የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g05 7/8 ገጽ 12-14
  • ሜይ ዴይ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሜይ ዴይ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
  • ንቁ!—2005
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የበዓሉ ጥንታዊ አመጣጥ
  • የሜይ ዴይ አከባበር
  • በዓሉ እውቅና ያገኘባቸው የተለያዩ መንገዶች
  • ሜይ ዴይ የላብ አደሮች ቀን ሆነ
  • የጥንቱንና የዘመናችንን አከባበር የሚያመሳስሏቸው ነገሮች
  • የለውጥ ፍላጎትን ማሟላት
  • በዓላትን ማክበር
    ትምህርት ቤትና የይሖዋ ምሥክሮች
  • የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ በዓላትን የማያከብሩት ለምንድን ነው?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
  • በዓላት
    ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር
  • ክርስትያኖች በዘመን መለወጫ በዓል መካፈል ይኖርባቸዋልን?
    ንቁ!—2002
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—2005
g05 7/8 ገጽ 12-14

ሜይ ዴይ ለአንተ ምን ትርጉም አለው?

በብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሜይ ዴይ ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? ሰላማዊ ሰልፍና ትዕይንተ ሕዝብ? በረጅም ምሰሶ ዙሪያ የሚደረገው ባሕላዊ ጭፈራ? ወይስ የእረፍት ቀን መሆኑ?

ስለ ሜይ ዴይ የሚኖርህ አመለካከት እንደምትኖርበት አገር ይለያያል። ቢሆንም ሁሉንም ዓይነት አከባበሮች አንድ የሚያደርጓቸው ነገሮች አሉ። ስለ ሜይ ዴይ አመጣጥ አጠር ያለ ምርምር ማድረጋችን በዛሬው ጊዜ ስለሚከበረው በዓል ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል።

የበዓሉ ጥንታዊ አመጣጥ

በጥንቷ ሮም ግንቦት አንድ የሚውለው የጸደይና የአበቦች እንስት አምላክ በነበረችው በፍሎራ የተሰየመው የፍሎራሊያ በዓል በሚከበርባቸው ቀናት ውስጥ ነበር። በዓሉ የዘፈንና የጭፈራ ወቅት ሲሆን በአበቦች ያሸበረቀ ሰልፍም ይካሄዳል። በተለይ የሮም ዝሙት አዳሪዎች፣ ፍሎራ የእነርሱ ልዩ ጠባቂ እንደሆነች አድርገው ስለሚመለከቷት በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩት ነበር።

ሮማውያን ድል አድርገው በያዟቸው አገሮች ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውን ያስፋፉ ነበር። ሆኖም የኬልቲክ አገሮች ቤልታን የሚባለውን በዓል የሚያከብሩት ግንቦት አንድ ላይ እንደሆነ ተገነዘቡ። በእነዚህ አገሮች አዲስ ቀን የሚጀምረው አመሻሹ ላይ ሲሆን በግንቦት አንድ ዋዜማ ምሽት ላይ እሳት ሁሉ እንዲጠፋ ይደረጋል። ከዚያም ማለዳ ፀሐይ ስትወጣ ሰዎች ሕይወት እንደ አዲስ የሚጀምርበትን የበጋውን ወቅት ለመቀበል በኮረብቶች አናት ላይ ወይም እንደ አድባር በሚታዩ ዛፎች ሥር ደመራ ያበራሉ። ከብቶች ለግጦሽ እንዲሰማሩ ይደረጋል፤ እነርሱንም እንዲጠብቋቸው ለአማልክት ልመና ይቀርባል። ብዙም ሳይቆይ የፍሎራሊያ እና የቤልታን በዓላት ተጣመሩና የሜይ ዴይ ክብረ በዓል ተፈጠረ።

ጀርመንኛ ተናጋሪና የስካንዲኔቪያን አገሮች ሕዝቦች ደግሞ ቫልፐርጂስ የሚባል ከቤልታን ጋር የሚመሳሰል በዓል ያከብሩ ነበር። ቫልፐርጂስ መከበር የሚጀምረው ምሽት ላይ ችቦ በማብራት ሲሆን እንዲህ የሚደረገው ጠንቋዮችና ክፉ መናፍስት ከአካባቢው ይሸሻሉ በሚል እምነት ነው። ሌሎች አውሮፓውያን ሜይ ዴይን የሚያከብሩበት የራሳቸው ልማድ የነበራቸው ሲሆን ከእነዚህ ልማዶች መካከል ብዙዎቹ አሁን ድረስ ይዘወተራሉ።

