ቪክቶሪያ ሐይቅ በደረቅ ምድር የተከበበ ታላቁ የአፍሪካ ባሕር
ኬንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በ1858 አንድ ብቸኛ የሆነ እንግሊዛዊ ተጓዥ በአፍሪካ እምብርት በሚገኝ ገና ያልታሰሰ አካባቢ ይጓዛል። ጥቂት አፍሪካዊ ተሸካሚዎችን ብቻ ያስከተለውና በበሽታ፣ በድካምና ከፊቱ ምን እንደሚጠብቀው ባለማወቅ የተጎሳቆለው ይህ ሰው ሰዎቹን በርቱ እያለ ወደፊት ይገፋል። ጆን ሃኒን ስፒክ የናይልን መፍለቂያ ለማግኘት ነበር የሚጓዘው።
ስፒክን ያነሳሳው ከአረባውያን ባሪያ ፈንጋዮች የሰማው ኡኬሬዌ የሚባል በደረቅ ምድር የተከበበ በጣም ትልቅ ባሕር እንዳለ የሚገልጽ ታሪክ ሲሆን ማለቂያ የሚኖረው የማይመስለውን ቁጥቋጧማ አካባቢ ለማቋረጥ መታገሉን ቀጠለ። በመጨረሻም ከ25 ቀን ጉዞ በኋላ እነዚህ ጥቂት ተጓዦች በጣም አስደናቂ ነገር ለማየት በመቻላቸው ድካማቸው ሁሉ ተካሰ። ከፊት ለፊታቸው ዳርቻው ሊታይ የማይችል በጣም ሰፊና ጨዋማ ያልሆነ ባሕር ተንጣሏል። ስፒክ ከጊዜ በኋላ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ከእግሬ በታች ያለው ሐይቅ ስለ ምንጩ ብዙ ግምታዊ ሐሳብ የተሰጠበትና ብዙ አሳሾች ሲፈልጉት የቆዩት ወንዝ መወለጃ እንደሆነ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አልነበረኝም።” ይህን ያገኘውን ሐይቅ በጊዜው የእንግሊዝ ንግሥት በነበረችው በቪክቶሪያ ስም ሰየመው።
የናይል ምንጭ
ዛሬም በዚሁ ስም የሚጠራው ይህ ሐይቅ በስፋቱ ከዓለም ሁለተኛው ጨዋማ ያልሆነ ሐይቅ እንደሆነ ሲታወቅ የሚበልጠው በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ሱፒርየር ሐይቅ ብቻ ነው። የሐሩር አካባቢውን የፀሐይ ብርሃን እንደ አንድ ግዙፍ መስተዋት የሚያንጸባርቀው በሰፊው እንደ መስተዋት ተንጣልሎ የተኛው ቪክቶሪያ ሐይቅ 69,484 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሥፍራ ይሸፍናል። ሰሜናዊ ዳርቻውን የምድር መቀነት የሚያቋርጠው ሲሆን በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ምሥራቃዊና ምዕራባዊ ክንዶች መካከል ይገኛል። በአብዛኛው የሚገኘው በታንዛንያና በኡጋንዳ ክልል ውስጥ ሲሆን ከኬንያም ጋር ይዋሰናል።
የሐይቁ ዋነኛ መጋቢ ወንዝ በሩዋንዳ ተራሮች የሚገኙትን ወንዞች ሰብስቦ የሚወርደውና በታንዛንያ የሚገኘው ካጌራ ወንዝ ነው። ይሁን እንጂ ቪክቶሪያ ሐይቅ አብዛኛውን ውኃ የሚያገኘው የ200,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው የአካባቢው ረባዳ መሬት ላይ ከሚጠራቀመው ዝናብ ነው። ያለው መፍሰሻ አንድ ብቻ ሲሆን እርሱም በጂንጃ፣ ኡጋንዳ የሚገኘው ነው። በዚህ ቦታ ወንዙ ወደ ሰሜን ይፈስና ለነጭ አባይ መፈጠር ምክንያት ይሆናል። የናይል ወንዝ ምንጭ ቪክቶሪያ ሐይቅ ብቻ ባይሆንም ወንዙ ዓመቱን በሙሉ እንዲፈስና እስከ ግብጽ ድረስ ዘልቆ የበርካታ ነፍሳትን ሕይወት እንዲደግፍ የሚያስችለው በቂ የውኃ ክምችት እንዲኖር የሚያደርገው ይኸው ሐይቅ ነው።
