ከዓለም አካባቢ
ለምለም የስታድየም ሣር
ቪተሰ አርኔም ለተባለው የደች እግር ኳስ ክለብ የተገነባው 28,000 ሰዎች መያዝ የሚችለው ስታድየም በጥሩ ሣር የተሸፈነ የእግር ኳስ ሜዳና ከዳር እስከ ዳር ግጥም ብሎ የተዘረጋ ጣሪያ አለው። ሣር በጥሩ ሁኔታ ሊያድግ የሚችለው የተፈጥሮ ብርሃንና ዝናብ ሲያገኝ በመሆኑ እነዚህን ሁለት ገጽታዎች ማስታረቅ አስቸጋሪ ነው። ሣሩ እነዚህን ነገሮች ማግኘት ካልቻለ ወደ ቢጫነት ይለወጥና ይጠወልጋል። ይህ ችግር በግንባታው ንድፍ እልባት አግኝቷል ሲል ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። ከሥሩ የፕላስቲክ ምንጣፍ የተደረገለት የእግር ኳስ ሜዳው በሲሚንቶ ወለል ላይ ይቀመጣል። ጨዋታ በማይኖርበት ጊዜ 11,000 ቶን የሚመዝነው የእግር ኳስ ሜዳ በሃይድሮሊክ መሣሪያ አማካኝነት እንዳለ ከስታድየሙ ወጥቶ ግልጥ በሆነ ቦታ ላይ ሊቀመጥ ይችላል። ይህ አሠራር የሚያስገኘው ሌላ ጥቅም የስታድየሙን የሲሚንቶ ወለል ለሙዚቃ ትርዒት ማሳያነትና ለሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች መጠቀም መቻሉ ነው።
በዋጋ የማይተመነውን በዋጋ መተመን
ከበርካታ አገሮች የተውጣጡ አሥራ ሦስት ሳይንቲስቶች የተፈጥሮን ሀብት በዋጋ የተመኑበትን ሪፖርት አጠናቅረው ነበር። ሳይንቲስቶቹ ከእያንዳንዱ ሄክታር መሬት የሚገኘውን ጥቅም በዋጋ ለመተመን ከ100 የሚበልጡ በጽሑፍ የቀረቡ ጥናቶችን ተጠቅመዋል። (አንድ ሄክታር 10,000 ስኩዌር ሜትር ነው።) ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ረግረጋማ ቦታዎች ለቤቶችና ለሕንፃ ግንባታ መዋላቸው “ውኃ የሚያቁረውን መሬት እያመናመነው በመሆኑ” ረግረጋማ የሆነ አንድ ሄክታር መሬት ለግንባታ ሥራ መዋሉ “በዓመት ውስጥ በጎርፍ ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ከ3,300 እስከ 11,000 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ያደርገዋል” ሲል ሳይንስ መጽሔት አንድን ጥናት ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። ምንም እንኳ ብዙዎች የመሬትን ተፈጥሯዊ ምርትና ጥቅም አቅልለው የሚመለከቱት ቢሆንም ሳይንቲስቶቹ ይህ ከመሬት የሚገኘው ተፈጥሯዊ ምርትና ጥቅም በዓመት ውስጥ በገንዘብ ሲተመን 33,300,000,000,000 የአሜሪካን ዶላር እንደሚደርስ ገምተዋል። ይህ ደግሞ በዓመት ውስጥ በመላው ዓለም የሚመረተው ብሔራዊ ምርት ከሚያወጣው ዋጋ በእጥፍ ገደማ ይበልጣል።
አፈናን በተመለከተ የሚሰጥ ትምህርት
በአሁኑ ጊዜ በታይዋን ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ልጆች አፈናን በተመለከተ ትምህርት የሚሰጥበት አዲስ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ይከታተላሉ። “የታይዋን ልጆች ታፍኖ ለመወሰድ ያላቸው ዕድል ከፊሊፒንስ በስተቀር ከማንኛውም አገር የበለጠ ነው። በአማካይ በየሁለት ቀን ተኩል ውስጥ አንድ ልጅ ታፍኖ ይወሰዳል” ይላል ኤዥያዊክ። የወንጀል መጠን እየጨመረ በመሄዱ የራሳቸውም ልጆች የዚህ ዕጣ ተካፋዮች መሆናቸው እንደማይቀር ያሳሰባቸው ወላጆች ይህ ፕሮግራም እንዲጀመር ጠይቀዋል። በዚህ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ልጆች