አብያተ ክርስቲያናት ይህ አረማዊ በዓል እንዳይከበር ለማድረግ ያሳደሩት ተጽዕኖ በጣም ዝቅተኛ ነው። ጋርዲያን በተባለው የእንግሊዝ ጋዜጣ ላይ የሚከተለው አስተያየት ሰፍሯል:- “ሜይ ዴይ ወይም ቤልታን ከቤተ ክርስቲያንም ሆነ ከሌሎች ባለ ሥልጣናት ቁጥጥር ውጭ የሆነ ከዓመቱ ቀናት ውስጥ ሰዎች እንደፈለጋቸው የሚሆኑበት በዓል ነበር።”

የሜይ ዴይ አከባበር

በመካከለኛው መቶ ዘመን ሜይ ዴይ በእንግሊዝ አዳዲስ ልማዶች ተጨማምረውበት ተወዳጅ ዐውደ ዓመት ሆኗል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ጠዋት ፀሐይ ስትወጣ ‘ግንቦትን ለመቀበል’ ዋዜማው ምሽት ላይ አቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጫካ ሄደው አበቦችንና ለምለም ቅርንጫፎችን በመሰብሰብ ሌሊቱን እዚያው ያሳልፋሉ።a አጥባቂ ሃይማኖተኛ የነበረው ፊሊፕ ስተብዝ ዚ አናቶሚ ኦቭ አቢዩዝስ በተባለው ትራክቱ ላይ በጊዜው የሥነ ምግባር ብልግና በጣም ተስፋፍቶ እንደነበር ገልጿል። ፈንጠዝያ በሞላበት በዚህ በዓል ላይ የሚሳተፉ ሰዎች በመንደሩ መሃል ረጅም ምሰሶ ይተክሉና ቀኑን ሙሉ በዚያ ዙሪያ ሲጨፍሩና ሲጫወቱ ይውላሉ። ስተብዝ ይህን ምሰሶ “አስጸያፊ ጣዖት” በማለት ጠርቶታል። ሰዎቹ በዓሉን የሚያስተባብሩ የግንቦት ንግሥት ብዙውን ጊዜ ደግሞ የግንቦት ንጉሥ ይመርጣሉ። በሌሎች የአውሮፓ አገራት ግን በጣም የተለመደው ምሰሶ መትከልና የግንቦት ንግሥት መምረጥ ነው።

ከእነዚህ የሜይ ዴይ ባሕላዊ ልማዶች በስተ ጀርባ ያለው መልእክት ምንድን ነው? ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ያብራራዋል:- “መጀመሪያ ላይ ይህ በዓል ይከበር የነበረው አዝመራው አልፎ ተርፎም ከብቱና ሰዉ ፍሬያማ እንዲሆኑ መልካም ምኞትን ለመግለጽ በሚል ዓላማ ነበር። ውሎ አድሮ ግን ይህ ዓላማ ተዘንግቶ በዓሉ እንዲያው ተወዳጅ ክብረ በዓል ብቻ ሆኖ ቀረ።”

በዓሉ እውቅና ያገኘባቸው የተለያዩ መንገዶች

የፕሮቴስታንት ለውጥ አራማጆች እንደ አረማዊ በዓል ይታይ የነበረው ሜይ ዴይ እንዳይከበር ለማድረግ ሞክረው ነበር። በ1555፣ የጆን ካልቪን ተከታይ በነበረችው በስኮትላንድ ሜይ ዴይ እንዳይከበር ታግዶ ነበር። በ1644 ደግሞ በአጥባቂ ሃይማኖተኞች ይመራ የነበረው የእንግሊዝ ፓርላማ በሜይ ዴይ ዕለት ምሰሶ እንዳይተከል እገዳ ጣለ። እንግሊዝ ያለ ንጉሥ ትተዳደር በነበረበት ዘመን በሜይ ዴይ ዕለት “የብልግና ተግባሮችን” መፈጸም ተከልክሎ ነበር። ይሁን እንጂ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ በ1660 ዳግም ሲያንሰራራ በሜይ ዴይ ዕለት ምሰሶ የመትከል ልማድ እንደገና ቀጠለ።

