በአካል ክፍል ላይ በሚደርስ ተደጋጋሚ ውጥረት ምክንያት የሚፈጠር ሕመም—ልታውቃቸው የሚገቡ ነገሮች
በብራዚል የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
በብራዚል የሚኖር ማርሴሎ የተባለ አንድ የ24 ዓመት ቀለም ቀቢ በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት እንደ ልማድ የሚያደርገው አንድ ነገር ነበር። ሰዓቱን እጁ ላይ ያደርግና የቆዳ ማሰሪያውን ሁለት ጫፎች አገናኝቶ ያስራል። አሁን ግን ሰዓቱን ማሰር ተቸገረ። የእጁን አንጓ ሲመለከት ችግሩን ተረዳ። በጣም አብጦ ስለነበር ማሰሪያው ሊበቃው አልቻለም።
እያደር ማበጠሪያ ወይም የጥርስ ብሩሽ ሲይዝ እንኳ እጁን ያምመው ጀመር። ስለዚህ ማርሴሎ ወደ ሐኪም ሄደ። ሐኪሙ ማርሴሎን ከመረመረው በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል ግድግዳ በመፋቅ፣ በመለሰንና በመቀባት ሥራ ተሰማርቶ እንደቆየ ሲገነዘብ “እየተሰማህ ያለው ሕመም ከሥራህ ጋር የተያያዘ ነው። ሬፒቴቲቭ ስትሬን ኢንጁሪ [በአካል ክፍል ላይ በሚደርስ ተደጋጋሚ ውጥረት ምክንያት የሚፈጠር ሕመም (አር ኤስ አይ)] ይዞሃል” አለው።
አዲስ በሽታ ነው?
ይህ የማርሴሎ በሽታ እንደያዛቸው የተነገራቸው የፋብሪካና የቢሮ ሠራተኞች ብዙ ናቸው። አር ኤስ አይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ ፎልያ ዲ ኤስ ፓውሎ የተባለው ጋዜጣ “በዚህ መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ከሥራ ጋር ዝምድና ካላቸው በሽታዎች መካከል ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘ” ሲል ጠርቶታል። ብዙ ሰዎች አር ኤስ አይ ከዘመኑ በሽታዎች አንዱ መሆን አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሳቸው ምንም አያስገርምም! ግን በሽታው አዲስ ነው?
ማርሴሎ በ18ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በአውሮፓ ይኖር የነበረ ሰው ቢሆን እንኳ ሐኪሞች በሽታውን ማወቅ አያቅታቸውም ነበር። እርግጥ፣ ይህ ችግር በዚያን ጊዜ በአሁኑ ስሙ አይታወቅም ነበር። ቤርናርዲኖ ራማትሲኒ የተባለው ጣሊያናዊ ዶክተር ይህን ችግር ሪስት ቴኖሲነቫይተስ (የጅማትና በዙሪያው ያለው ሽፋን ብግነት) ሲል የገለጸው ሲሆን “የጽሑፍ ገልባጮችና የመዝገብ ቤት ሹሞች” በሽታ በማለት ጠርቶታል። እነዚህ የሙያ መስኮች የሚጠይቁት ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ጸሐፊዎች የ18ኛው መቶ ዘመን አር ኤስ አይ በሽታ ተጠቂ አድርጓቸዋል። ሆኖም በዚያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በአር ኤስ አይ የሚሠቃዩ ሠራተኞች ቁጥር ሊቀንስ ችሏል። ለምን?
