ከዓለም አካባቢ
2000 ዓመትና ክርስቶስ
እንደ ኢ ኤን አይ ቡለቲን አባባል ከሆነ “ከስድስት ብሪታናውያን መካከል 2000 ዓመትን ከክርስቶስ ጋር የሚያዛምደው አንድ እንኳን እንደማይሆን የተሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ያመለክታል።” በዚህ የሕዝብ አስተያየት የተደረገው ጥናት “ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል 37 በመቶ የሚሆኑት ይህ ዓመት ለምን ነገር መታሰቢያ እንደሆነ እንደማያውቁ፣ ... 18 በመቶ የሚሆኑት የአዲስ መቶ ዓመት መባቻ እንደሆነ ብቻ፣ 17 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የሁለተኛው ሺህ ዓመት መባቻ ብቻ እንደሆነ በመናገራቸው ጥናቱ ስለ ሁለተኛው ሺህ ዓመት አብዛኛው ሰው ምንም የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን አጋልጧል።” በ2000 ዓመትና በክርስቶስ ልደት መካከል ዝምድና መኖሩን ያወቁ 15 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የኤሰክስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር አንቶኒ ኪንግ እንዳሉት ለአብዛኞቹ ሰዎች ሁለተኛው ሺህ ዓመት “የሚጨፈርበት፣ ሻምፓኝ የሚጠጣበት፣ ከወዳጆች ጋር የሚመሽበት ወይም ወደ ውጭ አገር ጉዞ የሚደረግበት ቀን ከመሆን የበለጠ ትርጉም የለውም።” የአንግሊካን ጳጳስ የሆኑት ጋቨን ሬይድ “የምንኖረው ባሕላዊና መንፈሳዊ ትውስታዎቹን ባጣ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው” ብለዋል።
የሚሻለው ወረቀት ነው
ዲፒኤ-ባሲስዲንስት የተባለው የጀርመን ዜና ወኪል “የወረቀትን ያህል ለማንበብ የሚመች የኮምፒዩተር ሞኒተር የለም” ሲል ዘግቧል። ከኮምፒዩተር ሞኒተር ላይ ከማንበብ ይልቅ ከወረቀት ላይ ማንበብ አለብዙ ስህተት በፍጥነት ለማንበብ ያስችላል። በሙከራ እንደተረጋገጠው ከሞኒተር ማንበብ የሚወስደው ጊዜ በወረቀት ከማንበብ በአማካይ ከ10 በመቶ ይበልጣል። አነስተኛ መርገብገብና ከፍተኛ ብሩሕነት ካላቸው ባለ ከፍተኛ ጥራት ሞኒተሮች ማንበብ ሁኔታውን ሊያሻሽል ቢችልም የተገኘው ውጤት ከወረቀት ከማንበብ ጋር ሊተካከል አልቻለም። “በሞኒተር ላይ የሚሠራ ሰው ቀኑን በሙሉ የሚያጭበረብር፣ የሚርገበገብና የሚያንጸባርቅ ሰሌዳ ሲመለከት ይውላል” ይላሉ የአኸን፣ ጀርመን ሳይኮሎጂስቷ ማርቲና ሲፍለ። “የፊደሎቹ መስመሮች ግልጽ አይደሉም፤ የሰሌዳውም ብሩሕነት ደካማ ነው።” “ስለዚህ ኮምፒዩተር በምትገዙበት ጊዜ ለሞኒተሩ ተጨማሪ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል” በማለት ዲፒኤ አጠቃልሏል።
ጭንቀት የሚያስከትለው ከፍተኛ ኪሣራ
