ከዓለም አካባቢ
የአካል እንቅስቃሴና ረጅም ዕድሜ
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በቅርቡ ረጅም ዕድሜን በሚመለከት ስለተደረገ አንድ ጥናት ሲዘግብ “በወር ውስጥ ስድስት ጊዜ ያክል ፈጠን ፈጠን እያሉ ለግማሽ ሰዓት መራመድ [ያለ ጊዜ] የመቀጨትን ዕጣ 44 በመቶ ይቀንሳል” ብሏል። በፊንላንድ የሚገኙ ተመራማሪዎች 8,000 ጥንድ መንትያዎች ላይ በአማካይ ለ19 ዓመታት ባደረጉት ተከታታይ ጥናት አልፎ አልፎ እንኳ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት “ምንም እንቅስቃሴ ከማያደርጉት መንትዮቻቸው ይልቅ የመሞት አጋጣሚያቸው 30 በመቶ ያነሠ” እንደሆነ ገልጸዋል። እንቅስቃሴ ማድረግ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ለመገምገም በተካሄደው ጥናት ጄነቲካዊ ሁኔታዎችም ግምት ውስጥ መግባታቸው ለጥናቱ ክብደት ሰጥቶታል። የኤሮቢክስ ተመራማሪ የሆኑት ስቴቭ ፋረል በጥናቱ ውስጥ ባይኖሩም እንዲህ ብለዋል:- “ጤናማ ጂን እንኳን ባይኖራችሁ ይህ ጥናት አበክሮ እንደገለጸው የምታደርጉትን የአካል እንቅስቃሴ መጨመር ረዘም ያለ ዕድሜ እንድትኖሩ ሊረዳችሁ ይችላል።”
ሕፃናትን መደባበስ ያስፈልጋል
“ልጆችን ዘወትር እያቀፉ፣ እየደባበሱ ወይም ደግሞ እያሻሹ ካላሳደጓቸው . . . በሰውነታቸው ውስጥ የመረበሽ ስሜት የሚፈጥሩ ሆርሞኖች መጠን ከፍተኛ ይሆናል” ሲል ቶሮንቶ ስታር የተባለው ጋዜጣ አንድን ጥናት ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። ተመራማሪዎቹ፣ ልጆች ከእናቶቻቸው መለያየታቸው ወይም ቸል መባላቸው “በመማርና በማስታወስ ችሎታቸው ላይ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ችግር ሊያስከትልባቸው ይችላል” የሚል እምነት አላቸው። በተጨማሪም በሃርቫርድ ሜዲካል ስኩል ሳይንቲስት የሆኑት ሜሪ ካርልሰን ወላጆች በሥራ ቀናት ልጆቻቸው “ጥሩ እንክብካቤ በማይደረግባቸው የልጆች መዋያ ማዕከሎች እንዲውሉ በሚያደርጉበት ጊዜ ልጆቹ ከፍተኛ የመረበሽ ስሜት ይታይባቸዋል፤ ልጆቹ እቤት በሚውሉባቸው የሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ግን እንዲህ ዓይነት ስሜት አይታይባቸውም” ብለዋል። ይህ ጥናት ልጆችን መደባበስና በተለያዩ መንገዶች ፍቅርን መግለጽ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።
ዘራፊ እርግቦች
የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ እርግቦችን በመጠቀም የሚፈጸመውን አልማዝ በድብቅ የማሸሽ እንቅስቃሴ አጋልጧል። ፖሊስ እንዳስታወቀው በመንግሥት ሥር ባለ አንድ የአልማዝ ማዕድን ማውጫ የሚሠሩ ተቀጣሪዎች ለማዳ እርግቦችን በምሳ ዕቃዎቻቸው ወይም በሰፊ ልብሶቻቸው ውስጥ ደብቀው ወደ ማዕድን ማውጫው ይገባሉ። ከዚያም እርግቦቹን አልማዝ ጭነው እንደሚለቅቋቸው ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘግቧል። እነዚህ ለማዳ እርግቦች ማዕድኑን ተሸክመው ብዙ ኪሎ ሜትሮች መጓዝ ይችላሉ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት አራት እርግቦች ይህን የኮንትሮባንድ አልማዝ ተሸክመው ሲሄዱ የተያዙ ሲሆን በአንድ አጋጣሚ የተያዘች አንዲት ለማዳ እርግብ ስድስት ካራት ያልተቆረጠ አልማዝ በክንፎቿ ሥር ታስሮላት ተገኝታለች። እስካሁን ድረስ በዚህ ዘዴ ሲጠቀሙ የቆዩ 70 የሚያክሉ ሰዎች ታሥረዋል። ጋዜጣው እንዳለው ከሆነ በጥንት ጊዜ የወንዝ መውረጃ ከነበረ ሸለቆ በቁፋሮ ከሚወጣው ሦስት አልማዝ መካከል አንዱ በእምነት አጉዳይ ሠራተኞች እንደሚወሰድ የኩባንያው ባለ ሥልጣኖች ይገምታሉ።
ሙት ባሕር እየከሰመ ነው
በምድር ላይ ከሚገኙት ቦታዎች ሁሉ እጅግ ዝቅተኛና በጣም ጨዋማ የሆነው ሙት ባሕር በፍጥነት እየከሰመ በመሄድ ላይ ነው። በ1965 የሙት ባሕር ወለል ከባሕር ወለል በታች 395 ሜትር ያህል ነበር። አሁን ግን ከባሕር ወለል በታች 413 ሜትር የደረሰ ሲሆን ባሕሩን ለሁለት የሚከፍል ቀጭን ደረቅ ምድር ብቅ ብሏል። በባሕሩ ዳር ላይ የተሠሩት ሆቴሎች በአሁኑ ጊዜ ከባሕሩ ርቀዋል። “የውኃው ወለል በዓመት ውስጥ 80 ሴንቲ ሜትር ያህል እየቀነሰ የመጣ ሲሆን በሰዎች ፍጆታና በፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሣ ወደ ባሕሩ በቂ ውኃ አይገባም” ሲል ዘ ዳላስ ሞርኒንግ ኒውስ አትቷል። “ሙት ባሕር ሙሉ በሙሉ ሊጠፋ የሚችልበት ሁኔታ ላይ የሚገኝ መሆኑ በክልሉ ያለው የውኃ እጥረት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክት ሲሆን ችግሩ እልባት እንዳይገኝለት እንቅፋት የሆኑት ነገሮች ደግሞ ደረቅ በሆነው የመካከለኛው ምሥራቅ ምድር ውኃና ሰላም ምን ያህል የተቆራኙ ነገሮች እንደሆኑ ያሳያሉ። . . . በአሁኑ ጊዜ የሙት ባሕር ዋነኛ ምንጭ የሆነው የዮርዳኖስ ወንዝ . . . በእስራኤል፣ በሶርያና በዮርዳኖስ ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል፣ ተጠልፎ አገልግሎት ላይ ውሏል።” የሙት ባሕርን ታሪክ በተመለከተ ጽሑፉ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ከማንኛውም ታሪክ በበለጠ እጅግ ግልጽ በሆነ መንገድ የሠፈረው ታሪክ አምላክ የሥነ ምግባር ሕግጋትን በመጣሳቸው ምክንያት እጅግ አዝኖ ‘በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ በማዝነብ’ ጠፍ መሬት እስካደረጋቸው ጊዜ ድረስ የሜዳማው አገር ከተሞች ለም በሆነ ክልል እንዴት ተደላድለው ይኖሩ እንደነበር የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ነው።”
የእርሻ ውጤቶች ጠቃሚነታቸው ቀንሷል?