የአር ኤስ አይ መክሰም እና ማገርሸት
በራማትሲኒ ዘመን የነበሩት የቢሮ ጸሐፊዎች የቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን ተብሎ በሚጠራው ወቅት ይኖሩ የነበሩ ናቸው። በዚያ ዘመን ሰዎች ያለ ማሽኖች እርዳታ ለረጅም ሰዓት ይሠሩ ነበር። ሥራቸው ተደጋጋሚ እንቅስቃሴና ውልፍት የማያሰኝ ትኩረት የሚጠይቅ ነበር። ይህም የአር ኤስ አይ ባሕርይ ያለው ሕመም አስከትሏል።
ይሁን እንጂ በ18ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ ላይ አውሮፓ ወደ ኢንዱስትሪ ዘመን በመሸጋገሯ የሰው ኃይል በማሽን ኃይል ተተካ። ተደጋጋሚ የሆኑትን ሥራዎች ማሽኖች እንዲሠሩ በማድረጉ ሰው የሥራው ተቆጣጣሪ መሆን ቻለ። የአር ኤስ አይን ታሪክ ያጠኑ አንድ ዶክተር ይህ ለውጥ ሠራተኞች በአር ኤስ አይ የመያዛቸው ዕድል እንዲቀንስ አድርጎት ሊሆን ይችላል የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
እርግጥ ነው፣ በኢንዱስትሪው ዘመን ከሥራ ጋር ዝምድና ያላቸው አደጋዎች ቁጥር ከማደጉም በላይ የፋብሪካ ሠራተኞች ከሥራ ጋር በተያያዙ በሽታዎች የሚጠቁበት አጋጣሚ ጨምሯል። ሆኖም በዚያ ጊዜ ስለነበረው ሁኔታ የሚገልጹ የሕክምና ጽሑፎች አር ኤስ አይ ይታይ የነበረው በተወሰኑ ቡድኖች ላይ ብቻ እንደነበረ ያመለክታሉ። ለምሳሌ ያህል በ19ኛው መቶ ዘመን የነበሩ ፒያኖና ቫዮሊን ተጫዋቾች በላይኛው ክንዳቸው ውስጥ በሚገኙት ጅማቶች ላይ በሚከሰተው ብግነት ይሰቃዩ ነበር። ቴኒስ ተጫዋቾች ደግሞ ቴኒስ ኤልቦው የሚባለው የክርን ጅማቶች ብግነት ይይዛቸው ነበር።
ይሁን እንጂ እኛ ባለንበት በዚህ መቶ ዘመን በሥራ ጠባይ ምክንያት የሚመጣ አር ኤስ አይ አገርሽቷል። ለምን? አንደኛ ነገር፣ ሠራተኛው ምንና በምን ያህል ፍጥነት መሥራት እንዳለበት የሚወስኑት ከዕለት ወደ ዕለት ቅልጥፍናቸውና ምርታማነታቸው እየጨመረ የሄዱት ማሽኖች ናቸው። ይህ የአዛዥና ታዛዥ መለዋወጥ ሠራተኞች በሥራቸው እርካታ እንዲያጡና ለጤና ችግሮች እንዲጋለጡ ምክንያት ሆኗል። ሠራተኞች ብዙውን ጊዜ ድግግሞሽ የበዛበት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና አእምሯቸው ያላንዳች ፋታ በአንድ ነገር ላይ እንዲያተኩር በሚያስገድዱ ሥራዎች ላይ ረጅም ሰዓት ያሳልፋሉ። ይህ ምን ውጤት ያስከትላል? በዩናይትድ ስቴትስና በብራዚል ብቻ እንኳ ከሥራ ጋር ዝምድና ባላቸው በሽታዎች ከተያዙት ሠራተኞች መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአር ኤስ አይ የሚሠቃዩ ናቸው።
መንስኤዎቹና ለበሽታው የሚያጋልጡ የሥራ መስኮች
የአር ኤስ አይ ዋነኛ መንስኤ በብዙ የሥራ መስኮች የሚታየው ፈጣን የሆነ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ነው። የሚያሳዝነው ብዙውን ጊዜ ሠራተኞች ጤናቸውን ሊጎዳ የሚችል ሥራ እየሠሩ ከመኖር ሌላ ምንም አማራጭ የላቸውም። ብዙ ሠራተኞች በአንድ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥራ ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ አንድ ራዲዮ ገጥማ የመጨረስ ሥራ በነበራት ብራዚላዊት ሴት ሁኔታ ማዘናቸው አይቀርም። ፎልያ ዲ ኤስ ፓውሎ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ሌላዋ ሠራተኛ ደግሞ በአንድ ሰዓት ውስጥ 63 መሣሪያዎችን በፕላስቲክ መዶሻ እየመታች መፈተሽ አለባት። ሁለቱም ሴቶች ላይኛውን ክንዳቸውን ያማቸው ጀመር። ከጊዜ በኋላ አር ኤስ አይ አካለ ስንኩላን ስላደረጋቸው ከሥራቸው ተሰናበቱ።
