ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረበ እንስሳት
በፎቶው ላይ የምታዩት ሳም የተባለው የሦስት ዓመቱ ጎሬላ በእርግጥም ያዘነ ይመስላል። ይሁን እንጂ ይህ ሊያስገርመን አይገባም። አዳኞች እናቱን ገድለው ወላጅ አልባ ያደረጉት ከመሆኑም በላይ ይኖርበት ወደነበረው ዱር የመመለስ አጋጣሚውን አሳጥተውታል። የሚያሳዝነው ሳም ይህንን ፎቶ ከተነሳ ከጥቂት ወራት በኋላ በመተንፈሻ አካል ህመም ምክንያት ሕይወቱ አልፏል። ሆኖም ደህንነቱ አደጋ ላይ የወደቀበት ጎሬላ ሳም ብቻ ነው ማለት አይደለም።
በእነዚህ እንስሳት ተፈጥሮአዊ መኖሪያ ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ውድመት ጎሬላዎች የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው ዝርያዎች ተርታ እንዲመደቡ አድርጓቸዋል። በተጨማሪም በአንዳንድ አካባቢዎች ጎሬላዎች ለምግብነት ሲባል ስለሚገደሉ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቁ አዳኞች የእንስሳቱን ሕልውና አደጋ ላይ ጥለዋል። የጎሬላዎች የወደፊት ዕጣ አስጊ ደረጃ ላይ ይድረስ እንጂ የሌሎች ብዙ ዝርያዎች ዕጣ ከዚህ የከፋ ነው።
የዓለም የተፈጥሮና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሕብረት (IUCN) ያዘጋጀው አንድ ሪፖርት አብዛኛዎቹ የዱር አራዊት ዝርያዎች የሚገኙበትን አሳዛኝ ሁኔታ ይገልጻል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የሌሎች ዝርያዎች ሕልውና አደጋ ላይ የወደቀ ሲሆን ቁጥራቸው እየተመናመነ የመጣበት ፍጥነትም አስደንጋጭ ሆኗል። በቅርቡ በሺህ የሚቆጠሩትን እንስሳት ደህንነት በቅርብ የሚከታተለው የዓለም የተፈጥሮና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሕብረት አደጋ የተጋረጠባቸው የዱር አራዊት የሚገኙበትን አሳሳቢ ሁኔታ በተመለከተ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት በማሰብ አደጋ የተጋረጠባቸው ዝርያዎች በሚል አንድ ዝርዝር አውጥቷል።
በአሁኑ ጊዜ ከጠቅላላው አጥቢ እንስሳት ውስጥ ወደ አንድ አራተኛ የሚጠጉትና አንድ ስምንተኛ የሚሆኑት የአእዋፍ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል። ይህ ቁጥር የሚያመለክተው ደግሞ ስታትስቲካዊ መረጃ ያላቸውን ዝርያዎች ብቻ ነው። አብዛኞቹ የምድራችን ዝርያዎች የሚገኙበት ሁኔታ በትክክል አይታወቅም።
ይህ ሁኔታ አንተን የሚያሳዝንህ ከሆነ ፈጣሪያችንንማ ምን ያህል አሳዝኖት ይሆን? በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ . . . የእኔ ናቸው።” (መዝሙር 50:10) ስለዚህ በራሱ የእጅ ሥራ ላይ ይህ ነው የማይባል ጥፋት ሲደርስ ዝም ብሎ አይመለከትም። አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋ’ በራእይ መጽሐፍ ላይ ማረጋገጫ ሰጥቶናል።―ራእይ 11:18
