የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g99 12/8 ገጽ 3-5
  • መላውን ዓለም በዕፅ ሱስ ማጥመድ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መላውን ዓለም በዕፅ ሱስ ማጥመድ
  • ንቁ!—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዕፅ ያስከተለው ችግር ምን ያህል ከፍተኛ ነው?
  • ዕፅ የሚያስገኘው ገንዘብና ሥልጣን
  • ከዕፅ ጋር የሚደረገውን ውጊያ በድል አድራጊነት ማጠናቀቅ ይቻል ይሆን?
    ንቁ!—1999
  • የተከለከሉ ዕፆች ሕይወትህን የሚነኩትእንዴት ነው?
    ንቁ!—1999
  • ሰዎች ሱስ የሚያስይዙ ነገሮችን አላግባብ የሚወስዱት ለምንድን ነው?
    ንቁ!—2001
  • ወጣቶችና አደገኛ ዕፆች
    ንቁ!—2003
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1999
g99 12/8 ገጽ 3-5

መላውን ዓለም በዕፅ ሱስ ማጥመድ

ስፔይን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በስፔይን አገር በማድሪድ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የተወለደ ሕፃን እሪ ብሎ ይጮሃል። ነርሷ አባብላ ዝም ልታሰኘው የተቻላትን ያህል ብትሞክርም አልሆነላትም። ሕፃኑ የለመደውን ሄሮይን በማጣቱ በከፍተኛ ሥቃይ ላይ ይገኛል። ይባስ ብሎ ደግሞ በኤች አይ ቪ ቫይረስ ተለክፏል። እናቱ የሄሮይን ሱሰኛ ነች።

በሎስ አንጀለስ የምትኖር አንዲት እናት በመኪናዋ እየተጓዘች ሳለ ሳታውቀው የዕፅ ነጋዴዎች በሚቆጣጠሩት ጎዳና ውስጥ ገባች። ወዲያውኑ የጥይት እሩምታ ተቀበላትና ሕፃን ልጅዋ ተገደለችባት።

ከዚህ በሺህ የሚቆጠር ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በአፍጋኒስታን አንድ ገበሬ የፖፒ ማሳውን ይኮተኩታል። በዚህ ዓመት አዝመራው ጥሩ ሆኖለታል። ምርቱ በ25 በመቶ ጨምሮለታል። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ለሚማስነው የገበሬው ቤተሰብ ኦፒየም ፖፒ ጥሩ ዋጋ ያወጣለታል። ይሁን እንጂ ከሚያማምሩት የኦፒየም ፖፒዎች ሄሮይን ይሠራል። ሄሮይን ደግሞ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ይቀጥፋል።

በሲድኒ አውስትራሊያ የምትኖር አንዲት ዐይን አፋር ልጃገረድ ሁልጊዜ ቅዳሜ ማታ ወደ ዳንስ ቤት ትሄዳለች። በዚያ ከሚገኙት በርካታ ሰዎች ጋር መቀላቀል ያስቸግራት ነበር። በቅርቡ ግን ኤክስታሲ የተባለ ዕፅ ድፍረት እንድታገኝ አስችሏታል። የምትወስዳቸው የዕፅ እንክብሎች በኮንትሮባንድ ከኔዘርላንድ ወደ አውስትራሊያ የገቡ ቢሆኑም በአገሩ የሚገኙ ቤተ ሙከራዎችም ይህንኑ ዕፅ ሠርተው ማከፋፈል ጀምረዋል። ኤክስታሲ ሙዚቃው ይበልጥ እንዲያስደስታት ከማድረጉም በላይ ቁጥብነቷን ሙሉ በሙሉ ያስወግድላታል። እንዲያውም በጣም የምታምር እንደሆነች ይሰማታል።

በአንዲዝ ተራራዎች የሚገኘውን አነስተኛ ማሳ እያረሰ የሚኖረው ማንዌል የተባለ ታታሪ ገበሬ ኮካ መትከል ከጀመረ ወዲህ ኑሮው ተሻሽሎለታል። ማንዌል ይህን ተክል መትከሉን ለመተው ይፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ ይህን እርምጃ መውሰዱ በዚህ አካባቢ የሚገኘውን የኮካ ምርት የሚቆጣጠሩትን ጨካኝ ሰዎች ስለሚያስቆጣ ፈራ።

እነዚህ ዓለማችንን እያመሳት ካለው የዕፅ ሰደድ በስተጀርባ ያሉትን ሰዎች ማንነት የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች ብቻ ናቸው።a እነዚህ ሰዎች ሸማቾችም ሆኑ አምራቾች፣ ወይም ከምኑም ሳይኖሩበት ከዳር ቆመው የሚመለከቱ ንጹህ ሰዎች በዕፅ ምክንያት ሕይወታቸው በአጭሩ እየተቀጨ ነው።