የአፈር ለምነት በመመናመኑ ምክንያት ፍራፍሬዎችና ቅጠላ ቅጠሎች የሚሰጡት ጥቅም ቀንሷልን? እንደ አፈር ጥናት ሳይንቲስቶች አባባል ከሆነ አልቀነሰም። የካሊፎርኒያ በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ ዌልነስ ሌተር “በዕፅዋት ውስጥ የሚገኘውን ቫይታሚን የሚሠሩት ዕፅዋቶቹ ራሳቸው ናቸው” ብሏል። በመሆኑም አፈሩ አስፈላጊዎቹ ማዕድኖች የሚጎድሉት ከሆነ ዕፅዋቱ በሚገባ አያድጉም። አትክልቱ ማበብ አይችልም አለዚያም ጠውልጎ ሊሞት ይችላል። ይህ እንዳይሆን ገበሬዎች የአፈሩን ማዕድኖች ለመተካት ሲሉ ማዳበሪያ ይጠቀማሉ። ዌልነስ ሌተር እንዲህ ብሏል:- “የምትገዟቸው ፍራፍሬዎችና ቅጠላ ቅጠሎች ስታይዋቸው ጤናሞች ከሆኑ መያዝ የሚገባቸውን ንጥረ ነገሮች እንደሚይዙ እርግጠኞች ልትሆኑ ትችላላችሁ።”
ማዕድ ቤት ሳይኖራቸው የሚገነቡ ቤቶች
ግማሽ የሚሆነው የአውስትራሊያ ሕዝብ ምግባቸውን የሚመገቡት በምግብ ቤቶች እንደሆነ ይገመታል። ይህ ዓይነቱ ልማድ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት በሲድኒ አንዳንድ ቤቶች ማዕድ ቤት ሳይኖራቸው አንደሚገነቡ ዘ ከሪየር ሜይል ሪፖርት አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ አውስትራሊያውያን ምግብ በማዘጋጀት የሚያጠፉት ጊዜ በአማካይ 20 ደቂቃ ብቻ በመሆኑ ብዙ በአውስትራሊያ የሚገኙ የገበያ አዳራሾች የሚያቀርቡትን የምግብ ዓይነት እንደገና ለመገምገም ተገድደዋል። በሲድኒ የተለያዩ ትላልቅ የገበያ አዳራሾች ባለቤት የሆኑ አንዲት ሴት አውስትራሊያውያኑ የአሜሪካውያንን ፈሊጥ በመከተል በብዛት ከቤት ውጭ የመብላትን ልማድ አምጥተዋል ብለዋል።
“ዓለም በእሳት የተያያዘችበት ዓመት”
ኔቸር ኢንተርናሽናል የተባለው የደን ጥበቃ ፕሮግራም ዓለም አቀፍ መርጃ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ዣን ፖል ዣንርኖ “1997 ዓለም በእሳት የተያያዘችበት ዓመት ተብሎ ሊታወስ ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል። ከአንታርክቲካ በስተቀር በሁሉም አሕጉሮች ከፍተኛ መጠን ያለው ቃጠሎ ተከስቷል። ለምሳሌ ያህል በኢንዶኔዥያና በብራዚል የስዊዘርላንድን ምድር የሚያህል ስፋት ባላቸው ቦታዎች ላይ የሚገኙ ከፍተኛ ጠቀሜታ የነበራቸው ደኖች በእሳት ወድመዋል። መንስኤዎቹ ለእርሻ ተብሎ መሬት ለመመንጠር ሆን ተብለው ከተወሰዱ እርምጃዎች አንስቶ እስከ ድርቅ ድረስ የተለያዩ ናቸው። ድርቁ የተከሰተው በኤሊኖ ምክንያት ከፍተኛ ሙቀት ያለው የአየር ጠባይ በመፈጠሩ እንደሆነ ይታሰባል። ዚ ኢንዲፔንደንት የተባለው የለንደን ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በዚህ ቃጠሎ ምክንያት የተፈጠረው ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ለአየር ብክለትና ለዓለም አቀፍ የአየር ሙቀት መጨመር አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚል ስጋት አለ። ሚስተር ዣንርኖ እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል:- “በገዛ እጃችን የጥፋት እሽክርክሪት እየፈጠርን ነው። የቃጠሎ መጨመር በአየር ጠባይ ለውጥ ምክንያት የሚመጣ ነገር ሲሆን መልሶ ደግሞ የአየር ጠባዩ እንዲለወጥ አስተዋጽኦ ያደርጋል።”