በሐይቁ አካባቢ ያለው ሕይወት
ቀጥ ያለ የቢራቢሮ ክንፍ የሚመስል ነጭ ሸራ የሚያርገበግበው ጀልባ ሐይቁን ሰንጥቆ ያልፋል። ይህች ትንሽ ጀልባ በየቀኑ ከደረቁ ምድር በሚመጣ ነፋስ እየተገፋች ወደ ሐይቁ እምብርት ትደርሳለች። እኩለ ቀን ሲሆን የንፋሱ አቅጣጫ ስለሚቀየር እየገፋ ወደመጣችበት ቦታ ይመልሳታል። የሐይቁ ዓሣ አስጋሪዎች በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በዚህ ዓይነት ሲመላለሱ ኖረዋል።
በቪክቶሪያ ሐይቅ ዙሪያ እጅብ ያሉ ቡናማ መልክ ያላቸው ባለ ሣር ክዳን ቤቶች የሚገኙባቸው በርካታ መንደሮች አሉ። እነዚህ በናይል ዙሪያ የሚኖሩ መንደርተኞች ዋነኛ ምግባቸው ዓሣ ሲሆን መተዳደሪያቸውን የሚያገኙት ከሐይቁ ነው። አንድ ዓሣ አስጋሪ ዕለታዊ ሥራውን የሚጀምረው ጀንበር ከመውጣትዋ በፊት ነው። ወንዶቹ ውኃ በሚያስገባው ጀልባቸው ውስጥ ተጠራቅሞ ያደረውን ውኃ ቀድተው ካፈሰሱ በኋላ ገና ወገግ ሳይል ጉዟቸውን ይጀምራሉ። በኅብረት እየዘፈኑ ወደ ጥልቁ ባሕር ከደረሱ በኋላ አሮጌ ሸራቸውን ይወጥራሉ። ሴቶቹ ትናንሾቹ ጀልባዎች ከዓይናቸው ርቀው በአድማሱ ውስጥ እስኪሰወሩ ድረስ ቆመው ይመለከታሉ። ግን ብዙ ሥራ ስለሚጠብቃቸው ወዲያው ይመለሳሉ።
ትናንሽ ልጆች በሐይቁ ዳር ባለው ውኃ እየተንቦራጨቁ ሲጫወቱ ሴቶች ልብስ ያጥባሉ፣ ለመጠጥ የሚሆን ውኃ ይቀዳሉ። በመጨረሻም በሐይቁ ዳር የሚያከናውኑት ሥራ ይጠናቀቃል። እንስራቸውን አናታቸው ላይ አስቀምጠው፣ ልጆቻቸውን ጀርባቸው ላይ አዝለውና የታጠቡ ልብሶች ያሉባቸውን ቅርጫቶች በሁለቱም እጆቻቸው ይዘው ወደየቤታቸው ያዘግማሉ። እንደደረሱም በጓሯቸው ያለውን የበቆሎና የባቄላ አነስተኛ ማሳ ይኮተኩታሉ፣ ማገዶ ይለቅማሉ እንዲሁም እበትና አመድ ቀላቅለው የጭቃ ቤታቸውን ይጠጋግናሉ። ከሐይቁ ዳርቻ ራቅ ብሎ ሴቶች ቃጫ እየገመዱ የሚያማምሩ ቅርጫቶችና ጠንካራ ገመዶች ይሠራሉ። አንዳንድ ወንዶች ትልቅ ዛፍ ጥለው ጀልባ ለመሥራት እንጨታቸውን ሲጠርቡ ከሩቅ ይሰማል።
ምሽቱ እየተቃረበ ለዓይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር የሴቶቹ ዓይን ወደ ሰፊው ባሕር በድጋሚ ማቅናት ይጀምራል። ከአድማስ ባሻገር የሚታዩት የሸራዎቹ ጫፍ የወንዶቹን መመለስ ያበስራል። ባሎቻቸውንና የሚያመጧቸውን ዓሣዎች ለማየት ስለሚጓጉ ይህ በናፍቆት የሚጠብቁት ነገር ነው።