አምላክ ‘ሁሉን አዲስ በሚያደርግበት’ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ሁለት አጣዳፊ ሥራዎች ይኖሩታል። አንደኛው የምድራችንን የዱር አራዊት መጠበቅ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሁላችንም ሕልውና የተመካበትንና አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰውን አካባቢያችንን መንከባከብ ይሆናል።—ራእይ 21:5፤ ማቴዎስ 6:10
[በገጽ 21 እና 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ነብር (ፓንቴራ ቲግሪስ)
◼ በዱር አለ ተብሎ የሚገመተው ብዛት:- ከ5, 000 እስከ 7, 500 ይደርሳል። (ይህ ቁጥር ከመቶ ዓመት በፊት 100, 000 ገደማ ነበር)
◼ ሕልውናውን በዋነኛነት አደጋ ላይ የጣሉት ነገሮች:- ሕገ ወጥ አደን፣ መመረዝ፣ የመኖሪያ እጦት እና የዝርያዎቹ መበታተን
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ጃይንት ፓንዳ (ኤሉሮፖዳ ሚላኖሉካ)
◼ በዱር አለ ተብሎ የሚገመተው ብዛት:-1, 000 ሲሆን ይህ ቁጥር እንስሳውን በጣም ከተመናመኑት አጥቢ እንስሳት ጎራ ይመድበዋል።
◼ ሕልውናውን በዋነኛነት አደጋ ላይ የጣሉት ነገሮች:- የመራባት ሂደታቸው ዘገምተኛ መሆንና ለምግብነት የሚጠቀሙበት በተራራ ላይ ያሉ የቀርከሃ ደኖች መመናመን
[ምንጭ]
Foto: Zoo de la Casa de Campo, Madrid
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ኦራንጉታን (የጦጣ ዝርያ) (ፖንጎ ፒግሚዩስ)
◼ በዱር አለ ተብሎ የሚገመተው ብዛት:- 20,000 ገደማ
◼ ሕልውናውን በዋነኛነት አደጋ ላይ የጣሉት ነገሮች:- የደን ቃጠሎ፣ በደን የተሸፈኑ ቦታዎች መመናመን፣ ሕገ ወጥ አደንና የለማዳ እንስሳት ንግድ
[ምንጭ]
Foto: Zoo, Santillana del Mar, Cantabria, España
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሌሰር (ቀይ) ፓንዳ (ኤሉረስ ፉልጄንስ)
◼ በዱር አለ ተብሎ የሚገመተው ብዛት:-አይታወቅም። ሆኖም ሰዎች አካባቢያቸውን ከማጥፋታቸውና ካለው ዘገምተኛ የመራባት ሂደት የተነሳ ዝርያው በመመናመን ላይ ያለ ይመስላል።
◼ ሕልውናውን በዋነኛነት አደጋ ላይ የጣሉት ነገሮች:- ሕገ ወጥ አደን፣ በተራራ ላይ የሚገኙት የቀርከሃ ደኖች መውደም እና በአካባቢው ከብቶች ለግጦሽ መሠማራታቸው
[ምንጭ]
Foto: Zoo de la Casa de Campo, Madrid
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ጎልዲ (የጦጣ ዝርያ)(ካሊሚኮ ጎልዲ)
◼ በዱር አለ ተብሎ የሚገመተው ብዛት:- አይታወቅም። (ይህ አጥቢ እንስሳ መኖሩ የታወቀው በ1904 ነው።)
◼ ሕልውናውን በዋነኛነት አደጋ ላይ የጣሉት ነገሮች:- የአማዞን ደኖች መውደምና የዝርያው መበታተን
[ምንጭ]
Foto: Zoo, Santillana del Mar, Cantabria, España
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሬድ ክራውንድ ክሬን (የወፍ ዝርያ)(ግሩስ ጃፖነንሲስ)
◼ በዱር አለ ተብሎ የሚገመተው ብዛት:- 2, 000 ገደማ
◼ ሕልውናውን በዋነኛነት አደጋ ላይ የጣሉት ነገሮች:- ከኤሌክትሪክ ኬብሎች ጋር መጋጨት፣ የመራቢያ አካባቢ ውድመት እና ብክለት
[ምንጭ]
© 1986 Steve Kaufman