ኤድስ ለወደፊቱስ ምን ተስፋ አለ?
ከኤች አይ ቪ ኢንፌክሽን የሚፈውሱ ወይም የሚከላከሉ መድኃኒቶች ካለመኖራቸው በተጨማሪ በሽታውን መቆጣጠር አስቸጋሪ እንዲሆን ያደረጉ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። አንደኛው ምክንያት ብዙ ሰዎች የአኗኗር ዘይቤአቸውን ለመለወጥ እምቢተኛ መሆናቸውና በዚህ ምክንያት የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ በመጨረሻው የኤድስ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም በቫይረሱ የሚለከፉ ሰዎች ቁጥር ግን አልቀነሰም። ምክንያቱ “ብዙ ሰዎች ከበሽታው ስለመጠበቅ የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆናቸው” እንደሆነ አሶሲዬትድ ፕሬስ ገልጿል።
በኤች አይ ቪ ከተመረዙ ሰዎች መካከል 93 በመቶ የሚሆኑት ይኖሩባቸዋል በሚባሉት ያልበለጸጉ አገሮች በሽታውን በመዋጋት ረገድ ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች አጋጥመዋል። ከእነዚህ አገሮች መካከል አብዛኞቹ መሠረታዊ የሆኑ የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶችን እንኳን ለሕዝቦቻቸው ሊያዳርሱ አልቻሉም። አዳዲሶቹ መድኃኒቶች ወደ እነዚህ አገሮች ሊደርሱ አይችሉም እንጂ፣ ቢደርሱ እንኳን የአንዱ ዓመት ሕክምና ብቻ ብዙ ሰዎች ዕድሜ ልካቸውን ሠርተው ከሚያገኙት ገንዘብ የበለጠ ወጪ የሚጠይቅ ይሆናል።
እንዲህም ሆኖ፣ በሽታውን የሚያድን ዋጋው ያልተወደደ አዲስ መድኃኒት ተገኘ ብለን እናስብ። ይህ መድኃኒት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በሙሉ ሊዳረስ ይችላል? አይችል ይሆናል። በየዓመቱ በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ሪፖርት መሠረት አራት ሚልዮን የሚያክሉ ሕፃናት ውድ ባልሆኑና በቀላሉ ሊገኙ በሚችሉ ክትባቶች ሊወገዱ በሚችሉ አምስት በሽታዎች ምክንያት ይሞታሉ።
ለሕክምና የሚያስፈልጉት መድኃኒቶች ሊገኙ በማይችሉባቸው አገሮች የሚኖሩ በበሽታው የተመረዙ ሰዎችስ? በሳንታ ክሩዝ፣ ካሊፎርንያ የሚኖሩትና የዓለም አቀፍ ጤና ፕሮግራም ባልደረባ የሆኑት ሩት ሞታ በደርዘን በሚቆጠሩ ታዳጊ አገሮች የኤች አይ ቪ መከላከያና እንክብካቤ ፕራግራሞች እንዲቋቋሙ እርዳታ አድርገዋል። እንዲህ ይላሉ:- “ከተሞክሮዬ እንዳገኘሁት ብሩሕ አመለካከት መያዝ መድኃኒት ለማግኘት ከመቻል ያላነሰ አስፈላጊነት አለው። ምንም ዓይነት መድኃኒት ሳይወስዱ ከኤች አይ ቪ ጋር ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊኖሩ የቻሉ ሰዎች አውቃለሁ። መድኃኒት የሚሰጠው ጥቅም ቢኖርም ወደ ሰውነታችሁ ኬሚካሎች ስላስገባችሁ ብቻ አትፈወሱም። የሚኖራችሁ አስተሳሰብ፣ ማኅበራዊ ድጋፍ ማግኘት፣ መንፈሳዊነትና ጥሩ አመጋገብ አስፈላጊነት አላቸው።”
መፍትሔ ይገኛል
ኤድስ አንድ ቀን ይሸነፋል ብለን ተስፋ እንድናደርግ የሚያስችል ምክንያት ይኖራል? አዎን፣ አለ። ብዙ ሰዎች የጌታ ጸሎት ወይም ‘አቡነ ዘበሰማያት’ ብለው በሚጠሩት ጸሎት ውስጥ ከሁሉ የተሻለው ተስፋ ይገኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ በሚገኘው በዚህ ጸሎት ውስጥ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ በምድር ላይ ደግሞ እንዲሆን እንለምናለን። (ማቴዎስ 6:9, 10) የሰው ልጆች ለዘላለም በበሽታ እየማቀቁ እንዲኖሩ የአምላክ ፈቃድ አይደለም። አምላክ ለዚህ ጸሎት መልስ ይሰጣል። ኤድስን ብቻ ሳይሆን የሰውን ልጅ እየረፈረፉ የሚገኙትን ሌሎች በሽታዎች በሙሉ ያጠፋል። ከዚያም “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24
ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን ከመከላከል የተሻለ ልናደርግ የምንችለው ነገር የለም። ብዙዎቹ በሽታዎች ሁለት አማራጮች አሏቸው። አስቀድሞ መከላከል ወይም ታክሞ መዳን ይቻላል። በኤች አይ ቪ ረገድ ግን ምርጫው አንድ ብቻ ነው። መከላከል ይቻላል፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ታክሞ መዳን አይቻልም። ሕይወትህን ለአደጋ ለምን ታጋልጣለህ? በእርግጥ ታምሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ይሻላል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ወደ ሰውነታችሁ ኬሚካሎች ስላስገባችሁ ብቻ አትፈወሱም። የሚኖራችሁ አስተሳሰብ፣ ማኅበራዊ ድጋፍ ማግኘት፣ መንፈሳዊነትና ጥሩ አመጋገብ አስፈላጊነት አላቸው።”—ሩት ሞታ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
“በእርግጥ የሚደነቅ ጉባኤ ነው”
ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ” ሲል ክርስቲያኖችን አጥብቆ መክሯል። (ገላትያ 6:10) በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው የካረን እናት ልጅዋ የምትገኝበት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ካረንና ቢል ኤች አይ ቪ እንደያዛቸው ሲያውቅ ያደረገውን ስትናገር እንዲህ ብላለች:- “በእርግጥ የሚደነቅ ጉባኤ ነው። ቢል ሳንባ ምች ይዞት በተኛበት ጊዜ ካረንም አሟት ስለነበር ባልዋን ለማስታመምና ልጆቿን ለመንከባከብ ትታገል ነበር። ወንድሞች ቤታቸውን አጸዱላቸው፣ መኪናቸውን ጠገኑላቸው፣ ልብሶቻቸውን አጠቡላቸው። ሕግ ነክ ጉዳዮቻቸውን አስፈጸሙላቸው፣ ወደ ሌላ ቤት እንዲዛወሩም ረዷቸው። ምግብ ገዝተው አበሰሉላቸው። ከልባቸው ስሜታዊ፣ መንፈሳዊና፣ ቁሳዊ ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል።”
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው ታማኝ በመሆን ከኤች አይ ቪ ሊርቁ ይችላሉ