ለልጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት
ባለፉት ርዕሶች ላይ እንደተመለከትነው ትንንሽ ልጆች ከወላጆቻቸው ብዙ ትኩረት ማግኘት ቢያስፈልጋቸውም ብዙዎቹ ግን ይህን አላገኙም። የዘመኑ ወጣቶች ሁኔታ የሚያሳየው ይህንን ነው። አንዲት ተመራማሪ በቶሮንቶ፣ ካናዳ በሚታተመው ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው ጋዜጣ ላይ “ወጣቶቻችን የአሁኑን ያህል ከወላጆቻቸው የተነጠሉበትና ተግባራዊ ተሞክሮና ጥበብ ያጡበት ጊዜ የለም” በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል።
ችግሩ ምንድን ነው? ለችግሩ በተወሰነ መጠን አስተዋጽኦ ያበረከተው ነገር ለልጆቻችን ትኩረት የመስጠትን አስፈላጊነት አለመገንዘብ ይሆን? አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች አራስ ልጆቻቸውን እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸው የሚመክሩ አንዲት የሥነ ልቦና ተመራማሪ “ሁላችንም ወላጅ መሆን የሚጠይቀውን ችሎታ መማር ያስፈልገናል” በማለት ገልጸዋል። “አሁን ከትንንሽ ልጆቻችን ጋር የምናጠፋው ጊዜ ሲያድጉ እጥፍ ድርብ ሆኖ እንደሚመለስልን መገንዘብ ያስፈልገናል።”
ሕፃናትም እንኳን ሳይቀሩ በየጊዜው መመሪያ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። አልፎ አልፎ ሳይሆን አዘውትሮ፣ ማለትም ቀኑን ሙሉ መመሪያ ማግኘት ያሻቸዋል። ትንንሽ ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ጊዜ ወስዶ ማሠልጠን ለተሟላ እድገታቸው አስፈላጊ ነው።
የዝግጅት አስፈላጊነት
ወላጆች ይህን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ልጁ ከመወለዱ በፊት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድሚያ እቅድ የማውጣትን አስፈላጊነት አስመልክቶ ከተናገረው መሠረታዊ ሥርዓት ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ። እንዲህ ብሏል:- “ከእናንተ ግንብ ሊሠራ የሚወድ ለመደምደሚያ የሚበቃ ያለው እንደ ሆነ አስቀድሞ ተቀምጦ [ኪ]ሳራውን የማይቆጥር ማን ነው?” (ሉቃስ 14:28) የ20 ዓመት ፕሮጀክት በመባል የሚታወቀው ልጅ የማሳደግ ኃላፊነት ግንብ ከመገንባት የበለጠ የተወሳሰበ ሥራ ነው። ስለዚህ አንድ ግንበኛ ንድፍ እንደሚያስፈልገው ሁሉ አንድን ልጅ በተሳካ መንገድ ለማሳደግም እቅድ ማውጣት ያስፈልጋል።
በመጀመሪያ፣ የወላጅነት ኃላፊነቶችን ለመቀበል አእምሯዊና መንፈሳዊ ዝግጅት አስፈላጊ ነው። በጀርመን በ2,000 ነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ የተካሄደ ጥናት እንዳሳየው ቤተሰብ ለመመሥረት አልመው የተነሱ እናቶች የወለዷቸው ልጆች፣ ሳይፈለጉ ከተወለዱት ልጆች ይልቅ በስሜትም ሆነ በአካል ይበልጥ ጤነኞች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ተመራማሪ በሰጡት አኃዛዊ ግምት መሠረት ፍቅር በሰፈነበት ትዳር ውስጥ ከምትገኝ ሴት ጋር ሲወዳደር ሁከት በነገሠበት ትዳር ውስጥ ያለች ሴት በስሜትም ሆነ በአካል የተጎዳ ሕፃን የመውለድ አጋጣሚዋ 237 በመቶ ነው።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ለተሳካ የልጅ እድገት የአባትየው ድርሻ ወሳኝ ነው። ዶክተር ቶማስ ቬርኒ እንደተናገሩት “ነፍሰ ጡር ሚስቱን ከሚያመናጭቅ ወይም ችላ ከሚል አባት የበለጠ ለአንድ ልጅ ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ደኅንነት አደገኛ የሆኑ ነገሮች በጣም ጥቂት ናቸው።” በእርግጥም አንድ ልጅ ሊያገኝ ከሚችለው ስጦታ ሁሉ የተሻለው እናቱን የሚወድለት አባት ስለመሆኑ ብዙ ተብሎአል።
