የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g01 4/8 ገጽ 15-17
  • ስለ ፀጉራችሁ ያላችሁን ግንዛቤ ማስፋት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ ፀጉራችሁ ያላችሁን ግንዛቤ ማስፋት
  • ንቁ!—2001
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የፀጉር እድገትና የፀጉር መርገፍ
  • የራስ ቆዳችሁንና ፀጉራችሁን መንከባከብ
  • የፀጉራችሁ አሠራር
  • ፀጉራችሁ ስለ እናንተ ምን ይናገራል?
  • ስለ ፀጉርህ ትጨነቃለህን?
    ንቁ!—2002
  • አለባበሳችሁና የሰውነታችሁ አቋም ስለ እናንተ ይናገራል
    ወጣትነትህን በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት
  • ኢየሱስ ምን ይመስል ነበር?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ንቁ!—2001
g01 4/8 ገጽ 15-17

ስለ ፀጉራችሁ ያላችሁን ግንዛቤ ማስፋት

“በየትኛውም ዘመን ሆነ ባሕል” ይላል አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ፣ “ፀጉር ስለ አንድ ሰው ውስጣዊ ማንነት የሚያስተላልፈው መልእክት አለው።” እንግዲያው አብዛኞቹ ሰዎች ፀጉራቸው የሚያምርና የሚማርክ ሆኖ እንዲታይ ለማድረግ ቢጥሩ ምንም አያስደንቅም።

ንቁ! መጽሔት የፀጉር ባሕርይንና አያያዝን በተመለከተ ከፍተኛ ልምድ ላካባቱ አራት ፀጉር ሠሪዎች አንዳንድ የተለመዱ ጥያቄዎች አቅርቦላቸዋል። ይህ ቃለ መጠይቅ ፀጉራችሁ ከምታስቡት በላይ ውስብስብ አሠራር ያለው መሆኑን እንድትገነዘቡ ያደርጋችኋል።

የፀጉር እድገትና የፀጉር መርገፍ

ጥያቄ:- ፀጉር የተሠራው ከምንድን ነው?

መልስ:- ፀጉር እንደ ቃጫ ያለ ኬረቲን የተሰኘ ፕሮቲን አለው። እያንዳንዱ ፀጉር የሚወጣው በራስ ቆዳ ላይ በሚገኝ ጉብር የተሰኘ ስንጥቅ በኩል ነው። ከእያንዳንዱ ጉብር በታች ከፍተኛ የደም አቅርቦት ያለው ፓፒላ የሚባል ህብረህዋስ ይገኛል። ይህ ህብረህዋስ በጉብሩ በኩል የሚያድጉና ወደ ፀጉርነት የሚለወጡ የፀጉር ሕዋሳት ያመነጫል።

ጥያቄ:- ብዙዎች ፀጉር ሲቆረጥ ቶሎ ያድጋል ብለው ያምናሉ። ይህ እውነት ነው?

መልስ:- በፍጹም። አንዳንድ ሰዎች የአንድ ዛፍ ቅርንጫፎች በግንዱ አማካኝነት የሚያስፈልጋቸውን ንጥረ ነገሮች እንደሚያገኙ ሁሉ ፀጉርም ከሰውነት ምግብ እንደሚያገኝ አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ፀጉር አንዴ ከራስ ቆዳ አልፎ ከወጣ በኋላ ሙት ንጥረ ነገር ይሆናል። በመሆኑም ፀጉርን መከርከም በእድገቱ ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም።

ጥያቄ:- ፀጉር የሚሸብተው ለምንድን ነው?

መልስ:- የፀጉር ውስጣዊ ንብር ፀጉርን የሚያቀልም ንጥረ ነገር አለው። የዚህ ንጥረ ነገር ሕዋሳት ሲሞቱ ፀጉር ይሸብታል። ይህ የእርጅና ሂደት አንዱ ክፍል ነው። በዘር ውርስ ወይም በበሽታ ምክንያት አስቀድሞ የመሸበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ፀጉር በአንድ ጊዜ ይሸብታል የሚለው አባባል ግን ከእውነት የራቀ ነው። ፀጉርን የሚያቀልመው ንጥረ ነገር የሚገኘው ከራስ ቆዳ በታች ነው። ስለዚህ የሸበተው ፀጉር አድጎ (በወር 1.25 ሴንቲ ሜትር ገደማ) ከራስ ቆዳ በላይ መታየት እስኪጀመር ድረስ ጊዜ ይወስዳል።

ጥያቄ:- ፀጉር የሚረግፈው ለምንድን ነው?

