ተፈጥሮ ምን ያስተምረናል?
“እስቲ እንስሶችን ጠይቁ፤ ያስተምሯችኋል፤ የሰማይ ወፎችንም ጠይቁ፣ ይነግሯችኋል፤ ለምድር ተናገሩ፤ ታስተምራችኋለች፤ የባሕርም ዓሣ ይነግራችኋል።”—ኢዮብ 12:7, 8
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሳይንስና የምሕንድስና ሊቃውንት ከዕፅዋትና ከእንስሳት ቃል በቃል ተምረዋል ለማለት ይቻላል። አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመፍጠርም ሆነ በሥራ ላይ የሚገኙ መሣሪያዎችን ጥራት ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት እንዲያግዛቸው የተለያዩ ፍጥረታትን ንድፍ እያጠኑና እየኮረጁ ሲሆን ይህ የጥናት መስክ ባዮሚሜቲክስ ይባላል። ቀጥሎ የቀረቡትን ምሳሌዎች በምትመለከትበት ጊዜ ‘እንዲህ ላለው የረቀቀ ንድፍ ሊመሰገን የሚገባው ማነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።
ከዓሣ ነባሪ መቅዘፊያ ክንፎች ትምህርት ማግኘት
የአውሮፕላን ንድፍ አውጪዎች ሃምፕባክ ከሚባለው ዓሣ ነባሪ ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ? በርካታ ትምህርቶችን ማግኘት የሚችሉ ይመስላል። በዕድሜ ትልቅ የሆነ አንድ ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ ክብደቱ 300 ኩንታል የሚደርስ ሲሆን ሙሉ ጭነት ከተጫነ ከባድ መኪና ጋር ይተካከላል። መላ ሰውነቱ እንደልብ የማይተጣጠፈው ይህ ዓሣ ነባሪ በጣም ትላልቅ ክንፍ መሰል መቅዘፊያዎች አሉት። ይህ 12 ሜትር ርዝመት ያለው እንስሳ ውኃ ውስጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴው በጣም ቀልጣፋ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የባሕር እንስሳት ወይም አንድ ዓሣ ለመብላት በሚፈልግበት ጊዜ ከዓሣው በታች ሆኖ ቀጥ ብሎ በመቆም በፍጥነት እየሾረ አረፋ በማውጣት መረብ ይሠራል። መሃል ለመሃል ከ1.5 ሜትር የማይበልጥ ርዝመት ያለው ይህ የአረፋ መረብ ከላይ ያሉትን ፍጥረታት በሙሉ እየሳበ አንድ ላይ ይሰበስብለታል። ከዚያም ዓሣ ነባሪው በቀላሉ ይውጣቸዋል።
ተመራማሪዎቹን በእጅጉ ያስደነቃቸው፣ እንደልቡ ሊተጣጠፍ የማይችለው ይህ ፍጡር ጠባብ ስፋት ያለው ክብ ነገር የሚሠራበት መንገድ ነው። ተመራማሪዎቹ ምሥጢሩ ያለው በዓሣ ነባሪው መቅዘፊያ ክንፎች ቅርጽ ላይ እንደሆነ ደርሰውበታል። የፊተኛው ጠርዝ እንደ አውሮፕላን ክንፍ የተስተካከለ ሳይሆን በርካታ አባጣ ጎርባጣዎች አሉት።
ዓሣ ነባሪው ውኃውን እየሰነጠቀ በፍጥነት በሚንቀሳቀስበት ጊዜ እነዚህ አባጣ ጎርባጣዎች የውኃውን ግፊት በመቀነስ ወደፊት የመወንጨፍ ኃይል ይጨምሩለታል። እንዴት? ናቹራል ሂስትሪ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው አባጣ ጎርባጣዎቹ ዓሣ ነባሪው ቀጥ ብሎ ሽቅብ በሚወጣበት ጊዜም እንኳ ከፊቱ ያለው ውኃ ሥርዓት ባለው መንገድ በክብ ቅርጽ መልክ እየተሽከረከረ እንዲያልፍ ያስችሉታል። የክንፎቹ ፊተኛ ጠርዝ የተስተካከለ ቢሆን ኖሮ ከክንፉ አልፎ የሚሄደው ውኃ ሞገድ እንዲፈጠር ስለሚያደርግ በቀላሉ ሽቅብ ሊወጣ አይችልም ነበር።
ታዲያ ይህ ግኝት ምን ተግባራዊ ጠቀሜታ ያስገኛል? በዚህ መንገድ የተሠራ የአውሮፕላን ክንፍ በርካታ የነፋስ አቅጣጫ ማስቀየሪያዎች ወይም አየር መቅዘፊያ መሣሪያዎች አያስፈልጉትም። በተጨማሪም ይበልጥ አስተማማኝ ከመሆኑም በላይ ለመጠገንም ከባድ አይደለም። የባዮሜካኒክስ ሊቅ የሆኑት ጆን ሎንግ አንድ ቀን “እያንዳንዱ አውሮፕላን የሃምፕባክ ዓሣ ነባሪ ዓይነት አባጣ ጎርባጣ ክንፍ ተገጥሞለት ማየታችን አይቀርም” ብለዋል።
ሲጋል የተባለውን ወፍ ክንፍ መቅዳት
