የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 10/8 ገጽ 20-23
  • ልጃችሁን ከአደጋ ጠብቁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልጃችሁን ከአደጋ ጠብቁ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቤት ውስጥ
  • ከቤት ውጭ
  • ትራፊክ ባለበት አካባቢ
  • ልጆቻችሁን ከጥቃት መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
    ንቁ!—2007
  • ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • የወላጅነት የሥራ ድርሻ
    ንቁ!—2004
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 10/8 ገጽ 20-23

ልጃችሁን ከአደጋ ጠብቁ

ስዊድን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ሦስት ዓመት ገደማ የሚሆናት ሃና ወላጆቿ ካርል ኤሪክና ቢርጊታ የሟቹን ጎረቤታቸውን ቤት ሲያጸዱ አብራቸው ነበረች። ጥቂት እንደቆዩ ሃና ከአንድ ክፍል ውስጥ የመድኃኒት ብልቃጥ ይዛ ብቅ አለች። የተወሰነውን መድኃኒት በልታው ነበር። ቢርጊታ ብልቃጡ ምን መድኃኒት እንደያዘ ስትመለከት ደርቃ ቀረች። የጎረቤታቸው የልብ መድኃኒት የነበረበት ብልቃጥ ነበር።

ሃና ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ ሌሊቱን በሙሉ ከፍተኛ የሕክምና እርዳታ ሲደረግላት ቆየች። የበላችው መድኃኒት መጠን በጤንነቷ ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስ ይችል የነበረ ቢሆንም ምንም ዓይነት መዘዝ አላስከተለባትም። ለምን? መድኃኒቱን ከመብላቷ ትንሽ ቀደም ብሎ ምግብ በልታ ስለነበር ነው። በምታስመልስበት ጊዜ ከሰውነቷ የወጣው ምግብ የተወሰነውን የመድኃኒቱን መርዝ ሰብስቦ ይዞ ነበር።

ሃና የገጠማት ነገር እንግዳ አይደለም። በየዕለቱ በዓለም ዙሪያ በሺህ የሚቆጠሩ ሕፃናት ወደ ሐኪም ወይም ወደ ሆስፒታል እንዲወሰዱ የሚያስገድድ አደጋ ያጋጥማቸዋል። በየዓመቱ ስዊድን ውስጥ ከስምንት ሕፃናት አንዱ በሚያጋጥመው አደጋ ምክንያት የሕክምና እርዳታ ይደረግለታል። እንግዲያው ወላጅ ከሆናችሁ ልጃችሁ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመው የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ልብ በሉ።

ብዙውን ጊዜ ልጆች በለመዷቸው አካባቢዎች እያሉ ማለትም ከቤታቸው አካባቢ ሳይርቁ አደጋ ያጋጥማቸዋል። ይህ የተለመደ ነገር ነው። እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ የሚደርስባቸው ጉዳት ዓይነት ይለያያል። አንድ ሕፃን ከአልጋው ላይ ሊወድቅ ወይም ደግሞ ምግብ ሲበላ ሊያንቀው አለዚያም ትንሽ ነገር ውጦ ጉሮሮው ላይ ሊሰነቀርበት ይችላል። ትናንሽ ልጆች ብዙውን ጊዜ አንድ ነገር ላይ ሲንጠላጠሉ ሊወድቁ ወይም ደግሞ ያገኙትን ነገር ሲነካኩ ወይም ሲቀማምሱ ሊቃጠሉ አለዚያም ራሳቸውን ለመርዝ ሊያጋልጡ ይችላሉ። ትምህርት ቤት መግባት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ደግሞ የትራፊክ አደጋዎች ሊገጥሟቸው ወይም ከቤት ውጭ ሲጫወቱ ሊጎዱ ይችላሉ።

ከእነዚህ አደጋዎች መካከል ብዙዎቹን ማስወገድ ይቻላል። ትንሽ አርቃችሁ በማሰብና ልጃችሁ ያለበትን የእድገት ደረጃ ግምት ውስጥ በማስገባት ጉዳት እንዳይደርስበት አልፎ ተርፎም ለሞት የሚዳርግ አደጋ እንዳይገጥመው ማድረግ ትችላላችሁ። ከ1954 ጀምሮ ስዊድን ውስጥ በተደራጀ መልክ ሲካሄድ የቆየው የልጆች ደህንነት ፕሮግራም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ሆኗል። ከዚያ በፊት በየዓመቱ ከ450 የሚበልጡ ልጆች በአደጋ ምክንያት ይሞቱ ነበር። ዛሬ ግን በየዓመቱ የሚሞቱት ሕፃናት ቁጥር ወደ 70 ዝቅ ብሏል።

