ይመክራሉ። በተጨማሪም በየቀኑ በጥርስና ጥርስ መካከል በሚገባ ክር ተጠቅማችሁ ጥርሳችሁን ማጽዳታችሁን አትዘንጉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