የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
በትዳር ውስጥ ሃይማኖታዊ አንድነት መኖሩ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ቤተሰቡ ራት ለመመገብ ተሰባስቧል። አባትየው ጸሎት እያቀረበ ሳለ እናትየው ድምፅ ሳታሰማ ለሌላ አምላክ ትጸልያለች። ሌላ ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ሚስት ለአምልኮ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትሄድ ባል ወደ አንድ ምኩራብ ይሄዳል። በአንዳንድ ቤተሰቦች አንደኛው ወላጅ ሃኑካ ስለተባለው ስለ አይሁድ የቤተ መቅደስ መታደስ ለልጆቹ ሲያስተምር ሌላኛው ወላጅ ደግሞ ስለ ሳንታ ክሎዝ ያስተምራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከራሳቸው ሃይማኖት ውጭ ያለን ሰው የሚያገቡ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መሄድ ለዚህ ዓይነቱ ሁኔታ መስፋፋት ምክንያት ሆኗል። በአሜሪካ 21 በመቶ የሚሆኑ ካቶሊኮች፣ 30 በመቶ የሚሆኑ ሞርሞኖች፤ 40 በመቶ የሚሆኑ ሙስሊሞችና ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ከእነሱ የተለየ እምነት ካለው ሰው ጋር ተጋብተው እንደሚኖሩ አንድ ጥናት አመልክቷል። ሃይማኖታዊ ጥላቻ ነግሦ ከኖረባቸው ካለፉት በርካታ መቶ ዘመናት አንጻር ሲታይ የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች በጋብቻ ተሳስረው መኖራቸው ተቻችሎ የመኖርን ሁኔታ የሚያሳይ ስለሆነ በአንዳንዶች ዘንድ እንደ አንድ ትልቅ ድል ተቆጥሯል። አንድ የጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ “የትኛውም ዓይነት ቅይጥ የጋብቻ ጥምረት ሊወደስ ይገባዋል” በማለት ጽፏል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ነውን?
በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ የዘር ወይም የጎሳ ጥላቻን እንደማይደግፍ መታወቅ ይኖርበታል። የአምላክ ቃል የዘር መድልዎን ፈጽሞ ያወግዛል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” በማለት ሁኔታውን በግልጽ አስቀምጦታል። (ሥራ 10:34, 35) ይህ በእንዲህ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የይሖዋ አገልጋዮች “በጌታ ብቻ” ማግባት እንዳለባቸው ያስተምራል። (1 ቆሮንቶስ 7:39 NW) ለምን?
የጋብቻ ዓላማ
አምላክ ጋብቻን ያቋቋመው በተጋቢዎቹ መካከል ልዩ የሆነ የጠበቀ ትስስር እንዲኖር በማሰብ ነው። (ዘፍጥረት 2:24) አምላክ ጋብቻን ያቋቋመው በባልንጀርነት አብሮ መኖርን ብቻ በአእምሮው በመያዝ አይደለም። ይሖዋ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ልጆች የማሳደግና ምድራዊ መኖሪያቸውን የመንከባከብ ሥራ ሲሰጣቸው ፈቃዱን ለመፈጸም ሁለቱም አንድ ላይ ተባብረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክቷል። (ዘፍጥረት 1:28) ወንድዬውና ሴቲቱ በዚህ ረገድ አምላክን ለማገልገል መተባበራቸው እንዲያው በባልንጀርነት አብሮ መኖር ብቻ ሳይሆን የተቀራረበና ዘላቂ ትዳር እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።—ከሚልክያስ 2:14 ጋር አወዳድር።
ኢየሱስ “ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት በተናገረ ጊዜ እንዲህ ያለውን የትዳር ጓደኝነት በተዘዋዋሪ መንገድ መጥቀሱ ነበር። (ማቴዎስ 19:6) ኢየሱስ የጋብቻ ጥምረትን አንድን ዕቃ በጋራ እንዲጎትቱ ወይም እንዲያንቀሳቅሱ አንድ ላይ ከሚጠመዱ የጭነት እንስሳት ጋር በማወዳደር በምሳሌ ተናግሯል። በአንድ ቀንበር የተጠመዱ ሁለት እንስሳት ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ለመጎተት ቢሞክሩ ሊደርስባቸው ስለሚችለው ሥቃይ ለአንድ አፍታ አስብ! በተመሳሳይም ከእውነተኛው እምነት ውጭ የሚገኝን ሰው የሚያገባ አንድ ግለሰብ የትዳር ጓደኛው የሚቃወመውን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ጠብቆ ለመኖር በሚያደርገው ጥረት ሥቃይ ውስጥ ሊገባ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ብሎ መናገሩ የተገባ ነው።—2 ቆሮንቶስ 6:14
የተሻለ ጋብቻ
በእውነተኛ አምልኮ አንድ መሆን አንድን ትዳር በእጅጉ ሊያጠናክር ይችላል። “በአምልኮ የተባበሩ መሆን ቤተሰቦች ጤናማና ደስተኛ እንዲሆኑ ከሚያስችሏቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው” በማለት አንድ ጸሐፊ ሐሳብ ሰጥተዋል። መክብብ 4:9, 10 (የ1980 ትርጉም) “የሥራቸው ውጤት መልካም ሊሆን ስለሚችል፣ አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። ከሁለቱ አንዱ ቢወድቅ ሌላው ያነሣዋል” በማለት ይናገራል።
አንድ ባልና ሚስት መላ ሕይወታቸው በአምልኳቸው ዙሪያ እንዲያተኩር ሲያደርጉ በአካል ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም የተባበሩ ይሆናሉ። አንድ ላይ ሆነው ሲጸልዩ፣ አንድ ላይ ሆነው የአምላክን ቃል ሲያጠኑ፣ ከክርስቲያን ባልደረቦቻቸው ጋር ሲሰበሰቡና እምነታቸውን ለሌሎች ሲያካፍሉ በትዳራቸው ውስጥ ያለውን መቀራረብ የሚያጠናክር መንፈሳዊ ሰንሰለት ይገነባሉ። አንዲት ክርስቲያን ሴት ሐሳብ ስትሰጥ “እውነተኛ አምልኮ የሕይወት መንገድ ነው። ለእኔነቴና ለማንነቴ መሠረት የሆነውን ነገር የማይጋራ ሰው ለትዳር መምረጥን ከቶ አላስበውም” ብላለች።—ከማርቆስ 3:35 ጋር አወዳድር።
“በጌታ” የሚያገቡ ሁሉ የትዳር ጓደኛቸው የኢየሱስን ባሕርይ ይከተላል ብለው ሊጠብቁ ይችላሉ። ኢየሱስ ጉባኤውን በፍቅር እንደያዘ ሁሉ ክርስቲያን ባሎችም ሚስቶቻቸውን በዚያው መንገድ መያዝ ይጠበቅባቸዋል። ክርስቲያን ሚስቶች ባሎቻቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:25, 29, 33) ክርስቲያኖች ይህን የሚያደርጉት የትዳር ጓደኞቻቸውን ለማስደሰት ብቻ ብለው ሳይሆን አንዱ ሌላውን ስለያዘበት መንገድ በፊቱ ተጠያቂ የሚያደርጋቸውን አምላክ ለማስደሰት ብለው ነው።—ሚልክያስ 2:13, 14፤ 1 ጴጥሮስ 3:1-7
ክርስቲያን ባልና ሚስቶች በእምነት መመሳሰላቸው አለመግባባቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ይረዳቸዋል። ክርስቲያኖች ‘የራሳቸውን ጥቅም ብቻ’ ሳይሆን ‘የባልንጀራቸውንም ጥቅም እንዲመለከቱ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይመክራቸዋል። (ፊልጵስዩስ 2:4) በእምነት የተሳሰሩ የትዳር ጓደኛሞች ምንም እንኳ የራሳቸው የሆነ የግል ምርጫ ቢኖራቸውም የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለማስተካከል የአምላክን ቃል እንደ ጋራ ባለ ሥልጣን አድርገው ይመለከቱታል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በዚህ መንገድ ክርስቲያኖች “አንድ አሳብ” እንዲኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ይከተላሉ።—1 ቆሮንቶስ 1:10፤ 2 ቆሮንቶስ 13:11፤ ፊልጵስዩስ 4:2
