የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 2/8 ገጽ 22-24
  • መንገዶች የሥልጣኔ የደም ሥሮች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መንገዶች የሥልጣኔ የደም ሥሮች
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጥንቶቹ መንገዶች
  • ወታደራዊ ጠቀሜታ
  • የመንገድ ግንባታ ራሱን የቻለ ሳይንስ ነው
  • የአሳዛኝ ገጠመኞች መንስኤ
  • ለጥንቱ የምህንድስና ጥበብ ቅርስ የሆኑት የሮማውያን መንገዶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • ሁሉም ሃይማኖቶች ጥሩ ናቸው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • ሁሉም ሃይማኖቶች ወደ አምላክ የሚያደርሱ የተለያዩ መንገዶች ናቸውን?
    ንቁ!—2001
  • መልእክቱ መድረስ አለበት
    ንቁ!—2006
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 2/8 ገጽ 22-24

መንገዶች የሥልጣኔ የደም ሥሮች

ሰዎች በውል ከማይታወቁ ዘመናት አንስቶ እንደ ድር እርስ በርስ የተያያዙ መንገዶችና አውራ ጎዳናዎች አማካኝነት ግንኙነት ሲያደርጉ ኖረዋል። ይህ ሁኔታ የሰውን ልጅ የመጓዝና የንግድ ልውውጥ የማድረግ እንዲሁም የመዋጋትና ግዛትን የማስፋፋት ፍላጎት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አዎን፣ መንገዶች የሰውን ልጅ ክፋትም ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።

የሰዎችና የእንስሳት ኮቴ የጥንቶቹን መንገዶች ካወጣበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዘመናዊዎቹ ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች ድረስ ያለው የመንገዶች ታሪክ እንዲሁ በሐሳብ ጉዞ ወደ ኋላ እንድንመለስ ብቻ የሚያደርገን አይደለም። የሰውን ልጅ ተፈጥሮም የምናጠናበት ነው።

የጥንቶቹ መንገዶች

“ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራዬ ብለው መንገዶችን መገንባት የጀመሩት” ይላል ዘ ኒው ኢንሳይክለፒድያ ብሪታኒካ፣ “መስጴጦምያውያን ሳይሆኑ አይቀሩም።” እነዚህ ሰዎች በጤግሮስና በኤፍራጥስ ወንዞች አካባቢ ይኖሩ ነበር። ይኸው ጽሑፍ አክሎ ሲናገር ሰልፍ ያደርጉባቸው የነበሩት መንገዶች “የተተኮሰ ጡብና ድንጋይ በቅጥራን እያጣበቁ ያነጠፏቸው መንገዶች ነበሩ” ሲል ይገልጻል። ይህ መግለጫ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥንቶቹ የግንባታ መሣሪያዎች የሚሰጠውን ሐሳብ ያስታውሰናል:- “ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ የምድርም ዝፍት [“ቅጥራን፣” የ1980 ትርጉም] እንደ ጭቃ ሆነችላቸው።”—ዘፍጥረት 11:3

የጥንቶቹ እስራኤላውያን ሃይማኖታዊ ግዴታዎቻቸውን ማሟላት እንዲችሉ መንገዶች በእጅጉ ያስፈልጓቸው ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ከ1,500 ዓመታት ገደማ በፊት እስራኤላውያን የሚከተለው ትእዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር:- “በዓመት ሦስት ጊዜ፣ . . . ወንዶችህ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት [መንፈሳዊ በዓል ለማክበር] እርሱ በመረጠው ስፍራ ይታዩ።” (ዘዳግም 16:16) ይህ ቦታ ኢየሩሳሌም ሆነ። ብዙውን ጊዜ ደግሞ መላው የቤተሰብ አባላት በእነዚህ አስደሳች በዓላት ላይ ይገኙ ነበር። በመሆኑም የግድ ጥሩ መንገዶች መኖር ነበረባቸው!

