የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 10/8 ገጽ 24-25
  • የትዳር ጓደኛ መምረጥ የሚቻልበት መንገድ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የትዳር ጓደኛ መምረጥ የሚቻልበት መንገድ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከአካላዊ ቁመና ባሻገር ተመልከት
  • ‘በጌታ ብቻ አግቡ’
  • በሌሎች መራጭነት የሚፈጸም ጋብቻ
  • የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የሚረዳ መለኮታዊ መመሪያ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ጋብቻ​—አፍቃሪ ከሆነው አምላክ የተገኘ ስጦታ
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ጋብቻ—ከአምላክ የተገኘ ስጦታ
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • በዘመናችን ትዳር የሰመረ ሊሆን ይችላል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 10/8 ገጽ 24-25

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የትዳር ጓደኛ መምረጥ የሚቻልበት መንገድ

አንዲት ነጠላ ሴት “ስለ ትዳር አስበሽ ታውቂያለሽ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላት ነበር። “ማሰብ? በጣም እንጂ” ስትል ፈጠን ብላ መለሰች።

ይህች ሴት የሰጠችው ቀጥተኛ መልስ አንዳንድ ሰዎች ለመፈቀርና ጓደኛ ለማግኘት ያላቸውን ጠንካራ ፍላጎት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ብዙዎች የትዳር ጓደኛ ማግኘት በሕይወታቸው ውስጥ እጅግ አንገብጋቢ ከሆኑት ነገሮች አንዱ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። ከዚህ የተነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ሰዎች የትዳር ጓደኛ እንዲያገኙ ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ እንደ አሸን የፈሉ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አሉ። ሆኖም በብዙ የዓለም ክፍሎች ከሰመሩት ትዳሮች ይልቅ የፈረሱት ትዳሮች ቁጥር በልጦ ተገኝቷል።

በምዕራባውያን አገሮች ሰዎች የራሳቸውን የትዳር ጓደኛ መምረጣቸው የተለመደ ነገር ነው። በአንጻሩ ደግሞ በአንዳንድ የእስያና የአፍሪካ አገሮች በወላጆች መራጭነት የሚፈጸም ጋብቻ አሁንም የተለመደ ነገር ነው። በዚያም ሆነ በዚህ የትዳር ጓደኛ የመምረጡ ጉዳይ በቸልታ የሚታይ ነገር አይደለም። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ከሚገጥሙት ውሳኔ ከሚጠይቁ ነገሮች መካከል ትዳርን በተመለከተ የሚያደርገውን ውሳኔ ያህል ሕይወቱን አስደሳች አለዚያም ሐዘን የሞላበት በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነገር የለም ማለት ይቻላል። ፍቅር የሰፈነበት ትዳር እጅግ አስደሳችና አርኪ ሊሆን ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ ጠብ በበዛበት ትዳር ማብቂያ የሌለው የስቃይና የውጥረት ምንጭ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 21:19፤ 26:21

እንደ ሌሎች ሰዎች ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም የጋብቻ ቁርኝታቸው ደስታና እርካታ እንዲያስገኝላቸው ይፈልጋሉ። እንዲሁም አምላክን የማስደሰትና ለእርሱ ክብር የመስጠት ፍላጎትም አላቸው። (ቆላስይስ 3:23) አምላክ የጋብቻ ፈጣሪና መሥራች እንደመሆኑ መጠን የሚያስፈልጉን ነገሮች ምን እንደሆኑና ለእኛ የሚበጀው ነገር ምን እንደሆነ በሚገባ ያውቃል። (ዘፍጥረት 2:22-24፤ ኢሳይያስ 48:17-19) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሰው ልጅ በኖረባቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ጥሩም ሆኑ መጥፎ ትዳሮች ተመልክቷል። ጋብቻ እንዲሳካም ሆነ እንዳይሳካ የሚያደርገው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። (መዝሙር 32:8) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ማንኛውም ክርስቲያን በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያደርግ ሊረዱት የሚችሉትን ግልጽና ተጨባጭ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች አስፍሯል። ከእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ከአካላዊ ቁመና ባሻገር ተመልከት

