ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ...
ካለሁበት አካባቢ ርቆ ከሚኖር ሰው ጋር ለጋብቻ መጠናናት የምችለው እንዴት ነው?
“በይሖዋ ምሥክሮች ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የተገኘን አንድ የልዑካን ቡድን ወዳረፈበት ሆቴል ሸኝቼ መመለሴ ነበር። ወደ ቤት ልመለስ ስል ሌላ ቡድን መጣና ቆሜ ከእነርሱ ጋር ማውራት ጀመርኩ። በዚህ ወቅት ነበር ከኦዴት ጋር የተዋወቅነው። ከሳምንት በኋላ በሌላ አጋጣሚ እንደገና ተገናኘን። ደብዳቤ ለመጻጻፍ አድራሻ ተለዋወጥን። ደብዳቤ መጻጻፍ ከጀመርን ከሁለት ዓመት በኋላ ለጋብቻ መጠናናት ጀመርን።”—ቶኒ
ዓለም በጣም ከመቀራረቧ የተነሳ እንደ አንድ ትንሽ መንደር ሆናለች። ካለፉት አሥርተ ዓመታት ወዲህ በቅናሽ ዋጋ በአውሮፕላን መጓዝ መቻሉ፣ በዓለም ዙሪያ የተዘረጋው የስልክ መስመር፣ ፈጣን የደብዳቤ ልውውጥና ኢንተርኔት በፍቅር ዓለም ውስጥ አዳዲስ ምቹ ሁኔታዎች ፈጥረዋል። በተጨማሪም በመቶዎች እንዲያውም በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው በሚኖሩ ሰዎች መካከል ለጋብቻ መጠናናት የሚለው ሐሳብ የብዙ ሰዎችን በተለይ ደግሞ የትዳር ጓደኛ የማግኘቱ አጋጣሚ አነስተኛ በሆነበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ቀልብ የሚስብ ሊሆን ይችላል።
ተራርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች ጋብቻን አስመልክቶ ያደረጉት መጠናናት በረከት አስገኝቶላቸዋል። “ደስተኛ ትዳር ከመሠረትን እነሆ አሁን 16 ዓመት ሆኖናል” በማለት ቶኒ ይናገራል። እንዲያውም አንድ ወንድና አንዲት ሴት ጉድለትን እንዳያዩ ሊያሳውራቸው የሚችለው አካላዊ መሳሳብ ሳይኖር በርቀት የሚያደርጉት መጠናናት የተሻለ ውጤት ሊያስገኝላቸው ይችላል ብለው የሚከራከሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ። በተራራቁ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የሚያደርጉት መጠናናት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ሊኖሩ ቢችልም የራሱ የሆኑ ችግሮችም አሉት።
እርስ በርስ መተዋወቅ
ለትዳር የምታስቡትን ሰው የቻላችሁትን ያክል ማወቃችሁ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ፍራንክ የተባለ አንድ ባል ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “የግለሰቡን ማንነት ማለትም ‘የተሰወረውን የልብ ሰው’ ማወቅ ቀላል አይደለም።” (1 ጴጥሮስ 3:4) በሌላ አገር ከምትኖር ከአንዲት ሴት ጋር ለጋብቻ የተጠናና ደግ የተባለ አንድ ሌላ ክርስቲያን ደግሞ “ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስበው የሚፈለገውን ያክል እርስ በርሳችን እንዳልተዋወቅን ይሰማኛል” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል።
በመቶዎች እንዲያውም በሺዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚኖርን አንድ ግለሰብ በደንብ ማወቅ ይቻላል? አዎን፣ ይቻላል። ሆኖም ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። “ለስልክ የምንከፍለው ገንዘብ ስላልነበረን በሳምንት አንድ ጊዜ መጻጻፍ ጀመርን” በማለት ደግ ይናገራል። ጆአን እና ፍራንክ ግን ደብዳቤ መጻጻፉ ብቻውን በቂ ሆኖ አላገኙትም። “በመጀመሪያ ደብዳቤ ተጻጻፍን፤ ከዚያም በስልክ መነጋገር ጀመርን” በማለት ጆአን ተናግራለች። “በመጨረሻም ፍራንክ ትንሽ ቴፕ ላከልኝና በየሳምንቱ ድምፃችንን እየቀረጽን መላላክ ጀመርን።”