“በዓለም ውስጥ ከሥራ ለመቅረትና ለምርታማነት መቀነስ ዋነኛው ምክንያት ከአካላዊ ሕመም ይበልጥ ጭንቀት ነው” ይላል ኦ ግሎቦ የተባለው የብራዚል ጋዜጣ። አንድ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት በ1997 የአእምሮ በሽታ ለ200,000 ሰዎች መሞት ምክንያት እንደሆነ ያመለክታል። በተጨማሪም እንደ ብስጭትና ትካዜ ያሉት ቀለል ያሉ የአእምሮ ቀውሶች በመላው ዓለም 146 ሚልዮን በሚያክሉ ሰዎች የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ተጽእኖ ሲያሳድር ይህ ቁጥር በመስማት ችግር ምክንያት የሥራ እክል ከተፈጠረባቸው 123 ሚልዮን ሠራተኞች ወይም ሥራ ላይ እንዳሉ አደጋ ከሚደርስባቸው 25 ሚልዮን ሠራተኞች ይበልጣል። የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑ ጋይ ጉድዊን ባደረጉት ጥናት መሠረት በመጪዎቹ ዓመታት በጭንቀት የሚሠቃዩ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምርና በዚህም ምክንያት የሚከተለው የምርታማነት መቀነስና የሕክምና ወጪ መጨመር በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል። በአሁኑ ጊዜ እንኳን በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በጭንቀት ምክንያት የሚደርሰው ኪሣራ በዓመት 53 ቢልዮን ዶላር ደርሷል።
የዘመኑ ምልክት
ዘ ቶሮንቶ ስታር ሪፖርት እንዳደረገው “ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የኒውፋውንድላንድ ፖሊሶች ትጥቅ መያዝ ሲጀምሩ አንድ ለብዙ ዘመናት የቆየና ያረጀ የካናዳ ባሕል ይጠፋል።” በ1729 የተቋቋመው የኒውፋውንድላንድ ንጉሣዊ ፖሊስ ሠራዊት “በሰሜን አሜሪካ አለ ጦር መሣሪያ ጸጥታ የሚቆጣጠር የመጨረሻው የፖሊስ ኃይል ነበር።” አዲስ የወጣው ሕግ ይህን የቀድሞ መርሕ ሽሯል። ይህ ሕግ ማንኛውም ፖሊስ ትጥቅ የመያዝ ፈቃድ እንዲሰጠው የቅርብ አለቃውን እንዲጠይቅ ያዝዛል። ፈቃድ ከተሰጠው ፖሊሱ መሣሪያውን በመኪናው ዕቃ ማስቀመጫ ውስጥ በሣጥን ቆልፎ ያስቀምጠዋል። ከዚያም ድንገተኛ ጥሪ ሲያጋጥመው መኪናውን ያቆምና ዕቃ ማስቀመጫውን ከፍቶ መሣሪያውን ከተቆለፈው ሣጥን ውስጥ በማውጣት ያቀባብላል። ጠቅላይ ሚንስትር ብራያን ቶቢን “የቀድሞው መርሕ ቅንነት ያለበትና ለየት ያለ ቢሆንም በዚህ በ1998 ዓመት አንድ የሠለጠነ የፖሊስ ሠራዊት ባለሞያ መሣሪያ አይያዝ ማለት የማይመስል መርሕ ነው” ብለዋል። አሁንም ቢሆን አለቷ በመባል በቁልምጫ የምትጠራው ኒውፋውንድላንድ ከመላው ካናዳ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ወንጀል የሚፈጸምባት አገር እንደሆነችና እስከ አሁን ድረስ ጸጥታ በማስከበር ሥራ ላይ እንዳለ የተገደለ አንድም ፖሊስ እንደሌለ ይነገርላታል።
ያልተመዘገቡ ሕፃናት
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “የልደት ምዝገባ ያልተደረገላቸውና በባለ ሥልጣኖች የተረሱት ሕፃናት ከጠቅላላዎቹ ሕፃናት ሲሶ ያህል ሳይሆኑ አይቀሩም፤ ይህም የትምህርትና የጤና እንክብካቤ እንዳያገኙ ሊያደርግ ይችላል” ሲል ዘግቧል። የልደት ምዝገባ በባሰ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮችና እንደ ካምቦድያ፣ ሕንድ፣ ማያንማርና ቬትናም ባሉት አንዳንድ የእስያ አገሮች ነው። ይህን ጥናት ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ዲሬክተር