የወጣቶች ጥያቄ . . .
እንደማፈቅረው እንዴት ብዬ ልገልጽለት እችላለሁ?
“ፍቅር እንደያዘው አስቀድሞ መግለጽ ያለበት ማን ነው? ወንዱ ነው ሴቷ? ለዚህ ጥያቄ መልስ ባገኝ ደስ ይለኛል።”—ላውራa
በቅርቡ የተዋወቅሽው ወይም ደግሞ በሆነ ምክንያት ቀደም ሲል የምታውቂው ሰው አለ፤ ትውውቃችሁ ወደ ፍቅራዊ ግንኙነት እንዲያድግ ፈለግሽ እንበል። እርሱም ልክ የአንቺ ዓይነት ስሜት እንደሚሰማው፣ ነገር ግን ድፍረት ስላጣ ወይም ዓይናፋር ስለሆነ ብቻ ሊነግርሽ እንዳልቻለ እርግጠኛ ነሽ። ስለዚህ ቀዳሚ ሆነሽ ስሜትሽን ገልጸሽ ማስረዳቱ የተሻለ መስሎ ታይቶሻል።b
እስቲ በመጀመሪያ በአካባቢሽ ያሉ ሰዎች ማለትም ቤተሰቦችሽና ኅብረተሰቡ ስለ ጉዳዩ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል እንነጋገር። ለምሳሌ ያህል በአካባቢሽ ባሕል ለልጆቻቸው የትዳር ጓደኛ የሚመርጡት ወላጆች ናቸው?c መጠናናትና ጋብቻ የግል ጉዳዮች ናቸው የሚል አመለካከት ሊኖርሽ እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች በተቻለ መጠን ለሌሎች አላስፈላጊ እንቅፋት እንዳይፈጥሩ ይጠነቀቃሉ። እንዲሁም የቤተሰብ አባሎቻቸውና የሌሎች የሚወዷቸው ሰዎች ስሜት እንዳይጎዳ ያስባሉ።
በዛሬው ጊዜ በበርካታ አገሮች ወንድና ሴት በራሳቸው ምርጫ ለመጋባት መጠናናታቸው የተለመደ ነገር ሆኗል። አንዲት ሴት አንድን ወንድ እንደወደደችው ብትነግረው ስህተት ነው? በዚህ ጊዜም ቢሆን ቤተሰብና የአካባቢው ኅብረተሰብ ምን ሊሰማው እንደሚችል ሊታሰብበት ይገባል። ይህ ጉዳይ ሌሎችን ያስደነግጥና ያደናቅፍ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ሴት ሥርዓት ባለው መንገድ ቅድሚያውን ወስዳ ፍቅሯን መግለጽ ስለመቻሏ በተነሳው ጥያቄ ላይ ምን ተጨማሪ ምክር ይሰጣል? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ፈሪሃ አምላክ የነበራት ሩት የተባለች ሴት ቦዔዝ የተባለን ሰው ስለ ትዳር ጠይቃው ነበር። ይሖዋ አምላክም ጥረቷን ባርኮላታል! (ሩት 3:1-13) መበለት የነበረችው ሩት ማግባት በምትችልበት ዕድሜ ላይ እንጂ በጉርምስና ዕድሜ የምትገኝ ሴት አልነበረችም። እንዲሁም ከቦዔዝ ጋር የነበራት ቀረቤታ እንዲሁ ተራ የፍቅር ግንኙነት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ጋብቻን በተመለከተ ያወጣውን ሕግ በሚገባ ተግባራዊ አድርጋለች።—ዘዳግም 25:5-10