ዋና ዋናዎቹ መንገዶች በጥሩ ሁኔታ የተገነቡ እንደነበሩ መረዳት ይቻላል። አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ ክርስቶስ ከመወለዱ ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ይገዛ የነበረውን ሰሎሞንን በተመለከተ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የመንገዶቹን ሥራ ቸል አላለም፤ ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስዱ ጥቁር ድንጋይ የተነጠፈባቸው ሰፋፊ ጎዳናዎች ዘርግቷል።”

በእስራኤል ውስጥ ሳያውቅ ነፍስ ያጠፋ ሰው ጥገኝነት የሚያገኝባቸው ስድስት የመማጸኛ ከተሞች ነበሩ። ወደነዚህ ከተሞች የሚወስዱት መንገዶችም በጥሩ ሁኔታ የተያዙ ነበሩ። በተጨማሪም የአይሁድ ወግ እንደሚያመለክተው በእያንዳንዱ መስቀለኛ መንገድ ላይ በአቅራቢያ የሚገኘውን የመማጸኛ ከተማ የሚጠቁሙ በደንብ የተሠሩ ምልክቶች ነበሩ።—ዘኁልቁ 35:6, 11–34

መንገዶች ለንግድ መስፋፋት በጣም አስፈላጊ ሆነው ነበር። በጥንት ዘመን ደግሞ በጣም ተፈላጊ ከነበሩት ዕቃዎች አንዱ ሐር ነበር። እስራኤላውያን አንድ ብሔር ከመሆናቸው ከብዙ ጊዜ በፊት ቻይናውያን የሐር ትል ከሚሠራው ድር ሐር እንዴት እንደሚሠራ ማወቅ የቻሉ ቢሆንም የአሠራር ዘዴውን ይፋ ያደረጉት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነበር። ከዚያም በፊት ግን በምዕራቡ ዓለም ሐር በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ሆኖ ነበር፤ በመሆኑም በጄፍሪ ሂንድሊ የተዘጋጀው ኤ ሂስትሪ ኦቭ ሮድስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው በሐር መጠቀም “ሴታ ሴትነት ተደርጎ ይቆጠር” ስለነበር “ወንዶች በሐር እንዳይጠቀሙ ለማገድ” አዋጆች ወጥተው ነበር።

ሐር ከቻይና በማጓጓዝ የንግድ ልውውጥ ይካሄድበት የነበረው መንገድ የሐር መንገድ በመባል ይታወቅ ነበር። በ13ኛው መቶ ዘመን እዘአ መገባደጃ ላይ ማርኮ ፖሎ በዚህ መንገድ ወደ ቻይና በተጓዘበት ወቅት ይህ መንገድ 1,400 ዓመታት አስቆጥሮ ነበር። ይህ የሐር መንገድ ከ2,000 ለሚበልጡ ዓመታት ያህል በዓለም ረጅሙ መንገድ ሆኖ ቆይቷል። የሐር አገር ከሆነችው ከቻይናዋ ሻንጋይ ከተማ አንስቶ ስፔን ውስጥ እስከምትገኘው እስከ ጋዴስ (ዘመናዊቷ ካዲዝ) ድረስ የተዘረጋው ይህ መንገድ 12,800 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርዝመት አለው።

ወታደራዊ ጠቀሜታ

የመንገዶች ግንባታ እንዲጧጧፍ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ነገር ግዛትን የማስፋፋት ጥማት ነው። ለምሳሌ ያህል በቄሣሮች ይመራ የነበረው የሮማ ግዛት በአውሮፓ፣ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የዘረጋው መንገድ በድምሩ 80,000 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ ይገመታል። የሮማ ወታደሮች ጦርነት ላይ በማይሆኑበት ጊዜ አንዳንዴ መንገዶችን በመገንባትና በመጠገን ሥራ እንዲሰማሩ ይደረግ ነበር።

መንገዶች ድል በማግኘት ረገድ ያላቸው ጠቀሜታ በቅርብ ጊዜ በተከናወነ ሁኔታም ታይቷል። አዶልፍ ሂትለር በ1934 የጀመረው ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች የመገንባት ፕሮግራም ሌሎች ሕዝቦችን ለመግዛት የነበረውን ፍላጎት በእጅጉ አጠናክሮለታል። ታሪክ ጸሐፊው ሂንድሊ እንዳሉት ከሆነ ይህ ፕሮግራም ጀርመን “እንደ ድር እርስ በርሳቸው የሚገናኙ ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች በመገንባት በዓለም አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያዋ አገር” እንድትሆን አድርጓታል።