መልስ:- ፀጉር በተፈጥሮ የመርገፍ ባሕርይ አለው። በየቀኑ በአማካይ ከእያንዳንዱ ሰው የራስ ቅል ላይ ከ50 እስከ 80 የሚገመቱ ፀጉሮች ይረግፋሉ። ሆኖም በወንዶች ላይ የሚታየው ራሰ በራነት በዘር የሚተላለፍ ሲሆን በሆርሞን አለመመጣጠን ሳቢያ የሚከሰት ይመስላል። ይህም ፀጉር ለዘለቄታው እንዲረግፍ ያደርጋል። በተጨማሪም አሎፒሺያ የተባለ ፀጉር እንዲረግፍ የሚያደርግ በሽታ አለ።a

ጥያቄ:- አንዳንዶች ፀጉር የጤንነት ነጸብራቅ ነው ይላሉ። ይህን አስተውላችኋል?

መልስ:- አዎ። ደም ከራስ ቆዳ በታች ለፀጉር አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ያቀርባል። ስለዚህ ጤናማ ፀጉር አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ የደም አቅርቦት እንዳለ ሊጠቁም ይችላል። ይሁን እንጂ ጥሩ የአመጋገብ ልማድ የሌለው ወይም የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ የሚጠጣ ሰው ደሙ ለፀጉሩ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች አሟልቶ ማቅረብ ስለማይችል ፀጉሩ ጥንካሬ ሊጎድለውና በቀላሉ ሊሰባበር ይችላል። እንዲያውም የፀጉር መርገፍ ወይም መሰባበር መጀመሪያ ላይ የሚታይ የሕመም ወይም የእርግዝና ምልክት ሊሆን ይችላል።

የራስ ቆዳችሁንና ፀጉራችሁን መንከባከብ

ጥያቄ:- ስለ ሻምፖ አጠቃቀም ብትገልጹልን?

መልስ:- ከተሞክሮ ማየት እንደተቻለው እጅግ አዘውትረው ሻምፖ የሚጠቀሙ ሰዎች በአብዛኛው የራስ ቆዳቸው ይደርቃል። እርግጥ በፀጉራችሁ ላይ ያለው ቅባት ቆሻሻና የቆዳ ብናኞች በመሰብሰብ ከጉብሮቹ ጋር የተያያዙትን የቅባት ቱቦዎች ሊደፍን ይችላል። ስለዚህ ዘወትር በሻምፖ መታጠብ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ የፀጉራችሁ ተፈጥሯዊ ቅባት ቆዳችሁን ጎጂ ከሆኑ ባክቴሪያዎች የሚጠብቅ ከመሆኑም በላይ አስፈላጊ የሆነ እርጥበት በመፍጠር ቆዳችሁን ይሸፍነዋል። እጅግ አዘውትራችሁ ሻምፖ የምትጠቀሙ ከሆነ ግን የራስ ቆዳችሁ ይህን ጥበቃ ሊያጣና እንደ ቆዳ መድረቅ ያሉ ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። አብዛኞቹ ባለሙያዎች የራስ ቆዳ ወይም ፀጉር በሚቆሽሽበት ጊዜ በሻምፖ መታጠብ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። በተፈጥሮው ቅባት የሚበዛው ፀጉር ያላቸው ሰዎች ቅባት የማይበዛው ወይም ደረቅ የሆነ ፀጉር ካላቸው ሰዎች ይበልጥ ሻምፖ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል።

በሻምፖ በምትታጠቡበት ጊዜ የራስ ቆዳችሁን እሹት። እንዲህ ማድረጋችሁ የሞቱ ሕዋሳት ከራስ ቆዳችሁ ላይ እንዲወገዱ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ለፀጉራችሁ አስፈላጊ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች የሚያቀርበው ደማችሁ በጥሩ ሁኔታ እንዲዘዋወር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ከዚያም በደንብ አድርጋችሁ በመታጠብ ሻምፖውን ማስለቀቅ እንዳለባችሁ አትዘንጉ! እጃችሁን በሳሙና ስትታጠቡ ሳሙናውን በደንብ ካላስለቀቃችሁት ቆዳችሁ እንደሚደርቅና እንደሚሰነጣጠቅ ሁሉ ሻምፖውን በደንብ ካላስለቀቃችሁት የራስ ቆዳችሁ ሊደርቅና መቀረፍ ሊጀምር ይችላል።

ጥያቄ:- የራስ ቆዳ በሚደርቅበት ጊዜ ምን ማድረግ ይበጃል?