በተጨማሪም በጡንቻዎችና በአንጓዎች ላይ ጫና ማብዛት (ከባድ ጆንያዎችን በመሸከምና በመሳሰሉት ሁኔታዎች) እንዲሁም ጡንቻዎች የአካል ክፍሎች ባሉበት ሁኔታ ሳይንቀሳቀሱ እንዲቆዩ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት (static efforts) አር ኤስ አይ ሊያስከትል ይችላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች በተለይ አንድ ሰው አመቺ ባልሆነ ሁኔታ ላይ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ተመራማሪዎች ለአር ኤስ አይ በይበልጥ የተጋለጡ ናቸው ብለው ከፈረጁአቸው ሞያተኞች መካከል የሥነ ብረታብረት ባለሙያዎች፣ የባንክ ጸሐፊዎች፣ በቁልፍ ሰሌዳ (keyboard) የሚሠሩ ሰዎች፣ የስልክ ኦፕሬተሮች፣ በገበያ አዳራሽ ውስጥ የሚሠሩ ገንዘብ ተቀባዮች፣ አስተናጋጆች፣ ቀለም ቀቢዎች፣ አሻንጉሊት የሚሠሩ ሰዎች፣ ልብስ ሰፊዎች፣ ፀጉር አስተካካዮች፣ ሹራብ ሠሪዎች፣ ሸንኮራ አገዳ የሚቆርጡ ሰዎችና ሌሎች የጉልበት ሠራተኞች ይገኙበታል።
በእንቅስቃሴ ምክንያት ብቻ የሚመጣ አይደለም
አብዛኞቹ ሰዎች አር ኤስ አይ የሚመጣው ተደጋጋሚ በሆነ ሥራ ምክንያት ብቻ እንደሆነ አድርገው ቢያስቡም የብራዚል ዋና ከተማ በሆነችው በብራዚልያ ስለ አር ኤስ አይ ለመምከር በተሰበሰበው የመጀመሪያ ብሔራዊ ሴሚናር ላይ የተገኙ ጠበብት ችግሩ የሚከሰተው በተደጋጋሚ እንቅስቃሴ ብቻ እንዳልሆነ ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል።
በብራዚልያ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ጤናና የሥራ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ቫንደርሌ ኮዱ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሥራው የተደራጀበት መንገድ ማለትም የሚሠራው ነገር፣ በአስተዳደሩና በሠራተኛው መካከል ያለው ግንኙነት፣ በሥራው አካባቢ ያለው አጠቃላይ መንፈስ፣ የሠራተኛው የተሳትፎ መጠንና የሥራው ሂደት ከበሽታው ጋር ጠንካራ ትስስር ካላቸው ነገሮች አንዱ ነው።”
በአር ኤስ አይ ሴሚናር ላይ የተገኙ ሌሎች የሕክምና ጠበብትም በበሽታውና በሥራ ቦታው አደረጃጀት መካከል ያለውን ዝምድና ጠበቅ አድርገው ገልጸዋል። የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አንዱ ደካማ ጎን ሠራተኛው ሥራው ከቁጥጥሩ ውጪ እንዲሆን የሚያደርግ አደረጃጀት መፍጠራቸው ነው፤ ይህ ደግሞ ሠራተኛው በአር ኤስ አይ እንዲያዝ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ቀደም ባሉት አሥርተ ዓመታት አንዳንድ ሠራተኞች ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ ሥራ ሲያከናውኑ የኖሩ ቢሆኑም አር ኤስ አይ ያልያዛቸው አንድ ሥራ የሚደራጅበትና የሚከናወንበት መንገድ ከአር ኤስ አይ ጋር የቅርብ ትስስር ያለው በመሆኑ ነው። አንዳንድ ጠበብት ከዚህ መደምደሚያ ሊደርሱ ችለዋል።
የበሽታውን ምልክቶች ለይቶ ማወቅ