የመንገድ ግንባታ ራሱን የቻለ ሳይንስ ነው

ሮማውያን መንገድ ቀያሾች ግሮማ የተባለ መሣሪያ በመጠቀም እንደ ቀስት ቀጥ ያሉ መንገዶች ቀይሰዋል። ግንበኞች ርቀትን የሚጠቁሙ ድንጋዮችን ውብ በሆነ መንገድ ጠረቡ፤ መሃንዲሶች ደግሞ የጭነት ልክ አወጡ። መንገዶቹ መሠረትና ቶሎ የማይበላሽ ወለል ነበራቸው። ይሁን እንጂ ረጅም ዕድሜ እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደረገው ዋነኛው ነገር መንገዱ በተወሰነ ደረጃ የደጋን ቅርጽ እንዲኖረውና በዙሪያው ካለው ገጠራማ ክልል ከፍ እንዲል በማድረግ ከፍተኛ ጥበብ የተንጸባረቀበት የውኃ ማውረጃ ዘዴ መጠቀማቸው ነው። “ሃይዌይ (ከፍ ያለ መንገድ)” የሚለው የእንግሊዝኛ ስያሜም የመጣው ከዚሁ ነው። ሌላው ቀርቶ ሱቆች እንኳ መንገድ ጠቋሚ ካርታዎች ይሸጡ ነበር።

አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ሮማውያን በመንገድ ግንባታ ረገድ ያከናወኑት ሥራ ድንቅ በመሆኑ አንድ ጸሐፊ ሁኔታውን በጣም ያጋነነ እንዳይመስል ጥንቃቄ ለማድረግ ይገደዳል። ከኢጣሊያ መንገዶች ይበልጥ ለረጅም ጊዜ ግልጋሎት የሰጠ ሌላ ቅርስ መኖሩ ያጠራጥራል።”

ኤ ሂስትሪ ኦቭ ሮድስ የተባለው መጽሐፍ በሚገልጸው መሠረት ከሮም ተነስቶ ወደ ደቡብ የሚያቀናው የአፒያን ጎዳና “በምዕራቡ ዓለም ታሪክ የመጀመሪያው በድንጋይ የተነጠፈ መንገድ ነው።” ይህ የታወቀ አውራ ጎዳና በአማካይ 6 ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በትልልቅ ትፍ ቅላጭ ድንጋዮች የተነጠፈ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም ሲሄድ በዚህ መንገድ የተጓዘ ሲሆን የዚህ መንገድ የተወሰኑ ክፍሎች አሁንም ግልጋሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።—ሥራ 28:15, 16

የጥንቶቹ የደቡብ አሜሪካ ሕንዶች የነበራቸው የመንገድ ግንባታ ሙያም ልክ እንደዚሁ ብዙዎችን ሊያስደንቃቸው ይችላል። ከ1200ዎቹ እስከ 1500ዎቹ ዓመታት ድረስ በነበረው ጊዜ የኢንካ ሕዝቦች 10,000,000 ገደማ የሚሆን ሕዝብ ያለውን አገር አንድ ያደረጉ 16,000 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸው እርስ በርሳቸው የተያያዙ መንገዶች ሠርተዋል። እነዚህ መንገዶች በረሃና ጥቅጥቅ ያለ ደን አልፎ ተርፎም ታላቁን ፔሩቪያን ኤንዲዝ በማቋረጥ እጅግ አስቸጋሪና ወጣ ገባ በሆነ አካባቢ የሚያልፉ ናቸው!

ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ ስለ አንድ መንገድ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “የኤንዲዝ መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው። መንገዱ 25 ጫማ (7.5 ሜትር) ስፋት ያለው ከመሆኑም በላይ ጠመዝማዛ ቦታዎች እንዲሁም ዳገትና ቁልቁለት የበዛባቸውን ትልልቅ ሸንተረሮች አቋርጦ ይሄዳል። በተጨማሪም በተፈለፈሉ ጠንካራ አለቶች ውስጥ የሚያልፍ ሲሆን መንገዱን ደግፈው የሚይዙ በመቶ ሜትር የሚቆጠር ከፍታ ያላቸው ግምቦች ተገንብተዋል። ገደላ ገደሎቹንና ሸለቆዎቹን በጠጣር ድንጋዮች ሞልተዋቸዋል፤ በትላልቆቹ የተራራ ወንዞች ላይ ደግሞ በሱፍ ወይም በቃጫ ካቦዎች አማካኝነት ተንጠልጣይ ድልድዮች ዘርግተዋል። ወለሉ ከድንጋይ የተሠራ ሲሆን በብዙ ቦታዎች ላይ እንደ ሬንጅና ጠጠር ያሉ ነገሮችን ተጠቅመዋል።”