አሁንም ቢሆን የአውሮፕላን ክንፍ ቅርጽ የተሠራው ከወፎች ክንፍ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው። ይሁን እንጂ መሐንዲሶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን ጥበብ ይበልጥ አሻሽለውታል። ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንደዘገበው “የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደ ሲጋል በአየር ላይ ቀጥ ብሎ የመቆም፣ ቁልቁል የመወርወርና ሽቅብ የመውጣት ችሎታ ያለው ያለአብራሪ የሚንቀሳቀስ አውሮፕላን ሠርተዋል።”
ሲጋል የተባለው ወፍ ይህን የመሰለ አስደናቂ እንቅስቃሴ የሚያደርገው በክንፎቹ ላይ ያሉትን የተለያዩ መገጣጠሚያዎች እንደሁኔታው በማንቀሳቀስ ነው። መጽሔቱ እንደገለጸው “ሁለት ጫማ ርዝመት ያለው ይህ የሙከራ አውሮፕላን” እንደልብ ከሚተጣጠፈው የሲጋል ወፍ ክንፍ ጋር በሚመሳሰል መልኩ “በክንፎቹ ላይ ያሉትን የብረት ዘንጎች ለመቆጣጠር የሚያስችል ትንሽ ሞተር አለው።” እነዚህ በከፍተኛ ጥበብ የተሠሩ ክንፎች ትንሿ አውሮፕላን በረጃጅም ሕንጻዎች መካከል ቀጥ ብላ እንድትቆምና ቁልቁል እንድትወርድ ያስችሏታል። የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል እንዲህ ያለውን እንደልብ የሚተጣጠፍና የሚንቀሳቀስ አውሮፕላን በትላልቅ ከተሞች ኬሚካላዊና ባዮሎጂያዊ መሣሪያዎችን አስሶ ለማግኘት ሊጠቀምበት ይፈልጋል።
የእንሽላሊት እግሮችን አፈጣጠር መቅዳት
ሰዎች ከየብስ እንስሳትም ብዙ የሚማሩት ነገር አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ጌኮ የምትባለው ትንሽ እንሽላሊት ቀጥ ያለ ግድግዳ ላይ መውጣትና ኮርኒስ ላይ ተገልብጣ መሄድ ትችላለች። ይህች ፍጥረት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሳይቀር በዚህ አስደናቂ ችሎታዋ ትታወቃለች። (ምሳሌ 30:28 NW) ጌኮ የስበትን ኃይል እንድትቋቋም ያስቻላት ምንድን ነው?
ጌኮን እንደመስታወት ባለ ልሙጥ ነገር ላይ ሳይቀር እንድትለጠፍ ያስቻሏት እግሮቿን የሸፈኑት ሴታ የሚባሉ ጥቃቅን ጸጉር መሰል ነገሮች ናቸው። እግሮቿ እንደሙጫ የማጣበቅ ችሎታ ያለው ፈሳሽ አያመነጩም። ከዚህ ይልቅ በሞለኪውሎች መሳሳብ ምክንያት በሚፈጠርና በጣም ረቂቅ በሆነ ኃይል ትጠቀማለች። በሁለት ነገሮች ላይ የሚገኙ ሞለኪውሎች በመካከላቸው ባለ ቫን ደር ዋልስ ተብሎ በሚጠራ በጣም ደካማ ኃይል እርስ በርስ ይያያዛሉ። አብዛኛውን ጊዜ ይህ የመሳሳብ ኃይል ከመሬት ስበት በእጅጉ ያነሰ ነው። እጃችንን እየለጠፍን ግድግዳ መውጣት የማንችለው በዚህ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ ሴታ የሚባሉት የጌኮ ጥቃቅን ጸጉር መሰል ነገሮች በግድግዳው ላይ የሚያርፈውን የእግሯን ስፋት በጣም እንዲጨምር ያደርጉታል። የቫን ደር ዋልስ ኃይል በጌኮ እግር ላይ በሚገኙት በሺዎች በሚቆጠሩት ሴታዎች ሲባዛ አነስተኛ የሆነውን የጌኮዎች ክብደት ሊሸከም የሚያስችል ኃይል ያስገኛል።
ታዲያ ይህ ግኝት ምን ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል? በጌኮ እግሮች አምሳል የተሠራ ሰው ሠራሽ ጨርቅ ቬልክሮ ለሚባል ማያያዣ ምትክ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፤ ለነገሩ ቬልክሮም ቢሆን የተሠራው ተፈጥሮን በመኮረጅ ነው።a ዚ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት አንድ ተመራማሪ በጌኮ እግር ላይ ካሉ ፀጉር መሰል ነገሮች የተሠራ ጨርቅ በተለይ “በሕክምናው መስክ ኬሚካላዊ ማያያዣዎችን መጠቀም በማይቻልባቸው ወቅቶች” ልዩ ጠቀሜታ እንደሚኖረው መናገራቸውን ጠቅሷል።
ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ማነው?