የሆኑት ካርል በላሚ “የልደት ምሥክር ወረቀት የሌለው ሕፃን ያልተወለደ ያህል ነው” ብለዋል። ብዙ ብሔራት አንድ ልጅ ሕክምና እንዲያገኝ ወይም ትምህርት ቤት እንዲገባ በሚጠየቅበት ጊዜ የልደት ምሥክር ወረቀት እንዲያቀርብ ይጠይቃሉ። ምሥክር ወረቀት የሌላቸው ልጆች ወደ ዝቅተኛ ሥራዎች ወይም ወደ ዝሙት አዳሪነት ለመሰማራት ይገደዳሉ። “ሪፖርቱ እንዳረጋገጠው ለብዙ ሕፃናት አለመመዝገብ ምክንያቱ ድህነት ብቻ አይደለም። ምክንያቱም በአብዛኞቹ የላቲን አሜሪካ፣ ማዕከላዊ አሜሪካና ሰሜናዊ አፍሪካ ያለው የምዝገባ መጠን በጣም ከፍተኛ ነው” ሲል ይህ ጽሑፍ ይገልጻል።
ጠበኛ የፊልም ኮከቦች
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት በመገናኛ ብዙሐን የሚቀርቡ የዓመፅ ድርጊቶች ስለሚያሳድሩት ተጽእኖ ባደረገው ጥናት መሠረት ሕፃናት በአብዛኛው በአድናቆት የሚመለከቱትና ለመምሰል የሚጣጣሩት የኃይል ድርጊት የሚታይበትን ፊልም ኮከቦች ነው። በ23 አገሮች ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው አምስት ሺህ የሚያክሉ የ12 ዓመት ልጆች መካከል 26 በመቶ የሚሆኑት “ከፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኞች እንዲሁም (18.5 በመቶ) ከሙዚቀኞች፣ (8 በመቶ) ከሃይማኖት መሪዎች፣ (3 በመቶ) ከፖለቲካ ሰዎች” አስበልጠው እንደሚመለከቱና ጠባያቸውንም ለመቅዳት እንደሚጣጣሩ መናገራቸውን የብራዚሉ ዦርናል ዳ ታርድ ገልጿል። የጥናቱ አስተባባሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆ ግሮበል ሕፃናት ጠበኛ የሆኑ የፊልም ኮከቦችን ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች መወጣጫ በመፈለግ ረገድ እንደ አርዓያዎቻቸው አድርገው እንደሚመለከቱ ተናግረዋል። ሕፃናት ከኃይል አድራጎቶች ጋር በይበልጥ በተላመዱ መጠን በጣም የከፋ ጠባይ ለማሳየት ይዳፈራሉ። አክለውም “መገናኛ ብዙሐን ጠበኝነት ምንም ስህተት እንደሌለውና የሚያዋጣ ባሕርይ እንደሆነ ያሳምናሉ” ብለዋል። ልጆች ልብ ወለድን ከእውነተኛው ሕይወት እንዲለዩ በመርዳት ረገድ ወላጆች መሠረታዊ ሚና እንዳላቸው ግሮበል አበክረው ተናግረዋል።
በጆሮ ማዳመጫዎች ምክንያት የሚደርስ መደንቆር
የአውስትራሊያ ብሔራዊ የድምፅ ላቦራቶሪ ባካሄደው ምርምር ጆሮ ላይ የሚደረጉ የስቴሪዮ ማዳመጫዎች ከሌላው ጊዜ ባልተለየ ሁኔታ እንኳን መጠቀም ጆሮ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የብርስቤን ዘ ኩርየር ሜይል ገልጿል። ተመራማሪው ዶክተር ኤሪክ ለፓዥ ወጣቶች እንደነዚህ ያሉትን ማስጠንቀቂያዎች ከቁም ነገር አይቆጥሩም ብለዋል። “ለተደጋጋሚ ጊዜያት ወይም ለበርካታ ዓመታት ራሳቸውን ጮክ ላለ ድምፅ ወይም ሙዚቃ አጋልጠው ከቆዩ በኋላ ምንም ጉዳት እንዳላስከተለባቸው ይናገራሉ” ይላሉ። አንድ ጥናት “ሰዎች መደንቆር እስኪጀምሩ ድረስ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ከጉዳይ አይቆጥሩትም” ሲል ማመልከቱን ጋዜጣው ተናግሯል። ይህ አዲስ ጥናት ከ16 እስከ 24 