በሐይቆቹ ዳርቻዎች ዙሪያና በደሴቶቹ የሚኖሩት እነዚህ ትናንሽ ማኅበረሰቦች የሰላም መልእክት የሚያደርሱላቸውን ጎብኚዎች በመቀበል ላይ ናቸው። እያንዳንዱ መንደርና ሠፈር በእግርና በጀልባ ተዳርሷል። ሰዎቹ ትሁቶችና የመስማት ጉጉት ያላቸው ናቸው። በተለይ በገዛ ራሳቸው ቋንቋዎች በናይሎቲክና በባንቱ የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎችን ለማንበብ በጣም ደስተኞች ናቸው።
የውኃ ውስጥ እንስሳት
በቪክቶሪያ ሐይቅ ከ400 የሚበልጡ የዓሣ ዝርያዎች ሲኖሩ አንዳንዶቹ ደግሞ በማንኛውም የዓለም ክፍል የማይገኙ ናቸው። ከሁሉም ይበልጥ በብዛት የሚገኘው ሲችሊድ የሚባለው ዝርያ ነው። እነዚህ ባለ ብዙ ቀለም ትናንሽ ዓሦች እንደ ባለ ችቦ ጀርባ፣ ቀይማ ወይን ጠጅና የኪሱሙ ባለ እንቁራሪት አፍ የሚሉ መልካቸውን የሚያመለክቱ ስሞች አሏቸው። አንዳንድ ሲችሊዶች ልጆቻቸውን ከአደጋ የሚከላከሉበት የተለየ ዓይነት ዘዴ አላቸው። አደገኛ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ወላጂቱ ዓሣ አፏን በሰፊው ትከፍትና ልጆቿ ተሯሩጠው ይገባሉ። አደገኛው ሁኔታ ካለፈ በኋላ ትተፋቸውና ወደ ወትሮ እንቅስቃሴያቸው ይመለሳሉ።
ቪክቶሪያ ሐይቅ ዓይነታቸው በርካታ የሆኑ አስደናቂ የባሕር ላይ አእዋፍ መኖሪያ ነው። ግሬቤ፣ ኮርሞራንትና አንሂንጋ የሚባሉት ወፎች ወደ ባሕር ተወርውረው ይገቡና ሹል በሆነ አፋቸው ወግተው ዓሦችን ይይዛሉ። ክሬን፣ ሄሮን፣ ስቶርክ እና ስፑንቢል የሚባሉት አእዋፍ ደግሞ ወደ ባሕሩ ጠልቀው ሳይገቡ ከዳር አድፍጠው ይቆሙና በአጠገባቸው የምታልፈውን ዓሣ ለማጥመድ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ። ከላይ ደግሞ በርካታ ፔሊካኖች እንደ አውሮፕላን ያንዣብባሉ። በርካታ ፔሊካኖች አንድ ላይ ሆነው በሚዋኙበት ጊዜ አንድ ላይ እጅብ ያሉ ዓሦችን ከብበው ከያዙ በኋላ ቅርጫት በሚመስሉት ትላልቅ ምንቃራቸው ይዘው ያወጧቸዋል። ሰማዩን በበላይነት የሚቆጣጠረው ግን ጠንካራ ክንፎች ያሉት የዓሣ ንሥር ነው። ከባሕሩ በላይ ከሚገኝ ከአንድ የዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ይነሳና በጠንካራ ክንፎቹ ከፍተኛ የሆነ የሽውታ ድምፅ እያሰማ በከፍተኛ ፍጥነት ይወረወርና በሐይቁ ላይ የምትገኘውን ዓሣ አለብዙ ችግር ለቀም ያደርጋል። ደማቅ ቀለም ያላቸው ዊቨርበርድ የሚባሉት ወፎች በሐይቁ ዳርቻ በሚገኘው ጥቅጥቅ ያለ ደንገል ውስጥ ጎጆአቸውን ሠርተው ይኖራሉ። ሆርንቢል የሚባሉት ወፎች የወዮታ ድምፅ ደግሞ ከባሕሩ ዳርቻ ራቅ ብሎ እስከሚገኘው የግራር ጫካ ድረስ ይሰማል።
በማለዳና በምሽት ሰዓቶች የጉማሬዎች ጎርናና ጩኸት ጸጥ ባለው ሐይቅ ላይ ያስተጋባል። እኩለ ቀን ሲሆን በባሕሩ ዳርቻ አካባቢ ግማሽ ሰውነታቸውን ውኃ ውስጥ ቀብረውና የተስተካከለ ግራጫ ዲብ መስለው እንቅልፋቸውን ይተኛሉ። በሐይቁ ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች አደገኛ ከሆነው የናይል አዞ በጣም ይጠነቀቃሉ። እነዚህ አስፈሪ ገበሎ አስተኔዎች ከአብዛኛው የቪክቶሪያ ሐይቅ አካባቢ በሰዎች ቢባረሩም በአንዳንድ ራቅ ያሉ አካባቢዎች አሁንም ይገኛሉ።