በእናቲቱ ደም ውስጥ የሚረጩት ከጭንቀትና ከውጥረት ጋር የሚዛመዱ ሆርሞኖችም ሽሉን ሊነኩት ይችላሉ። ይሁን እንጂ በጣም አደገኛ የሚሆነው በእናቲቱ ላይ አልፎ አልፎ የሚከሰት አሉታዊ ስሜት ወይም ውጥረት የሚፈጥር ሁኔታ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነና ለረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ጭንቀት ነው። ከሁሉ ይበልጥ ክብደት ያለው ነገር ነፍሰ ጡሯ እናት በሆዷ ውስጥ ስላለው ልጅ ያላት ስሜት ይመስላል።a
ነፍሰ ጡር ብትሆኚና ባልሽ ግን የማይደግፍሽ ቢሆን ወይም አንቺ ራስሽ ልጅ መውለድ የማትፈልጊ ብትሆኚ ምን ታደርጊያለሽ? አንዲት ሴት በማርገዟ እንድታዝን ሊያደርጓት የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች መኖራቸው አዲስ ነገር አይደለም። ሆኖም የተጸነሰው ልጅ ያጠፋው ነገር እንደሌለ ምንጊዜም አስታውሺ። ታዲያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም የተረጋጋ መንፈስ መያዝ የምትችይው እንዴት ነው?
በአምላክ ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ያለበት መመሪያ ለብዙ ሰዎች ትልቅ እርዳታ አበርክቷል። እንዲህ ይላል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” እነዚህን ቃላት በሥራ ላይ ማዋል “በአንዳች አትጨነቁ” የሚለውን ምክር በተግባር እንድታውዪ እንዴት እንደሚረዳሽ ስታዪ ትገረሚያለሽ። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አሳቢ የሆነውን ፈጣሪ እርዳታ ታገኚያለሽ።—1 ጴጥሮስ 5:7
በአንቺ ላይ ብቻ የደረሰ አይደለም
አንዳንድ ወጣት ሴቶች ከወለዱ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ምክንያቱ የማይታወቅ ኀዘንና ከባድ ድካም ይሰማቸዋል። ልጅ ለመውለድ በደስታ ሲጠባበቁ የነበሩ ሴቶችም እንኳን ስሜታቸው ተለዋዋጭና ብስጩ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ የስሜት መለዋወጥ ያልተለመደ ነገር አይደለም። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሴቶች ከወለዱ በኋላ በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የሆርሞን መጠን በድንገት ስለሚለዋወጥ ነው። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ ለወለዱ ሴቶች እናትነት የሚያስከትላቸው ኃላፊነቶች ማለትም ልጁን መመገብ፣ ሽንት ጨርቅ መቀየርና የጊዜ ትርጉም ምንም ለማይገባው ሕፃን እንክብካቤ ማድረግ ከአቅም በላይ መሆኑ የተለመደ ነው።
አንዲት እናት ልጅዋ የሚያለቅሰው እሷን ለማሰቃየት እንደሆነ ተሰምቷት ነበር። በጃፓን የሕፃናት አስተዳደግ ስፔሻሊስት የሆኑ አንድ ሰው “ልጅ ከማሳደግ ጋር ከሚመጣው ውጥረት ነፃ የሚሆን ሰው የለም” ማለታቸው አያስደንቅም። እኚህ ስፔሻሊስት እንደተናገሩት “ለእናቲቱ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ነገር ራሷን ከሰው አለማግለሏ ነው።”
አንዲት እናት አንዳንድ ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት ቢሰማትም ልጅዋ በእሷ የስሜት መለዋወጥ እንዳይነካ መከላከል ትችላለች። ታይም መጽሔት “የተከዙ እናቶች ለልጆቻቸው በቂ ትኩረት በመስጠትና በማጫወት ኀዘንና ትካዜያቸውን አሸንፈው ሲወጡ ይበልጥ ደስተኛ መንፈስ የተላበሰ አእምሮ ያላቸው ልጆች ሊኖራቸው ችሏል” ብሏል።b