አር ኤስ አይ አንድን የተለየ በሽታ ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ተዛማጅ በሽታዎችን የሚያመለክት ስያሜ መሆኑን መዘንጋት የለብህም። በዚህ ሥር የሚካተቱት ሕመሞች በሙሉ በተለይ የላይኛዎቹን የእጅና የእግር ጡንቻዎች፣ ጅማቶች፣ አንጓዎችና ምራኖች (ligaments) ይጎዳሉ። አር ኤስ አይ በርከት ያሉ በሽታዎችን የሚያመለክት በመሆኑ የተለያዩ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ። ምልክቶቹ ግልጽ ላይሆኑ ይችላሉ፤ በተጨማሪም በመንስኤዎቹና በምልክቶቹ መካከል ያለው ዝምድና ወዲያው ላይታወቅ ይችላል። የሚከተሉትን ዋና ዋና ምልክቶች ተመልከት።
አንዱ ምልክት በተጎዳው የአካል ክፍል ላይ (ትከሻ እና/ወይም ክንድ ሊሆን ይችላል) የሚሰማ እንደ ጭነት የሚከብድና ዕረፍት የሚነሳ ስሜት ነው። ይህ ደግሞ እያደገ ይሄድና ፋታ የማይሰጥ ሕመምና ውርር የሚያደርግ ስሜት ያስከትላል። በተጨማሪም ከቆዳ ሥር ቁጥር ያሉ ትንንሽ እበጦች ሊወጡ ይችላሉ። አር ኤስ አይ የከፋ ደረጃ ላይ በሚደረስበት ጊዜ እብጠቱና ሕመሙ በጣም ከባድ ስለሚሆን ግለሰቡ ፀጉር እንደ ማበጠርና ጥርስ እንደ መቦረሽ ያሉ ቀላል ተግባሮችን እንኳን ማከናወን ይሳነዋል። አር ኤስ አይ ሕክምና ካልተደረገለት የቅርፅ መበላሸትና አካለ ስንኩልነት ሊያስከትል ይችላል።
አር ኤስ አይን መዋጋት
ሥራህ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ ከሆነና የአር ኤስ አይ ምልክቶች እየታዩብህ ከሆነ ከመሥሪያ ቤትህ የሕክምና አገልግሎት ክፍል እርዳታ እንዲሰጥህ ልትጠይቅ ትችላለህ። ይህ የማይቻል ከሆነ ችግርህን መርምሮ ሊያገኝና አንተን ለመርዳት አስፈላጊ እርምጃዎችን ሊወስድ የሚችል የአጥንት ስፔሺያሊስት ወዳለበት የጤና አገልግሎት ተቋም መሄድ ትችል ይሆናል። የበሽታው የመጀመሪያ ምልክቶች በሚታዩበት ወቅት ለአር ኤስ አይ ተገቢውን ትኩረት ከሰጠህ የመዳን ዕድልህ በጣም የተሻለ ይሆናል።
ሌላው አር ኤስ አይን ለመዋጋት በጣም ጠቃሚ የሆነው መንገድ ለኤርጎኖሚክስ ትኩረት መስጠት ነው። ኤርጎኖሚክስ ምንድን ነው? ቃሉ “ሰዎችና መሣሪያዎች እጅግ ምቹ በሆነና ለጉዳት በማያጋልጥ መንገድ ተጣጥመው መሥራት የሚያስችላቸውን ንድፍና ቅርጽ የሚያወጣ ተግባራዊ ሳይንስ ነው” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል።
ስለዚህ ኤርጎኖሚክስ የሥራ ቦታ ከሰው ጋር እንዲሁም ሰው ከሥራው ቦታ ጋር መጣጣማቸውን የሚከታተል የእውቀት ዘርፍ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ጥበብ የአንድን የቁልፍ ሰሌዳ ወይም መዶሻ ቅርጽ በማሻሻል ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። የሠራተኛውን አእምሯዊና ስሜታዊ ፍላጎቶችም ግምት ውስጥ ማስገባትን ይጨምራል። ይህን ግብ ለመምታት ኤርጎኖሚክስ “ከሁሉም መስኮች የሚገኘውን ዳታ፣ መረጃና እውቀት ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚጠቀም [ከመሆኑም በላይ] ስለ ሰውና ስለ ሥራው አንድ አዲስና የተሟላ እውቀት ላይ ለመድረስ ይጥራል” ሲሉ ኤርጎኖሚስት የሆኑት ዶክተር ኢንግቦርግ ዜል ተናግረዋል።
እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ ሠራተኞች የሥራ ቦታቸውን ኤርጎኖሚክስ የመለወጥ ሥልጣን ላይኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ በብራዚልያ ከተማ በአር ኤስ አይ ላይ በተካሄደው ሴሚናር የተካፈሉ የሕክምና ጠበብት “በኤርጎኖሚክስ ተሳትፎ ማድረግ” ከሠራተኞች ሥልጣን ውጭ መሆን የለበትም ሲሉ ገልጸዋል። በኤርጎኖሚክስ ተሳትፎ ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?