አንቺም ምናልባት ጋብቻ መመሥረት በምትችይበት ዕድሜ ላይ ትገኚ ይሆናል፤ እንዲሁም አንድ የማረከሽ ወጣት ሊኖር ይችላል። ሆኖም ለአንቺ ያለው ስሜት እንደጠበቅሽው ካልሆነ ስሜትሽን አውጥተሽ መግለጽሽ ከባድ የልብ ስብራት ሊያስከትልብሽ ይችላል። ሁኔታውን ቃል በቃል ልብሽን አውጥተሽ ለሌላ ሰው ከመስጠት ጋር ልታመሳስይው ትችያለሽ። በደንብ ተጠንቅቆ ይይዘዋል ወይስ መሬት ላይ ይጥለዋል? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተልሽ አላስፈላጊ እፍረት እንዳትከናነቢ ወይም የስሜት መጎዳት እንዳይደርስብሽ ይረዳሻል።
አስተዋይ ሁኚ
ከአንድ ሰው ጋር ፍቅራዊ ግንኙነት ስለመጀመር ማለም ቀላል ነው። እንዲያውም ሠርግሽና ከዚያ በኋላ ያለው ጊዜ በዓይነ ኅሊናሽ ይታይሽ ይሆናል። እንደዚህ ያሉት ሐሳቦች የሚያስደስቱ ቢመስሉም ከቀን ቅዠትነት አልፈው አይሄዱም። እንዲያውም ልታገኚያቸው የማትችያቸውን ምኞቶች ሊዘሩብሽ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል።” (ምሳሌ 13:12) ከዚህም በተጨማሪ የቀን ቅዠቶች የማስተዋል ችሎታሽን ሊያዛቡብሽ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 14:15 ላይ “አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። አስተዋይ መሆን ማለት በተፈጥሮ እውቀትና በማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ማለት ነው። ፍቅር በሚይዝሽ ጊዜ አስተዋይ መሆን የምትችይው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ ያሰብሽውን ነገር ‘በዕውቀት ለማከናወን’ ሞክሪ። (ምሳሌ 13:16) አንዲት ወጣት ሴት እንደተናገረችው “አንድን ሰው በደንብ እስከምታውቂው ድረስ የእውነት ልትወጂው አትችይም።” ስለዚህ ለአንድ ሰው ልብሽን ከመስጠትሽ በፊት የሚያደርገውንና የሚናገረውን ነገር በጥሞና ተከታተይ። ሌሎችን እንዴት እንደሚይዝ ተመልከቺ። “ጓደኞቹንና ጥሩ አድርገው የሚያውቁትን ትልልቅ ሰዎች ስለ እርሱ ጠይቂ” በማለት አንድ ወጣት መክሯል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉትስ ስለ እርሱ “መልካም ምስክርነት” ይሰጣሉ? (የሐዋርያት ሥራ 16:2) እንዲሁም “በቡድን ሆኖ አብሮ መዝናናትና ቤተሰቦቹን ማወቅ ይጠቅማል” በማለት ኢሳቤል የተባለች ወጣት ትመክራለች። በቡድን ወጣ ብሎ መጫወት ብዙም ሳትጨነቂ እንድትመለከቺው ያስችልሻል።
አንድን ሰው በዚህ መልኩ ማወቅ ጊዜና ትዕግሥት ቢጠይቅም እንኳን አስተሳሰቡን፣ ባሕርዩንና ጠባዩን ለማወቅ ስለሚያስችልሽ ለእርሱ ያለሽ ስሜት እንዲጠናከር አሊያም ሐሳብሽን እንድትቀይሪ ያደርግሻል። ምሳሌ 20:11 “ሕፃን [ወይም ወጣት] እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል” ይላል። አዎን፣ ውሎ አድሮ ድርጊቱ ትክክለኛ ማንነቱን ይገልጻል።