ዓመት ከሚሆናቸው ምልምል ወታደሮች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ጮክ ያለ ሙዚቃ በማዳመጥ የተነሣ በመስማት ችሎታቸው ላይ ጉዳት እንዳደረሱ ያመለከተውን የጀርመን ምርምር ትክክለኛነት ያረጋግጣል። በተጨማሪም “ከ16 እስከ 18 ዓመት ከሚሆናቸው ተማሪዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት በመስማት ችሎታቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት በመድረሱ በመጠነኛ ድምፅ የሚደረጉ ጭውውቶችን መከታተልና መረዳት አቅቷቸዋል።”
“ቁጥር 1 የወጣት ሴቶች ቀሳፊ”
በኢኮኖሚ በበለጸጉ አገሮች ሳንባ ነቀርሳ የሚያጠቃው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸውን ሰዎች እንደሆነ ናንዶ ታይምስ ሪፖርት አድርጓል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ግን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደሚለው ሳንባ ነቀርሳ “ቁጥር 1 የወጣት ሴቶች ቀሳፊ ሆኗል” ሲል ሪፖርቱ ገልጿል። የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ ሳንባ ነቀርሳ ፕሮግራሙ ዶክተር ፖል ዶሊን “ሚስቶች፣ እናቶችና ባለ ሥራዎች በለጋ ዕድሜያቸው እየተቀጩ ናቸው” ብለዋል። በቅርቡ በጎተበርግ፣ ስዊድን በተደረገ የሕክምና ሴሚናር ላይ ተገኝተው የነበሩት ጠበብት በመላው ዓለም ከ900 ሚልዮን የሚበልጡ ሴቶች በሳንባ ነቀርሳ እንደተለከፉ ተናግረዋል። ከእነዚህ መካከል አንድ ሚልዮን የሚሆኑት በየዓመቱ ሲሞቱ አብዛኞቹ ከ15 እስከ 44 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። የሟቾቹ ቁጥር ይህን ያህል ከፍ ካለባቸው ምክንያቶች አንዱ ኦ ኤስታዶ ደ ኤስ ፓውሎ የተባለው የብራዚል ጋዜጣ እንደሚለው ብዙዎቹ በሽታው ጨርሶ ከመዳኑ በፊት መድኃኒታቸውን ማቋረጣቸው ነው።
ብክለት የማያስከትል መኪና
በትላልቆቹ የዓለም ከተሞች ለአየር ብክለት ዋነኞቹ ምንጮች መኪናዎች ናቸው። ይህን ችግር ለመቅረፍ አንድ ፈረንሳዊ መሐንዲስ ድምፅና ሽታ አልባ የሆነ፣ “በአካባቢያችን በሚገኘው አየር የሚንቀሳቀስ” የከተማ መኪና እንደፈለሰፈ የለንደኑ ዘ ጋርድያን ዊክሊ ዘግቧል። የሞተር ንድፍ አውጭው ጋይ ኔግር በታመቀ አየር የሚንቀሳቀስ ሞተር ሠርቷል። የእምቅ አየሩን በርሜል ለመሙላት ሁለት ዶላር ብቻ የሚያወጣ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠይቅ ሲሆን መኪናው ከተሞላ በኋላ በከተማ ውስጥ አነዳድ 100 ኪሎ ሜትር በሰዓት በሚደርስ የመጨረሻ ፍጥነት ለአሥር ሰዓት መጓዝ ይችላል። መኪናው ፍሬኑ ተይዞ ሲቆም የውጭውን አየር ስቦ ያስገባል። ካርቦን የሚያጣራ መሣሪያ ስላለው ከሞተሩ የሚወጣው አየር ከገባው አየር የበለጠ ንጹሕ ነው። የሜክሲኮ ባለሥልጣኖች በሌሎች ብክለት የማያስከትሉ ተሽከርካሪዎች ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ የከተማይቱን 87,000 ታክሲዎች በዚህ መኪና ለመተካት መርጠዋል።
ቤተሰብ አንድ ላይ ሲመገብ