ቤት ውስጥ

የሕፃናት የስነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ኬሽቲን ባክስትሮም “የአንድ፣ የሁለት ወይም የሦስት ዓመት ልጆችን ከአደጋ እንዲርቁ ስላስተማራችኋቸው ብቻ እነርሱን አምናችሁ ልትቀመጡ አትችሉም” ብለዋል። እንግዲያው ልጃችሁን ከአደጋ የመጠበቁ ኃላፊነት የተጣለው በእናንተ በወላጆች ላይ ወይም ከልጁ ጋር በሚውሉ አዋቂዎች ላይ ነው ማለት ነው።

ከቤታችሁ እንጀምር። ከጎን ባለው ሣጥን ላይ የሰፈረውን ዝርዝር ተጠቀሙ። ምናልባት አንዳንዶቹ የአደጋ መከላከያ መሣሪያዎች በሁሉም አገሮች አይገኙ ይሆናል ወይም ደግሞ ቢገኙም ዋጋቸው ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁንና ጥቂት ብልሃትና ፈጠራ በመጠቀም ለእናንተ ሁኔታ የሚሠራ መፍትሔ ልትፈጥሩ ትችሉ ይሆናል።

ለምሳሌ ያህል ማዕድ ቤታችሁ ውስጥ ያሉት መሳቢያዎች እጀታቸው እንጨት ማስገባት የሚያስችል ክፍተት ካለው በእጀታዎቹ መካከል እንጨት በመሸጎር ልጆች እንዳይከፍቷቸው ማድረግ ትችላላችሁ። የምድጃችሁንም በር እንዲሁ በተመሳሳይ መንገድ መቀርቀር ትችሉ ይሆናል። በፌስታል የምታስቀምጡት ነገር ሲኖር መቋጠራችሁ አደጋውን ሊቀንሰው ይችላል።

ምናልባትም በቤት ውስጥና በቤቱ አካባቢ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ሌሎች ቀላል አማራጮች ወደ አእምሯችሁ ይመጡ ይሆናል። እነዚህን ዘዴዎች ትናንሽ ልጆች ላሏቸው ወዳጆቻችሁ እንዲሁም ለምታውቋቸው ሰዎች ማካፈል ትችላላችሁ።

ከቤት ውጭ

ልጃችሁ የሚጫወትባቸውን ቦታዎች ተመልከቱ። ከአራት ዓመት በላይ የሆናቸው አብዛኛዎቹ ልጆች ጉዳት የሚደርስባቸው ከቤት ውጭ ሲጫወቱ ነው። ከብስክሌታቸውም ላይ ሆነ በሌላ ምክንያት ወድቀው ጉዳት ይደርስባቸዋል። ከሦስት እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ልጆች በአብዛኛው ለሞት የሚዳረጉት በትራፊክ አደጋና ውኃ ውስጥ በመስጠም ነው።

የመጫወቻ ቦታዎቹን ሁኔታ ስትገመግሙ ልጆቻችሁ እንዳይጎዱባቸው በዚያ ያሉት መጫዎቻዎች በትክክል የሚሠሩ መሆናቸውን አረጋግጡ። ከዥዋዥዌዎች እንዲሁም እየተጠንጠላጠሉ ከሚጫወቱባቸውና ከመሳሰሉት ነገሮች ሥር ያለው ወለል እንደ ተከመረ አሸዋ ያለና ልጆቹ ቢወድቁ እንኳ ለጉዳት የማይዳርግ ነውን?

በቤታችሁ አካባቢ የተጠራቀመ ውኃ ወይም ጅረት አለ? የአንድና የሁለት ዓመት እድሜ ያላቸው ልጆች ለመስመጥ ጥቂት ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ያለው ውኃ ይበቃቸዋል። “ሕፃናት በተጠራቀመ ውኃ ውስጥ በፊታቸው ከወደቁ የትኛው ላይ የትኛው ታች እንደሆነ መለየት ስለማይችሉ እንደገና መነሳት ያቅታቸዋል” ሲሉ የሕፃናት የስነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ባክስትሮም ተናግረዋል።