መሳሳብና የጋራ አስተሳሰብ
በአንድ ዓይነት እምነት ከመታቀፍም ባሻገር ለጋብቻ ዝምድና የሚረዱ ሌሎች ነገሮችም አሉ። እርስ በርስ መሳሳብም ትልቅ ድርሻ አለው። (መኃልየ መኃልይ 3:5፤ 4:7, 9፤ 5:10) ይሁን እንጂ አንድ ትዳር ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ የጋራ አስተሳሰብ መያዙ ወሳኝ ነው። አር ዩ ዘ ዋን ፎር ሚ? የተሰኘው መጽሐፍ “ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው አንድ ወንድና ሴት ደስተኛ፣ የተስማማና ዘላቂ የሆነ ዝምድና የመመሥረት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው” ብሏል።
የሚያሳዝነው ግን እርስ በርስ የተሳሳቡ ሰዎች ተጋብተው መኖር እስኪጀምሩ ድረስ ሥር የሰደዱ ልዩነቶች እንዳሏቸው መገንዘብ አለመቻላቸው ነው። ይህን ሁኔታ በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አሠራሩ ስለ ማረከህ ብቻ አንድ ቤት ለመግዛት አሰብክ እንበል። ይሁን እንጂ ቤቱን ገዝተህ ከገባህበት በኋላ የቤቱ መሠረት ጽኑ ሆኖ እንዳልተመሠረተ ትገነዘባለህ። ምንም ያክል ቤቱ ያማረ ቢሆን ጽኑ መሠረት ከሌለው ምንም ዋጋ አይኖረውም። በተመሳሳይም አንድ ሰው ምናልባት ለእርሱ ተስማሚ እንደሆነ አድርጎ ካሰበው ሆኖም ከእርሱ የተለየ እምነት ባለው ሰው ሊማረክ ይችላል። ይሁን እንጂ ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ዝምድናቸው አደጋ ሊገጥመው ይችላል።
የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች ጋብቻ ከመሠረቱ በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ አንዳንድ ችግሮችን ተመልከት:- ቤተሰቡ አምልኮውን የሚያከናውነው የት ነው? ለልጆች የሚሰጠው ሃይማኖታዊ ማሠልጠኛ ምን ዓይነት ነው? ቤተሰቡ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው ለየትኛው ሃይማኖት ነው? አንደኛው የትዳር ጓደኛ እንደ አረማዊ አድርጎ የሚመለከተውን ሃይማኖታዊ ልማድ ወይም በአል እንዲያከብር ሌላኛው የትዳር ጓደኛ ሊጠብቅበት ይገባልን? (ኢሳይያስ 52:11) ማንም ሰው ትዳር ሲመሰርት ምክንያታዊ የሆኑ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረጉ የሚጠበቅ ነገር ቢሆንም ትዳርን ለመታደግ ተብሎ እንኳ ሳይቀር የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሆነ ብሎ መጣስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።—ከዘዳግም 7:3, 4 ጋር አወዳድር፤ ነህምያ 13:26, 27
በሃይማኖት የተከፋፈለ ትዳር ያላቸው አንዳንድ ባልና ሚስት የትዳራቸውን ሰላም ለመጠበቅ ሲሉ የራሳቸውን እምነት በተናጠል ያከናውናሉ። የሚያሳዝነው ግን በተናጠል አምልኮን ማካሄድ በትዳር ውስጥ መንፈሳዊ ክፍተትን ይፈጥራል። በእምነቷ የማይመሳሰላትን አንድ ሰው ያገባች አንዲት ክርስቲያን ሴት ስትናገር “ጋብቻ መሥርተን መኖር ከጀመርን 40 ዓመት ያለፈን ቢሆንም ባለቤቴ ፈጽሞ አያውቀኝም” ብላለች። በተቃራኒው ደግሞ “በመንፈስና በእውነት” አምልኳቸውን የሚያከናውኑ ባልና ሚስት በትዳራቸው ውስጥ አምላክ ማዕከላዊውን ቦታ ይይዛል። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ “በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም” ብሎ ከሚናገረው አባባል ጋር የሚስማማ ነው።—ዮሐንስ 4:23, 24፤ መክብብ 4:12
ልጆችን በተመለከተስ?
