የአምላክ ስም ውዝግብ አስነሳ
ኔዘርላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
አንድ አዲስ የደች መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያዘጋጁ ተርጓሚዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንም ሆነ በተራው ሰው መካከል ውዝግብ አስነስተዋል። የውዝግቡ መንስኤ የአምላክን ስም ሄር ወይም “ጌታ” በሚለው ቃል ለመተካት መወሰናቸው ነው።
ተርጓሚዎቹ የሥራቸውን ናሙና ካወጡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በታኅሣሥ 1998 ኬርክ ኤን ቪሮልድ (ቤተ ክርስቲያን እና ዓለም) የተሰኘው የፕሮቴስታንት ድርጅት አባላት የሆኑ ሴቶች ተቃውሟቸውን በደብዳቤ ገልጸዋል። ምክንያታቸው ምን ነበር? “ጌታ” የሚለው ቃል “ወደ ተባዕታይ ጾታ ያደላ” እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ወዲያው ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶችም የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰሙ። የካቲት 1999 ሦስት ምሁራን በዕብራይስጥ የአምላክን ስም የሚወክሉትን አራት ፊደላት የ-ሐ-ወ-ሐ ብሎ መተርጎም እንደሚሻል በመናገር ተቃውሞውን ደገፉ። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፣ ተርጓሚዎች እና የሃይማኖት ምሁራን በጉዳዩ ላይ ለመምከር በአምስተርዳም ተሰባሰቡ። በውይይቱ መደምደሚያ ላይ ሁሉም ተሳታፊዎች በሚስማሙበት አተረጓጎም ላይ ድምፅ እንዲሰጡ ተደረገ።
ኒዩስብላት ፈን ሄት ኖርደን የተሰኘው ጋዜጣ “ስለ ፈጣሪ ብላችሁ በአምላክ ስም አንከራከር” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ ላይ የምርጫውን ውጤት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ጌታ” የሚለው ትርጉም ያገኘው ድምፅ ሰባት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ምርጫዎችም የተሻለ ድምፅ አላገኙም:- ስም (1)፣ . . . መሐሪ (6)፣ የማይሰየም (7)፣ ሕያው (10) እና ዘላለማዊ (15) ድምፅ አግኝተዋል። ከሁሉ የበለጠ ድምፅ ያገኘው . . . የ-ሐ-ወ-ሐ የሚለው ትርጉም ነው!” መጋቢት 15, 2001 የአዲሱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ በበላይነት የሚከታተለው ኮሚቴ መለኮታዊው ስም ደቀቅ ብለው በተጻፉ ትላልቅ የእንግሊዝኛ ሆሄያት (capital letters) ሄር (ጌታ) ተብሎ እንዲተረጎም ወሰነ።
በደች ቋንቋ የትኛው የአምላክ ስም አተረጓጎም የተሻለ እንደሚሆን አለመግባባት ቢኖርም፣ ይህ ውዝግብ ምሁራን አምላክ የግል ስም ያለው መሆኑን እንደሚቀበሉ የሚያሳይ ነው። በዕብራይስጥ የአምላክ ስም יהוה ወይም የ-ሐ-ወ-ሐ የሚሉትን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት የያዘ ነው። ቀደም ሲል የነበሩትና አሁንም ያሉት ሌሎች የደች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የ-ሐ-ወ-ሐን የሚተረጉሙት እንዴት ነው?
በ1762 ኒኮላስ ኩትዜ የተባለ አንድ የደች ሰው ትላልቅ ገጾች ያሉትን የስታተን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጅቶ ነበር። በመቅደሙ ላይ እንዲህ ይላል:- “በሰፊው የሚታወቁና ክብደት የሚሰጣቸውን ምክንያቶች መሠረት በማድረግ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የመታሰቢያ ስም አልተረጎምነውም።” እንደ ፕሮፌሰር ኒኮላስ ቤትስ እና ፔትሩስ አውኩስተስ ደ ኬነስቴት ያሉ ሌሎች ታዋቂ የደች ምሁራንም ይሖዋ በሚለው ስም ተጠቅመዋል።
የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም a ይሖዋ የሚለውን ስም ወጥ በሆነ መንገድ የሚጠቀምበት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። በደች ቋንቋ በተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የመጨረሻ ገጾች ላይ የሚገኘው ተጨማሪ መግለጫ እንዲህ ይላል:- “የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ‘ይሖዋ’ የሚለውን አጠራር የሚጠቀመው በሰዎች ዘንድ ለዘመናት ሲሠራበት የቆየና የተለመደ ስለሆነ ነው። ከዚህም በላይ የ-ሐ-ወ-ሐ የሚሉት የመለኮታዊው ስም አራት ፊደላት . . . ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደርጋል።” በመሆኑም የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክ ስም እውነቱን እንዲያውቁ ረድቷል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።