በመሆኑም ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ያለ አዋቂዎች ጥበቃ ከቤት ውጭ እንዲጫወቱ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በአካባቢያችሁ የተጠራቀመ ውኃ ካለ ልጁ በደንብ ከፍ እስኪል ድረስ ያለማንም ጥበቃ ከቤት ውጭ እንዲጫወት አትፍቀዱለት።

ትራፊክ ባለበት አካባቢ

በቤታችሁ አካባቢ ትራፊክ ካለም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። “ትምህርት ቤት መግባት የሚችሉበት ዕድሜ ላይ ያልደረሱ ልጆች ሊቀበሉ የሚችሉት ግልጽና የማያሻሙ መልእክቶችን ብቻ ሲሆን በአንድ ጊዜ ማተኮር የሚችሉትም አንድ ነገር ላይ ብቻ ነው” ሲሉ ባክስትሮም ተናግረዋል። “ይሁን እንጂ ትራፊክ ግራ ሊያጋባና ሊያምታታ ይችላል።” ልጃችሁ ትምህርት ቤት መግባት የሚችልበት ዕድሜ ላይ ሳይደርስ ብቻውን የመኪና መንገድ እንዲያቋርጥ አታድርጉ። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ልጆች ቢያንስ ቢያንስ 12 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ትራፊክ በሚበዛባቸው ጎዳናዎች ላይ ብስክሌት ለማሽከርከር ብቁ አይሆኑም።

ልጃችሁ ብስክሌት ሲነዳ፣ ተፈናጥጦ ሲሄድ፣ በመንሸራተቻዎች ሲሄድ የራስ መከላከያ ቁር እንዲያደርግ አስተምሩት። በራስ ቅል ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ማከም አስቸጋሪ ሲሆን ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትሉ አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርጉ ይችላሉ! በአንድ የሕፃናት ክሊኒክ የብስክሌት አደጋ ደርሶባቸው የሕክምና እርዳታ ካገኙት መካከል 60 በመቶዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው በራሳቸውና በፊታቸው ላይ ነው። ይሁን እንጂ የራስ መከላከያ ቁር ያደረጉት በራስ ቅላቸው ላይ ያን ያህል የከፋ ጉዳት አልደረሰባቸውም።

በመኪናም ስትጓዙ የልጃችሁ ደህንነት አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጡ። ብዙ አገሮች ልጆች በመኪና ውስጥ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጁ መቀመጫዎች ታሥረው እንዲቀመጡ የሚጠይቅ ሕግ አላቸው። ይህም የትራፊክ አደጋዎች በሚደርሱበት ጊዜ በልጆቹ ላይ የሚደርሰውን የመቁሰልና የሞት አደጋ በእጅጉ ቀንሶታል። በምትኖሩበት አካባቢ እንደነዚህ ዓይነቶቹ መቀመጫዎች ካሉ በእነርሱ መጠቀሙ ለልጃችሁ ሕይወት ዋስትና ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ተቀባይነት ያለው ዓይነት መሆኑንም አረጋግጡ። ለትናንሽ ሕፃናት የሚያገለግለው መቀመጫ ከሦስት ዓመት በላይ ዕድሜ ላላቸው ልጆች ከሚያገለግለው የተለየ እንደሆነ አስታውሱ።

ልጆቻችን ከይሖዋ ያገኘናቸው ውድ ስጦታዎች በመሆናቸው በማንኛውም መንገድ በሚገባ ልንንከባከባቸው ይገባል። (መዝሙር 127:4) ካርል ኤሪክና ቢርጊታ ሃናን ከገጠማት አሳዛኝ ሁኔታ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ልጆቻቸውን ከአደጋ በመጠበቅ ረገድ ያለባቸው ኃላፊነት የሚያሳስባቸው ጥሩ ወላጆች ናቸው። “እርግጥ ከዚያ በኋላ ይበልጥ ጠንቃቆች ሆነናል” ሲል ካርል ኤሪክ ሳይሸሽግ ተናግሯል። ቢርጊታ “ዛሬ የልጅ ልጆች አሉን፤ በመሆኑም መድኃኒቶቻችንን ሁልጊዜ ቆልፈን እናስቀምጣቸዋለን” ስትል ደምድማለች።

[ገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ቤታችሁ ውስጥ የምታደርጉት ጥንቃቄ

• መድኃኒቶች:- መድኃኒቶችን ልጆች እንዳያገኟቸው ቆልፋችሁ አስቀምጡ። ይህ አባባል ያለ ሐኪም ትእዛዝ ለሚገኙና ከቅጠላ ቅጠል ለሚቀመሙ መድኃኒቶችም ቢሆን ይሠራል። ቤታችሁ ለማደር የሚመጡ እንግዶችም መድኃኒቶቻቸውን ልጆቹ በማያገኙት መንገድ እንዲያስቀምጡ ንገሯቸው።

