ግብር መክፈል ይኖርብሃል?
“ለእያንዳንዱ የሚገባውን ስጡ፤ ግብር ከሆነ ግብርን፣ ቀረጥ ከሆነ ቀረጥን፣ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፣ ክብር ለሚገባውም ክብርን ስጡ።”—ሮሜ 13:7
ግብር ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ ከመሄዱ አንጻር ሲታይ ከላይ የተጠቀሰውን ምክር መከተል አስቸጋሪ ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ቃላት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ከመሆናቸውም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ ናቸው። ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት እንዳለህ አይጠረጠርም። ‘ክርስቲያኖች ሁሉንም ዓይነት ግብር፣ ምክንያታዊ ወይም ፍትሐዊ አይደለም ብለው የሚያስቡትን ጭምር መክፈል ይኖርባቸዋል?’ ብለህ ታስብ ይሆናል።
ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ ስለሰጠው ምክር አስብ። የአገሩ ሰዎች የሆኑት አይሁዳውያን፣ ሮማውያን የጣሉባቸውን ግብር አምርረው ይቃወሙ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” ብሏል። (ማርቆስ 12:17) ኢየሱስ የመከረው ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለሚገድለው መንግሥት ግብር እንዲከፈል ነው።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ጳውሎስ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ምክር ሰጠ። በግብር ይሰበሰብ የነበረው ገንዘብ በአብዛኛው ይውል የነበረው የሮማውያንን ሠራዊት ለማንቀሳቀስና የነገሥታቱን የቅንጦት ኑሮ ለመደገፍ ቢሆንም ክርስቲያኖች ግብር እንዲከፍሉ መክሯል። ጳውሎስ ይህን የመሰለ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የማይሆን አቋም የያዘው ለምንድን ነው?
የበላይ ባለ ሥልጣናት
ጳውሎስ በተናገራቸው ቃላት ዙሪያ ያለውን ሐሳብ እንመልከት። በሮሜ 13:1 ላይ “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምንት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” ሲል ጽፏል። የእስራኤል ብሔር ፈሪሐ አምላክ ያላቸው ገዥዎች በነበሩት ጊዜ ብሔሩን በገንዘብ መደገፍ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ ግዴታ እንደሆነ አድርጎ መመልከት አስቸጋሪ አልነበረም። ይሁን እንጂ ገዥዎች የማያምኑና ጣዖት አምላኪዎች በሚሆኑበት ጊዜ ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ግዴታ ይኖርባቸዋል? አዎ፣ ይኖርባቸዋል! የጳውሎስ ቃላት ገዥዎች የመግዛት “ሥልጣን” እንዲኖራቸው የፈቀደው አምላክ እንደሆነ ያመለክታሉ።
መንግሥታት ሥርዓት በማስከበር ረገድ የሚያከናውኑት ሥራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ክርስቲያኖች የተለያዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ለማካሄድ የሚችሉት በዚህ ምክንያት ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ ዕብራውያን 10:24, 25) ስለሆነም ጳውሎስ በሥልጣን ላይ ስለሚገኘው መንግሥታዊ ባለ ሥልጣን ሲናገር “ለአንተ መልካሙን ለማድረግ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው” ብሏል። (ሮሜ 13:4) ጳውሎስ ራሱ የሮማ መንግሥት ይሰጥ በነበረው ጥበቃ ተጠቃሚ ሆኗል። ለምሳሌ ከረብሸኞች እጅ ሊድን የቻለው በሮማ ወታደሮች ነው። በኋላም የሚስዮናዊነት አገልግሎቱን ለመቀጠል እንዲችል በሮማውያን የፍትሕ ሥርዓት መሠረት ይግባኝ ጠይቋል።—የሐዋርያት ሥራ 22:22-29፤ 25:11, 12