ብቻቸውን ሲሄዱ፣ አሳንሰር ውስጥ ሲገቡና በሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ ሲሳፈሩ መውሰድ ስለሚኖርባቸው ጥንቃቄዎች ይማራሉ። አጠራጣሪ የሆኑ ሰዎችን በንቃት እንዲከታተሉና ታፍነው ከተወሰዱም ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል። ትምህርቱ ደስ የማያሰኝ ገጽታ ቢኖረውም ልጆች ለሕይወት ብሩሕ አመለካከት እንዲኖራቸው ለመርዳት ጥረት ይደረጋል።
ሦስት የተለያዩ የታሪክ አመለካከቶች
በቦስኒያ የሚገኙ ተማሪዎች የክልሉን ታሪክ፣ ኪነ ጥበብና ቋንቋ በተመለከተ የሚማሩት ትምህርት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሦስት ዓይነት አመለካከቶች ይንጸባረቁበታል። የሚማሩት ትምህርት የተመካው ሥርዓተ ትምህርቱን በሚመሩት ሦስት ዋና ዋና የጎሳ ቡድኖች ላይ ነው ሲል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ለምሳሌ ያህል ሰርቦች በሚቆጣጠሩት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ክልል የሚገኙ ተማሪዎች የኦስትሪያውን መስፍን ፈርዲናንትን በ1914 የገደለውና አንደኛውን የዓለም ጦርነት የቀሰቀሰው ሰው “ጀግናና ባለቅኔ” እንደሆነ ይማራሉ። የሮማ ካቶሊክ ተከታዮች የሆኑት የክሮሽያ ተማሪዎች ደግሞ ይህ ሰው “ይህን የሽብርተኝነት ተግባር እንዲፈጽም በሰርቦች ሥልጠናና መመሪያ የተሰጠው ነፍሰ ገዳይ” እንደሆነ ይነገራቸዋል። ስለዚህ ክንውን የሚተርከው የሙስሊሙ ታሪክ ደግሞ “ከሦስቱም የጎሳ ቡድኖች የተውጣጣ የፖሊስ ኃይል ብቻ ሊገታው የቻለውን ፀረ-ሰርቦች ረብሻ የቆሰቆሰ ድርጊት የፈጸመ የብሔረተኝነት ስሜት ያለው” ሰው አድርጎ ይገልጸዋል። በዘር ተለይተው በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ለማስተማር እንዲቻል ሲባል ተማሪዎቹ ሰርቦች፣ ሙስሊሞች አለዚያም ደግሞ ክሮአቶች መሆናቸውን ለይተው እንዲናገሩ የሚጠየቁ መሆኑን ዘገባው ይገልጻል።
ፍቅር አይወድቅም
“ከወላጆቻቸውና ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ጠንካራ ፍቅራዊ ትስስር ያላቸው አፍላ ጎረምሶች አልኮል ጠጪዎችና የአደገኛ ዕፅ ተጠቃሚዎች የመሆን፣ ራስን የመግደል ሙከራ የማድረግ፣ ጠበኛ የመሆን ወይም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ወሲባዊ ድርጊት የመፈጸም ዕድላቸው በጣም አነስተኛ ነው” ሲል ዘ ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። በተጨማሪም የሚነሶታ ዩኒቨርሲቲና በቻፐል ሂል የኖርዝ ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ልጁ የሚኖርበት ቤተሰብ በአንድ ወላጅ ወይም በሁለት ወላጆች የሚተዳደር መሆኑ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ተገንዝበዋል። አስፈላጊው ነገር ልጁ የሚወደድና የሚፈለግ መሆኑ እንዲሰማው መደረጉና ስሜቱን የሚረዳለት ሰው ማግኘቱ ነው። ጥናቱ ጠበቅ አድርጎ የገለጸው ሌላው ነገር “ወላጆች በልጁ አስተዳደግ ረገድ የነበራቸው ሚና ወደማብቃቱ እንደተቃረበ በሚሰማቸው ጊዜ ሳይቀር የአፍላ ጉርምስና ሕይወቱን እንዴት በመምራት ላይ እንደሚገኝ የቅርብ ክትትል ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን ነው” ይላል ፖስት።