• የቤት ውስጥ መገልገያ ኬሚካሎች:- ልጆች እንዳያገኙት ቁም ሣጥን ውስጥ ቆልፋችሁ አስቀምጡ። ምን መሆናቸው በግልጽ ይታወቅ ዘንድ በተገዙበት በራሳቸው ዕቃ ውስጥ አስቀምጧቸው። ስትጠቀሙባቸውም ቢሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል። ለአጭር ጊዜም እንኳ ቢሆን ክፍሉን ለቅቃችሁ የምትሄዱ ከሆነ ሁልጊዜ ደብቃችሁት ሂዱ። የዕቃ ማጠቢያ ኬሚካሎችን ዝቃጭ በዕቃ ማጠቢያ ማሽን ውስጥ ትታችሁ አትሂዱ።

• ምድጃ:- በማንኛውም ጊዜ ቢሆን የመጥበሻዎች እጀታ ወደ ውጭ ብቅ እንዲል አታድርጉ። የሚቻል ከሆነ ልጆቹ የተጣደ ብረት ድስት እንዳይነኩ መከላከያ ማስገጠሙ አስፈላጊ ነው። ልጁ በተከፈተው የምድጃው በር ላይ ቢንጠለጠል እንኳ ምድጃው ላዩ ላይ የሚወድቅ ዓይነት እንዳይሆን ጥንቃቄ አድርጉ። የምድጃው በር ራሱ መቆለፊያ ያለው መሆን ይኖርበታል። ልጁ የምድጃውን በር ሊነካውና ሊቃጠል ይችል ይሆን? ከሆነ የምድጃው በር ጋር እንዳይደርስ መከላከያ አድርጉለት።

• አደገኛ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች:- ቢላዎች፣ መቀሶችና ሌሎች አደገኛ መሣሪያዎች መቀመጥ የሚኖርባቸው ቁልፍ አለዚያም መሸጎሪያ ባላቸው ቁም ሣጥኖች ወይም መሳቢያዎች ውስጥ ወይም ልጆች በማይደርሱባቸው ቦታዎች ነው። እንደነዚህ ያሉትን ዕቃዎች ስትጠቀሙና ለጊዜውም ስታስቀምጡ ቢሆን ልጁ እንዳይደርስበት ከጠረጴዛው ወይም ከባንኮኒው ጠርዝ ራቅ አድርጋችሁ ወደ መሃል አስቀምጡ። ለሕፃናት ልጆች ክብሪቶችና ፌስታሎች እንኳ ሳይቀሩ አደገኛ ናቸው።

• ደረጃዎች:- በደረጃው ግራና ቀኝ ቢያንስ ከ70 እስከ 75 ሳንቲ ሜትር ከፍታ ያለው መከላከያ አጥር አስገጥሙ።

• መስኮቶችና የሰገነት በሮች:- ልጆች እንዳይከፍቷቸው ወይም ወደ ክፍሉ አየር እንዲገባ ሲባል በሚከፈቱበት ጊዜ በዚያ እንዳይሾልኩ ለመከላከል ልጆች ሊከፍቷቸው የማይችሉ መቀርቀሪያዎች ወይም ከፍ ብለው የተገጠሙ ሠንሰለቶች አለዚያም ሌላ መከላከያ እንዲኖሯቸው አድርጉ።

• የመጻሕፍት መደርደሪያዎች:- ልጁ መንጠላጠልና አንዳንድ ነገሮች ላይ መውጣት የሚወድ ከሆነ የመጻሕፍት መደርደሪያዎችና ሌሎች ረጃጅም የቤት ውስጥ ዕቃዎች እንዳይወድቁ ከግድግዳው ጋር የተያያዙ መሆን አለባቸው።

• የኤሌክትሪክ መስመሮች:- አገልግሎት ላይ የማይውሉ የኤሌክትሪክ መስመሮች በደንብ የታሸጉ መሆን አለባቸው። የራስጌ መብራትና የመሳሰሉት ገመዶች ከግድግዳ ጋር ወይም ከአንድ የቤት ዕቃ ጋር መያያዝ አለባቸው። እንደዚያ ከሆነ ልጁ ገመዱን ሲጎትት ዕቃው ወድቆ አይመታውም። አለዚያ ደግሞ እነዚህን መብራቶች አርቆ ማስቀመጥ ነው። የኤሌክትሪክ ካውያ በጠረጴዛው ላይ ትታችሁ አትሂዱ እንዲሁም ገመዱ ወደ መሬት እንዲንጠለጠል አታድርጉ።

