የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምንድን ነው?
“ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ፣ መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤ የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል ድምፅም ከሰማይ መጣ።”—ሉቃስ 3:21, 22
ሐዋርያው ጳውሎስ በጥንቷ ግሪክ ለነበረ አንድ የፈላስፎች ቡድን ንግግር ሲያደርግ አምላክን “የሰማይና የምድር ጌታ” በማለት ጠርቶታል። ጳውሎስ “ዓለምንና በዓለም ያለውን ሁሉ የፈጠረው” እንዲሁም “ሕይወትንና እስትንፋስን፣ ሌሎችንም ነገሮች ለሰው ሁሉ የሚሰጥ” በማለት የተናገረው ስለዚሁ አምላክ ነው። (ሥራ 17:24-28 የ1980 ትርጉም) አምላክ ይህን ሁሉ ሊያከናውን የቻለው እንዴት ነው? በመንፈስ ቅዱሱ ወይም በአንቀሳቃሽ ኃይሉ አማካኝነት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ብዙ ኃይልና ከፍተኛ ብርታት’ እንዳለው ይገልጻል። (ኢሳይያስ 40:26) አዎን፣ አምላክ መላውን ጽንፈ ዓለም መፍጠሩ ከፍተኛ ኃይልና ብርታት እንዳለው ማረጋገጫ ይሰጣል።
በሥራ ላይ ያለ ኃይል
መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ኃይል ነው ማለት ሙሉ በሙሉ ትክክል አይሆንም። ይህ የሆነበት ምክንያት ኃይል ሥራ ላይ እንዳልዋለ ሆኖም ተሞልቶ እንደተቀመጠ አዲስ ባትሪ በአንድ አካል ወይም በአንድ ዕቃ ውስጥ ታምቆ ወይም ያለ ሥራ ሊቀመጥ ስለሚችል ነው። ይሁን እንጂ ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክን መንፈስ የሚገልጹት አገልግሎት እየሰጠ ካለ ባትሪ ከሚወጣ የኤሌክትሪክ ዥረት (current) ጋር በሚመሳሰል መንገድ በእንቅስቃሴ ላይ እንዳለ አድርገው ነው። (ዘፍጥረት 1:2 NW) ስለዚህ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ከእርሱ የሚወጣ ወይም በሥራ ላይ ያለ ኃይሉ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን አንድን ተግባር እንደሚያከናውን ወይም ከአምላክ ተለይቶ በአንድ ሥፍራ እንዳለ አድርጎ ይገልጸዋል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሉቃስ 3:21, 22፤ ሥራ 8:39፤ 13:4፤ 15:28, 29) እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ያነበቡ አንዳንድ ሰዎች መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ የተለየና የራሱ ስብዕና ያለው እንደሆነ አድርገው አስበዋል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ በመሰለ አነጋገር የሚጠቀሙት ለምንድን ነው? መንፈስ ቅዱስ ከአምላክ የተለየ ራሱን የቻለ ነገር ነውን?
ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕልውና ከግዑዛን ፍጥረታት ሁሉ እጅግ የተለየ ነው። መንፈስ ስለሆነ አቅመ ውስን በሆነው የስሜት ሕዋሳችን ልናየው አንችልም። (ዮሐንስ 4:24) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክ በሰማይ እንደሚኖርና እዚያም ሆኖ የሰው ልጆችን እንደሚመለከት ይናገራል። (መዝሙር 33:13, 14) ይህ ለመረዳት የሚያዳግት ነገር አይደለም። ፈጣሪ ከሚጠቀምባቸው ንጥረ ነገሮች የሚበልጥ መሆኑ አያጠያይቅም። ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፣ በፈለገው መንገድ ይጠቀምባቸዋል፣ መልክ ያስይዛቸዋል እንዲሁም ይቆጣጠራቸዋል።—ዘፍጥረት 1:1
አምላክ ከማይታየው መኖሪያ ቦታው ሆኖ በማንኛውም ሰዓት ወይም በየትኛውም ቦታ አንድ ነገር እንዲከናወን ማድረግ ይችላል። ስለዚህ በሥራ ላይ ያለው ኃይሉ በሚንቀሳቀስበት ቦታ መገኘት አያስፈልገውም። አንድ ተግባር እንዲያከናውን መንፈሱን መላክ ይችላል። (መዝሙር 104:30) በርቀት የመቆጣጠሪያ መሣሪያ በመጠቀም የቤት ውስጥ ዕቃዎቻቸውን የሚያሠሩ ሰዎች ይህን ጉዳይ በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ። ዛሬ እንደ ኤሌክትሪክ ወይም እንደ ታህተቀይ ሞገድ (infrared wave) ያሉ በዓይን የማይታዩ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን። በተመሳሳይም አምላክ በማይታየው ቅዱስ ኃይሉ ወይም መንፈሱ አማካኝነት ራሱን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ ሳያስፈልገው ዓላማዎቹን በሙሉ ከዳር ማድረስ ይችላል።—ኢሳይያስ 55:11
