በለጋ ዕድሜ ማርገዝ የሚያስከትለውን ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም
በለጋ ዕድሜ ማርገዝ ትላልቅ ሰዎች ብቻ ሊጋፈጧቸው ከሚገቡ ውሳኔዎች ጋር ፊት ለፊት ያፋጥጣል። ልጅነቷን ሳትጨርስ የልጅ እናት የሆነች አንዲት ወጣት “40 ዓመት የሆነኝ ሆኖ ይሰማኛል። የልጅነት ሕይወቴ አመለጠኝ” ብላለች። በእርግጥም አንዲት ወጣት ሴት ማርገዟን እንዳወቀች ወዲያው በፍርሐትና በጭንቀት መዋጥዋ አይቀርም።
አንቺም ገና በልጅነትሽ ያረገዝሽ ከሆንሽ እንዲሁ ሊሰማሽ ይችላል። ይሁን እንጂ አፍራሽ በሆኑ ስሜቶች ተሽመድምዶ መቀመጥ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚያይ አያጭድም” ይላል። (መክብብ 7:8፤ 11:4) ስለ አየሩ ሁኔታ በመጨነቅ እጁን አጣጥፎ የተቀመጠ ገበሬ አስፈላጊ እርምጃዎችን ሊወስድ አይችልም። አንቺም እጅሽን አጣጥፈሽ አትቀመጪ። ይዋል ይደር እንጂ ኑሮሽን መቋቋምና ኃላፊነትሽን መሸከም ይኖርብሻል።—ገላትያ 6:5
ታዲያ ምን አማራጮች ይኖሩሻል? አንዳንዶች አስወርጂው ይሉሽ ይሆናል። ይህ ግን ዳግመኛ አምላክን ወደሚያስደስት ኑሮ ለመመለስ የሚፈልጉ ሰዎች የሚያስቡት አማራጭ አይደለም። ማስወረድ የአምላክን ሕግ እንደሚጻረር መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያመለክታል። (ዘፀአት 20:13፤ 21:22, 23፤ መዝሙር 139:14-16) በአምላክ ዓይን የማንኛውም ጽንስ፣ ከጋብቻ ውጭ የተፈጠረ ጽንስ ሕይወት ጭምር ክቡር ነው።
የልጁን አባት ማግባትና ሕፃኑን አብሮ ማሳደግስ? የልጁን አባት ማግባትሽ ሌላው ቢቀር እንኳ ከእፍረት ሊያድንሽ እንደሚችል ይሰማሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንድ ወጣት አባት ልጁን የማሳደግ ኃላፊነት እንዳለበት ቢሰማው እንኳን መጋባቱ ሁልጊዜ ጥሩ ምርጫ ይሆናል ማለት አይደለም።a አንድ ወጣት ልጅ መውለድ ስለቻለ ብቻ ጥሩ ባልና አባት ለመሆን የሚያስችል የስሜትና የአእምሮ ብስለትም ሆነ ሚስቱንና ልጁን ለማኖር የሚያስችል የገንዘብ አቅም ይኖረዋል ማለት አይደለም። ከዚህም በላይ ይህ ወጣት ሃይማኖታዊ እምነትሽን የማይጋራ ከሆነ እንዲህ ካለው ሰው ጋር መጋባት ‘በጌታ ብቻ አግቡ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ያስጥስሻል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) በለጋ ዕድሜ፣ ምናልባትም በአጭሩ ተቀጭቶ ሊቀር የሚችል ትዳር መመሥረት ተጨማሪ ሥቃይና መከራ ከማስከተል ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው በተሞክሮ የታየ ነገር ነው።
ሕፃኑን ለጉዲፈቻ መስጠትስ? ከማስወረድ የተሻለ አማራጭ መሆኑ የማያከራክር ቢሆንም የምትገኚበት ሁኔታ የማያመች ቢሆንም ልጅሽን ተንከባክበሽ የማሳደግ አጋጣሚ እንዳለሽ ማሰብ ይኖርብሻል።
ችግሩን መጋፈጥ
ያለ አባት እርዳታ ለብቻ ልጅ ማሳደግ ቀላል ነገር እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በተቻለሽ መጠን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በመከተልና አምላክ በሚሰጥሽ መመሪያና ብርታት በመታመን ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቋቋም ትችያለሽ። የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድሽ ችግሩን ለመቋቋም ይረዳሻል።
● ከአምላክ ጋር የነበረሽን ዝምድና አስተካክዪ። ከጋብቻ ውጭ የጾታ ግንኙነት መፈጸም በአምላክ ላይ የሚፈጸም ከባድ ኃጢአት እንደሆነ ማለትም ከፍተኛ ከሆኑት የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር የሚጻረር ድርጊት እንደሆነ ተገንዘቢ። (ገላትያ 5:19-21፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3, 4) ስለዚህ የመጀመሪያውና ዋነኛው እርምጃ ንስሐ መግባትና አምላክን ይቅርታ መጠየቅ ነው። (መዝሙር 32:5፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) እርግጥ፣ የአምላክን እርዳታ ማግኘት የሚገባኝ ሰው አይደለሁም ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ይቅር እንደሚልና ከበደላቸው ንስሐ የሚገቡትን እንደሚረዳ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 55:6, 7) ይሖዋ በኢሳይያስ 1:18 ላይ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል” ብሏል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በደለኞች የተሾሙ የጉባኤ ሽማግሌዎች በሚሰጡት መንፈሳዊ እርዳታ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ያበረታታል።—ያዕቆብ 5:14, 15
● ከጋብቻ ውጭ የጾታ ግንኙነት መፈጸም አቁሚ። ይህም ከልጅሽ አባት ጋር የነበረሽን ግንኙነት ፈጽሞ ማቋረጥ ሊጠይቅብሽ ይችላል። የነበረሽን ከጋብቻ ውጭ የሆነ ግንኙነት መቀጠል አምላክን የሚያስቀይም ድርጊት እንድትፈጽሚ የሚገፋፋሽን ተጽዕኖ ከማጠናከር ውጭ የሚፈይድልሽ ነገር አይኖርም። የአምላክ ሕግ ጥብቅ ቢሆንም እኛኑ ከመጥፎ ነገር ለመጠበቅ ሲባል የተሰጠ መሆኑን ፈጽሞ አትርሺ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኒኮል “አምላክ ትክክል መሆኑን ተገነዘብኩ። እኛን ለመጥቀም ይፈልጋል” ብላለች።—ኢሳይያስ 48:17, 18
● ለወላጆችሽ ንገሪ። ወላጆቼ ይቆጡኛል ብለሽ ትፈሪ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እርጉዝ መሆንሽን ሲያውቁ በጣም መበሳጨታቸውና መጨነቃቸው አይቀርም። እንዲያውም ጥፋቱ የእነርሱ እንደሆነና ለመጥፎ ድርጊትሽ ምክንያት የሆኑት እነርሱ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ወላጆችሽ በእውነት አምላክን የሚፈሩ ከሆነ የተሰማቸው የሐዘንና የምሬት ማዕበል ከጊዜ በኋላ ጋብ ማለቱ አይቀርም። ወላጅ ስለሆኑ ስህተት ብትሠሪም ይወዱሻል። የመጸጸት ዝንባሌ እንዳለሽ ሲመለከቱ የአባካኙን ልጅ አባት ለመምሰል እንደሚገፋፉና ይቅር እንደሚሉሽ ምንም ጥርጥር የለውም።—ሉቃስ 15:11-32
● አመስጋኝ መሆንሽን አሳዪ። ብዙ ጊዜ ወላጆች፣ ዘመዶችና ወዳጆች ብዙ እርዳታና ድጋፍ ይሰጣሉ። ለምሳሌ ወላጆችሽ የሕክምና ክትትል የምታገኚበትን መንገድ ሊያዘጋጁልሽ ይችላሉ። ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ የልጅ አያያዝ ዘዴዎችን ሊያስተምሩሽና ሊይዙልሽም ይችላሉ። ኒኮል “ልጁ የእኔ ቢሆንም በጣም ብዙ ረድታኛለች” በማለት ስለ እናቷ ትናገራለች። ወዳጆችሽ የልጅ ልብሶችና ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች ነገሮችን በዘዴ በመስጠት ተመሳሳይ ድጋፍ ይሰጡሽ ይሆናል። (ምሳሌ 17:17) የደግነት ድርጊት ሲደረግልሽ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል ‘አመስጋኝ መሆንሽን አሳዪ።’ (ቆላስይስ 3:15) አመስጋኝነትሽንና አድናቆትሽን ከገለጥሽላቸው መልካም ሥራቸው ከውለታ እንዳልተቆጠረላቸው አይሰማቸውም።
● የልጅ አያያዝ ዘዴ ተማሪ። ዝንተ ዓለም የቤተሰቦችሽና የወዳጆችሽ ሸክም ሆነሽ መኖር እንደማትፈልጊ የታወቀ ነው። ስለዚህ መጠነኛ የሆነ የልጅና የቤት አያያዝ ችሎታ ማዳበር መጀመር ይኖርብሻል። ሙሉ በሙሉ የሌላ ሰው እርዳታ ለሚያስፈልገው ሕፃን እንክብካቤ ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም። ስለ ሥነ ምግብ ስለ ጤናና ስለሌሎች የሕፃን አስተዳደግ ዘርፎች ብዙ መማር የሚኖርብሽ ነገሮች ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በዕድሜ የበሰሉ ክርስቲያን ሴቶች ወጣት ሴቶችን ‘በቤት የሚሠሩ እንዲሆኑ’ መምከር እንዳለባቸው መናገሩ ተገቢ ነው። (ቲቶ 2:5) በዚህ ረገድ እናትሽ፣ እንዲሁም ሌሎች በዕድሜ በሰል ያሉ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ጥሩ ሥልጠና ሊሰጡሽ እንደሚችሉ አያጠራጥርም።
● በገንዘብ አያያዝ ረገድ ጥበበኛ ሁኚ። መጽሐፍ ቅዱስ “ገንዘብ ለጥበቃ ይሆናል” ይላል። (መክብብ 7:12 NW) የልጅ መወለድ ቀላል ያልሆነ ወጪ ያስከትላል።