• ሙቅ ውኃ:- የሙቅ ውኃውን መጠን ማስተካከል የምትችሉ ከሆነ ከ50 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በታች እንዲሆን ማድረግ አለባችሁ። እንዲህ ማድረጋችሁ ልጁ ቧንቧውን ቢከፍተው እንዳይቃጠል ይረዳዋል።

• መጫወቻዎች:- ስለታም ጠርዝ ያላቸውን መጫወቻዎች አስወግዱ። ልጁ ወደ አፉ ካደረጋቸው ጉሮሮው ውስጥ ሊሰነቀሩበት ስለሚችሉ ትናንሽ መጫወቻዎችን ወይም የሚነቃቀል አነስተኛ ክፍል ያላቸውን መጫወቻዎች አስወግዱ። የትላልቅ አሻንጉሊቶች ዓይንና አፍንጫ ጥብቅ መሆን አለበት። ልጁ በወለል ላይ ቁጭ ብሎ በሚጫወትበት ጊዜ ትላልቅ ወንድሞቹና እህቶቹ ትናንሽ መጫወቻዎቻቸውን እንዲያርቁ አስተምሯቸው።

• ጣፋጭ ነገሮች:- እንደ ኦቾሎኒ ወይም ከረሜላ ያሉትን ጣፋጭ ነገሮች ልጆቹ በሚያገኙበት ቦታ አታስቀምጡ። ልጁ ጉሮሮ ውስጥ ሊሰነቀሩ ይችላሉ።

[ምንጭ]

ምንጭ:- የልጆች ጉዳይ ቢሮ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አደጋ በሚደርስበት ጊዜ

• መርዝ:- አንድ ልጅ መርዘኛ ፈሳሽ ከወሰደ አፉን ሙልጭ አድርጋችሁ ካጠባችሁ በኋላ አንድ ወይም ሁለት ብርጭቆ ውኃ ወይም ወተት እንዲጠጣ አድርጉት። ከዚያም ሐኪም ወይም የመርዝ መከላከያ ጣቢያ አማክሩ። ዓይኑ ውስጥ የሚያቃጥል ነገር ከገባበት ደግሞ ወዲያውኑ ቢያንስ ለአሥር ደቂቃ ብዙ ውኃ እያፈሰሳችሁ እጠቡት።

• የቃጠሎ ጉዳት:- ቀላል ቃጠሎ ከሆነ በተጎዳው አካል ላይ ቀዝቃዛ ውኃ (በጣም ቀዝቃዛ መሆን የለበትም) ለ20 ደቂቃ ያህል አፍስሱበት። በቃጠሎው የተጎዳው ቦታ ከልጁ መዳፍ የሚሰፋ ከሆነ ወይም ጉዳቱ ፊቱ ላይ፣ በመገጣጠሚያ አካላት ወይም በወገቡ አካባቢ ወይም ብልቱ አካባቢ የደረሰ ከሆነ ልጁን ወደ ድንገተኛ አደጋ እርዳታ መስጫ ክፍል ልትወስዱት ይገባል። ጥልቀት ያላቸው ቁስሎች ሁልጊዜም መታከም ያለባቸው በሕክምና ባለሙያ ነው።

• ጉሮሮው ውስጥ አንድ ነገር ሲሰነቀር:- አንድ ነገር ወደ አየር ባንቧው ገብቶ ከተሰነቀረ ይህንን ነገር ወዲያውኑ ማስወጣት ይኖርባችኋል። ይህን ማድረግ የሚቻልበት አንደኛው ውጤታማ መንገድ የሄምሊክ ዘዴ ነው። ይህን ዘዴ የማታውቁት ከሆነ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሐኪማችሁን አነጋግሩት ወይም ይህንን ዘዴ በሚመለከት ትምህርት በሚሰጥባቸው በልጆች ላይ የሚደርስ አደጋ መከላከያ ወይም የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ ኮርስ ላይ ተገኙ።

[ምንጭ]

ምንጭ:- የስዊድን ቀይ መስቀል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብስክሌት ሲነዱ የራስ መከላከያ ቁር ማድረግ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መኪና ውስጥ አስተማማኝ በሆነ መንገድ መቀመጥ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