በሌላ በኩል ብሔራዊ የበረራና ሕዋ አስተዳደር (NASA) እንደ ጊንጥ የሚራመድ ባለ ብዙ እግር ሮቦት በመሥራት ላይ ነው። የፊንላንድ መሐንዲሶች ደግሞ እንደ አንዳንድ ነፍሳት በትላልቅ እንቅፋቶች ላይ ተረማምዶ ሊያልፍ የሚችል ባለ ስድስት እግር ትራክተር ሠርተዋል። ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ ልክ እንደ ፈረንጅ ጥድ የዘር መያዣዎች አየሩ ሞቃት ሲሆን የሚከፈቱና እርጥበት ሲኖር የሚዘጉ ትናንሽ ተካፋቾች ያሉት ልብስ ሠርተዋል። አንድ የመኪና አምራች ኩባንያ ቦክስፊሽ በሚባል የዓሣ ዝርያ አምሳል የአየሩን ግፊት በቀላሉ ጥሶ ማለፍ የሚችል መኪና በመሥራት ላይ ነው። ሌሎች ተመራማሪዎች ደግሞ አባሎኒ የሚባሉት የባሕር ፍጥረታት ያላቸውን ንቅናቄ የማብረድ ችሎታ በመቅዳት ይበልጥ ቀላልና ጠንካራ የሆነ የጥይት መከላከያ ለመሥራት እየሞከሩ ነው።
ከተፈጥሮ የሚገኙት ሐሳቦች በጣም ብዙ በመሆናቸው ተመራማሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ባዮሎጂያዊ አሠራሮችን ያካተተ የመረጃ ዝርዝር አዘጋጅተዋል። ዚ ኢኮኖሚስት እንደገለጸው ሳይንቲስቶች “ለዲዛይን ችግሮቻቸው ከተፈጥሮ መፍትሔ” ለማግኘት እነዚህን ዝርዝሮች መመርመር ይችላሉ። በእነዚህ የመረጃ ስብስቦች ውስጥ የሚገኙት የተፈጥሮ አሠራሮች “ባዮሎጂካል ፓተንትስ” ወይም ባዮሎጂያዊ የፈጠራ ባለቤትነት ይባላሉ። እንደሚታወቀው የፈጠራ ባለቤት የሚሆነው አንድን አዲስ ሐሳብ ወይም መሣሪያ በሕግ ያስመዘገበ ሰው ወይም ኩባንያ ነው። ዚ ኢኮኖሚስት ስለ ባዮሎጂያው የፈጠራ ባለቤትነት የመረጃ ስብስብ ሲያብራራ “ተመራማሪዎች በተፈጥሮ ያሉ ነገሮችን አስመስሎ የመሥራት ዘዴዎችን ‘ባዮሎጂያዊ የፈጠራ ባለቤትነት’ ብለው ሲጠሩ የፈጠራው ባለ መብት ተፈጥሮ ራሷ መሆኗን ማጉላታቸው ነው” ይላል።
ታዲያ ተፈጥሮ እነዚህን ድንቅ ሐሳቦች ልታፈልቅ የቻለችው እንዴት ነው? ብዙ ተመራማሪዎች በተፈጥሮ ውስጥ የሚታዩት አስደናቂ ንድፎች በሚሊዮን በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ በሙከራ የተገኙ የዝግመተ ለውጥ ውጤቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። ሌሎች ተመራማሪዎች ግን ከዚህ የተለየ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ማይክል ቢሂ የተባሉ ማይክሮባዮሎጂስት በ2005 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በተባለ መጽሔት ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “[በተፈጥሮ ውስጥ] የሚታየው አስደናቂ ንድፍ ማንም በቀላሉ ሊረዳው የሚችል የመከራከሪያ ሐሳብ ያቀርባል:- አንድ ነገር ዳክዬ የሚመስል፣ እንደ ዳክዬ የሚራመድና እንደ ዳክዬ የሚጮህ ከሆነ ዳክዬ ላለመሆኑ በቂ መረጃ እስካልተገኘ ድረስ ዳክዬ ነው ብለን ለመደምደም እንገደዳለን።” ታዲያ እርሳቸው የደረሱበት መደምደሚያ ምንድን ነው? “በግልጽ የሚታይ ንድፍ እንደ አልባሌ ነገር በቸልታ መታለፍ የለበትም።”