ገናናው ዶላር
ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “ብዙዎቹ አሜሪካውያን አይወቁት እንጂ አብዛኛው የአሜሪካ ገንዘብ በዝውውር ላይ የሚገኘው ከዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ባሉ አገሮች ነው። በሰዎች የገንዘብ ቦርሳ፣ ገንዘብ በሚመዘግቡና በሚያስቀምጡ መሣሪያዎች፣ በባንክና በአልጋ ፍራሽ ውስጥ ከሚገኙት 450 ቢልዮን የአሜሪካ የገንዘብ ኖቶችና ሳንቲሞች ውስጥ ሁለት ሦስተኛው ማለትም 300 ቢልዮን የሚያክለው የሚገኘው በባዕድ አገር ነው።” እንዲሁም ይህ የገንዘብ መጠን በዓመት ውስጥ ከ15 ቢልዮን እስከ 20 ቢልዮን በሚያክል መጠን ያሻቅባል። በአብዛኛው በዩናይትድ ስቴትስ የሚሠራባቸው የ20 ዶላር ኖቶች ሲሆኑ በውጭ አገር ግን በብዛት የሚሠራባቸው የ100 ዶላር ኖቶች ናቸው። ይህ ደግሞ በውጭ አገር ያለው ዶላር ለዕለት ጉርስ የሚሆኑ ትናንሽ ሸቀጣሸቀጦች ለመግዛት ሳይሆን በባንክ ገንዘብ ለማስቀመጥና የንግድ ልውውጥ ለማካሄድ የሚያገለግል መሆኑን ያሳያል። ይህ ሁኔታ በተለይ የዋጋ ንረት ባለባቸውና ሰዎች በባንኮች ላይ እምነት በማይጥሉባቸው አገሮች በስፋት የሚታይ ነገር ነው። ባለፈው ዓመት ከታተሙት የ100 ዶላር ኖቶች መካከል 60 በመቶ የሚሆነው በቀጥታ ወደ ባሕር ማዶ ተልኳል። በዩ ኤስ መንግሥት አመለካከት መሠረት በውጭ አገር በዝውውር ላይ የሚገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የዩ ኤስ መንግሥት ከወለድ ነፃ በሆነ መንገድ እንደተበደረ ያክል ተደርጎ የሚቆጠር ሲሆን ይህንንም ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ መልሶ ለማስገባት የአሜሪካ መንግሥት ሸቀጣሸቀጦችን ማቅረብ ወይም የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት አያስፈልገውም። ይህ ደግሞ በቢልዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ያተርፍለታል።
የዝርፊያ ፈቃድ
“የብራዚል የሮማ ካቶሊክ መሪዎች ድሆችና የተራቡ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ቢሰርቁ ሊኮነኑ አይገባም ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራክረዋል” ሲል ኢ ኤን አይ ቡሌቲን ሪፖርት አድርጓል። በብራዚል ሰሜን ምሥራቅ ከባድ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት የገበያ አዳራሾችና መጋዝኖች መዘረፍ ተቀባይነት አግኝቷል። በቤሎ ሆሪዞንቴ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ሴራፌ ፈርናንደስ ደ አራውዡ “ራቡን ለማስታገስ ሲል ካገኘበት ቦታ ሁሉ ምግብ የሚወስድን ሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አያወግዙትም” ብለዋል። ካርዲናል ፓውሎ ኢቫርስቱ አርነስ ደግሞ “ድሆች በድህነት እየቆረቆዙና ሀብት በጥቂት ባለ ጠጎች እጅ ብቻ እየተከማቸ እንዲሄድ የሚያደርገውን አዲስ የነፃ ገበያ ሥርዓት ለመዋጋት ቆርጠን ተነስተናል” ሲሉ ተደምጠዋል። በመጨመርም “በከተማና በገጠር ያሉ ሁሉ ዓይናቸውን የሚገልጡበት ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።