ሐቀኝነት፣ አማራጭ የሌለው መንገድ
የምትገናኙት በየትኛውም የመገናኛ መስመር ይሁን ሐቀኛ መሆናችሁ አማራጭ የሌለው ነገር ነው። “የምትዋሹ ከሆነ የኋላ ኋላ መገለጡ ስለማይቀር ዝምድናችሁን ይጎዳዋል” በማለት ኤስተር የተባለች አንዲት ክርስቲያን ሚስት ትናገራለች። “እርስ በርሳችሁ ሐቀኞች ሁኑ። ለራሳችሁም ሐቀኞች ሁኑ። የማትስማሙበት አንድ ጉዳይ ካለ ችላ ብላችሁ አትለፉት። ተነጋገሩበት።” ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” በማለት ጥሩ ምክር ይለግሳል።—ኤፌሶን 4:25፤ ከዕብራውያን 13:18 ጋር አወዳድሩ።
የግድ ልትወያዩባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ለትዳር የሚጠናኑ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ስለ ግቦቻቸው፣ ስለ ልጆች፣ ስለ ገንዘብና ስለ ጤና ነክ ጉዳዮች መወያየት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ የተለየ ትኩረት የሚያሻቸው ሌሎች ጉዳዮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል ከተጋባችሁ አንዳችሁ ወይም ሁለታችሁም የመኖሪያ ቦታ መቀየር ይኖርባችሁ ይሆናል። ታዲያ ይህን ለማድረግ በአእምሮም ሆነ በስሜት ዝግጁዎች ናችሁ? ዝግጁ መሆናችሁን እንዴት ልታውቁ ትችላላችሁ? ከዚህ ቀደም አካባቢ ቀይራችሁ ወይም ለተወሰኑ ጊዜያት ከወላጆቻችሁ ተለይታችሁ ታውቃላችሁ? የጆአን እጮኛ ሁለቱም ፈቃደኛ ሠራተኞች ሆነው የዚህ መጽሔት አዘጋጅ በሆነው በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት እንዲያገለግሉ ይፈልግ ነበር። “በትንሽ ገንዘብ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ መኖር እችል እንደሆነ ጠየቀኝ” በማለት ጆአን ታስታውሳለች። “በዝርዝር መነጋገር አስፈልጎን ነበር።”
ለጋብቻ የምታጠኑት ሰው ከባሕር ማዶ የሚኖር ከሆነ የዚያን አገር ባሕል ለመልመድ ፈቃደኞች ናችሁ? “በዕለታዊ ሕይወታችሁ የአንዳችሁ ባሕል ሌላውን ያስደስተዋልን?” በማለት ፍራንክ ይጠይቃል። “ዝምድናችሁ እየጠነከረ ከመሄዱ በፊት በጣም አስፈላጊ ስለሆነው ስለዚህ ጉዳይ ቀደም ብላችሁ ተነጋገሩ። ስሜታችሁ ከማየሉ ወይም ብዙ ገንዘብ ከማውጣታችሁ በፊት ቀደም ብላችሁ ስለ ጉዳዩ ብትወያዩ ትጠቀማላችሁ።” አዎን፣ በሌላ ባሕል ሥር ሆኖ ዕለታዊ ሕይወትን መግፋት ጎብኚ ሆኖ ጥቂት ቀናት ከማሳለፍ ፈጽሞ የተለየ ነው። ሌላ ቋንቋ መማር ይኖርባችሁ ይሆን? በኑሮ ሁኔታዎች ረገድ ያሉትን ትልቅ ልዩነቶች ማስተካከል ትችሉ ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ ከግለሰቡ ይልቅ ይበልጥ የማረካችሁ ባሕሉ ይሆን? እንዲህ ያለው ስሜት ከጊዜ በኋላ መጥፋቱ አይቀርም። የጋብቻ ማሰሪያ ግን ሁለት ሰዎችን የሚያጣምረው ለዘለቄታው ነው።—ማቴዎስ 19:6