ይበልጥ አስተማማኝና የተቀላጠፈ በረራ ለማድረግ የሚያስችል የአውሮፕላን ክንፍ ንድፍ ያወጣ መሐንዲስ ለልፋቱ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ሁለገብ የሆነ ፋሻ ወይም ይበልጥ ምቹ የሆነ ልብስ አሊያም ነዳጅ ቆጣቢ መኪና ለመሥራት የሚያስችል ንድፍ ያወጣ ሰው ለሥራው ይመሰገናል። እንዲያውም ለንድፍ አውጪው እውቅና ሳይሰጥ ወይም የእርሱን ፈቃድ ሳያገኝ ግኝቱን የቀዳ አንድ አምራች ኩባንያ እንደ ወንጀለኛ ይቆጠራል።
የተፈጥሮ ንድፎችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቀድተው የምሕንድስና ችግሮቻቸውን የፈቱ ከፍተኛ ሥልጠና ያገኙ ተመራማሪዎች ዋነኛው ንድፍ ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌለው የዝግመተ ለውጥ ውጤት ነው ማለታቸው ምክንያታዊ ይመስልሃል? ቅጂውን ለመሥራት ከፍተኛ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ ካስፈለገ የመጀመሪያውን ለመሥራት የበለጠ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ አያስፈልግም? የበለጠ ምስጋና መሰጠት ያለበት ለማን ነው? ለዋናው ሠዓሊ ወይስ የአሳሳል ስልቱን ተምሮ ሥዕሉን አስመስሎ ለሠራ ተማሪ?
ምክንያታዊ መደምደሚያ
ጥሩ አስተሳሰብ ያላቸው በርካታ ሰዎች በተፈጥሮ ውስጥ የሚታየውን አስደናቂ ንድፍ ከተመለከቱ በኋላ እንደሚከተለው ሲል የጻፈውን መዝሙራዊ ቃላት አስተጋብተዋል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች።” (መዝሙር 104:24) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ጳውሎስም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሷል። “ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 1:19, 20
ይሁን እንጂ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያላቸውና በአምላክ የሚያምኑ በርካታ ቅን ሰዎች አምላክ በዓለም ውስጥ የሚገኙትን በጣም አስደናቂ ነገሮች የፈጠረው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስተምራል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቬልክሮ፣ በርዶክ የሚባለውን ተክል እሾሃማ ፍሬ በመቅዳት የተሠራ እንደመንጠቆ የሚሰካኩ ጥቃቅን ጭረቶች ያሉት ማያያዣ ነው።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ተፈጥሮ እነዚህን ድንቅ ሐሳቦች ልታፈልቅ የቻለችው እንዴት ነው?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የተፈጥሮ የፈጠራ ባለቤት ማነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ቅጂውን ለመሥራት ከፍተኛ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ ካስፈለገ የመጀመሪያውን ለመሥራት የበለጠ እውቀት ያለው ንድፍ አውጪ አያስፈልግም?