መልስ:- ብዙ ውኃ መጠጣትና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ጠቃሚ ነው። ይህ ቆዳችሁ እርጥበት እንዲኖረው የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ደማችሁ አስፈላጊ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች ማቅረብ እንዲችል ይረዳዋል። ቆዳችሁን የማያደርቅ ለስላሳ ሻምፖ ተጠቀሙ። የራስ ቆዳችሁን አዘውትራችሁ እሹት። በተጨማሪም አንዳንድ ሰዎች የራስ ቆዳቸው እርጥበት እንዲኖረው ለማድረግ ሲሉ ለዚህ ዓላማ የተዘጋጁ ቅባቶች ይጠቀማሉ።

የፀጉራችሁ አሠራር

ጥያቄ:- አንድ ሰው ወደ ጸጉር ሠሪ ሲሄድ በአእምሮው ሊይዘው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

መልስ:- የፀጉር አሠራራችሁን መለወጥ ከፈለጋችሁ የምትፈልጉትንና የማትፈልጉትን የፀጉር አሠራር የሚያሳይ ጽሑፍ ይዛችሁ ብትሄዱ ይመረጣል። ፍላጎታችሁንና በየዕለቱ ለፀጉራችሁ እንክብካቤ ልታውሉት የምትችሉትን ጊዜ በግልጽ ተናገሩ። ምክንያቱም አንዳንዶቹ የፀጉር አሠራሮች ከሌሎቹ የበለጠ ትኩረት የሚሹ ናቸው። ብዙውን ጊዜ አንድ ፀጉር ሠሪ የፀጉራችሁን ባሕርይ የሚረዳውና ከእናንተ ጋር ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት የሚጀምረው ሁለት ሦስቴ ከሄዳችሁ በኋላ ነው። ስለዚህ ወዲያውኑ ተስፋ ቆርጣችሁ ሌላ ፀጉር ሠሪ ጋር ለመሄድ አትጣደፉ!

ፀጉራችሁ ስለ እናንተ ምን ይናገራል?

የፀጉር አያያዝና አሠራር የአንድን ሰው ማንነት ይገልጻል። ፋሽን ለመከተል፣ ከሃይማኖታዊ እምነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመመላለስ፣ አልፎ ተርፎም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰብን ለማንጸባረቅ ሲባል ፀጉርን መቆረጥ፣ ማሳደግ፣ መተኮስ፣ መጠቅለል፣ ቀለም መቀባትና በተለያዩ መንገዶች መሠራት የተለመደ ነገር ነው። ትንሽ ቆም ብላችሁ ስለ ራሳችሁ ፀጉር ለማሰብ ሞክሩ። ፀጉራችሁ ስለ እናንተ ምን ይናገራል? በሚያምር መንገድ የተሠራ ጤናማ ፀጉር ለባለቤቱ ውበት የሚያጎናጽፍ ከመሆኑም በላይ የሌሎችን አድናቆት ያተርፍለታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በሚያዝያ 22, 1991 የንቁ! እትም (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “አሎፒሺያ​—⁠የፀጉር መርገፍ ችግርን ደብቆ መኖር” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የተመጣጠነ ምግብ መመገብና ብዙ ውኃ መጠጣት የራስ ቆዳን ከድርቀት ለመከላከል ሊረዳ ይችላል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽበት ከእርጅና ጋር ተያይዞ የሚመጣ የተለመደ ሂደት ነው

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እጅግ አዘውትሮ በሻምፖ መጠቀም የራስ ቆዳ ተፈጥሯዊውን ቅባት እንዲያጣና ለጉዳት እንዲጋለጥ ሊያደርግ ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