በችግር ላይ የሚገኝ ባሕር
የአፍሪካ ሕዝብ ጆን ስፒክ ቪክቶሪያን ለመጀመሪያ ጊዜ ካየበት ጊዜ ይበልጥ በጣም ጨምሯል። በሐይቁ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩት ሰዎች ብዛት በአሁኑ ጊዜ ከ30 ሚልዮን በላይ የደረሰ ሲሆን የእነዚህ ሁሉ ሕልውና በሐይቁ ላይ የተመካ ነው። በቀድሞዎቹ ዘመናት የአካባቢው ዓሣ አጥማጆች የሚጠቀሙት ባሕላዊ በሆኑ ዓሣ የማስገር ዘዴዎች ነበር። በዓሣ ወጥመዶች፣ ከደንገል በተሠሩ መረቦች፣ በመንጠቆዎችና በጦሮች በመጠቀም የሚያስፈልጓቸውን ያህል ዓሣዎች ብቻ ይይዙ ነበር። ዛሬ ግን በረዥም ርቀት ሊዘረጉና ወደ ባሕር ጠልቀው ገብተው በቶን የሚመዘን በጣም ብዙ ዓሦችን ጠራርገው ሊያወጡ የሚችሉ መረቦች በመሠራታቸው የሐይቁ ሥነ ምህዳር በከባድ ሥጋት ላይ ወድቋል።
ለአካባቢው ባዕዳን የሆኑ የዓሣ ዝርያዎች መራባት መጀመራቸውም በቀድሞዎቹ የዓሣ ዝርያዎች ላይ ችግር አስከትሏል። ሃያሲንት የሚባሉት የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ውብ አበባ የሚያወጡ የባሕር ላይ ተንሳፋፊ እጸዋትም ለሐይቁ ተጨማሪ ወዮታ ሆነውበታል። ይህ ከደቡብ አሜሪካ የመጣው የአረም ዝርያ እድገቱ በጣም ፈጣን በመሆኑ በጣም ሰፊ የሆኑ የሐይቁን ዳርቻዎችና መግቢያዎች ሊሸፍን ችሏል። በዚህም ምክንያት የጭነት፣ የመንገደኞችና የዓሣ ማስገሪያ ጀልባዎች ወደ እነዚህ አካባቢዎች መድረስ አቅቷቸዋል። በሐይቁ አካባቢ ያለው ረባዳ አካባቢ የፍሳሽ ቆሻሻ መድፊያ በመሆኑ፣ በአካባቢው የነበረው ደን በመመናመኑና በኢንዱስትሪ መስፋፋት ምክንያት የሐይቁ የወደፊት ዕጣ ሥጋት ላይ ወድቋል።
ታዲያ ቪክቶሪያ ሐይቅ ከጥፋት ይተርፍ ይሆን? ይህ ብዙዎችን በማከራከር ላይ የሚገኝ ጥያቄ ሲሆን እነዚህ ሁሉ በርካታ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ሰው የለም። ይሁን እንጂ ቪክቶሪያ ሐይቅ የአምላክ መንግሥት ‘ምድርን የሚያጠፉትን ካጠፋ’ በኋላ ለበርካታ ዘመናት በምድር ላይ የሚቆይ የተፈጥሮ ገጽታ ሳይሆን አይቀርም። (ራእይ 11:18) በዚያ ጊዜ የሰው ልጅ ይህን በደረቅ ምድር የተከበበ ታላቅ የአፍሪካ ባሕር ውበት ለዘላለም ለማድነቅ ይችላል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሐይቁን በመዋጥ ላይ የሚገኘው ዓሣ