ዕፅ ያስከተለው ችግር ምን ያህል ከፍተኛ ነው?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን “ዕፆች የወንጀል መቀፍቀፊያ በመሆን፣ እንደ ኤድስ ያሉትን በሽታዎች በማዛመት፣ ወጣቶቻችንንና የወደፊት ተስፋችንን በማመናመን ኅብረተሰባችንን እያፈራረሱ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። በማከልም “ዛሬ በመላው ዓለም 190 ሚልዮን የሚያክሉ የዕፅ ተጠቃሚዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። ይህ ችግር የማይነካው አንድም አገር የለም። የዕፅ ንግድ ወደ ድንበሩ ዘልቆ እንዳይገባ ብቻውን መቆጣጠር የሚችል አገርም የለም። የዕፅ ንግድ ያለው ዓለም አቀፋዊ ባሕርይ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንድንወስድ ያስገድደናል” ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰው ሠራሽ ዕፆችb መመረትና መሸጥ መጀመራቸው ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል። እነዚህ ሰው ሠራሽ ኬሚካሎች ተጠቃሚው ሰው የመፈንጠዝ ስሜት እንዲሰማው ወይም ደስ ደስ እንዲለው የሚያደርጉ ናቸው። ሰው ሠራሽ ዕፆች አለ ብዙ ወጪ፣ በየጓዳው ሊሠሩ የሚችሉ በመሆናቸው ፖሊሶች ፈጽሞ ሊቆጣጠሯቸው አልቻሉም። በ1997 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የናርኮቲክ መድኃኒቶች ኮሚሽን በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ሰው ሠራሽ ዕፆች “የሸማቹ ሕዝብ ባሕል ዋነኛ ክፍል” በመሆናቸው “በሚቀጥለው ምዕተ ዓመት የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዋነኛ ሥጋት” ሆነው መታየት እንዳለባቸው አስጠንቅቋል።

አዲሶቹ ዕፆች ያላቸው ኃይል ከቀዳሚዎቹ የሚተናነስ አይደለም። እንዲያውም ክራክ ኮኬይን የተባለው ከተራው ኮኬይን የበለጠ ሱስ የማስያዝ ባሕርይ አለው። አዲሶቹ የካናቢስc ዓይነቶች የቅዠት ዓለም ውስጥ የመክተት ከፍተኛ ኃይል ያላቸው ሲሆን አይስ የተባለው አዲስ ሰው ሠራሽ ዕፅ ከፍተኛ ጉዳት ከሚያስከትሉት የዕፅ ዓይነቶች አንዱ ነው።

ዕፅ የሚያስገኘው ገንዘብና ሥልጣን

ዕፅ ተጠቃሚዎች ከጠቅላላው ኅብረተሰብ ጋር ሲወዳደሩ በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም ለዕፅ ቱጃሮች ማለትም የዕፆችን ምርትና ስርጭት ለሚቆጣጠሩት ሰዎች በጣም ከፍተኛ የሆነ ሥልጣንና ኃይል ለማስገኘት ችለዋል። እነዚህ ሰዎች የሚያካሂዱት ሕገ ወጥ ንግድ በዓለም ላይ ከሚካሄደው ንግድ ሁሉ በትልቅነቱና በአትራፊነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሊሆን ችሏል። ባሁኑ ጊዜ የዕፅ ንግድ ከጠቅላላው ዓለም አቀፍ ንግድ 8 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፣ ወይም በዓመት ወደ 400,000,000,000 የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይህን የሚያክለው በዕፅ ንግድ የሚገኘው ገንዘብ በዓለም ዙሪያ በሚሽከረከርበት ጊዜ ወንበዴዎችን ያበለጽጋል፣ የፖሊስ አባሎች በሙስና እንዲዘፈቁ ያደርጋል፣ የፖለቲከኞችን መዳፍ ያረጥባል አልፎ ተርፎም የአሸባሪዎችን ወጪ ይሸፍናል።

ታዲያ ዕፅ የሚያስከትለውን ችግር ለመቅረፍ ሊደረግ የሚችል ነገር ይኖር ይሆን? የዕፅ ንግድ ኪስህን፣ የራስህን ደህንነትና የልጆችህን ሕይወት የሚነካው እስከ ምን ድረስ ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ ጽሑፍ ዕፅ (drugs) የሚለው አጠራር ከሕክምና አገልግሎት ውጭ፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚሠራጩትን ሱስ የሚያስይዙ አደገኛ መድኃኒቶችንና ዕፆችን ያመለክታል።

b እነዚህ ዕፆች በተከለከሉ ናርኮቲኮችና አደገኛ መድኃኒቶች ላይ ከተጣለው እገዳ ለማምለጥ ሲባል ኬሚካላዊ አወቃቀራቸው በትንሹ ለወጥ እንዲል የተደረጉ ናቸው።

c ማሪዋና የሚሠራው ከካናቢስ የደረቁ አበቦች የላይኛ ክፍል ነው። ከዚሁ ተክል የሚወጣው ሙጫው ሐሺሽ ይሆናል። ሁለቱም በዕፅ ወሳጆች የሚጨሱ ናቸው።

[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዓለም አቀፍ የዕፅ ምርትና ዝውውር

ዋነኞቹ የማምረቻ አካባቢዎች:-

ካናቢስ—ቅጠሉ (ማሪዋና) ሙጫው ደግሞ (ሐሺሽ)

ሄሮይን

ኮኬይን

ቀስቶቹ የሚያመለክቱት የዕፅ ዝውውር የሚካሄድባቸውን ዋና ዋና መስመሮች ነው።

[ምንጭ]

ምንጭ:- የተባበሩት መንግሥታት ዎርልድ ድራግ ሪፖርት

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

የዩ ኤስ ባሕር ኃይል ፎቶ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