ቶኒ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በአንድ አገር የምትኖር አንዲት የማውቃት ሴት የካሪቢያን ተወላጅ የሆነ አንድ ሰው ታገባለች። ሆኖም የደሴት ኑሮ በጣም ይከብዳታል። የአየሩ ጠባይ ሁልጊዜ ሞቃታማ ነው፤ በመሆኑም ጤናዋ ተቃወሰ። ምግቡም ጭምር የተለየ ነበር፣ በዚህ ላይ ደግሞ የቤተሰቧን ናፍቆት መቋቋም አልቻለችም። በዚህ ምክንያት ወደ እሷ አገር ሄደው ለመኖር ተስማሙ። ይሁን እንጂ ባሏም በተራው የዚያ አገር ኑሮ በፍቅረ ነዋይ ላይ በጣም ያተኮረ ሆኖ አገኘው፤ እንዲሁም አገሩ ሳለ ያገኘው የነበረውን የቤተሰብና የጎረቤት ቅርርብ እዚህ ፈጽሞ ሊያገኝ አልቻለም። አሁን ሁለቱም ተለያይተው በየትውልድ አገራቸው ይኖራሉ። ሁለቱ ልጆቻቸው የሁለቱን ወላጆቻቸውን ፍቅርና ትኩረት ማግኘት ሳይችሉ ቀሩ።”
በጣም ርቆ በሚገኝ አካባቢ የሚኖርን ምናልባትም የተለየ ባሕል ያለውን ሰው ማግባት ሌሎች ተፈታታኝ ችግሮችንም ሊያስከትል ይችላል። ለጉዞና ለስልክ የሚሆን ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት ዝግጁዎች ናችሁ? ሊዲያ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ፊል ለስልክ የማወጣው ወጪ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ መጋባት አለብን እያለ ይቀልድ ነበር። ዞሮ ዞሮ ግን አሁንም እናቴን በስልክ ለማነጋገር ወጪ ማውጣታችን አልቀረም!” ልጆች ቢወለዱስ? አንዳንድ ልጆች ስለ ዘመዶቻቸው ምንም የሚያውቁት ነገር ሳይኖር ያድጋሉ፤ ሌላው ቀርቶ በቋንቋ ልዩነት ምክንያት ዘመዶቻቸውን በስልክ ለማነጋገር እንኳ ሳይችሉ ይቀራሉ! ይህ ማለት ግን እንደነዚህ ያሉት ችግሮችን መወጣት አይቻልም ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እንዲህ ወደመሰለው ትዳር ውስጥ ከመግባቱ በፊት ወጪውን ማስላት ይኖርበታል።—ከሉቃስ 14:28 ጋር አወዳድር።
ምን ዓይነት ሰው ነው (ነች)?
ጓደኛችሁ ግልጽና እውነተኛ መሆኑን እንዴት ማወቅ ትችላላችሁ? ማቴዎስ 7:17 “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል” ይላል። ስለዚህ ድርጊቶቹ ምን ያሳያሉ? ድርጊቱና የሚናገራቸው ቃላት የሚስማሙ ናቸው? ያለፉት ታሪኮቹ ለወደፊቱ ያወጣውን ግብ እንደሚፈጽም የሚያሳምኑ ናቸው? “በአንደኛ ደረጃ የተነጋገርነው ስለ ወደፊቱ መንፈሳዊ ግቦቻችን ነበር” በማለት ኤስተር ትናገራለች። “የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኖ ለስምንት ዓመት አገልግሏል። ለዚህን ያህል ጊዜ ማገልገሉ አሁንም በዚሁ ለመቀጠል ያለውን ፍላጎት እንዳምንበት አድርጎኛል።”
ሆኖም ለጋብቻ የምታጠኑት ሰው አንዳንድ ጉዳዮችን ሸፋፍኖ ለማለፍ የሚሞክር ነው እንበል። ወደፊት ይስተካከላል በሚል ጉዳዩን ቸል ብላችሁ አትለፉት። በጥልቀት መርምሩ! ለምን? ብላችሁ ጠይቁ። አንድ ምሳሌ እንዲህ ይላል:- “ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል።” (ምሳሌ 20:5) ሌላ ምሳሌ ደግሞ “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ሲል ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 14:15
ፊት ለፊት መገናኘት
ስለ አንድ ሰው በደብዳቤ ወይም በስልክ ማወቅ የምትችሉት በተወሰነ ደረጃ ብቻ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ ለክርስቲያን ወንድሞቹ በርካታ ደብዳቤዎች ጽፎላው ነበር። እነዚህ ደብዳቤዎች እርስ በርስ የነበራቸውን ፍቅር ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ቢሆንም ዮሐንስ እንዲህ ብሏል:- “እንድጽፍላችሁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፣ ዳሩ ግን . . . ወደ እናንተ ልመጣ አፍ ለአፍም ልናገራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።” (2 ዮሐንስ 12) በተመሳሳይም ከአንድ ሰው ጋር በአካል ተገናኝቶ ጊዜ ከማሳለፍ የተሻለ ምንም ነገር ሊኖር አይችልም። እርስ በርሳችሁ ይበልጥ መቀራረብ ትችሉ ዘንድ አንዳችሁ ሌላው ወገን ወዳለበት ቦታ ሄዳችሁ የተወሰነ ጊዜ ብታሳልፉ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይህ ዓይነቱ ጉዞ ወደፊት መኖሪያችሁ ሊሆን የሚችለውን አገር የአየር ጠባይና የአኗኗር ሁኔታ እንድታዩም አጋጣሚ ሊከፍትላችሁ ይችላል።
አንድ ላይ የምትሆኑበትን ይህን ጊዜ በተሻለ መንገድ ልትጠቀሙበት የምትችሉት እንዴት ነው? አንዳችሁ የሌላውን ጠባይ በደንብ አድርጋችሁ መመልከት እንድትችሉ አንዳንድ ሥራዎችን አብራችሁ ሥሩ። የአምላክን ቃል አንድ ላይ አጥኑ። በጉባኤ ስብሰባዎችና በአገልግሎት አንዱ የሚያደርገውን ተሳትፎ ሌላው ይመልከት። ጽዳትንና ገበያ ወጥቶ መሸመትን የመሰሉ የዕለት ተዕለት የቤት ውስጥ ሥራዎችን አንድ ላይ አከናውኑ። በጣም በተጣበበ የጊዜ ፕሮግራም ውስጥ አንዱ የሚያሳየውን ጠባይ መመልከቱም ስለ ግለሰቡ ባሕርይ ተጨማሪ ፍንጭ ሊሰጣችሁ ይችላል።a
ከዚህም በተጨማሪ ወደፊት አማች ወይም አማት ከሚሆኗችሁ ጋር ጊዜ ማሳለፉም ቢሆን ተገቢ ነው። ከእነርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት ጥረት አድርጉ። ሁለታችሁ ከተጋባችሁ የቤተሰባችሁ አካል መሆናቸው አይቀርም። ታውቋቸዋላችሁ? በመካከላችሁ ጥሩ ወዳጃዊ ዝምድና አለ? ጆአን “በተቻለ መጠን የሁለቱም ቤተሰቦች ቢገናኙ ጥሩ ይሆናል” የሚል ምክር ሰጥታለች። ቶኒም “ጓደኛችሁ ለቤተሰቡ የሚያሳየው ባሕርይ ወደፊት ለእናንተ የሚኖረውን ባሕርይ የሚያሳይ ይሆናል።”
ለጋብቻ የምትጠናኑት ፊት ለፊት በመገናኘትም ይሁን ወይም በስልክና በደብዳቤ በችኮላ ከመወሰን ተቆጠቡ። (ምሳሌ 21:5) ስኬታማ ትዳር ልትመሠርቱ እንደማትችሉ ሆኖ ከተሰማችሁ የጀመራችሁትን መጠናናት ተነጋግራችሁ ብታቋርጡ የጥበብ አካሄድ ይሆናል። (ምሳሌ 22:3) በሌላው በኩል ደግሞ ግልጽና በሐቀኝነት ላይ የተመሠረተ ውይይት ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋችሁ ይሆናል።
ራቅ ብሎ ከሚኖር ሰው ጋር ለጋብቻ መጠናናት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የሚክስም ሊሆን ይችላል። በዚያም ሆነ በዚህ፣ በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። አትቻኮሉ። እርስ በርሳችሁ በሚገባ ተዋወቁ። እንዲህ ካደረጋችሁ በኋላ ለመጋባት ብትወስኑ በመጠናናት ያሳለፋችሁት ጊዜ የምትደሰቱበት እንጂ የምትቆጩበት አይሆንም።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለጋብቻ መጠናናትን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 255-260 ተመልከቱ።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ ግቦቻችሁ፣ ስለ ልጆችና ስለ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች መወያየት የሚኖርባችሁ በመጠናናት ብዙ ከመግፋታችሁ በፊት ነው