ስለዚህ ተቻኩለሽ እንደምትወጂው ከመንገር መቆጠብሽ ጠቃሚ ነው። እንደምትወጂው ተጣድፈሽ ነግረሽው ጥሩ ምላሽ ከሰጠሽ በኋላ ለትዳር የሚሆን ሰው እንዳልሆነ ቀስ በቀስ ልትገነዘቢ ትችያለሽ።d ስሜትሽን ከገለጽሽለት በኋላ ለመለያየት ብትፈልጊ ደግሞ በጣም ሊጎዳ ይችላል።
በእሱ ላይ ልታሳድሪ የምትችይው ስሜት
ይህ ወጣት በበኩሉ አንቺን እያጠናሽ ሊሆን ይችላል! አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ታንጸባርቂያለሽ? ኢሳቤል “በርካታ ልጃገረዶች ጥሩ አለባበስ እንደሌላቸው አስተውያለሁ፤ መንፈሳዊ የሆነን ሰው ትኩረት መሳብ ከፈለጋችሁ ጥሩ አለባበስ ሊኖራችሁ ይገባል” በማለት ትመክራለች። ዓለም ምንም ዓይነት የአለባበስ ፋሽን ቢያቀርብ ‘በጨዋነትና ራስን በመግዛት ተገቢ በሆነ ልብስ’ ራስሽን ማስዋብሽ መንፈሳዊ በሆነ ሰው ፊት ይበልጥ ማራኪ ሆነሽ እንድትታዪ ያደርግሻል።—1 ጢሞቴዎስ 2:9
ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ወጣት ክርስቲያኖች “በንግግር . . . አርኣያ” እንዲሆኑ ያበረታታቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:12) የምትናገሪበት መንገድ ስለ አንቺ ብዙ የሚገልጸው ነገር አለ። ከእርሱ ጋር የምትነጋገሪበት አጋጣሚ በሚፈጠርበት ጊዜ ምን ማድረግ አለብሽ? ዓይናፋር ከሆነ ሊሸበርና ሊደናገጥ ይችላል። አቢ የተባለች ወጣት “ስሜቱን ለማወቅ ጨዋታውን አንቺ መጀመር ሊኖርብሽ ይችላል” ብላለች።
ጨዋታ መጀመር የምትችይው እንዴት ነው? ስለ ራስሽ ያለማቋረጥ የምታወሪ ከሆነ ራስ ወዳድና ጥራዝ ነጠቅ እንደሆንሽ አድርጎ ሊያስብ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” በማለት ይመክረናል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ስለ ራሱም ሆነ ስለ ፍላጎቱና ስለ ስሜቱ ተገቢ የሆኑ ጥቂት ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ የውስጡን አውጥቶ በነፃነትና በሐቀኝነት እንዲናገር ማድረግ ትችያለሽ።
በዚህ ጊዜ ‘በሐሰተኛ ከንፈር’ ወይም ‘በአታላይ ምላስ’ መሸንገል ተገቢ አይደለም። (መዝሙር 120:2) አስተዋይ የሆነ ሰው እንዲህ ያሉት ንግግሮች ከልብ የመነጩ እንዳልሆኑ መረዳት አይሳነውም። በተጨማሪም አንድን ነገር ሊያስደስተው ይችላል በሚል ስሜት ብቻ ተገፋፍተሽ ከማውራት ተቆጠቢ። በተለይ የግል መንፈሳዊ ግቦቻችሁን የመሳሰሉ ከባድ ጉዳዮች አንስታችሁ ስትነጋገሩ መጠንቀቅ ይኖርብሻል። ሁልጊዜ ራስሽን ሆነሽ በሐቀኝነት፣ በእውነትና ከልብ በመነጨ ስሜት ተናገሪ። አንድ ዓይነት ግብ እንዳላችሁ ማወቅ የምትችይው በዚህ መንገድ ብቻ ነው።
ምላሽ ባይሰጥሽስ?