በረጅም ምሰሶ ዙሪያ የሚደረገው ሥርዓት በ18ኛው እንዲሁም በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ቀስ በቀስ ከስሞ ነበር፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በጋለ ስሜት መከበር ጀምሯል። የሜይ ዴይ ጥንታዊ ልማዶች እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩት በርካታ ድርጊቶች ለምሳሌ ያህል ልጆች በተለያዩ ሪባኖች ባጌጠ ረጅም ምሰሶ ዙሪያ የሚያደርጉት ጭፈራ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣ ባሕል ነው። ሆኖም የሜይ ዴይን ጥንታዊ መሠረት ያጠኑ ሰዎች በበዓሉ ዕለት የሚደረጉት ብዙዎቹ ነገሮች አረማዊ አመጣጥ እንዳላቸው ደርሰውበታል።

ከአውሮፓ የፈለሱ ሰዎች በሜይ ዴይ ዕለት የሚከበሩትን ሃይማኖታዊ ልማዶች ወደ ሌሎች ቦታዎች ይዘው የሄዱ ሲሆን ዝርያዎቻቸው በዓሉን አሁን ድረስ በባሕላዊ መንገድ ያከብሩታል። ሆኖም በበርካታ አገሮች ውስጥ ሜይ ዴይ ወይም የግንቦት ወር የመጀመሪያው ሰኞ የላብ አደሮች ቀን ተደርጎ ይከበራል።

ሜይ ዴይ የላብ አደሮች ቀን ሆነ

በዘመናችን በሜይ ዴይ ዕለት ሰላማዊ ሰልፎችና ትዕይንተ ሕዝቦች ማድረግ የተጀመረው ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ነበር። በዚያ የተጀመረው ለምንድን ነው? የኢንዱስትሪው አብዮት ያለማቋረጥ የሚሠሩ አዳዲስ ማሽኖችን በማስገኘቱ የፋብሪካ ባለቤቶች ሠራተኞቻቸው ከእሁድ በስተቀር በየቀኑ 16 ሰዓት እንዲሠሩ ይጠብቁባቸው ነበር። የዩናይትድ ስቴትስና የካናዳ የንግድና የሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን የሠራተኞችን ኑሮ ለማሻሻል ከግንቦት 1, 1886 ጀምሮ ሠራተኞች በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሠሩ ጥያቄ አቀረበ። ብዙ ቦታ የሚገኙ አሠሪዎች በጥያቄው ባለመስማማታቸው ግንቦት አንድ ቀን ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ።

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የላብ አደሮችን ንቅናቄ በመደገፋቸው ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል የመጀመሪያዎቹ የተገደሉት ቺካጎ፣ ኢሊኖይ ውስጥ በሄይማርኬት አደባባይ ላይ በተነሳው ረብሻ ሲሆን በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በሆላንድ፣ በጣሊያን፣ በሩሲያና በስፔይን የሚገኙ ሠራተኞችም ንቅናቄውን ደግፈዋል።b የዓለም ሶሻሊስት ፓርቲዎች ምክር ቤት በ1889 ፓሪስ ውስጥ ባደረገው ስብሰባ ላይ፣ የሥራ ሰዓት ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሆን የቀረበውን ሐሳብ ለመደገፍ ግንቦት 1, 1890 በመላው ዓለም ትዕይንተ ሕዝብ እንዲደረግ አዋጅ አወጣ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ግንቦት አንድ ሠራተኞች ተስማሚ የሥራ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ለመጠየቅ ሰልፍ የሚወጡበት ዓመታዊ በዓል ሆነ።

በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሪፑብሊኮች ውስጥ፣ ሜይ ዴይ ወታደራዊ ሰልፍ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ግኝቶችን በአደባባይ በማሳየት ይከበር ነበር። በዛሬው ጊዜ በርካታ አገሮች ግንቦት አንድን የላብ አደሮች ቀን ወይም ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በማለት ያከብሩታል። ሆኖም በዩናይትድ ስቴትስና በካናዳ የላብ አደሮች ቀን የሚከበረው በመስከረም ወር የመጀመሪያው ሰኞ ላይ ነው።