አባት እርዳታ ማበርከት የሚችልበት መንገድ
ብዙውን ጊዜ የሕፃኑ አባት እርዳታና ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል የተሻለ ሁኔታ አለው። ሌሊት ሕፃኑ ሲያለቅስ ሚስቱ አርፋ እንድትተኛ አባትየው ለልጁ የሚያስፈልገውን ነገር ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ሆይ፤ . . . በኑሮአችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ አስቡላቸው” ይላል።—1 ጴጥሮስ 3:7 አ.መ.ት
ኢየሱስ ክርስቶስ ባሎች ሊከተሉት የሚገባውን ፍጹም ምሳሌ ትቷል። ለተከታዮቹ ሲል ሕይወቱን እንኳን ሳይቀር ሰጥቷል። (ኤፌሶን 5:28-30፤ 1 ጴጥሮስ 2:21-24) በመሆኑም ልጆችን በማሳደጉ ሥራ በራሳቸው ተነሳሽነት እርዳታ ለማበርከት ሲሉ የራሳቸውን ምቾት ለመሠዋት ፈቃደኞች የሆኑ ባሎች ክርስቶስን ይመስላሉ። በእርግጥም ልጆችን ማሳደግ ሁለቱም ወላጆች ሊረባረቡበት የሚገባ የጋራ ሥራ ነው።
የጋራ ጥረት
የሁለት ዓመት ሴት ልጅ አባት የሆነው ዮኤቼሮ “ባልና ሚስት እንደመሆናችን መጠን ልጃችንን እንዴት ማሳደግ እንዳለብን በዝርዝር ተወያይተናል” ብሏል። “አንድ አሳሳቢ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ምን ማድረግ እንዳለብን እንወያያለን።” ዮኤቼሮ ሚስቱ በቂ እረፍት ማግኘት እንዳለባት ስለሚገነዘብ ወደ ሱቅም ሆነ ለአንዳንድ ጉዳይ ወጣ ሲል ልጁን ይዟት ይሄዳል።
ብዙ አባሎች ያሉባቸው ቤተሰቦች አንድ ላይ ይኖሩ በነበሩበት ቀደም ባሉት ዓመታት ወላጆች ልጆቻቸውን ለመንከባከብ የትልልቅ ልጆቻቸውንና የዘመዶቻቸውን እርዳታ ያገኙ ነበር። ስለዚህ በጃፓን ካዋሳኪ በሚገኘው የሕፃናት ማሳደጊያ ድጋፍ ሰጪ ማዕከል የምትሠራ አንዲት ሴት የሚከተለውን አስተያየት መስጠቷ አያስደንቅም:- “እናቶች ችግራቸውን ለሌሎች ሲናገሩ በአብዛኛው መፍትሔ ያገኛሉ። ብዙ እናቶች ጥቂት እርዳታ ብቻ በማግኘታቸው በርካታ መሰናክሎችን መቋቋም ችለዋል።”
ፔሬንትስ የተባለው መጽሔት ወላጆች “በቸገራቸው ጊዜ ጠርተው የሚያዋዩአቸው ሰዎች ያስፈልጓቸዋል” ይላል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ማግኘት የሚችሉት የት ነው? ልጅ ለማሳደግ አዲስ የሆኑ እናቶችና አባቶች አእምሯቸውን ክፍት አድርገው የራሳቸው ወላጆች ወይም አማቶች የሚነግሯቸውን በማዳመጥ ብዙ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ልጆቹን በሚመለከት የመጨረሻ ውሳኔ ማድረግ ያለባቸው ወጣት ባልና ሚስቱ መሆናቸውን አያቶቹ መገንዘብ አለባቸው።c
ወጣት የሆኑ ወላጆች ከእምነት አጋሮቻቸውም አስተማማኝ እርዳታ ማግኘት ይችላሉ። በአካባቢያችሁ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ልጆች በማሳደግ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ያካበቱና ችግራችሁን ለማዳመጥ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ልታገኙ ትችላላችሁ። ጠቃሚ ምክር ሊሰጧችሁ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “አሮጊቶች ሴቶች” ብሎ የሚጠራቸውን በክርስቲያናዊ ኑሮ ከፍተኛ ተሞክሮ ያካበቱና ወጣት ሴቶችን ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ እህቶችን እርዳታ መጠየቅ ትችላላችሁ።—ቲቶ 2:3-5