ይህን የመሰለ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥረት አድርገሽ ምንም ዓይነት የፍቅር ስሜት ባያሳይሽስ? በርካታ ሳምንታት ምናልባትም ወራት ቢያልፉም ምንም ፍላጎት አላሳየም እንበል። ዓይናፋር ስለሆነ ነው ብለሽ መደምደም ይገባሻል? እንዲህ እያልሽ ራስሽን ጠይቂ:- ‘ይህን ያህል ዓይናፋር ከሆነ ትዳር ለመመሥረት ይችላል? ባገባው እንኳን ቤተሰብ የመምራቱን ኃላፊነት ይወጣል ወይስ ለእኔ ይተወዋል?’ (1 ቆሮንቶስ 11:3) ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጥያቄ ‘በእርግጥ ዓይናፋር ነው ወይስ ከእኔ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲኖረው አይፈልግም?’ የሚለው ነው። እንዲህ ብሎ መደምደሙ ሊከብድ ይችላል። ሆኖም ይህን ሐቅ መቀበልሽ የፍቅር ስሜትሽን፣ ለአንቺ ጨርሶ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት ለሌለው ሰው ነግሮ ከማፈር ያድንሻል።
ሆኖም የፍቅር ግንኙነት የመመሥረት ፍላጎት እንዳለው የሚጠቁም ምልክት ያየሽ ሊመስልሽ ይችላል። ይህን ስሜቱን ለመግለጽ በጣም ዘገየ እንጂ ትንሽ መንደርደሪያ ካገኘ ይናገራል ብለሽ ታስቢ ይሆናል። ነገሩ ምናልባት እውነት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እንደምትወጂው አንቺ ቀድመሽ ለመንገር ከወሰንሽ ይህን ማድረግሽ ጉዳት ሊኖረውም እንደሚችል ማሰብ አለብሽ። ምን መናገር እንዳለብሽ ብቻ ሳይሆን መቼ መናገር እንዳለብሽም ጭምር በጣም ልታስቢበት ያስፈልጋል።
ምናልባት ተጣድፈሽ “እንደምትወጂው” ከመግለጽ ይልቅ ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚያስደስትሽ ብትጠቁሚው የተሻለ ሊሆን ይችላል። ዘና ብለሽ ጨዋነት በተሞላ ሁኔታ ይበልጥ መተዋወቅና መቀራረብ እንደምትፈልጊ ልትነግሪው ትችያለች። ሐሳብሽን የገለጽሽበት መንገድ ቅልጥፍና የጎደለው ቢሆን ምንም አትጨነቂ። እንድትናገሪ ያነሳሳሽ ከልብ የመነጨ ስሜት ከምትጠቀሚባቸው ቃላት የበለጠ ይናገራል። በተጨማሪም ጥናታዊ ቅርርብ እንድታደርጉ ጠየቅሽው እንጂ እንጋባ እንዳላልሽው አስታውሺ። ሆኖም ያላሰበው ነገር ሊሆንበት ስለሚችል በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት በቂ ጊዜ ስጪው።
ማንነቱን በደንብ አድርገሽ ካወቅሽ እንዲሁም ደግና አሳቢ እንደሆነ ከተሰማሽ፣ ስሜት የሚጎዳ ወይም እንዳፍር የሚያደርግ ምላሽ ይሰጠኛል ብለሽ አትፍሪ። ነገር ግን የፍቅር ግንኙነት መመሥረት እንደማይፈልግ በደግነት ቢገልጽልሽ ምን ማድረግ ይኖርብሻል? በተጨማሪም አንድ ወጣት ይህን የመሰለ ሁኔታ ቢያጋጥመው ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ይገባዋል? ወደፊት የሚወጣው እትም እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
b ይህ ርዕስ ወጣት ሴቶችን የሚመለከት ቢሆንም ጥናታዊ ቅርርብ ለመጀመር ላሰቡ ወጣት ወንዶችም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ጠቃሚ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን ይዟል።
c በቤተሰብ ምርጫ የተከናወነ ጋብቻ ሁሉ ደስታ ያሳጣል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይስሐቅና ርብቃ በቤተሰብ ምርጫ የተጋቡ ቢሆንም ይስሐቅ ሚስቱን ‘ወዷታል።’ (ዘፍጥረት 24:67) ከዚህ ምን እንማራለን? የአንድ አገር ባሕሎች የአምላክን ሕግ እስካላስጣሱን ድረስ መጥፎ ናቸው ብለን ለመደምደም መቻኮል የለብንም።—የሐዋርያት ሥራ 5:29
d በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች በተባለው መጽሐፍ ላይ ከምዕራፍ 28 እስከ 31 ውስጥ ያለው ሐሳብ፣ አንድ ሰው ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ሊሆን ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን ጉዳይ ለመወሰን ይረዳሻል።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሕርዩን ማወቅሽ ስለ እርሱ ያለሽን ስሜት ሊቀይረው ይችላል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያፈቀርሽው ሰው ካለ ግለሰቡን የሚያውቁትን እምነት የሚጣልባቸው ትልልቅ ሰዎች አነጋግሪ