ይህ እንደልቡ የሚታጠፍ አውሮፕላን በሲጋል ክንፍ አምሳል የተሠራ ነው
የጌኮ እግር አይቆሽሽም፣ አሻራ አይተውም፣ ቴፍሎን በተቀባባቸው ነገሮች ላይ ካልሆነ በስተቀር በማንኛውም ነገር ላይ በቀላሉ ሊጣበቅ ወይም ሊነሳ ይችላል። ተመራማሪዎች ይህን ለመቅዳት በሙከራ ላይ ናቸው
ቦክስፊሽ የተባለው የዓሣ ዝርያ ያለው አስደናቂ ንድፍ የአየርን ግፊት በቀላሉ ጥሶ ማለፍ የሚችል መኪና ንድፍ ለማውጣት አስችሏል
[ምንጭ]
አውሮፕላን:- Kristen Bartlett/ University of Florida; የጌኮ እግር:- Breck P. Kent; ቦክስፊሽ ዓሣ እና መኪና:- Mercedes-Benz USA
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
በተፈጥሯቸው ጠቢባን የሆኑ ተጓዦች
ብዙ ፍጥረታት ቦታ ሳይጠፋቸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ አካባቢ የመጓዝ በተፈጥሮ ያገኙት ‘ጥበብ’ አላቸው። (ምሳሌ 30:24, 25) እስቲ ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት።
◼ የጉንዳን ትራፊክ ቁጥጥር ምግባቸውን ለመቃረም የሚሰማሩ ጉንዳኖች መንገድ ሳይጠፋቸው ወደ ጉድጓዳቸው የሚመለሱት እንዴት ነው? የእንግሊዝ ተመራማሪዎች እነዚህ ፍጥረታት ጠረናቸውን እንደ ዱካ ትተው ከማለፋቸውም በተጨማሪ አንዳንድ ጉንዳኖች በቀላሉ ወደ ቤታቸው የሚመለሱበትን መንገድ ለመሥራት በጂኦሜትሪ እንደሚጠቀሙ ደርሰውበታል። ለምሳሌ ፋሮ የሚባሉት የጉንዳን ዝርያዎች “ከጉድጓዳቸው ሲወጡ ከ50 እስከ 60 ዲግሪ የሚታጠፉ የተለያዩ መንገዶችን ተከትለው ይሄዳሉ” በማለት ኒው ሳይንቲስት ዘግቧል። ታዲያ ይህ ምን የሚያስደንቅ ነገር አለው? አንዲት ጉንዳን ወደ ጉድጓዷ በምትመለስበት ጊዜ መገንጠያ ላይ ስትደርስ በመጠኑ የሚታጠፈውን መንገድ ተከትላ በመሄድ ወደ ጉድጓዷ ትደርሳለች። ይኸው ጽሑፍ “እንደባላ የሚገነጠል መንገድ መኖሩ” ጉንዳኖቹ በሁለት አቅጣጫ ያለ ችግር እንዲጓዙ የሚረዳቸው ከመሆኑም በላይ መንገድ ስተው የሚያባክኑትን ጊዜ በእጅጉ ይቀንስላቸዋል” ይላል።
◼ የአእዋፍ ኮምፓስ በርካታ ወፎች በተለያየ የአየር ሁኔታ ውስጥ ረዥም ርቀት ተጉዘው ምንም ዝንፍ ሳይሉ ትክክለኛው ቦታ ላይ ይደርሳሉ። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ተመራማሪዎች አእዋፍ የምድርን ስበት የመለየት ችሎታ እንዳላቸው ደርሰውበታል። ይሁን እንጂ ሳይንስ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው “የምድር የስበት መሥመር ከቦታ ቦታ ስለሚለያይ ሁልጊዜ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ላያመለክት ይችላል።” ታዲያ ከቦታ ቦታ የሚፈልሱ አእዋፍ አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ የሚያስችላቸው ምንድን ነው? አእዋፍ በእያንዳንዱ ምሽት ውስጣዊ ኮምፓሳቸውን በምትጠልቀው ጀምበር አቅጣጫ ያስተካክላሉ። ፀሐይ የምትጠልቅበት አቅጣጫ እንደየወራቱና አካባቢው ከምድር ወገብ ባለው ርቀት መጠን ስለሚለያይ ተመራማሪዎች ወፎቹ “የዓመቱን ወራትና ጊዜ የሚነግራቸውን ተፈጥሯዊ ሰዓት” ተጠቅመው ለውጡን ያስተካክላሉ ብለው እንደሚያስቡ ሳይንስ ዘግቧል።
ጉንዳን የጂኦሜትሪ እውቀት እንዲኖራት ያስቻላት ማን ነው? አእዋፍ ኮምፓስ፣ ተፈጥሯዊ ሰዓትና እነዚህ መሣሪያዎች የሚያስተላልፉትን መረጃ ለመተርጎም የሚያስችል አንጎል እንዲኖራቸው ያደረገው ማነው? ምንም ዓይነት የማሰብ ችሎታ የሌለው ዝግመተ ለውጥ ነው? ወይስ የረቀቀ ችሎታ ያለው ፈጣሪ?
[ምንጭ]
© E.J.H. Robinson 2004