የጥንቱንና የዘመናችንን አከባበር የሚያመሳስሏቸው ነገሮች

ሜይ ዴይ ምንጊዜም ቢሆን ሕዝባዊ በዓል ነው። ሠራተኞች አሠሪዎቻቸው ፈቀዱላቸውም አልፈቀዱላቸው እረፍት ይወጣሉ። ለዚያን ዕለት የገዥው መደብና የሕዝቡ ቦታ የተገላቢጦሽ ይሆን ነበር። የዕለቱ ንጉሥና ንግሥት ከተራው ኅብረተሰብ ይመረጣሉ፤ የገዢውም ክፍል መሳለቂያ ይሆናል። በዚህ መንገድ ሜይ ዴይ ያለ ምንም ችግር ከላብ አደሮች ንቅናቄ ጋር የተያያዘ ከመሆኑም በላይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሶሻሊስት ፓርቲ ዓመታዊ ክብረ በዓል እንዲሆን ተወሰነ።

እንደ ጥንታዊው ሜይ ዴይ ሁሉ ዓለም አቀፋዊው የሠራተኞች ቀንም ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ሰልፍ የሚያሳይበት ወቅት ሆኗል። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሜይ ዴይ በዓል ወቅት ረብሻ መፈጠሩ እየተለመደ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል በ2000 በተከበረው ሜይ ዴይ ላይ ዓለም አቀፋዊ ካፒታሊዝምን በመቃወም በምድር ዙሪያ ሰልፎችና ስብሰባዎች ተደርገዋል። በዚህ ጊዜ ተቃዋሚዎች ባነሱት ረብሻ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

የለውጥ ፍላጎትን ማሟላት

በእርግጥ ሰዎች ልበ ቅን የሆኑትን ሁሉ የሚጠቅሙ ዓለም አቀፋዊ ለውጦች ማምጣት ይችላሉ? እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ፈጽሞ አይችሉም። ‘ሰው አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ አይችልም’ የሚለው ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እውነተኝነት በተደጋጋሚ ታይቷል።—ኤርምያስ 10:23

ሰላም የሰፈነበት ዓለም ለማምጣት የሰው ልጆች ካላቸው እጅግ የላቀ ኃይል ያስፈልጋል። እንዲህ ያለው ኃይል ምንጭ የምድር ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ” በማለት ስለ እርሱ ተናግሯል። (መዝሙር 145:16) አምላክ በሰጣቸው ሌሎች ተስፋዎች ላይ ምርምር እንድታደርግ እንጋብዝሃለን።

የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማረው የናሙና ጸሎት ሲፈጸም የአምላክ መንግሥት ይመጣል፤ ፈቃዱም በምድር ላይ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የሾመው ገዢ ኢየሱስ ክርስቶስ “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ለድኾችና ለችግረኞች ይራራል፤ ምስኪኖችንም ከሞት ያድናል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል” በማለት ቃል ገብቷል።—መዝሙር 72:12-14

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የጎርጎሳውያን የቀን አቆጣጠር ሥራ ላይ ከመዋሉ ከ400 ዓመታት በፊት ግንቦት አንድ የሚጀምረው ከአሁኑ 11 ቀናት ዘግይቶ ነበር፤ ስለሆነም ብዙውን ጊዜ የግንቦት መባቻ ሞቅ ያለ የአየር ሁኔታ የሚኖረው ከመሆኑም በላይ ሁሉም ዛፎች ቅጠሎቻቸው እጅብ የሚሉበት ወቅት ነበር።

b ይህ ረብሻ የተቀሰቀሰው በተቃዋሚ ሰልፈኞችና በፖሊሶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ብዙ ሠራተኞች በተገደሉ ማግሥት ነው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ16ኛው መቶ ዘመን ሜይ ዴይ በመጣ ቁጥር ለንደን ውስጥ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ላይ የሚተከል ምሰሶ

[ምንጭ]

ኦብዘርቬሽንስ ኦን ፖፑላር አንቲክዊቲስ ከተባለው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2000 በሜይ ዴይ ዕለት በለንደን እንግሊዝ የተደረገ ፀረ-ካፒታሊስት ተቃውሞ ሰልፍ

[ምንጭ]

© Philip Wolmuth/Panos Pictures

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