ኢንካዎች በፈረስ አይጠቀሙም ነበር፤ ሆኖም እርስ በርሳቸው የሚገናኙት መንገዶቻቸው “ለነገሥታቱ መልእክተኞች የተመቸ የመሮጫ ሜዳ” ሆነውላቸው ነበር። አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በየሁለት ኪሎ ሜትሩ ጥቂት ጠባቂዎችና በፈረቃ የሚሮጡ ፕሮፌሽናል ሯጮች የሚገኙባቸው ጣቢያዎች አሉ። መልእክቱን በፍጥነት እየተቀባበሉ ለመሮጥ እንዲቻል ከአንዱ ጣቢያ እስከሚቀጥለው ጣቢያ ድረስ ያለው ርቀት አጭር ሲሆን ጣቢያዎቹ ሌት ከቀን የሚሠሩ ናቸው፤ በዚህም መንገድ የሚሰጠው ግልጋሎት አንድን መልእክት ከዋና ከተማዋ ኩስኮ 2,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ኪቶ በአምስት ቀናት ውስጥ ሊያደርስ ይችላል። ይህ ማለት ከባሕር ወለል በላይ ከ4,000 ሜትር የሚበልጥ ከፍታ ባለው መንገድ ላይ በአማካይ በሰዓት አሥራ አምስት ኪሎ ሜትር መሮጥ ማለት ነው፤ የሮማ ንጉሠ ነገሥታዊ የፖስታ አገልግሎት በዚህ ፍጥነት ፖስታ መላክ ችሎ አያውቅም!”

የአሳዛኝ ገጠመኞች መንስኤ

በሰው አካል ውስጥ የሚገኙት የደም ሥሮች ሊዘጉና አስከፊ መዘዝ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ሕይወትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል አስተዋጽኦ ያበረከቱ መንገዶችም ልክ እንደዚሁ ሊዘጉና ሕይወትን የከፋ ሊያደርጉት ይችላሉ። ጥቅጥቅ ባለ ደን፣ በምድረ በዳ፣ በዱርና በብሔራዊ ፓርክ የሚያልፉ መንገዶች የዱር አራዊትን ሕይወት ለጥፋት እየዳረጉ ነው። ብዙውን ጊዜም የአካባቢው ተወላጆችና በዙሪያቸው ያለው ጫካ ለአደጋ ይጋለጣል። ሃው ዊ ቢልድ ሮድስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የትራንስ-አማዞንያን አውራ ጎዳና የተሠራው ለእድገት ተብሎ ቢሆንም እንኳ ሰፊ ቦታ የሸፈነ ደን ያጠፋ ከመሆኑም በላይ በጫካው ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች ሕይወት በማመሰቃቀል ለአደጋ አጋልጧቸዋል።”

በየዓመቱ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ጎዳናዎችን እያጨናነቁ በመሆናቸው በከተሞች ውስጥም አስከፊ መዘዝ እያስከተለ ነው። የገንዘብ አቅሙ ካለ እያደር ሰፋፊ አውራ ጎዳናዎች ይሠራሉ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ እነዚህ መንገዶች ብዙ ተሽከርካሪዎችን ስለሚጋብዙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለበሽታ የሚዳርገው ብክለት እየጨመረ ይሄዳል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 500,000 የሚሆኑ ሰዎች በመንገድ ላይ በሚከሰቱ አደጋዎች ይሞታሉ። ሌሎች 15 ሚልዮን ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ይደርስባቸዋል፤ ከእነዚህ መካከል በአንዳንዶቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እጅግ ዘግናኝ ነው። ከዚህ ጋር ሲወዳደር አንደኛው የዓለም ጦርነት የቀጠፈው ዘጠኝ ሚልዮን የሚሆኑ ተዋጊዎችን ሕይወት ነው። ከዚያ በኋላ ጦርነቱ አብቅቷል። በመንገድ ላይ በሚደርሱ አደጋዎች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ግን ማቆሚያ የለውም፤ ቀን አልፎ ቀን በተተካ ቁጥር በየዕለቱ ከ1,000 የሚበልጡ ሰዎች ይሞታሉ!

አዎን፣ መንገዶቻችን በብዙ መልኩ ስለ እኛ የሚናገሩት ነገር አለ፤ ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችንን በመጠቆም ምግባራችንን ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። በተጨማሪም በአደራ ለተሰጠችን ለዚህች ዕጹብ ድንቅ ፕላኔት ያለንን አመለካከት ይጠቁሙናል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያው ጳውሎስ የተጓዘበት የአፒያን ጎዳና ዛሬም አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ 500,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በመንገድ ላይ በሚከሰቱ አደጋዎች ይሞታሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