እርግጥ፣ ወላጆች የሌሎችን አስተያየት በሚያዳምጡበት ጊዜ መራጭ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ዮኤቼሮ ሲናገር “በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በድንገት የልጆች አስተዳደግ ባለሞያዎች ሆነው ቁጭ አሉ” ብሏል። ባለቤቱ ታካኮም “መጀመሪያ ላይ ሌሎች ምክር የሚሰጡኝ ተሞክሮ እንደሚጎድለኝ ለመጠቆም ብለው ስለሚመስለኝ የሚሰጡት ሐሳብ ያናድደኝ ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ይሁን እንጂ ብዙ ባሎችና ሚስቶች ከሌሎች በመማር ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን በማቅረብ በኩል ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራቸው ችሏል።
ከሁሉ የተሻለ እርዳታ
እርዳታ ሊሰጣችሁ የሚችል ያለ ባይመስልም እንኳን አንድ አስተማማኝ የሆነ የብርታት ምንጭ አለ። እሱም የፈጠረንና በምድር ላይ የተወለዱትን ሰዎች ‘ያልተሠራ አካል’ ማየት የሚችለው ይሖዋ አምላክ ነው። (መዝሙር 139:16) በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ይሖዋ በአንድ ወቅት ለጥንት ሕዝቦቹ እንደሚከተለው ብሏቸው ነበር:- “በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፣ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፣ እኔ ግን አልረሳሽም።”—ኢሳይያስ 49:15፤ መዝሙር 27:10
በእርግጥም ይሖዋ ወላጆችን አይረሳም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚረዱ ግሩም መመሪያዎችን ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት የአምላክ ነቢይ የነበረው ሙሴ “አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ” በማለት ጽፏል። ቀጥሎም እንዲህ አለ:- “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል [ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት የሰጣቸውን ማሳሰቢያ ጨምሮ] በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።”—ዘዳግም 6:5-7
የዚህ በአምላክ ቃል ውስጥ የሠፈረው መመሪያ ፍሬ ሐሳብ ምን ይመስልሃል? ልጆችህን ማስተማር በየቀኑ መደረግ ያለበት ቀጣይነት ያለው ሂደት መሆን የለበትም? ከልጆችህ ጋር የምታሳልፈው አጭር ሆኖም የታሰበበት ሰዓት አልፎ አልፎ መመደቡ በቂ አይደለም። ጠቃሚ የሐሳብ ልውውጥ የሚደረግባቸው ሁኔታዎች የሚፈጠሩት ሳይታሰብ ስለሆነ ዘወትር ከልጆችህ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ ሊኖርህ ይገባል። እንዲህ ማድረግህ “ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ለመፈጸም ያስችልሃል።—ምሳሌ 22:6
ለትንንሽ ልጆች የሚሰጥ ሥልጠና ለእነሱ ጮክ ብሎ ማንበብንም ይጨምራል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዝሙር የነበረው ጢሞቴዎስ ‘ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያውቅ’ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ስለዚህ ገና ሕፃን ሳለ እናቱ ኤውንቄና ሴት አያቱ ሎይድ ጮክ ብለው ያነቡለት ነበር ማለት ነው። (2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:14, 15) ከሕፃን ልጅህ ጋር መነጋገር እንደጀመርክ ጮክ ብለህ ብታነብለት መልካም ነው። ነገር ግን ምን ልታነብለት ትችላለህ? ገና ሕፃን የሆነን ልጅ እንዴት ልታስተምር ትችላለህ?