ሠራተኞቹ በኤርጎኖሚክስ ማሻሻያዎች እንዲሳተፉ የሚያበረታታ አንድ አሠሪ የሠራተኞቹን አስተያየት ግምት ውስጥ ያስገባል። ሠራተኛው የሚሠራበትን ቦታና ሁኔታ እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ሐሳብ እንዲሰጥ ይጋብዘዋል። በተጨማሪም እንዲህ ዓይነቱ አሠሪ ከሠራተኞቹና ከአስተዳደሩ የተውጣጣ አንድ የአር ኤስ አይ ኮሚቴ እንዲቋቋም ያደርጋል። ይህ ኮሚቴ በሥራ ቦታው ለጉዳት የማያጋልጥ ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ የማያቋርጥ ክትትል ያደርጋል። የአር ኤስ አይ መንስኤዎችን ያስወግዳል፣ መከላከል የሚቻልበትን መንገድ ያመቻቻል እንዲሁም በተቋሙ ውስጥ አር ኤስ አይን በመቆጣጠር ብሎም ጨርሶ በማስወገድ ረገድ አሠሪውና ሠራተኞቹ ያለባቸውን ኃላፊነት በግልጽ ያስቀምጣል።
በቤትም ሆነ በሥራ ቦታ የመከላከያ እርምጃዎች መውሰድ
አር ኤስ አይን ለመከላከል የምንወስደው እርምጃ ከቤት ይጀምራል። ምን ማድረግ ትችላለህ? ከእንቅልፍህ ስትነሳ ውሻህ ወይም ድመትህ የሚያደርጉትን አድርግ። እንቅስቃሴ ከመጀመራቸው በፊት በመንጠራራት ጡንቻዎቻቸውን እንዴት እንደሚያፍታቱ ተመልከት። አንተም እንደዚያው አድርግ። በቀን ውስጥም አልፎ አልፎ ብትደጋግመው ጥሩ ነው። እንዲህ ማድረግህ የአጥንቶችህንና የጡንቻዎችህን ጤንነት ለመጠበቅ ይረዳሃል። ጡንቻዎችህን ለማሟሟቅ ትንሽ የአካል እንቅስቃሴ አድርግ። ይህ የደም ዝውውርን የሚያፋጥን ከመሆኑም በላይ ጡንቻዎችህ ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ የሚረዳቸውን የኦክሲጅን መጠን ይጨምራል። በተጨማሪም ቅዝቃዜ ሲኖርና በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከመሳተፍህ በፊት ይህን አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግህ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። በብዛት የምትጠቀምባቸውን ጡንቻዎች የሚያጠነክር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ። ጠንካራ ጡንቻዎች በሥራ ቦታ የምታከናውናቸውን ነገሮች በብቃት እንድትሠራ ይረዱሃል።
በቤት ውስጥ ከምትወስዳቸው እርምጃዎች በተጨማሪ በሥራ ቦታም የመከላከያ ፕሮግራም መኖር አለበት። አሠሪው በመካከሉ ዕረፍት የሚሰጥና የሥራ ለውጥ የሚፈጥር የሥራ ፕሮግራም በማውጣት እንዲሁም የተለያዩትን ሥራዎች የተለያዩ ሠራተኞች በየተራ እንዲሠሩ በማድረግ በሠራተኞቹ መካከል የአር ኤስ አይ ችግር እንዳይኖር ሊከላከል ይችላል።