በመጀመሪያ ማግኘት የምትችይው መንግሥታዊ እርዳታ ይኖር እንደሆነ ማጣራት ይኖርብሻል። ቢሆንም ልጅነቷን ሳትጨርስ እናት የሆነች ሴት የወላጆቿን የገንዘብ ድጋፍ መፈለጓ አይቀርም። እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥምሽ ከሆነ በተቻለ መጠን ወጪያቸው እንዳይበዛ ብትጥሪ ጥበብም አዛኝነትም ይሆናል። ልጅሽ አዳዲስ ነገሮች እንዲኖሩት ፍላጎትሽ ቢሆንም የተለበሱ ጨርቆችንና ያገለገሉ ዕቃዎችን በመግዛት ገንዘብ ልትቆጥቢ ትችያለሽ።
● አንድ ዓይነት ሥልጠና ለማግኘት ሞክሪ። ምሳሌ 10:14 “ጠቢባን ዕውቀት ያከማቻሉ” ይላል። ይህ በተለይ የሚሠራው ለመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ቢሆንም በሥጋዊ ትምህርት ረገድም ይሠራል። ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችልሽን ክህሎት ማግኘት ያስፈልግሻል።
ልጅ እያሳደጉ ትምህርት መማር አስቸጋሪ እንደሚሆን አይካድም። ይሁን እንጂ መሠረታዊ ትምህርት አለማግኘትሽ አንቺንም ሆነ ልጅሽን መውጫ ለሌለው የተመጽዋችነት፣ የድህነትና የረሐብተኝነት ኑሮ ይዳርጋችኋል። ስለዚህ የሚቻል ከሆነ ትምህርትሽን አታቋርጪ። የኒኮል እናት ልጅዋ ትምህርት እንድትጨርስ አጥብቃ መከረቻት። ይህን በማድረጓም የሕግ ባለሞያ ረዳት ሆና ለመሥራት ያስቻላትን ሥልጠና ማግኘት ቻለች።
ምን ዓይነት የሥልጠና ዕድል ማግኘት እንደምትችይ ለምን አታጣሪም? ትምህርት ቤት ሄዶ መማር የሚያስቸግርሽ ከሆነ እቤትሽ ሆነሽ ትምህርቱን መከታተል ትችይ እንደሆነ አጣሪ። ለምሳሌ በተልእኮ መከታተል ይቀልሽ ይሆናል።
ሊሳካልሽ ይችላል
ከጋብቻ ውጭ የተወለደ ልጅ ማሳደግ በዕድሜ ላልበሰለች ልጅ ቀላል አይሆንም። ቢሆንም ሊሳካልሽ ይችላል! ትዕግሥተኛና ቆራጥ ከሆንሽ በይሖዋ አምላክ እርዳታ አፍቃሪና ጎበዝ ወላጅ መሆን ትችያለሽ። በተጨማሪም ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆች አድገው ጨዋና ጥሩ ሰዎች መሆን ይችላሉ። ልጅሽ የምትሰጭውን ሥልጠናና ትምህርት ተቀብሎ አምላክን የሚወድ ሰው ሲሆን ማየት የሚያስገኘውን ደስታ ልታጣጥሚ ትችያለሽ።—ኤፌሶን 6:4
ኒኮል እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “በአምላክ እርዳታ፣ ያጋጠሙኝን ችግሮች በሙሉ ተወጥቼ ሕፃን ልጄ አድጋ ደግ፣ ሰው አክባሪና ኃላፊነት የሚሰማት ወጣት ሴት ስትሆን የማየት ደስታ አግኝቻለሁ። ባየኋት ቁጥር እንቅልፍ ባይኔ ሳይዞር ያሳለፍኳቸው ሌሊቶች ትዝ ቢሉኝም ልቤ በደስታ ይሞላል።”
ይሁን እንጂ ትላልቅ ሰዎች ገና ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ እናት ለሆኑ ወጣት ሴቶችና ለልጆቻቸው እንዴት ያለ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ወጣቶች በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ማርገዝ ከሚያስከትለው ሥቃይና መከራ እንዲጠበቁ መርዳት የሚቻልበት መንገድ ይኖራል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከጋብቻ ውጭ ልጅ የሚወልዱ ወጣት አባቶች ስለሚደቀንባቸው ኃላፊነትና ተፈታታኝ ሁኔታ በሰኔ 2000 እና በሐምሌ 2000 ንቁ! እትሞች ላይ “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .” በሚለው ዓምድ ሥር በወጡት ርዕሶች ተገልጿል።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ ልጅ የሚወልዱ እናቶች ልጆቻቸውን በማሳደግ ረገድ በርካታ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተጣድፎ አለዕድሜ ማግባት መፍትሔ አይሆንም
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከመንገድ የሳቱ ወጣቶች ከአምላክ ጋር የነበራቸውን ዝምድና እንዲያስተካክሉ ሊረዷቸው ይችላሉ
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነጠላ እናቶች መሠረታዊ ትምህርታቸውን ቢጨርሱ ጥሩ ይሆናል