መጽሐፍ ቅዱስን ለልጅህ አንብብለት። ለጢሞቴዎስ ይነበብለት የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ግልጽ ነው። ልጆች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እንዲተዋወቁ የሚያስችሉ ማራኪ የሆኑ ሥዕሎች ያሏቸው መጻሕፍትም አሉ። እነዚህ መጻሕፍት ልጁ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ነገር በዓይነ ህሊናው እንዲያይ ይረዱታል። ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ እና እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተሰኙት መጻሕፍት አሉ። በእነዚህ መጻሕፍት አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትንንሽ ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በአእምሯቸውና በልባቸው ላይ ሊቀረጽ ችሏል።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው።” (መዝሙር 127:3) ፈጣሪህ የክብርና የደስታ ምንጭ ሊሆን የሚችል “ስጦታ፣” ማለትም ደስ የሚል ልጅ በአደራ ሰጥቶሃል። ልጆችን ማሳደግ፣ በተለይ ደግሞ ሲያድጉ ፈጣሪያቸውን የሚያወድሱ እንዲሆኑ መርዳት በእርግጥ አርኪ ሥራ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በውጥረት ጊዜ የሚረጩ ሆርሞኖች ብቻ ሳይሆኑ ኒኮቲን፣ አልኮልና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችም በሽሉ ላይ ጎጂ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል። ነፍሰ ጡር እናቶች ማንኛውንም አደገኛ ንጥረ ነገር ከመውሰድ ቢቆጠቡ ጥሩ ነው። በተጨማሪም መድኃኒቶች በሽሉ ላይ ስለሚያስከትሉት ውጤት ሐኪም ማማከር አስፈላጊ ነው።
b አንዲት እናት ከልክ ያለፈ ኀዘንና ተስፋ መቁረጥ እንዲሁም ከልጅዋና ከተቀረው ዓለም የመገለል ስሜት የሚሰማት ከሆነ የእመጫትነት የመንፈስ ጭንቀት እያሰቃያት ሊሆን ይችላል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ያዋለዳትን ሐኪም ማማከር አለባት። የሐምሌ 22, 2002 ንቁ! ገጽ 19-23ን እና የሰኔ 8, 2003 ንቁ! ገጽ 21-3ን (እንግሊዝኛ) ተመልከት።
c በመጋቢት 22, 1999 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ላይ የወጣውን “አያት መሆን የሚያስገኘው ደስታና ፈታኝ ሁኔታ” የሚለውን ርዕስ አንብብ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እናት ገና ላልተወለደው ልጅዋ ያላት ስሜት በጣም ወሳኝ ነው
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት እናት ልጅ ከወለደች በኋላ የስሜት መለዋወጥ ቢያጋጥማትም እንኳ ልጅዋ እንደሚወደድና ደኅንነት እንዲሰማው ለማስቻል ብዙ ነገር ማድረግ ትችላለች
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቶች ሕፃኑን የመንከባከቡን ኃላፊነት መጋራት አለባቸው
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለልጅ ማንበብ መጀመር የሚኖርበት ከሕፃንነቱ አንስቶ ነው