አምላክ የሌለበት መጽሐፍ ቅዱስ
አንድ ዴንማርካዊ ሐኪም አምላክን ጨርሶ የማያነሳ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም አዘጋጅተው አሳትመዋል። ዶክተር ስቬን ሊንግስ አምላክና እምነት “ዘመን ያለፈባቸውና ነጻነታችንን ከመገደብ በቀር ምንም ፋይዳ የሌላቸው ነገሮች ናቸው” ብለው እንደሚያምኑ ክሪስተሊት ዳውብለት የተባለው የዴንማርክ ጋዜጣ ዘግቧል። ሊንግስ ብዙ ሰዎች ደስታ የራቃቸውና የብቸኝነት ስሜት ያጠቃቸው እንደሆኑ ይናገራሉ። “የምንኖረው በአይሁድና በክርስትና ጥምር ባሕል ውስጥ ነው። በመሆኑም ደስታ ያሳጣን ይኸው የአይሁድና የክርስትና ባሕል መሆን አለበት” ይላሉ። ሊንግስ ይህን አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉማቸውን ያዘጋጁበት ዓላማ “የባሕላችንን መሠረት ጨርሶ ለመናድ” ነው ሲል ጋዜጣው ዘግቧል። ሊንግስ ባዘጋጁት አምላክ የሌለበት መጽሐፍ ቅዱስ ዘፍጥረት 3:12 እንዲህ ይነበባል:- “አዳም እንዲህ ሲል አሰበ:- ‘ከአጠገቤ ያለችው ሴት ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ።’” ክሪስተሊት ዳውብለት “ታዲያ ይህ የሚቀረውን ነገር ለማየት ሲባል በአንድ የበረዶ ቅንጣት ውስጥ ያለውን ውኃ ለማስወገድ እንደመሞከር አይቆጠርምን?” ሲል ጠይቋል።
ላቲን ገና አልሞተም
ላቲን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቅዳሴ የሚፈጸምበት ቋንቋ መሆኑ የቀረው በ1960ዎቹ ዓመታት ቢሆንም አሁንም የቫቲካን ከተማ ኦፊሴላዊ ቋንቋ ነው። ከመንበረ ጵጵስናው የሚወጡ ሰነዶች ለዚሁ ሥራ በተመደቡ ሊቃውንት ከመተርጎማቸው በስተቀር በከተማይቱ ውስጥ እምብዛም አይሠራበትም። ይሁን እንጂ በኅዳር ወር 1997 ሊቀ ጳጳሱ የላቲን ተናጋሪዎች እያነሱ መሄድ ያሳዘናቸው መሆኑን ከገለጹ በኋላ በዚህ ረገድ መሻሻል እንዲደረግ ተማጽነዋል። በዚሁ ወቅት አንድ የቫቲካን ምሁራን ቡድን ስምንት ዓመት የፈጀበትን ዘመናዊ የላቲን መዝገበ ቃላት አሳትሞ አውጥቷል። ባሁኑ ጊዜ እንደ “ፍሊት”፣ “የአውሮፕላን ማረፊያ”፣ “የገበያ አዳራሽ”፣ “ታክሲ” እና “የትራፊክ መጨናነቅ” ያሉት ቃላት የላቲን አቻቸውን አግኝተዋል። በዛሬው ጊዜ በሰፊው የተሠራጨው ተንቀሳቃሽ ቴሌፎን እንኳን ቴሌፎንየም ቼሉላሬ የሚል ስያሜ አግኝቷል። ለላቲን አፍቃሪዎች ሌላም የምሥራች አለ። በሮም የሚኖሩ አንድ ቄስ በኢንተርኔት ላይ የላቲን ቋንቋ መረጃ የሚሰጥ የዌብ ሳይት እንደጀመሩ የለንደኑ ዘ ታይምስ ዘግቧል።
የዓለማችን ረጅሙ ፀጉር
በሰሜናዊ ታይላንድ የሚኖሩትና የሆንግ ጎሣ አባል የሆኑት ሁ ሳቲኦ የ85 ዓመት አረጋዊ ሲሆኑ ወደ 70 ለሚጠጉ ዓመታት ያክል ፀጉራቸውን አልቆረጡትም። “አሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ ቆርጬው ነበር፤ ግን በጣም ታመምኩ” ሲሉ ሁ ገልጸዋል። በቅርቡ የጊነስ ቡክ ኦቭ ወርልድ ሪከርድስ ተወካይ በሆነ ሰው ሲለካ 5 ሜትር ከ20 ሴንቲ ሜትር የደረሰው ፀጉራቸው የዓለማችን ረጅሙ ፀጉር ነው ተብሎ እንደሚታመን አሶሲዬትድ ፕረስ ዘግቧል። ሁ ፀጉራቸውን የሚያጥቡት በዓመት አንዴ ሲሆን በእንጨት ርብራብ ላይ አስጥተው ያደርቁታል። የቅርብ ተፎካካሪያቸው የ87 ዓመት ወንድማቸው ዪ ሲሆኑ እሳቸው ደግሞ ፀጉራቸውን ለመጨረሻ ጊዜ የቆረጡት በ1957 ነው። ሆኖም የዪ ፀጉር ከዚህ ቀደም ሪኮርዱን ይዘውት ከነበሩትና 4 ሜትር ከ20 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ፀጉር ካላቸው ሕንዳዊት ሴት ፀጉር ይበልጣል። ሁ እንዲህ ያለ ረጅም ፀጉር በተለይ ቅዝቃዜ ባለባቸው የታይላንድ ተራራማ ቦታዎች ለሚኖር ሰው ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አላቸው። “ሙቀት ይሰጠኛል” ይላሉ።
የተመጣጠነ ምግብ ጉድለት ሕፃናትን እየጨረሰ ነው
“ከማንኛውም ወረርሽኝ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ወይም ጦርነት ይበልጥ ለበርካታ ሕፃናት መሞት ምክንያት የሆነው የተመጣጠነ ምግብ ጉድለት” እንደሆነ የፈረንሳይ ዕለታዊ ጋዜጣ የሆነው ለ ሞንድ ዘግቧል። በየዓመቱ ሰባት ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት እንደሚሞቱ ይገመታል። የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የ1997 ሪፖርት እንደሚያመለክተው በየዓመቱ አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ከሚሞቱት 12 ሚልዮን ሕፃናት መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት የሚሞቱት በተመጣጠነ ምግብ ጉድለት ምክንያት ነው። የምግብ አለመመጣጠን ለሕፃናት ሞት ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ ለበርካታ አካላዊና አእምሮአዊ ጉድለቶች እንዲሁም ለሰውነት የበሽታ መከላከል አቅም መዳከም ምክንያት ሆኗል። በደቡብ እስያ ከ2 ልጆች መካከል አንዱ በምግብ አለመመጣጠን የሚጠቃ ሲሆን በአፍሪካ ከ3 ልጆች አንዱ በዚሁ ችግር ይጠቃል። በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮችም ቢሆኑ ከዚህ ችግር አላመለጡም። ለምሳሌ በዩናይትድ ስቴትስ ከ12 ዓመት በታች ከሚገኙ 4 ሕፃናት መካከል አንዱ የሚያስፈልገውን የተመጣጠነ ምግብ እንደማያገኝ ዩኒሴፍ ዘግቧል።
ጨረቃ ላይ ውኃ?
ሉናር ፕሮስፔክተር የተባለችው የጠፈር መንኮራኩር በጨረቃ ዋልታ አካባቢ በረዶ የሆነ ውኃ መሳይ ነገር እንዳገኘች ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። በመንኮራኩሪቱ ላይ የተገጠሙ መሣሪያዎች ሃይድሮጅን መኖሩን ያመለከቱ ሲሆን ሃይድሮጅን የውኃ ክፍል ሆኖ ካልሆነ በስተቀር ጨረቃ ላይ ሊኖር የሚችልበት ሌላ መንገድ እንደሌለ ይታሰባል። ይህ ውኃ ከአቧራ ቅንጣቶች ጋር በተደባለቁ ጥቃቅን የበረዶ ቅንጣቶች መልክ ሊኖር እንደሚችል ይታመናል። እነዚህ የበረዶ ቅንጣቶች የዓለታማው አፈር 1 በመቶ የሚሆኑ ይመስላል። አንዳንድ ሳይንቲስቶች ይህ ውኃ ሰዎችን ሊያኖር እንደሚችልና ከጨረቃ ለሚላኩ የጠፈር መንኮራኩሮች ነዳጅ የሚሆን ሃይድሮጅንና ኦክስጅን ሊያስገኝ እንደሚችል መተንበይ ጀምረዋል። ሌሎች ደግሞ ውኃ ቢኖርም ውኃውን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚጠይቀው ወጪ የሚያዋጣ አይሆንም ብለው ያስባሉ። የካሊፎርንያ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ብሩስ ሙሬይ ከጨረቃ ውኃ ከማውጣት ከምድር ጭኖ መውሰድ ይቀላል ብለዋል።