ብዙ ቅባት አለው፣ በልቶ በቃኝ አይልም፣ በፍጥነት መራባት ይችላል፣ ቁመቱ እስከ ስድስት ጫማ ይደርሳል። ይህ ምንድን ነው? ላተስ ኒሎቲከስ ይባላል! በአብዛኛው ናይል ፐርች ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ግዙፍና ሆዳም ዓሣ ወደ ቪክቶሪያ ሐይቅ ገብቶ መራባት የጀመረው በ1950ዎቹ ዓመታት ሲሆን በሐይቁ ሥነ ምህዳር ላይ ከፍተኛ አደጋ አስከትሏል። በ40 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከሐይቁ 400 ነባር የዓሣ ዝርያዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑትን በልቶ ጨርሷል። ይህ ከፍተኛ የሆነ ውድመት እንደ ቲላፕያና ሲችሊድ የመሰሉትን ትናንሽ ዓሣዎች እያጠመዱ ቤተሰቦቻቸውን ይመግቡ የነበሩትን በሚልዮን የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ችግር ላይ ጥሏል። በተጨማሪም እነዚህ ትናንሽ ዓሣዎች የሐይቁን ጤናማነት ይጠብቁ ነበር። አንዳንዶቹ በጣም አደገኛ በሽታ ለሆነው ቢልሃርዚያ ምክንያት የሚሆኑትን ቀንድ አውጣዎች ስለሚበሉ ይህን በሽታ በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታሉ። ሌሎቹ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ አላንዳች ገደብ በማደግ ላይ የሚገኙትን አልጌዎችና ሌሎች የባሕር እጸዋት ይበላሉ። እነዚህ እጸዋት አላንዳች ቁጥጥር ለማደግ በመቻላቸው ውሃደብሪያ የሚባለው ሁኔታ ሊከሰት ችሏል። ውሃደብሪያ የእጸዋቱ ብስባሽ በጣም በመብዛቱ ምክንያት በውኃው ውስጥ ያለው ኦክስጅን ሲሟጠጥ የሚፈጠር ሁኔታ ነው። ይህን ቆሻሻ የሚያጸዱ ነባር ዓሦች እየተመናመኑ በመሄዳቸው ኦክስጅን የሌለባቸው የውኃ አካባቢዎች፣ ማለትም “ሕይወት አልባ” አካባቢዎች እየተስፋፉ ሄደዋል። ይህም ለተጨማሪ ዓሣዎች እልቂት ምክንያት ሆኗል። ጠገብኩኝ ማለትን የማያውቀው ናይል ፐርች ይበላቸው የነበሩት ዓሣዎች እያለቁበት በመሄዱ አዲስ ዓይነት መብል ለመፈለግ በመገደዱ የገዛ ራሱን ልጆች መብላት ጀምሯል! ሐይቁን ሲውጥ የቆየው ዓሣ አሁን ራሱን ሊውጥ ተቃርቧል!
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኡጋንዳ
ኬንያ
ታንዛንያ
ቪክቶሪያ ሐይቅ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቪክቶሪያ ባሕር ዳርቻዎች መመስከር
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዊቨርበርድ
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፔሊካኖች
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢግረት
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የናይል አዞ
[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሄሮን በጉማሬ ላይ ቆማ