ስለዚህ ጳውሎስ ግብር ለመክፈል የሚያስገድዱ ሦስት ምክንያቶች ሰጥቷል። በመጀመሪያ መንግሥታት ሕግ አፍራሾችን ስለሚቀጡበት “ቁጣ” ተናግሯል። ሁለተኛ፣ የአንድ አምላካዊ የሆነ ሰው ሕሊና በግብር ረገድ ቢያጭበረብር በጣም እንደሚጎዳ ገልጿል። በመጨረሻም ግብር መንግሥታት የሕዝብ አገልጋይ በመሆን ለሚያከናውኑት አገልግሎት የሚከፈል ዋጋ እንደሆነ አመልክቷል።—ሮሜ 13:1-6
ታዲያ የጳውሎስ የእምነት ባልደረቦች ምክሩን ልብ ብለውት ነበር? ክርስቲያን ጸሐፊ እንደሆነ የሚነገርለት የሁለተኛው መቶ ዘመኑ ጀስቲን ማርቲር (ከ110 እስከ 165 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ክርስቲያኖች “ግብር ለመክፈል ከሁሉም ሰዎች ይበልጥ ፈቃደኞች ነበሩ” ሲል ጽፏል። ዛሬም መንግሥታት የገንዘብም ሆነ የጊዜ ክፍያ በሚጠይቁበት ጊዜ ክርስቲያኖች በፈቃደኝነት ይታዘዟቸዋል።—ማቴዎስ 5:41a
እርግጥ፣ ክርስቲያኖች በሕግ የተፈቀደላቸውን የቀረጥ ቅናሽ የመጠየቅና የማግኘት መብት አላቸው። ለምሳሌ ለሃይማኖታዊ ድርጅቶች አስተዋጽኦ ለሚያደርጉ ሰዎች በሚሰጠው ከግብር ነጻ የመሆን መብት ተጠቃሚዎች ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ቢሆንም እውነተኛ ክርስቲያኖች የአምላክን ቃል ስለሚታዘዙ ከግብር ወይም ከቀረጥ ለማምለጥ የሚያደርጉት ጥረት አይኖርም። ባለ ሥልጣናት የሰበሰቡትን ገንዘብ እንዴት እንደተጠቀሙበት ሙሉ በሙሉ በኃላፊነት እንደሚጠየቁበት ስለሚያውቁ የተጫነባቸውን ግብር በታዛዥነት ይከፍላሉ።
አግባብ ያልሆነ ከባድ ግብር መጠየቅ ‘ሰው ሰውን ለመጉዳት ከገዛባቸው መንገዶች’ አንዱ ብቻ ነው። (መክብብ 8:9) የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ በአምላክ መንግሥት ሥር ለሚተዳደሩ ሁሉ ፍትሕ እንደሚሰፍን በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይጽናናሉ። ይህ መንግሥት በሰዎች ላይ አግባብ ያልሆነ ግብር ወይም ቀረጥ አይጭንም።—መዝሙር 72:12, 13፤ ኢሳይያስ 9:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር” ስለመስጠት የሰጠው ምክር ግብር በመክፈል ብቻ የተወሰነ አይደለም። (ማቴዎስ 22:21) በሃይንሪክ ማየር የተዘጋጀው ክሪቲካል ኤንድ ኤክሰጀቲካል ሃንድቡክ ቱ ዘ ጎስፕል ኦቭ ማቲው የተባለው መጽሐፍ “የቄሣር ነገሮች . . . የግብርና የቀረጥ ግዴታዎችን ብቻ ሳይሆን ቄሣር በገዥነት ሥልጣኑ ምክንያት ያገኛቸውን መብቶችና ሥልጣኖች በሙሉ እንደሚያመለክት አድርገን መረዳት ይኖርብናል” ሲል ያብራራል።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የጥንት ክርስቲያኖች “ግብር ለመክፈል ከሁሉም ሰዎች ይበልጥ ፈቃደኞች ነበሩ።”—ጀስቲን ማርቲር
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች የግብርና የቀረጥ ሕጎችን ያከብራሉ
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ‘የቄሣርን ለቄሣር ስጡ’ ብሏል
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© European Monetary Institute