አር ኤስ አይን መከላከል የሚቻልበት ሌላው መንገድ ለሠራተኛው ትክክለኛውን ዓይነት መሣሪያ ማቅረብ ነው። ከእነዚህ መካከል ትክክለኛ ቁመት ያላቸው ጠረጴዛዎችና ወንበሮች፣ ለስላሳ የክርን ማስደገፊያዎች፣ ከፍተኛ ጉልበት የማይጠይቁ መሰርሰሪያዎችና ትንንሽ ጉጠቶች፣ ምቹ የሆኑ የኮምፒዩተር ቁልፍ ሰሌዳዎች፣ ወይም ከፍተኛ እርግብግብታን ለማስወገድ የሚያስችል ክውታ ሞሳሽ (shock absorber) ያለው ከባድ መሣሪያ ይገኙበታል።
መግቢያው ላይ የተጠቀሰው ማርሴሎ ከእነዚህ ሐሳቦች መካከል ብዙዎቹን ተግባራዊ አድርጓል። ይህና ያገኘው ሕክምና ታይተውበት የነበሩት የአር ኤስ አይ ምልክቶች እንዲጠፉ አድርጎለታል። ሙሉ በሙሉ መዳን የሚችልበት ሁኔታም ተፈጥሮለታል። አር ኤስ አይን ለመከላከል የግል ጥረትና የአደረጃጀት ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም በሥራ ቦታ የአር ኤስ አይ በሽተኞች ቁጥር እየተበራከተ በመሆኑ እነዚህን ለውጦች ማድረጉ የሚያስገኘው ጥቅም ከሚከፈለው መሥዋዕት የላቀ ይሆናል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አር ኤስ አይ በሙዚቀኞች ዘንድ
በአካል ክፍል ላይ በሚደርስ ተደጋጋሚ ድካም ምክንያት የሚፈጠር ሕመም (አር ኤስ አይ) በፕሮፌሽናል ሙዚቀኞች ዘንድ በብዛት የሚታይ ችግር ነው። በ1986 የታተመ አንድ ጥናት እንደገለጸው በአውሮፓ ውስጥ ባሉ ባለ ስምንት ሲምፎኒ ኦርኬስትራዎች ውስጥ ከሚጫወቱት ሙዚቀኞች መካከል ግማሾቹ በአር ኤስ አይ ይሰቃያሉ። በ19ኛው መቶ ዘመን በሽታው የሙዚቀኞች ጭብጠት (musician’s cramp) ተብሎ ይጠራ ነበር። በበሽታው መያዛቸው ከታወቀው የመጀመሪያ ሰዎች መካከል አንዱ ሮበርት ሹማን ነው። አር ኤስ አይ ፒያኖ መጫወቱን አቁሞ ሙዚቃ በመድረስ ላይ እንዲያተኩር አስገድዶታል።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለአር ኤስ አይ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ነገሮች
1. ትክክለኛ ያልሆነ አቀማመጥ ወይም አቋቋም
2. ረጅም ሰዓት መሥራት
3. ሥራ የሚፈጥረው ውጥረት
4. ቀደም ሲል በጡንቻዎችና በጅማቶች ላይ የደረሰ ጉዳት
5. በሥራህ አለመርካት
6. ለቅዝቃዜ መጋለጥ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አር ኤስ አይን መከላከል
መወገድ ያለባቸው ነገሮች
1. ከባድ ነገሮችን ተሸክሞ መቆየት
2. በአንጓዎች ላይ ከባድ ጫና መፍጠር
3. ክንዶችን ከደረት በላይ ከፍ አድርጎ ለረጅም ጊዜ መሥራት
4. ምቹ ባልሆነ ሁኔታ መሥራት
መደረግ ያለባቸው ነገሮች
1. ቀላል ሥራዎችንም እንኳ በምንሠራበት ጊዜ እጆቻችንን እያቀያየርን መሥራት
2. በቀን ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ገጽ 18 እና 19:- The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck