እግር ወይም እጅ ማጣት አንተም ላይ ሊደርስ የሚችል ነገር ነውን?
ቤንጃሚን በተቀበረ ፈንጂ ላይ ቆሞ ግራ እግሩን ያጣው በሳራዬቮ ከተማ ላይ የፈነጠቀችውን የጸደይ ፀሐይ ሲሞቅ ነበር። “ለመነሳት ሞክሬ ነበር” ሲል ቤንጃሚን ያስታውሳል። “ሆኖም አልቻልኩም።” ቤንጃሚን በየዓመቱ በተቀበሩ ፈንጂዎች ከሚሞቱት ወይም የአካል ጉዳት ከሚደርስባቸው 20,000 ሰዎች አንዱ ነው።
አንጎላ 15 ሚልዮን በሚደርሱ የተቀበሩ ፈንጂዎች የተሞላች ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ የሚኖር እያንዳንዱ ወንድ፣ ሴትና ሕፃን ከአንድ በላይ ይደርሰዋል። በአሁኑ ጊዜ በአንጎላ ውስጥ እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ 70,000 ሰዎች ይገኛሉ። ከስምንት ሚልዮን እስከ አሥር ሚልዮን የሚደርሱ ፈንጂዎች የተቀበሩባት ካምቦዲያ በዓለማችን ውስጥ እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ በርካታ ሰዎች ከሚገኙባቸው አገሮች ግንባር ቀደሙን ሥፍራ የያዘች ሲሆን ከ236 ሰዎች አንዱ እግሩን ወይም እጁን ያጣ እንደሆነ ይገመታል። በቦስኒያና ሄርዞጎቪና ከሦስት ሚልዮን በላይ ፈንጂዎች ተቀብረው እንደሚገኙ ይነገራል። ይህም በእያንዳንዱ ካሬ ኪሎ ሜትር 59 ፈንጂዎች ተቀብረው ይገኛሉ ማለት ነው።
ይሁን እንጂ ሰዎች እግራቸውን ወይም እጃቸውን የሚያጡት በጦርነት በሚታመሱ አገሮች ውስጥ ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እግራቸውን ወይም እጃቸውን ያጡ 400,000 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች አሉ። በዚህች አገር ውስጥ አብዛኞቹ ዐዋቂዎች እግራቸውን ወይም እጃቸውን የሚያጡት በደፈናው “ፐሪፈራል ቫስኩላር ዲዚዝ” ወይም ፒ ቪ ዲ ተብሎ በሚጠራ ሥር የሰደደ ሕመም ሳቢያ ነው። ፒ ቪ ዲ በርከት ያሉ በሽታዎችን የሚያመለክት አጠቃላይ የሆነ መጠሪያ ነው። ቴበርስ ሳይክለፒዲክ መዲካል ዲክሽነሪ ፒ ቪ ዲን “በእጅና በእግር ውስጥ የሚገኙትን ደም ወሳጅና ደም መላሽ ቧንቧዎች የሚያጠቁ በሽታዎችን፣ በተለይ ደግሞ ወደ እጅና እግር የሚሄደውን ወይም ከእጅና ከእግር የሚመለሰውን ደም ዑደት የሚያስተጓጉሉትን በሽታዎች” የሚያካትት አጠቃላይ የሆነ መጠሪያ ነው የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ለፒ ቪ ዲ ዋነኛው መንስኤ የስኳር በሽታ ነው። ዘ ወርልድ ሄልዝ ሪፖርት 1998 እንዳለው ከሆነ “በ1997 በዓለም አቀፍ ደረጃ በስኳር በሽታ የተያዙ ዐዋቂ ሰዎች ቁጥር 143 ሚልዮን የደረሰ ሲሆን በ2025 ከእጥፍ በላይ በመጨመር 300 ሚልዮን ይደርሳል።”
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብዙ ሰዎች እግራቸውን ወይም እጃቸውን እንዲያጡ ምክንያት የሚሆነው ሁለተኛው ግንባር ቀደም መንስኤ የመኪና፣ የማሽን፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎችና የጦር መሣሪያ አደጋዎችን ጨምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደርሰው የመቁሰል አደጋ ነው። ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆኑት እግራቸው ወይም እጃቸው የሚቆረጠው በእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ሳቢያ ነው። ከዚህም በተጨማሪ 6 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በእብጠት (tumors) እንዲሁም 4 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በፅንስ ወቅት በሚከሰት እክል የተነሳ እጃቸውን ወይም እግራቸውን ያጣሉ።
እጅን ወይም እግርን ያህል ውድ ነገር ማጣት ቀርቶ ማሰቡ ራሱ በጣም የሚረብሽ ነው። ለዚህ አደጋ የሚያጋልጡ ነገሮችን መቀነስ የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? እግርህን ወይም እጅህን ያጣህ ሰው ከሆንክ ሕይወትህን አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህንና ሌሎች ጥያቄዎችን ይዳስሳሉ።