በእምነት የማይመሳሰላቸውን ሰው ለማግባት የሚያስቡ አንዳንዶች ልጆቻቸው ለሁለቱም እምነቶች የተጋለጡ ሆነው እንዲያድጉና ከጊዜ በኋላም ራሳቸው እንዲመርጡ ማድረግ እንደሚችሉ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሁለቱም ወላጆች ለልጆቻቸው ሃይማኖታዊ ሥልጠና የመስጠት ሕጋዊም ሆነ ሥነ ምግባራዊ መብት አላቸው፤ ልጆቹም ውሎ አድሮ የራሳቸውን ውሳኔ ያደርጋሉ።a
ልጆች ለሁለቱም ወላጆቻቸው “በጌታ” እንዲታዘዙ መጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ይሰጣቸዋል። (ኤፌሶን 6:1) ምሳሌ 6:20 መታዘዝን በሚመለከት እንዲህ ይላል:- “ልጄ ሆይ፣ የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው።” ለተለያዩ መሠረተ ትምህርቶች ሳይጋለጡ ተመሳሳይ እምነት ባላቸው ወላጆች ያደጉ ልጆች መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ብሎ በሚጠራው አምልኮ አንድ ይሆናሉ።—ኤፌሶን 4:5፤ ዘዳግም 11:19
“በጌታ”
አንድ ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ ትዳርን የተሳካ ለማድረግ የሚያስችል ቁልፍ ከሆነ ማንኛውንም ክርስቲያን ማግባት ጥበብ ነውን? መጽሐፍ ቅዱስ “በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 2:6) ስለዚህ የማግባት አሳብ ያለው አንድ ክርስቲያን የኢየሱስን ዱካ ለመከተል ከልቡ የሚጣጣር እንደ እርሱ ክርስቲያን የሆነ ሰው ለማግኘት ይፈልጋል። የወደፊቱ የትዳር ጓደኛ ራሱን ለአምላክ የወሰነና የተጠመቀ መሆን ይኖርበታል። በፍቅር ላይ የተመሠረተውን የኢየሱስን ባሕርያትና የአምላክን መንግሥት ለመስበክ ያሳይ የነበረውን ቅንዓት ይኮርጃል። ልክ እንደ ኢየሱስ ሕይወቱን የአምላክን ፈቃድ በማድረጉ ሥራ ላይ እንዲያተኩር ያደርጋል።—ማቴዎስ 6:33፤ 16:24፤ ሉቃስ 8:1፤ ዮሐንስ 18:37
ለማግባት የሚያስቡ ሁሉ ከአምላክ የአምልኮ ቤተሰብ ውስጥ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለማግኘት በትዕግሥት በመጠባበቅ የአምላክን መንግሥት ፈቃድ በሕይወታቸው ውስጥ በአንደኛ ቦታ እንዳስቀመጡ ያሳያሉ። እንዲህ ያለው አኗኗር የኋላ ኋላ ደስታ የሞላበትና ይበልጥ አርኪ የሆነ ትዳር ለመመሥረት ያስችላል።—መክብብ 7:8፤ ኢሳይያስ 48:17, 18
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት:- ልጆች የራሳቸውን ሃይማኖት መምረጥ ይኖርባቸዋልን?” የሚለውን የመጋቢት 8, 1997 ንቁ! (የእንግሊዝኛ) ገጽ 26-27ን ተመልከት። በተጨማሪም በ1995 በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመውን የይሖዋ ምሥክሮችና ትምህርት የተባለውን ብሮሹር (እንግሊዝኛ) ከገጽ 24-25 ተመልከት።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሃይማኖት ለተከፋፈሉ ቤተሰቦች የሚሆን እርዳታ
በዛሬው ጊዜ ትዳር መሥርተው የሚኖሩ በርካታ ባልና ሚስቶች በተለያዩ ምክንያቶች በሃይማኖት የተከፋፈሉ ናቸው። አንዳንዶቹ የሌላ ሃይማኖት አባል የሆነን ሰው ለማግባት መርጠው ሊሆን ይችላል። ሌሎቹ ደግሞ መጀመሪያ ላይ ሲጋቡ ተመሳሳይ እምነት የነበራቸው ሲሆን ከጊዜ በኋላ አንደኛው የትዳር ጓደኛ የተለየ አምልኮ በመከተሉ ምክንያት በሃይማኖት የተከፋፈሉ ሆነዋል። በቤተሰብ ውስጥ ሃይማኖታዊ መከፋፈል እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ምክንያቱ ያም ሆነ ይህ የትዳር ጓደኛሞች የተለያየ ሃይማኖት ለመከተል መምረጣቸው የገቡትን የጋብቻ መሃላ አያፈርሰውም ወይም አያቃልለውም። የትዳር ጓደኛሞች በአምልኮ የተባበሩ ባይሆኑም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ትዳርን እንደ ቅዱስና ዘላቂ አድርጎ ይመለከተዋል። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ሐዋርያው ጳውሎስ “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 7:12) በትዳር የተሳሰሩ አንድ ወንድና ሴት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ቢያውሉ ትዳራቸው ፍቅርና አክብሮት የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ በሰላም ለመኖር ያስችላቸዋል።—ኤፌሶን 5:28-33፤ ቆላስይስ 3:12-14፤ ቲቶ 2:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 3:7-9