ግለሰቦች የሚያገቡትን ሰው ራሳቸው መምረጥ በሚችሉባቸው አገሮች የትዳር ጓደኛቸው ሊሆን ከሚችል ሰው ጋር በአጋጣሚ አሊያም በጓደኛ ወይም በቤተሰብ አማካኝነት ይተዋወቁ ይሆናል። በአብዛኛው፣ መጀመሪያ ላይ የፍቅር ስሜት የሚጠነሰሰው በውጫዊ መልክ በመሳብ ነው። ምንም እንኳ ይህ ተፈጥሯዊና ኃይለኛ ግፊት የሚያሳድር መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ትዳር ለመመሥረት ስናስብ ከውጫዊ መልክ ባሻገር እንድንመለከት ያበረታታናል።

ምሳሌ 31:30 “ውበት ሐሰት ነው፣ ደም ግባትም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርን የምትፈራ ሴት ግን እርስዋ ትመሰገናለች” ይላል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ስላለው የማይጠፋ ልብስ’ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 3:4) አዎን፣ ወደፊት የትዳር ጓደኛችሁ ሊሆን የሚችለው ሰው ያሉት መንፈሳዊ ባሕርያት ይኸውም ለአምላክ ያደረ መሆኑና ለአምላክ ያለው ፍቅር እንዲሁም ክርስቲያናዊ ስብዕናው ከአካላዊ ውበቱ ይበልጥ እጅግ ተፈላጊ ናቸው። ተመሳሳይ መንፈሳዊ ግቦች ያሉትን እንዲሁም የአምላክን የመንፈስ ፍሬዎች ለማሳየት የሚጥርን ሰው በመፈለግ ምክንያታዊ የሆነ ምርጫ ለማድረግ ጊዜ መውሰዱ ጠቃሚ ነው። ይህ ደስታ የሰፈነበት የትዳር ጥምረት ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።—ምሳሌ 19:2፤ ገላትያ 5:22, 23

‘በጌታ ብቻ አግቡ’

ልታገቡት የምትፈልጉት ሰው የእናንተ ዓይነት ግብና እምነት ያለው መሆኑ በጣም ወሳኝ ነው። ጋብቻ ሁለቱም ወገኖች በርካታ የባሕርይና የአመለካከት ማስተካከያዎች እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ተፈታታኝ ሁኔታ ነው። ወደፊት የትዳር ጓደኛችሁ ከሚሆነው ሰው ጋር መጀመሪያውኑ ብዙ ተመሳሳይ ነገሮች ካሏችሁ የምታደርጓቸው ለውጦች ይበልጥ ቀላል እንደሚሆኑ መጠበቁ ምክንያታዊ ይሆናል።

ይህ ነገር ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ እንዳይጠመዱ’ ክርስቲያኖችን አጥብቆ ያሳሰበበትን ምክንያት እንድናስተውል ይረዳናል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) ጳውሎስ፣ ተመሳሳይ እምነትና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እውቀት የሌለውን ሰው ማግባት ግጭትና አለመግባባት ሊፈጥር እንደሚችል ያውቅ ነበር። ‘በጌታ ብቻ አግቡ’ የሚለው ምክር ምክንያታዊ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:39 NW) ይህ ምክር የአምላክን አስተሳሰብ ያንጸባርቃል። በጥበብ ምክሩን የሚከተሉ ሰዎች በርካታ አሳሳቢ ችግሮችን ማስወገድ ይችላሉ።—ምሳሌ 2:1, 9

በሌሎች መራጭነት የሚፈጸም ጋብቻ

በሌሎች መራጭነት የሚደረጉ ጋብቻዎች አሁንም የተለመዱ ስለሆኑባቸው አገሮች ምን ለማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል በደቡባዊ ሕንድ ከሚከናወኑት ጋብቻዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በወላጆች መራጭነት እንደሚፈጸሙ አንዳንዶች ገምተዋል። ክርስቲያን ወላጆች ይህን ልማድ መከተል አለመከተላቸው በራሳቸው የግል ውሳኔ ላይ የተመካ ነው። ያም ሆነ ይህ እንዲህ ዓይነቱ በወላጆች መራጭነት የሚደረግ ጋብቻ ስኬታማ የሚሆነው ለመንፈሳዊ ነገሮች የሚሰጠው ዋጋ የላቀ ሲሆን ነው።

በሌሎች መራጭነት የሚደረግ ጋብቻን የሚመርጡ ሰዎች ውሳኔ የማድረጉ ጉዳይ ተሞክሮ ባላቸውና ጎልማሳ በሆኑ ሰዎች እጅ እንደሚወድቅ ይሰማቸዋል። በአፍሪካ የሚኖር አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ “አንዳንድ ወላጆች በልጆቻቸው ዕድሜና ተሞክሮ ማነስ የተነሳ ልጆቹ ለትዳር ያሰቡት ሰው ያለውን መንፈሳዊ ጉልምስና በትክክል መመዘን ይችላሉ ተብሎ ትምክህት ሊጣልባቸው እንደማይቻል ይሰማቸዋል” ብሏል። “ወጣቶች የሕይወት ተሞክሮ ስለሌላቸው ነገሮችን የሚወስኑት በስሜታዊነት ሊሆን ይችላል” ሲል በሕንድ የሚኖር አንድ ተጓዥ አገልጋይ አክሎ ተናግሯል። ወላጆች ከማንኛውም ሰው በተሻለ የልጆቻቸውን ባሕርይ ስለሚያውቁ ለልጆቻቸው ጥበብ ያለበት ምርጫ ለማድረግ ለየት ባለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይሰማቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የወንዱንም ሆነ የሴቷን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባታቸው የጥበብ እርምጃ ይሆናል።

ይሁን እንጂ ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ በማለታቸው በእነርሱ መራጭነት የተፈጸመው ጋብቻ ውሎ አደሮ ችግሮች ከገጠሙት ያልጠበቁት መጥፎ ውጤት ሊደቀንባቸው ይችላል። ወደፊት የትዳር ጓደኛሞች የሚሆኑት ወንድና ሴት አስቀድሞ አንዳቸው ሌላውን ጥሩ አድርጎ ለማወቅ ያላቸው አጋጣሚ በአመዛኙ አናሳ ስለሚሆን ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ “በወላጆች የማሳበብ አዝማሚያ ይፈጠራል” ሲል በሕንድ የሚኖር አንድ ክርስቲያን ወላጅ ተናግሯል።

ለልጃቸው የትዳር ጓደኛ የሚመርጡ ክርስቲያን ወላጆች ምርጫውን ለማድረግ የተነሳሱበትን ዓላማም መመርመር አለባቸው። የትዳር ጓደኛ ምርጫው በፍቅረ ነዋይ ግብ ወይም ክብር ለማግኘት በመፈለግ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ችግሮች ይከሰታሉ። (1 ጢሞቴዎስ 6:9) ስለዚህ ለልጃቸው የትዳር ጓደኛ የሚመርጡ ወላጆች ራሳቸውን እንዲህ እያሉ መጠየቅ አለባቸው:- ‘ይህ ምርጫ የሁለቱን ወገኖች ደስታና መንፈሳዊ ደህንነት ለመጠበቅ የተደረገ ነው? ወይስ የቤተሰቤን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ ወይም ሀብት አሊያም የሆነ የገንዘብ ጥቅም ለማግኘት ብዬ ያደረግሁት ነው?’—ምሳሌ 20:21

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ግልጽና ጠቃሚ ነው። የትዳር ጓደኛ ሲፈለግ፣ ምርጫው የተደረገበት መንገድ ምንም ይሁን ምን ወደፊት የትዳር ጓደኛ ሊሆን የሚችለው ሰው ያለው ምግባርና መንፈሳዊነት ምንጊዜም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት። ይህ ተግባራዊ ሲሆን የጋብቻ ዝግጅት መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ ይከበራል፤ እንዲሁም ተጋቢዎቹ ጠንካራ መንፈሳዊ መሠረት ያለው ጅምር ይኖራቸዋል። (ማቴዎስ 7:24, 25) ይህ ደስታ የሰፈነበት ግሩም ትዳር ለመመሥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