በአሥራዎቹ ዓመታት ዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 527 ወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ቢያንስ በሳምንት አምስት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አንድ ላይ እራት የሚመገቡ ወጣቶች “አገደኛ ዕፅ የመውሰዳቸው፣ ወይም በጭንቀት ስሜት የመያዛቸው አጋጣሚ ዝቅተኛ እንደሆነና በትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎቻቸው የበለጠ ትጋት እንደሚያሳዩ፣ ከእኩዮቻቸውም ጋር ያላቸው ግንኙነት የተሻለ እንደሆነ አመልክቷል” ሲል የካናዳው ቶሮንቶ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። “‘ጥሩ ምግባር የላቸውም’ የሚባሉ ወጣቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚመገቡት በሳምንት ውስጥ ለሦስት ወይም ከዚያ ላነሱ ቀናት ብቻ ነው።” ብሩስ ብራይን የተባሉት የስነ ልቦና ተመራማሪ የቤተሰብ መመገቢያ ሰዓት መኖር “የአንድ ጤናማ ቤተሰብ ባሕርይ” መሆኑን አረጋግጠዋል። አብሮ መመገብ የቤተሰቡን ትስስር እንደሚያጠናክር፣ ሐሳብ የመግለጽ ችሎታ እንደሚያዳብር እንዲሁም አንድ የመሆን መንፈስ እንደሚያሳድር ሪፖርቱ ይገልጻል። በተጨማሪም ጥሩ የገበታ ሥርዓት ለማስተማር፣ ለመጨዋወት፣ ለመቀላለድና ለመጸለይ ጥሩ አጋጣሚ ያስገኛል። ዘወትር አብሮ በሚመገብ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ልጅ ሁልጊዜ አብረን የማንመገብ ቢሆን ኖሮ “ከቤተሰቦቼ ጋር ይህን ያህል ቅርበት የሚኖረኝ አይመስለኝም” ብላለች።
ማግባት ጤናማ ነው
አንድ ተመራማሪ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ እንዳሉት ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች ባለትዳር መሆን “ዕድሜ ያስረዝማል፣ አካላዊና ስሜታዊ ጤንነት ያሻሽላል፣ የገቢ መጠን ከፍ እንዲል ያደርጋል።” የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሊንዳ ጄ ዌይት ያደረጉት ጥናት በ1972 ወጥቶ የነበረውን ባለ ትዳር ሴቶች የበለጠ ሥነ ልቦናዊ ጫና ይደርስባቸዋል የሚለውን ሪፖርት ያስተባብላል። ዶክተር ዌይት “ትዳር በሰዎች ባሕርይ ላይ” ብዙ አልኮል ከመጠጣት መቆጠብን የመሰለ “በጎ ለውጥ እንደሚያስከትል” ደርሰውበታል። በተጨማሪም ትዳር ጭንቀት የሚቀንስ ይመስላል። እንዲያውም “ወንደ ላጤዎች በአብዛኛው የመንፈስ ጭንቀት እንዳለባቸው በጥናቱ መጀመሪያ ላይ የታየ ሲሆን በላጤነታቸው በቆዩ መጠን ጭንቀታቸው እየጨመረ እንደሚሄድ ተረጋግጧል።” ይሁን እንጂ የሚነሶታ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ዊልያም ጀ ዶርቲ ይህ አኃዝ የሚያመለክተው አማካይ ሁኔታዎችን ብቻ እንደሆነና ያገባ ሁሉ የተሻለ ሕይወት ይመራል ወይም ጥሩ የትዳር ጓደኛ ምርጫ ያላደረገም ቢሆን ይበልጥ ደስተኛና ጤነኛ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።