የሽብርተኞች ጥቃት ሰለባ የሆኑ ልጆች
በሰሜናዊ ኡጋንዳ ቀኑ መሸትሸት ሲል ባዶ እግራቸውን የሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ልጆች ሲጓዙ ይታያሉ። ከመጨለሙ በፊት ከገጠር መንደሮቻቸው ወጥተው እንደ ጉሉ፣ ኪትገምና ሊራ ወደመሳሰሉት ትላልቅ ከተሞች በእግራቸው ይጓዛሉ። ከተማ ከገቡ በኋላ ይበታተኑና ወደ ሕንጻዎች፣ የአውቶቡስ ፌርማታዎች፣ መናፈሻዎችና አደባባዮች ይሄዳሉ። ፀሐይ ስትወጣ ደግሞ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ይታያሉ። ነጋ ጠባ እንዲህ የመሰለ ያልተለመደ ነገር የሚያደርጉት ለምንድን ነው?
አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ልጆች የሌሊት ተረኞች ይሏቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ወጣቶች ወደ ከተሞቹ የሚሄዱት በሌሊት ፈረቃ ለመሥራት አይደለም። ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ከቤታቸው የሚወጡት፣ ገጠራማው መኖሪያቸው በጨለማ አደገኛ በመሆኑ ነው።
ለሁለት አሥርተ ዓመታት ያህል የደፈጣ ተዋጊዎች የገጠር መንደሮችን እየወረሩ ልጆችን አፍነው ሲወስዱ ቆይተዋል። በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶችንና ልጃገረዶችን ከቤታቸው ይወስዱና ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ገብተው ይሰወራሉ። ዓማጺያኑ ልጆቹን አፍነው የሚወስዱት በተለይ በጨለማ ሲሆን ወታደርና እቃ ተሸካሚ ያደርጓቸዋል፤ ሴቶቹን ደግሞ የተዋጊዎቹ የጾታ ፍላጎት ማርኪያ አድርገው ይጠቀሙባቸዋል። ታፍነው የተወሰዱት ልጆች የታዘዙትን ካልፈጸሙ አፋኞቻቸው አፍንጫቸውን ወይም ከንፈራቸውን ሊቆርጧቸው ይችላሉ። ሊያመልጡ ሲሉ ከተያዙ ለመግለጽ በጣም የሚሰቀጥጥ አሟሟት ይጠብቃቸዋል።
የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሌሎች ወጣቶችም አሉ። በሴራ ሊዮን ገና ሕፃናት እያሉ ቆንጨራ በሚይዙ ሰዎች እጅና እግራቸውን ያጡ ወጣቶች ይገኛሉ። በአፍጋኒስታን የሚኖሩ ልጆች የቢራቢሮ ቅርጽ ባላቸው ፈንጂዎች ይጫወታሉ፤ እነዚህ የሚያማምሩ “መጫወቻዎች” ሲፈነዱም እጆቻቸውንና ዓይናቸውን ያጣሉ።
የሽብርተኞች ተጠቂ የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ያጋጠማቸው ደግሞ ለየት ያለ ሁኔታ ነው። ለምሳሌ ያህል በ1995 በኦክላሆማ ሲቲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በደረሰው የሽብርተኞች ጥቃት ከሞቱት 168 ሰዎች መካከል አሥራ ዘጠኙ ልጆች ሲሆኑ አንዳንዶቹ ገና ጨቅላ ሕጻናት ነበሩ። ኃይለኛ ነፋስ የሻማ ብርሃንን በአንድ ጊዜ ድርግም እንደሚያደርገው ሁሉ ፍንዳታው የእነዚህን ትንንሽ ልጆች ሕይወት በአንድ አፍታ ቀጥፏል። አሸባሪዎች ያደረሱት ይህ ጥቃት ልጆች የመሆን፣ የመጫወት፣ የመሳቅና በወላጆቻቸው የመታቀፍ መብታቸውን ነጥቋቸዋል።
እነዚህ በቅርብ ጊዜያት የተከሰቱ አደጋዎች ቢሆኑም ከዚህ ቀጥሎ እንደምንመለከተው ሽብርተኞች የሚፈጽሙት ዓመጽ የሰውን ዘር ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲያሰቃይ ኖሯል።
© Sven Torfinn/ Panos Pictures