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት እንዲህ ያለውን ጽንሰ ሐሳብ ለመረዳት አዳጋች ሊሆን ይችላል። መንፈስ ቅዱስ ራሱን የቻለ ኃይል እንደሆነ ተደርጎ መገለጹ አምላክ ሥራው ወደሚከናወንበት ቦታ ራሱን ማንቀሳቀስ ሳያስፈልገው ኃይሉን የሚጠቀምበትን መንገድ መረዳት እንዲችሉ አንባቢዎቹን እንደረዳቸው እሙን ነው። መንፈስ ቅዱስ አንድ ነገር እንዳከናወነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም ሲል ኃይሉን በሰዎች ወይም በነገሮች ላይ ማድረጉን ማመልከቱ ብቻ ነው።
የመንፈስ ቅዱስ የተለያዩ ሥራዎች
ይሖዋ ሕይወት ያላቸውንም ሆነ ሕይወት የሌላቸውን ነገሮች የፈጠረው በመንፈሱ ነው። (መዝሙር 33:6) በተጨማሪም አምላክ ዓመፀኛና ንስሐ የማይገባ የነበረውን ትውልድ በውኃ ለማጥፋት መንፈሱን ተጠቅሟል። (ዘፍጥረት 6:1-22) አምላክ ውድ የሆነውን የልጁን ሕይወት ማርያም ወደምትባል አይሁዳዊት ድንግል ማኅፀን ለማዘዋወር የተጠቀመውም ይህንኑ በሥራ ላይ ያለ ኃይሉን ነው።—ሉቃስ 1:35
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው እንኳን ሳይቀር በጠላቶቻቸው ፊት እውነትን በግልጥና በድፍረት እንዲናገሩ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷቸዋል። (ሚክያስ 3:8) እንዲሁም በዚህ ኃይል አማካኝነት በተለይ ደግሞ ትንቢትን በሚመለከት ልዩ የሆነ ማስተዋል ወይም መረዳት ያገኙ ወንዶችና ሴቶች እንዳሉ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ ቦታዎች ተገልጾ ይገኛል። የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘ አስረግጦ ሊናገር የሚችል አንድም ሰብዓዊ ፍጡር ስለ ሌለ ይህ የመንፈስ ቅዱስ አስደናቂ ሥራ ነው።—2 ጴጥሮስ 1:20, 21
ከዚህም በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስ ሰዎች ተዓምር እንዲፈጽሙ ኃይል ሊሰጣቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በዚህ መንፈስ አማካኝነት የተፈጥሮን ኃይል መቆጣጠር፣ ሕመምተኞችን መፈወስና ሙታንን ሳይቀር ማስነሳት ችሏል። (ሉቃስ 4:18-21፤ 8:22-26, 49-56፤ 9:11) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የአምላክ ምሥክሮች ሆነው በመላው ምድር ላይ እንዲያገለግሉ በማደራጀቱና ኃይል በመስጠቱ በኩል መንፈስ ቅዱስ እንደ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል።—ሥራ 1:8፤ 2:1-47፤ ሮሜ 15:18, 19፤ 1 ቆሮንቶስ 12:4-11
የአምላክ ኃይል ለእኛም ይሠራል
ዛሬ ያሉ የአምላክ ሰብዓዊ አገልጋዮች ከዚህ ያልተገደበ የኃይል ምንጭ ጥቅም ማግኘት ይችሉ ይሆን? አዎን! አምላክ ሕዝቦቹ ፈቃዱን እንዲረዱና እንዲያደርጉ ለመርዳት ሲል መንፈስ ቅዱሱን አትረፍርፎ ይሰጣቸዋል። አምላክ በቅን ልቦና አበክረው ለሚለምኑት፣ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ላላቸውና ከአቋም ደረጃዎቹ ጋር ተስማምተው ለሚኖሩት ሁሉ መንፈሱን ያድላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 2:10-16) ይህ መንፈስ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች እንቅፋቶች ቢኖሩባቸውም አምላክን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ‘ከወትሮው የተለየ ኃይል’ በመስጠት ይረዳቸዋል። በእርግጥም የአምላክን መንፈስ የማግኘትና መንፈሱን ሳያጡ መኖር ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ምኞት ነው።—2 ቆሮንቶስ 4:7 NW፤ ሉቃስ 11:13፤ ሥራ 15:8፤ ኤፌሶን 4:30
አምላክ በቅርቡ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ያሉትን የፍትሕ መጓደሎችና ሥቃይ ለማስወገድ ተወዳዳሪ በማይገኝለት ኃይሉ ይጠቀማል። በዚህ መንገድ ታላቁንና ቅዱስ ስሙን ይቀድሳል። መንፈስ ቅዱስ በመላው ዓለም ላይ መልካም ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ፍሬዎች ለሁሉም ግልጽ ሆነው ይታያሉ። ይህም ለፈጣሪ ክብር ያመጣለታል።—ገላትያ 5:22, 23፤ ራእይ 21:3, 4